ጾመ ነነዌ
ኤርምያስ ልዑለቃል (ዶ/ር)
ጥር 26 ቀን 2007 ዓ.ም.
“የነነዌ ሰዎች በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነስተው ይፈርዳሉ ፤ በዮናስ ስብከት ንስሐ ገብተዋልና፡፡” (ማቴ ፲፪፥፵፩)
ይህንን የተናገረው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ጌታችን ለዚህ ትምህርቱ መነሻ ያደረገው የጻፎችን እና የፈሪሳውያንን ጥያቄ ነው፡፡ “መምህር ሆይ ከአንተ ምልክት ልናይ እንወዳለን” ቢሉት “ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ይሻል ፤ ከነቢዩም ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም ። ዮናስ በአሳ አንበሪ ሆድ ሦስት ቀንና ሌሊት አንደነበረ የሰው ልጅም በምደር ልብ ሦስት ቀንና ሌሊት ይሆናል፡፡የነነዌ ሰዎች በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነስተው ይፈርዳሉ ፤ በዮናስ ስብከት ንስሐ ገብተዋልና፡፡ እነሆ ከዮናስ የሚበልጥ ከዚህ አለ” ብሏቸዋል፡፡ (ማቴ ፲፪፥፵፩) ጻፎችና ፈሪሳውያን ምልክት መጠየቃቸው ይገርማል! የተሰጣቸውን ምልክት ሳይጠቀሙ እና በሚያዩአቸው ተአምራት ሳያምኑ ሌላ ምልክት መሻታቸው ይደንቃል! አልተረዱትም እንጂ የእርሱ በመካከላቸው መገኘት በራሱ ምልክታቸው ነበረ:: “ስለዚህ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል፤ እነሆ ድንግል ትጸንሳለች ወንድ ልጅም ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች” አንዳለ ነቢዩ (ኢሳ ፯፥፲፬ )። ሰማያዊው መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ያበሰራት እመብርሃን ምልክታቸው ነበረች፤ በድንግልና ጸንሳ በድንግልና የወለደች እመቤታችን ምልክታቸው ነበረች፤ በጌታችን ልደት ወደ ቤተልሔም ወርደው የዘመሩ ቅዱሳን መላእክትም ምልክቶቻቸው ነበሩ፤ “የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው” እያሉ የመጡት ሰብአ ሰገልም ምልክቶቻቸው ነበሩ፡፡ ከዚህም በላይ በመካከላቸው ሆኖ ማየት ለተሳናቸው ዓይን ሲሰጥ፣ መስማት የተሳናቸው እንዲሰሙ ሲያደርግ፣ ለምጻሞችን ሲያነጻ እና ሙታንን ሲያስነሳ እያዩ እንደገና ሌላ ምልክት አምጣ ማለታቸው የሚገርም ነው! ለዚህም ነው “ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክትን ይሻል” ብሎ ወደ ነነዌ ሰዎች ትምህርት የወሰዳቸው፡፡
ነነዌ ማናት?
ነነዌ በሰሜናዊ ኢራቅ የምትገኝ በጤግሮስ ወንዝ አቅራቢያ የተከተመች ከተማ ነበረች፡፡ ከጤግሮስ በስተምዕራብ ሞሱል የተባለ ከተማ አለ፡፡ከባግዳድ እና ባስራ ቀጥሎ ሦስተኛው የኢራቅ ትልቅ ከተማ ነው፡፡ ነነዌ የምትገኘው ከሞሱል ከተማ ትይዩ ከጤግሮስ በስተምሥራቅ ነው፡፡ ሞሱሉንና ነነዌን የሚለያቸው የጤግሮስ ወንዝ ነው፡፡ አሁን በአምስት ድልድዮች ከአንዱ ከተማ ወደሌላው መሻገር ይቻላል፡፡ የጥንቷ ነነዌ አሁን ሁለት ክፍል አላት፡፡አንዱ ኩኒክ ሲባል ሁለተኛው ናቢዩኑስ (ነቢዩ ዮናስ) ይባላል፡፡ናቢዩኑስ አሁን ድረስ አረቦች በቅዱስ ስፍራነት ስለያዙት አይነካም፡፡ኩኒክ ግን ብዙ ጥናት ተካሂዶበታል፡፡
ነነዌን ማን መሰረታት?
