፮ተኛው ሐዊረ ህይወት በጀርመን ሀገር ሆክስተር ከተማ ተካሄደ።
ሚያዚያ 17 ቀን 2011 ዓ.ም
በጀርመን ንዑስ ማዕከል
በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ/ሰ/ት/ቤ/ማ/መ/ ማኅበረ ቅዱሳን አውሮፓ ማዕከል የጀርመን ንዑስ ማዕከል ያዘጋጀው፥ ፮ተኛው ሐዊረ ህይወት በጀርመን -ከሃኖቨር ከተማ 90 ኪሜ ርቀት ላይ በምትገኘው ሆክስተር ከተማ በሚገኘው የግብጽ ኦርቶዶክስ ቅድስት ማርያም እና ቅዱስ ማውሪስ ገዳም ከሚያዚያ ፬ እስከ ፮ ድረስ በተሳካ ሁኔታ ተካሄደ።
ዓርብ ማምሻውን አባቶች ካህናት በተገኙበት በጸሎት ተከፍቶ፥ ሊቀ ትጉኃን ቀሲስ አብርሃም እንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር አሰተላልፈዋል። በመቀጥልም ቀሲስ ግሩም ታየ የዕለቱን ትምህርት ካስተማሩ በኋላ፥ የእራት መስተንግዶ ተካሂዶ የምሽቱ መርሐ ግብር ተጠናቋል።
ቅዳሜ ጠዋት በቤተክርስቲያናችን ካህናትና ዲያቆናት ሥርዓተ ቅዳሴ የተፈጸመ ሲሆን፥ ከቅዳሴ በኋላ በነበረው የጠዋቱ መርሐግብር መክፈቻ ላይ የገዳሙ የበላይ ጠባቂ እና በግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የሰሜን ጀርመን ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ደሚያን “እንኳን ወደ ገዳማችሁ በደህና መጣችሁ፤ በመምጣታችሁ ተደስቻለሁ በርቱ ጠንክሩ በነፍስም በሥጋም ጎልምሱ” በማለት መልእክት አስተላልፈዋል።
ለጉባዔው ከተዘጋጁት ዋና ትምህርቶች መካከል፥ “ነገረ እግዚአብሔር” በሚል ርዕስ በመጋቤ ምሥጢር ዶ/ር ኅሩይ ኤርምያስ ተሰጥቷል። መምህሩ ሀልዎተ እግዚአብሔርን በሚመለከት የቤተክርስቲያንን አስተምህሮ፥ ከተለያዩ የፍልስፍና አስተምህሮዎች አንጻር በግልጽ አቀራረብ ያስተማሩ ሲሆን፥ በተጨማሪምየእግዚአብሔር ስሞችንና ባህርያት በሰፊው የዳሰሰና፥ ለተሳታፊዎች ብዙ ዕውቀትን ያስጨበጠ ትምህርት ነበር።
በመቀጠልም መልአከ ስብሐት ተክሌ ሲራክ ከትምህርቱ ርዕስ ጋር የሚሄድ ያሬዳዊ ዜማ “አነ ቀዳማዊ ወአነ ደኃራዊ ይስማ ሰማይ ወታጽምእ ምድር” ትርጉሙም “መጀመሪያ እኔ ነኝ፥ መጨረሻም እኔ ነኝ ፤ ሰማይ ይስማ ምድርም ታድምጥ” ካቀረቡ በኋላ፥ ሊቃውንት ለሚያዚያ 5 አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ በዓል ያዘጋጁትን የማኅሌት ዜማ አሰምተዋል።
የጀርመንና አካባቢው ሀገረ ስብከት ዋና ጸሐፊ ቆሞስ አባ ስብሐት ለአብ ሀገረ ስብከቱን ወክለው ባስተላለፉት መልእክት፥ ማኅበሩ እየሠራው ያለውን አገልግሎት አድንቀው፥ ሀገረ ስብከቱ እንደቀድሞው ማኅበሩ ቤተክርስቲያንን ለመደገፍ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ በቅርበት ለመክታተል እና እገዛ ለማድረግ፥ እንዲሁም ማኅበሩ አገልግሎቱን ከሌሎች የሀገረ ስብከቱ ክፍሎች ጋር በቅንጅት እንዲያደርገው ፍላጎቱ እንደሆነ ገልጸዋል።
በመቀጠልም ከምዕመናን ለቀረቡ መንፈሳዊ ጥያቄዎች በሊቃውንተ ቤተክርስቲያን መልስ ከተሰጠ በኋላ፥ በንዑስ ማዕከሉ ሚድያ ክፍል የማኅበረ ቅዱሳን ሚዲያ እንቅስቃሴ ዓላማ፥ ያለበት ደረጃ፥ ያሉት ተግዳሮቶች፥ የሚዲያ ሽፋኑ ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ጋር በንጽጽር የቀረበ ሲሆን፥ ከምዕመናን ምን አንደሚጠበቅም ጥናቱ ጠቁሟል።
በማስከተልም ለጉባዔው የተዘጋጀውን ትምህርት “ምሥጢረ ንስሐ” በሚል ርዕስ የሰጡት ቀሲስ ዶ/ር ያብባል ሙሉዓለም ናቸው። መምህሩ በተለይም በተሠራ ኃጢአት ከመጸጸት እና ከመመለስ በተጨማሪ ለካህን መናዘዝ የምሥጢረ ንስሐ ዋነኛው አካል መሆኑን ከመጽሐፍ ቅዱስ እና ከሥርዓተ ቤተክርስቲያን እየጠቀሱ በሚገባ ያስረዱ ሲሆን፥ በተጨማሪም የቅዱሳንን የንስሐ ሕይወት አሁን እኛ ከምንኖረው ሕይወት ጋር በማዛመድ ዘመኑን የዋጀ ትምህርት ሰጥተዋል።
ሌላው በሐዊረ ህይወቱ ትኩረት የተሰጠው፥ በማኅበረ ቅዱሳን እየተካሄደ ያለውን የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ ፕሮጀክቶችና ተግዳሮቶች፥ እንዲሁም የምዕመናንና ማኅበራት ሚና ምን መምሰል እንዳለበት በዲ/ን ዶ/ር መርሻ አለኸኝ ከቀረበ በሁዋላ ብዙሃንን በእንባ ያራጨው ከጉዳዩ ጋር ተያያዝነት ያለው የታየው ቪዲዮ ነው። ይህንንም ያዩ ካህናትና ምዕመናን እስካሁን ይህንን ነገር በደንብ ሳይገነዘቡ መቆየታቸው ምን ያህል እንደቆጫቸው ተናግረው፤ ከዚህ ቀን ጀምሮ ለታቀዱት ፕሮጀክቶች የተቻላቸውን እንደሚያበረክቱም ቃል ገብተዋል።
የቅዳሜ ፍጻሜ መርሐግብር የነበረው የገዳሙን ሙዚየም መጎብኘት ነው። ጉብኝቱም ታዳሚዎችን ያስተማረ ብቻ ሳይሆን በመንፈሳዊ ቅናት እንዲቃጠሉ ያደረገም ነበር። ከዚህም መካከል በጀርመን የሚኖሩ ግብጻውያን ቁጥራቸው ከኢትዮጵያውያን የሚያንስ ሲሆን፥ ነገር ግን በጀርመን ሀገር ሁለት ትልልቅ ገዳማትን እና ሌሎች ተቋማትን መግዛት የቻሉበት ትጋት እና አርቆ አሳቢነት፥ እንዲሁም ገዳሙ ውስጥ የግብጽን ቤተክርስቲያን ታሪክ እና አስተምህሮ ለማስተዋወቅ በጀርመንኛ ቋንቋ ያዘጋጁት ቋሚ ዐውደ ርዕይ ወዘተ ተጠቃሽ ናቸው።
በመጨረሻም እሁድ ጠዋት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንና የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ካህናትና ዲያቆናት በጋራ ሥርዓተ ቅዳሴ አካሂደው የ፮ተኛው ሐዊረ ህይወት መርሐ ግብር ፍጻሜ ሆኖዋል።
በመንፈሳዊ ጉባዔው ላይ ወደ 150 የሚጠጉ ምዕመናንና ህጻናት የተገኙ ሲሆን ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ሐዊረ ህይወት መርሐ ግብር ላይ ሲገኙ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሆነና በነበረው ጉባዔ እጅግ እንደተደሰቱ፥ ብዙ መንፈሳዊ ትምህርቶችንና በቤተክርስቲያን እየተካሄዱ ስላሉ አገልግሎቶች ዕውቀት እንዳገኙ ተናግረዋል።
የጀርመን ንዑስ ማዕከል ከዚህ በፊት 5 ሐውረ ሕይወቶችን ፍራንክፈርት አካባቢ በሚገኘው ክሩፈልባህ ከተማ ባለው የቅዱስ እንጦን ገዳም ማድረጉ የሚታወስ ነው።