ነነዌን ከጥፋት ውሃ በኋላ የኖኅ የልጅ ልጆች እንደመሰረቷት ተጽፏል፡፡ “አሦርም ከዚያች አገር ወጣ ፤ነነዌንም የርሆቦትን ከተማ ካላህን በነነዌና በካላህም መካከል ሬሴንን ሰራ፡፡” (ዘፍ ፲፥፲፩)
ነነዌ በመጽሐፍ ቅዱስ ምን ታሪክ አላት?
ነነዌ በንጉሡ በሕዝቅያስ ዘመን እግዚአብሔርን ተገዳድሮ በገዛ ልጆቹ እጅ የተገደለው የሰናክሬም አገር ናት፡፡ “የአሦርም ንጉሥ ሰናክሬም ተነስቶ ሄደ፤ ተመልሶም በነነዌ ተቀመጠ፤ በአምላኩም በናስራክ ቤት ሲሰግድ ልጆቹ አድራሜሌክና ሳራሳር በሰይፍ ገደሉት፡፡” (፪ኛ ነገ ፲፱፥፴፭–፴፮)፡፡ ነነዌ ነቢዩ ናሆም ደጋግሞ ያነሳት ከተማ ናት፡፡(ናሆም ፩፥፩–፲፬ ፣ ናሆም ፪፥፰ ፣ ናሆም ፫፥፩) ነቢዩ ናሆም መጽሐፉን ሲጀምር “ስለነነዌ የተነገረ ሸክም” ብሎ ነው ፡፡ ነቢዩ ሶፎንያስም ነነዌን ከኢትዮጵያ ጋር በአንድ ምዕራፍ አንስቷታል፡፡” እናንተም ኢትዮጵያውያን በሰይፌ ትገደላላችሁ፤ እርሱም በሰሜን ላይ እጁን ይዘረጋል ፤ አሦርንም ያጠፋል ፤ ነነዌንም ባድማ እንደበረሃም ደረቅ ያደርጋታል” (ሶፎ፪፥፲፬)፡፡
ይህች ነቢያት ደጋግመው ያነሷት ከተማ በነቢዩ በዮናስ ደግሞ የበለጠ ታውቃለች፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን የነነዌ ሰዎች ቢበድሉ እና በኃጢአት ቢተዳደፉ፣ ይመለሱ ዘንድ ወድዶ ነቢዩ ዮናስን ወደ ነነዌ ሄዶ እንዲያስተምራቸው አዝዞታል፡፡ “የእግዚአብሔርም ቃል ወደአማቴ ልጅ ወደ ዮናስ እንዲህ ሲል መጣ፡፡ ተነስተህ ወደዚያች ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደነነዌ ሂድ፤ ክፋታቸው ወደፊቴ ወጥቷልና በእርሷም ላይ ስበክ፡፡” (ዮናስ ፩፥፩–፫ ) የነነዌ ሰዎች በደላቸው በዝቶ ነበርና፣ ስርቆቱ፣ ዝሙቱ ፣ ሐሰቱ፣ ግድያው፣ አምልኮ ጣኦቱ፣ ግፉና በደሉ ምድሪቱን ስለሞላት እግዚአብሔር አምላክ “ክፋታቸው ወደፊቴ ወጥቷል” ብሎ ተናገረ ፡፡ ለእግዚአብሔር ጥሪ የዮናስ መልስ ግን የተለየ ነበረ፡፡ አንተ መሐሪ ነህ፤ እኔ ተናግሬ አንተ ምረሐቸው ቢድኑ ሐሰተኛ ነቢይ ታስብለኛለህ ብሎ ከእግዚአብሔር ፊት ይኮበልል ዘንድ ተነሳ፡፡ “ዮናስ ግን ከእግዚአብሔር ፊት ወደ ተርሴስ ይኮበልል ዘንድ ተነሳ… ወደ ዩኢዩጴ ወረደ። ወደ ተርሴስ የምታልፍ መርከብ አገኘ፤ ከእግዚአብሔርም ፊት ኮብልሎ ከእነርሱ ጋር ወደተርሴስ ይሄድ ዘንድ ዋጋ ሰጥቶ ገባ” (ዮና ፩፥ ፫)፡፡ አሁን ከፀሐይ መሰወር ይቻላል? አሁን እግዚአብሔር የሌለበት ቦታ አለን? ቅዱሳን አበው “ዮናስ አባቱን አዳምን መሰለ፡፡አዳም ከእግዚአብሔር ይሰወር ዘንድ ዛፍ ስር እንደተሸሸገ ዮናስም መርከብ ስር ተሸሸገ” ይላሉ፡፡
በእውነት ዮናስ የዋህ ነው፤ እንዲያው ገንዘቡን አወጣ፤ ጉልበቱንም ጨረሰ፡፡ቅዱስ ዳዊት ከእግዚአብሔር መሰወር እንደማይቻል ሲነግረን እንዲህ ብሏል፡፡ “አቤቱ ከመንፈስህ ወዴት እሄዳለሁ ከፊትህስ ወዴት እሸሻለሁ ወደሰማይ ብወጣ አንተ በዚያ ነህ ወደሲኦልም ብወርድ አንተ በዚያ አለህ እነደ ንስር የንጋትን ክንፍ ብወስድ እስከ ባሕር መጨረሻም ብበርር በዚያ እጅህ ትመራኛለች፤ ቀኝህም ትይዘኛለች” (መዝ ፻፴፰፥፯–፲)፡፡ እግዚአብሔር ያዘዘውን መንገድ ትቶ በራስ መንገድ መጓዝ ተገቢ አይደለምና እግዚአብሔር አምላካችን ለዮናስ መታዘዝን ያስተምር ዘንድ ግዑዛን ፍጥረታቱ ዮናስን እንዲይዙት አዘዘ፡፡ “እግዚአብሔር በባሕሩ ላይ ታላቅ ንፋስ አመጣ፤ በባሕሩ ላይም ታላቅ ማዕበል ሆነ። መርከቢቱም ልትሰበር ቀረበች፤ መርከበኞችም ፈሩ፤ እያንዳንዱም ወደ አምላኩ ጮኸ፤ መርከቢቱ እንድትቀልላቸው በውስጧ የነበረውን ዕቃ ወደ ባሕር ጣሉት፤ ዮናስ ግን ወደ መርከቡ ውስጠኛ ክፍል ወርዶ ነበር፤ በከባድ እንቅልፍም ተኝቶ ነበር።” (ዮና ፩፥፬) ለእግዚአብሔር ሁሉ ይታዘዝለታል፤ ንፋሱ፣ ባሕሩ፣ ማዕበሉ… እርሱ የሁሉ አስገኝ ነውና፡፡ ዮናስን ያሳፈሩት መርከበኞች የሚደነቁ ናቸው፡፡ ታሪካቸው መልካም ልብ እንዳላቸው ያሳያል፤ እንዴት?
-
መርከቡ ሲናወጥ ለጸሎት መቆማቸው የልባቸውን መልካምነት ያሳያል፡፡
-
የመርከቧ አለቃ ዮናስን የቀሰቀሰበት ቃል እንዲህ የሚል ነበር ፡– “እንዳንጠፋ እግዚአብሔር ያስበን እንደሁ ተነስተህ አምላክህን ጥራ” (ዮና ፩፥፮ )፡፡ይህም የልቦናውን ቅንነት የሚያሳይ ነው፡፡
-
መርከበኞቹ ባሕሩ የተናወጠው እና ማዕበሉ የተነሳው በኃጢአታችን ነው ማለታቸውም ግሩም ልብ እንዳላቸው ያሳያል፡፡ “እርስ በእርሳቸውም ይህ ክፉ ነገር በማን ምክንያት እንዳገኘን አናውቅ ዘንድ ኑ እጣ አንጣጣል ተባባሉ” (ዮና ፩፥፯ )፡፡ ይህ የሚገርም ነው! መርከበኞቹ ያናወጠን የአየሩ ጸባይ ነው፤ የነፋሱ ሁኔታ ነው አላሉም። ይህ መናወጥ የደረሰብን በበደላችን ነው አሉ እንጂ! አንዲህ ያለ ወደ ራስ የሚመለከት ልብ ለሁላችን ያድለን፡፡
-
መርከበኞቹ በሌላ ሰው ላይ ለመፍረድ የማይቸኩል ልብ ነበራቸው፤ እናም ዕጣ እንጣጣል ተባባሉ! “ዕጣም ተጣጣሉ ፤ ዕጣውም በዮናስ ላይ ወደቀ” (ዮና፩፥፯)፡፡ በዚህ ጊዜም አንተ ኃጢአተኛ ከእኛ ተለይ ብለው ሊፈርዱበት አልወደዱም፡፡ መርከቧ እየተናወጠች እነርሱ በአክብሮት ለዮናስ ጥየቄያቸውን ደረደሩለት እንጂ! “ይህ ክፉ ነገር በምን ምክንያት እነዳገኘን አባክህ ንገረን፤ ሥራህ ምንድን ነው? ከወዴት መጣህ? አገርህ ወዴት ነው? ከማን ወገን ነህ ?” (ዮና ፩፥፰) ፡፡ ዮናስ ስለ እራሱ አንዲህ አለ፤ “እኔ ዕብራዊ ነኝ ባሕሩንና የብሱን የፈጠረውን የሰማይን አምላክ እግዚአብሔርን አመልካለሁ….ከእግዚአብሔር ኮብልያለሁ…” (ዮና፩፥፱)፡፡ ዳግመኛም ይህን ስለምን አደረግህ? አሉት ።ማዕበሉ አልቆመም፤ እጣው ዮናስ ላይ ወጥቷል፤ ቢሆንም መርከበኞቹ ግን አልፈረዱበትም! “አትፍረዱ ይፈረድባችኋል” የሚለውን ቃል ሳይማሩት ከልባቸው መልካምነት የተነሳ ለፍርድ አልተነሱም፡፡ ይልቁን ዮናስን ስለራሱ እንዲፈርድ ተውት አንጂ። “ሞገዱ ከእኛ ጸጥ አንዲል ምን እናድርግብህ ?” ነው ያሉት…. “ዮናስም አንስታቸሁ ወደባሕር ጣሉኝ፤ ባሕሩ ጸጥ ይልላቸኋል” (ዮና ፩፥፲፩–፲፪) አላቸው፡፡
-
መርከበኞቹ ዮናስ በራሱ ላይም ከፈረደ በኋላ ከመርከቡ አንስተው ሊወረውሩት አልወደዱም፡፡ እንዲያውም “ወደ ምደር ለመድረስ አጥብቀው ቀዘፉ” ነው የሚለው ፡፡ (ዮና ፩፥፲፫) የባሕሩ መናወጥ ይበልጥ ሲበረታ ግን፣ መርከበኞቹ “አቤቱ ንጹሁን ደም በእኛ ላይ አንዳታደርግ እንለምንሃለን” ካሉ በኋላ ዮናስ በራሱ ላይ የፈረደውን አደረጉበት፡፡ ልክ ዮናስ ወደ ባሕር ሲወረወር ማዕበሉ ጸጥ አለ! መርከበኞቹና መርከቧም ፍጹም ሰላም አገኙ፡፡
ወደ ባሕር የተወረወረው ዮናስ ሌላ ነገር ገጠመው ። “እግዚአብሔርም ዮናስን የሚውጥ ታላቅ አሳ አሰናዳ፤ ዮናስም በአሳው ሆድ ውሰጥ ሦስት ቀንና ሌሊት ነበረ፡፡” (ዮና ፪፥፩–፲፩) ዮናስ በአሳው ሆድ ውስጥ ለጸሎት ቆመ ! አሳውም እግዚአብሔር እንዳዘዘ ዮናስን ወስዶ በነነዌ ተፋው፡፡ ሩህሩህና ይቅር ባይ የሆነው አምላካችን እግዚአብሔር ከፊቱ የኮበለለ ዮናስን በኃይሉ መልሶ ለአገልግሎት አቆመው ። “ዮናስም ተነስቶ እንደ አግዚአብሔር ቃል ወደ ነነዌ ሄደ፤ ነነዌም የሦስት ቀን መንገድ ያህል ታላቅ ከተማ ነበረች ፤ ዮናስም የአንድ ቀን መንገድ ያህል ወደ ከተማይቱ ውስጥ ሊገባ ጀመረ፤ ጮሆም በሦስት ቀን ውስጥ ነነዌ ትገለበጣለች አለ” (ዮና ፫፥፫)
የሚገርመው ነገር የነነዌ ሕዝብ መምህር ያጣ፣ ነገር ግን ቢማር የሚመለስ ልብ ያለው ሆኖ ተገኘ! ዮናስ ስብከቱን አንደጀመረ ሕዝቡ ሁሉ በንስሐ አና በጾም በእግዚአብሔር ፊት ቆሙ፡፡ ንስሐው እና ጾሙ ከተርታው ሕዝብ አስከ ንጉሡ ድረስ ነበረ፡፡ “የነነዌ ሰዎች እግዚአብሔርን አመኑ፤ ለጾም አዋጅ ነገሩ፤ ከታላቁ አሰከ ታናሹ ማቅ ለበሱ፡፡ ወሬው ወደ ንጉሡ ደረሰ፡፡ አርሱም ከዙፋኑ ተነስቶ መጎናጸፊያውን አወለቀ፤ ማቅም ለበሰ፤ በአመድም ላይ ተቀመጠ፤ አዋጅም አስነገረ፡፡ በነነዌም ውሰጥ የንጉሡንና የመኳንንቱን አዋጅ አሳወጀ፡፡ እንዲህም አለ ሰዎችና እንስሶች ላሞችና በጎች አንዳች አይቅመሱ፤ አይሰማሩ፤ ውኃም አይቅመሱ፡፡ ሰዎችና እንስሶች በማቅ ይከደኑ፤ ወደ እግዚአብሔርም በብርቱ ይጩሁ፡፡ ሰዎችም ሁሉ ከክፉ ሥራቸውና ከግፍ ይመለሱ፤ እኛ አንዳንጠፋ እግዚአብሔርም ተመልሶ ይጸጸት እንደሆነ ከጽኑ ቁጣውም ይመለስ እንደሆን ማን ያውቃል?” ( ዮና ፫፥፭)
የነነዌ ሕዝብ ታላቅ ንሰሐን አደረገ ፡፡ በእውነቱ ግሩም ድንቅ ንስሐ ነው። በአንድ ጊዜ ከ ፻፳ ሺህ የሚበልጠው የነነዌ ነዋሪ በጾም ወደ እግዚአብሔር ተመለሰ፡፡ ጾሙ ጡት የሚጠቡ ሕጻናት እና በበረት ያሉ እንስሳትንም ጭምር ያሳተፈ ነበር፡፡ በነነዌ የተጾመው ከጥሉላት ብቻ አልነበረም፣ ከመላው ምግብ አንጂ! በነነዌ የተጾመው ከምግብ ብቻ አልነበረም፤ ከማንኛውም ክፉ ሥራ እንጂ! ለመሆኑ ይህን ቁጥሩ እጅግ የበዛ የነነዌን ሕዝብ በእግዚአብሔር ፊት በጾም ያንበረከከው የስንት ሰዓት ስብከት ነበር? ስንት ገጽ የንስሐ መጽሐፍ ነበር? ስንት መንፈሳዊ ጉባኤ ነበር? ስንት የንስሐ መዝሙር ነበር? ስንት ሰባኪያን ነበሩ? የሚገርመው ሰባኪው አንድ ዮናስ፣ ስብከቱም አንድ አረፍተ ነገር ነበር፡፡ “በሦስት ቀን ውሰጥ ነነዌ ትገለበጣለች” የሚል ፡፡ (ዮና ፫፥፬) ስብከቱም የአጭር ሰዓት ስብከት ነበር፡፡ በእውነቱ አንዲህ ያለ ሕዝብ በአኛ ላይ ይፈርዳል፡፡ ሦስት መቶ ስድሳ አምስት ቀን ንስሐ ግቡ እየተባለን ንስሐ ሳንገባ በቀረን በእኛ ላይ ይፈርዳሉ፡፡ ስንት ቅዱሳት መጽሐፍ ተ ጽፈውልን፥ መጽሐፍ ቅዱሱ፣ ድርሳኑ፣ ገድሉ፣ ተአምራቱ፣… በዘመናችን ደግሞ በመጽሔቱ፣ በጋዜጣው፣ በድረ ገጹ … ሁሉ ቀርቦልን ንስሐ ሳንገባ በቀረን በእኛ ላይ ይፈርዳሉ፡፡ በርካታ ጉባኤያት ተዘጋጅተውልን፣ ሺህ ጊዜ የንስሐ መዝሙር ተዘምሮልን፣ ንስሐ ሳንገባ በቀረን በእኛ ላይ ይፈርዳሉ፡፡ በእርግጥ ጌታችን ለዚህ ነው “የነነዌ ሰዎች በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነስተው ይፈርዳሉ፤ በዮናስ ስብከት ንስሐ ገብተዋልና” ያለን ፡፡ የነነዌ ሰዎች ከኖኅ ዘመን ሰዎች ይለያሉ፤ የነነዌ ሰዎች ከሰዶም ሀገር ሰዎችም ይለያሉ፡፡ የኖኀ ዘመን ሰዎች ኖኅን ባይሰሙት በፈላ ውኃ ጠፍተዋል፡፡ የሰዶም ሰዎችም ሎጥን ባይሰሙት በእሳት ጠፍተዋል፡፡ የነነዌ ሰዎች ግን ዮናስን ቢሰሙት ድነዋል ፤ ይህም ሰምቶ በመጠቀምና ባለመጠቀም መካከል ያለውን ልዩነት ያሳየናል፡፡
የነነዌ ሰዎች ጾምና ጸሎት በእግዚአብሔር ፊት ደረሰ፤ ምሕረትም ተደረገላቸው፡፡ “እግዚአብሔርም ከክፉ መንገዳቸው እንደተመለሱ ሥራቸውን አየ ፤ እግዚአብሔርም ያደርግባቸው ዘንድ በተናገረው ክፉ ነገር ተጸጽቶ አላደረገውም“ (ዮና ፫፥፲)፡፡ ነነዌ በሦስት ቀን ጾም ዳነች፡፡ የዚያ ታላቅ ሱባኤ ማብቂያው ደስታ ሆነ፡፡ በዚያ ቀን በሰማይ አንዴት ያለ ደስታ ሆኖ ይሆን! “ንስሐ ከማያስፈልጋቸው ዘጠና ዘጠኝ ጻድቃን ይልቅ ንስሐ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ በሰማይ ታላቅ ደስታ ይሆናል። “(ሉቃ ፲፭፥፯) የሚገርመው በሰማይና በምድር ታላቅ ደስታ በሆነበት በዚያ ቀን አንድ ሰው ብቻ ነበር አዝኖ የተገኘው። “ይህም ዮናስን ከቶ ደስ አላሰኘውም፤ እርሱም ተቆጣ” (ዮና ፬፥፩) ሕዝብ ሲድን፣ ሕዝብ በሰማይ ያንዣበበ እሳት ሲመለስለት የእግዚአብሔር ነቢይ እንዴት ይቆጣል?! አበው ይህንን የዮናስ ቁጣ በሉቃስ ፲፭ ላይ ካለው የጠፋው ልጅ ታላቅ ወንድም ቁጣ ጋር ያመሳስሉታል። (ሉቃ፲፭፥፲፩–፴፪)” ተቆጣ ሊገባም አልወደደም“ ይላል፡፡ የጠፋው ልጅ አባት ግን እንዲህ ነው ያለው “ይህ ልጄ ሞቶ ነበር፤ ሕያው ሆኗል፤ ጠፍቶ ነበር ተገኝቷል፤ ፍስሐ እናድርግ!”
ዮናስ በየዋህነቱ ሐሰተኛ ነቢይ ልባል ነው ብሎ ቢቆጣም እግዚአብሔር ሊያስተምረው ወደደ። እናም ዮናስ ባረፈበት ቦታ ላይ ቅል አበቀለለት። “በራሱ ላይ ጥላ እንድትሆን እግዚአብሔር ቅሊቱን በዮናስ ላይ ከፍ ከፍ አደረጋት፤ ዮናስ ስለቅሊቱ እጅግ ደስ አለው፤ በነጋው ወገግ ባለ ጊዜ እግዚአብሔር ትልን አዘጋጀ፤ እርስዋም ቅሊቱን እስክትደርቅ ድረስ መታቻት፤ ፀሐይም በወጣ ጊዜ እግዚአብሔር ትኩስ የምሥራቅ ንፋስ አዘጋጀ፤ ዮናስም እስኪዝል ድረስ ፀሐይም ራሱን መታው” (ዮና ፬፥፮–፰) በዚህ ያዘነ ዮናስ ከቁጣው ብዛት ሞትን ለመነ፡፡ አሁንም እግዚአብሔር ዮናስን እንዲህ ብሎ አስተማረው። “አንተ ትበቅል ዘንድ ላልደከምህባት፣ ላላሳደግሃትም በአንድ ሌሊት ለበቀለች በአንድ ሌሊትም ለደረቀችው ቅል አዝነሃል፤ እኔስ ቀኝና ግራቸውን የማይለዩ ከአንድ መቶ ሃያ ሺህ የሚበልጡ ሰዎችና እንስሳት ላሉባት ለታላቂቱ ከተማ ለነነዌ አላዝንምን ? አለው” (ዮና ፬፥፲)
የነነዌ ታሪክ እግዚአብሔር አምላካችን ሰውን ምን ያህል እንደሚፈልግ የሚያስተምር ነው፡፡ እርሱ አምላካችን በርህራሄው መርከበኞቹን፣ ዮናስን፣ የነነዌ ሰዎችን በሙሉ እንዴት እንደፈለገ እና እንዴት እንዳዳነ ስናይ ለእኛ ለሁላችን ያለውን ፍጹም ፍቅር እንረዳለን፡፡ ብርሃነ አለም ቅዱስ ጳውሎስ እንደተናገረ “እርሱ ሰዎች ሁሉ እንዲድኑና እውነቱን ወደማወቅ እንዲደርሱ የሚወድ የፍቅር አምላክ ነው” (፩ጢሞ ፪፥፬) ፡፡ በእውነተኛ ንስሐ፣ በተሰበረ ልብ፣ በጾምና በጸሎት ወደ እርሱ ለሚመለሱ ፍጹም ይቅርታን የሚሰጥ ነው፡፡ የነነዌ ታሪክ የጾምን ፍጹም ኃይል እና ዋጋ የሚያስተምረን ነውና ይህንኑ እያሰብን ጾመን እንድንጠቀም የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የእመቤታችን አማላጅነት፣ የቅዱሳን ጸሎትና ምልጃ ከሁላችን ጋር ይሁን አሜን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር።