“ኦ ገብር ኄር ወምእመን ዘበውኁድ ምእመነ ኮንከ ዲበ ብዙኅ እሠይመከ” ማቴ. ፳፭፥፳፫።
በመ/ር ሳሙኤል ተስፋዬ
ሚያዚያ 1 ቀን 2008 ዓ.ም.
የዐቢይ ጾም ስድስተኛ ሳምንት ገብር ኄር ይባላል። ገብር ኄር ማለት ታማኝ አገልጋይ ማለት ነው። ስለ ታማኝ አገልጋይ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዓለም ስንኖር ለፈጣሪያችን ያለንን ታማኝነትና የምናገኘውን ዋጋ በመዋዕለ ሥጋዌው አስተምሯል። ቅዱስ ያሬድ ለዜማ መክፈያነት የዐቢይ ጾምን ሳምንታትን ሲከፍል ገብር ኄርን ተጠቅሟልና እኛም ስለ ገብር ኄር ጥቂት እንበል።
ልዑል እግዚአብሔር አምላካችን በነቢዩ አንደበት አድሮ፤ “እከሥት በምሳሌ አፉየ፤ ወእነግር አምሳለ ዘእምትካት፤ አንደበቴን /ነገሬን/ በምሳሌ እገልጣለሁ፤ ከቀድሞ ጀምሮ የነበረ ታሪክና ምሳሌ እናገራለሁ” አለ። ይህም ማለት ወንጌልን በምሳሌ አስተምራለሁ፤ በመልከ ጼዴቅ ዘመን አስቀድማ የተሠራችና ታይታ የጠፋችውን ወንጌልን እናገራለሁ። ይህን ታላቅ ምሥጢር ሐዋርያው ሲያብራራ “. . . ከመ በአሚን ያጸድቆሙ እግዚአብሔር ለአሕዛብ አቅደመ አሰፍዎቶ ለአብርሃም ከመ ቦቱ ይትባረኩ ኲሎሙ አሕዛብ፤ . . . በአንተ አሕዛብ ሁሉ ይባረካሉ ብሎ ወንጌልን ለአብርሃም አስቀድሞ ሰበከ” ብሏል ገላ. ፫፥፰፣ መዝ. ፸፯፥፪።
በዚሁ መሠረት ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌለ መንግሥተ ሰማያትን ለልዩ ልዩ ወገኖች በልዩ ልዩ ምሳሌ አስተምሯል፤ ከላይ በተገለጠው ኃይለ ቃል መነሻነት ሁለት ምሳሌያትና አንድ ቃለ ትንቢት ቀርበዋል። ከምሳሌያቱ የመጀመሪያው በዐሥሩ ደናግል አንጻር የቀረበው ምሥጢር ሲሆን፤ ሌላኛው ደግሞ ወጥተው ወርደው ነግደው ያተርፉበት ዘንድ ገንዘቡን ስለሰጠ አንድ ነጋዴ የሚናገረው ነው።
የትንቢቱ ምሥጢራዊ ይዘት የሚያስረዳውም ስለ ኅልቀተ ዓለም አይቀሬነት ነው። ስለሆነም በዚህ ዕትማችን ወጥተው ወርደው ነግደው እንዲያተርፉበት ከጌታቸው የተሰጣቸውን መክሊት ስለተቀበሉት አገልጋዮች ሕይወት እንመለከታለን። ፈጣሪያችን አእምሮውን ለብዎውን /ማስተዋሉን/ ያድለን።
ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀመዛሙርቱ ያስተማራቸው ምሳሌያዊ ትምህርቶች በቅዱስ መጽሐፋችን በሰፊው ተጽፈው እናገኛለን። የእነዚህ ትምህርታዊ ምሳሌዎች መሠረታዊ አሳብና ዓላማም የእግዚአብሔርን መንግሥት የምናገኝበትን የታማኝነትን ሥራ እንዴት መሥራት እንደሚገባንና መሥራትም እንደምንችል ማስተማር ነው።
ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለመንግሥተ ሰማያት ምሥጢር ያስተማራቸው ብዙ ምሳሌዎች ያሉ ሲሆን ከእነዚህ ብዙ ምሳሌያዊ ትምህርቶች መካከልም እንዲያተርፉበት መክሊት ስለተሰጣቸውና ስለተመሰገኑት መልካም አገልጋዮች፣ እንዲሁም መክሊቱን በመቅበሩ ምክንያት በጌታው ስለተወቀሰውና ፍርድን ስለተቀበለው ሰነፍ ሰው ታሪክ፣ የታሪኩም ምሥጢር ምን እንደሚመስል የተጻፈው ትምህርት ነው።
ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህንን ምሳሌ የተናገረው /ያስተማረው/ በሚከተለው መልኩ ነበር፤ ‹‹ወደ ሌላ ሀገር የሚሔድ ሰው ባሮቹን ጠርቶ ያለውን ገንዘብ እንደሰጣቸው እንዲሁ ይሆናልና ለእያንዳንዱ እንደ ዓቅሙ ለአንዱ አምስት መክሊት ለአንዱ ሁለት ለአንዱም አንድ ሰጠና ወደ ሌላ ሀገር ወዲያውኑ ሔደ። አምስት መክሊትም የተቀበለው ሔዶ ነገደበት ሌላም አምስት አተረፈ፣ እንዲሁም ሁለት የተቀበለው ሌላ ሁለት አተረፈ፣ አንድ የተቀበለው ግን ሔዶ ምድርን ቆፈረና የጌታውን ገንዘብ ቀበረ።
ከብዙ ዘመንም በኋላ የእነዚያ ባሮች ጌታ መጣና ተቆጣጠራቸው። አምስት መክሊት የተቀበለውም ቀረበና ሌላ አምስት መክሊት አስረክቦ፡– ጌታ ሆይ አምስት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፤ እነሆ ሌላ አምስት መክሊት አተረፍሁበት አለ። ጌታውም፡– መልካም አንተ በጎ ታማኝ ባሪያ በጥቂቱ ታምነሃል በብዙ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው። ሁለት መክሊት የተቀበለው ደግሞ ቀርቦ፡– ጌታ ሆይ ሁለት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር። እነሆ ሌላ ሁለት መክሊት አተረፍሁበት አለ። ጌታውም፡– መልካም አንተ በጎ ታማኝ ባሪያ በጥቂቱ ታምነሃልና በብዙ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው።
አንድ መክሊትም የተቀበለው ደግሞ ቀርቦ፡– ጌታ ሆይ ካልዘራህበት የምታጭድ ካልበተንህበትም የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው መሆንህን አውቃለሁ፤ ፈራሁም ሔጄም መክሊትህን በምድር ቀበርሁት፤ እነሆ መክሊትህ አለልህ አለው። ጌታውም መልሶ እንዲህ አለው፡– አንተ ክፉና ሐኬተኛ ባሪያ ካልዘራሁበት እንዳጭድ ካልበተንሁበትም እንድሰበስብ ታውቃለህን? ስለዚህ ገንዘቤን ለለዋጮች አደራ ልትሰጠው በተገባህ ነበር። እኔም መጥቼ ያለኝን ከትርፉ ጋር እወስደው ነበር። ስለዚህ መክሊቱን ውሰዱበት ዐሥር መክሊትም ላለው ስጡት። ላለው ሁሉ ይሰጠዋልና ይበዛለትማል። ከሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል። የማይጠቅመውንም ባሪያ በውጭ ወዳለው ጨለማ አውጡት፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል የሚል ነው።
መክሊት ጥንት የክብደት መለኪያ ነበር። አንድ መክሊት 30 ኪሎ ግራም ያህል ነው። በዚህ ምሳሌ ላይ እንደተገለጸውም መክሊት የሚለው ቃል ገንዘብን ያመለክታል።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ምሳሌ ውስጥ እርሱን የምናገለግል ሁላችን እንደየዓቅማችን ማድረግ የሚገባንን መንፈሳዊ የአገልግሎት ሥራንና በአገልግሎታችን ውጤታማ በመሆናችንም ከእርሱ የምናገኘውን ዘለዓለማዊ ክብርና ዋጋን እንዲሁም መሥራት የሚገባንን ባለማድረጋችንም ምክንያት የሚገጥመንን መለኮታዊ ቅጣትን አመልክቶናል።
በዚህ ምሳሌ ውስጥ ባለ አምስት የተባለው በቂና ፍጹም ትምህርት ተምሮ ሌላውን መክሮ አስተምሮ ራሱን አስመስሎ የተካ ያወጣ ነው። በተመሳሳይም ባለ ሁለት የተባለው እንደ መጀመሪያው ሁሉ ተምሮ ሌላውን መክሮ አስተምሮ ራሱን አስመስሎ ያወጣ ሲሆን ባለ አንድ የተባለው ደግሞ ተምሮ ሳያስተምር የቀረ በስንፍና በቸልተኝነት በማን አለብኝነት ሕይወት ተገድቦ የቀረ ሰው ነው።
በመሆኑም የባለ አምስትና የባለ ሁለት መክሊት ባለቤቶች የሆኑት ወጥተው ወርደው ደክመው፣ መከራ መስቀልን ሳይሰቀቁና ሳይፈሩ፤ ወድደው ፈቅደው የጀመሩትን አገልግሎት በማክበር ሕይወታቸውን ለታመነው አምላክ አደራ በመስጠት የተማሩትን ፍጹም ትምህርት ለሌላው አስተምረው፣ ሠርተው ያገኙትን ለሌላው አካፍለው ወገናቸውን እንደራሳቸው አድርገው ሲመለከቱ ባለ አንድ መክሊት የተባለው ግን ዓላውያን እሳት ስለት አሳይተው ሃይማኖቴን ሲያስክዱኝ መናፍቃን ተከራክረው ምላሽ ቢያሳጡኝ ብሎ ፈርቶ ሃይማኖቱን በልቡ ከመደበቅና ከመሠወር በቀር የተማረውን ትምህርት ሠርቶ ያገኘውን ሀብት ንብረት ለሌላው ሊያካፍልና የተሰጠውን አደራም ሊወጣ አልወደደም።
በምሳሌው ውስጥ እንደተገለጠው ሁለቱ ወገኖች በተሰጣቸው መክሊት ባለሁለቱ አራት ባለአምስቱ ዐሥር ማትረፋቸውን ለጌታቸው በገለጡ ጊዜ የመክሊቱ ባለቤት እጅግ አድርጎ እንዳመሰገናቸው ከላይ አንብበናል።
ይህ የመክሊቱ ባለቤት የተባለው ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲሆን የተሰጣቸውን ሓላፊነት በአግባቡና በጽንአት ለተወጡት ሁሉ እርሱ ፍጹም ዋጋን የሚሰጣቸው መሆኑን ያመለክታል። ይህም ሁኔታ “አንተ በጎ ታማኝ ባሪያ በጥቂቱ ታምነሃል በብዙ እሾምሃለሁ። ወደ ጌታህ ደስታ ግባ” በሚል ታላቅ የምስጋና ቃል ተገልጧል። ይህ ቃል በሃይማኖትና በበጎ ምግባር ለእግዚአብሔር የታመኑ ሁሉ ዘለዓለማዊና ፍጹም ደስታ ወደሚገኝበት መንግሥተ ሰማያት ለመግባት ለሚያደርጉት የእምነት ጉዞ እጅግ ተስፋ የሆነ ቃል ነው።
በዚህ ምንባብ ላይ እንደተገለጸው እግዚአብሔር አምላክ ለሁላችንም እርሱን የምናገለግልበትንና ለእርሱ በመታመን ዘለዓለማዊ ክብርን የምናገኝበትን ዕውቀትን፣ ማስተዋልን፣ እምነትን፣ ተስፋን፣ የሥነ ምግባር ሀብትን፣ ልዩ ልዩ ስጦታዎችን እንጠቀምባቸው ዘንድ ለእኛ ለሰው ልጆች እንደየዓቅማችን መጠን ሰጥቶናል። እነዚህ ሁሉ ነገሮች የሥጋችንን ምኞት ለማስፈጸም የተሰጡ ሳይሆኑ ነፍሳችን የምትከብርበትን መልካም ሥራን የምንሠራባቸው መሣሪያዎቻችን ናቸው።
በመሆኑም እርሱ በሰጠን የአገልግሎት በር ጸጋ በታማኝነት በማገልገል በሕይወት ዘመናችን ሁሉ መንፈሳዊውን ሀብት የምናተርፍ እንሆን ዘንድ የተላለፈልን አምላካዊ ምክር ነው። ምክንያቱም እኛ የተጠራነው ፍሬ ልናፈራና ሌላውንም ልናተርፍ መልካም ሥራን ልንሠራ እንጂ የሥጋችንን ፈቃድ በመከተል የኃጢአት ባሮች ልንሆን አይደለም። መጽሐፍ እንዲህ አለ “ወኲሉ ዘከመ ተጸውአ ከማሁ ለየሀሉ፤ ሁሉ እንደተጠራ እንዲሁ ይኑር” /፩ኛ ቆሮ. ፯፥፳/።
ከላይ እንደተመለከትነው በልዑል አምላክ በእግዚአብሔር አንደበት አንተ በጎ ታማኝ አገልጋይ በጥቂቱ ታምነሃልና በብዙ እሾምሃለሁ መባልን የመሰለ አስደሳችና አስደናቂ ነገር የለም። ይህ ደግሞ የሚገኘው ሃይማኖትን በሥራ በመግለጥ እንጂ ሃይማኖትን በልቡና በመያዝ ብቻ /ሙያ በልብ ነው/ በማለት ብቻ የሚገኝ አይደለም። ከእነዚህ እንደአቅማቸው መጠን መክሊት ተሰጥቷቸው በትጋታቸውና በቅንነታቸው ሌላ መክሊት ካተረፉት በጎና ታማኝ አገልጋዮች የምንማረው እውነታም ይህ ነው። በብዙ ለመሾም ለማደግ ለመጽደቅ በጥቂቱ መታመን መፈተን መጋደል ግድ ነው።
አንድ መክሊት የተሰጠውን ሰው ስንመለከተው ጌታውን ጨካኝና ፈራጅ አድርጎ ከመቁጠር ውጪ በተሰጠው መክሊት ወጥቶ ወርዶ ሊያተርፍ አልወደደም። መክሊቱንም ባስረከበ ጊዜ በጌታው ላይ የተናገራቸው ቃላት የእርሱን አለመታዘዝና አመጸኝነት ይገልጡ ነበር። በመሆኑም ይህ ሰው በጥቂቱ መታመን ያቃተውና በአስተሳሰቡ ደካማነት እጅግ የተጎሳቆለ ሰው ነው።
በዚህ ምሳሌ መሠረት ይህ ባለ አንድ መክሊት የተባለው ሰው ዓላውያን ነገሥታት እሳት ስለት አሳይተው ቢያስክዱኝ መናፍቃን ተከራክረው መልስ ቢያሳጡኝ በማለት ሃይማኖቱን በልቡ ሸሽጎና ቀብሮ በተቀደሰ ተግባር ሳይገልጠው ከመያዙ ባሻገር በጌታ ፊት በድፍረት ቆሞ አንተ ሕግ ሳትሠራ በአእምሮ ጠባይዕ አውቃችሁ፤ መምህራንንም ሳትመድብ በሥነ ፍጥረት ተመራምራችሁ በሠራችሁ ብለህ የምትፈርድ ጽኑ ጨካኝ መሆንክን አውቃለሁና ፈርቼ ሃይማኖቴን በልቡናዬ ይዠዋለው በአዕምሮዬ ጠብቄዋለሁ የሚል ሃይማኖቱን ግን በሥራ የማይገልጥ ሰነፍ ሰውን ያመለክታል።
ለዚህ ዓይነት ሰው የጌታ መልስ ደግሞ በምሳሌው መሠረት የሚከተለው ነው። እኔ ሕግ ሳልሠራ በአእምሮ ጠባይዕ አውቃችሁ፤ መምህር ሳልሰጥ በሥነ ፍጥረት ተመራምራችሁ አውቃችሁ በሠራችሁት ብዬ የምፈርድ ጽኑ ጨካኝ መሆኔን ታውቃለህን? እንዲህስ ካወቅህ ሹመትክን ልትመልስልኝ ይገባኝ ነበር። ወጥቶ ወርዶ ለሚያስተምር በሰጠሁት ነበር። አሁንም የእርሱን መምህርነት ሹመት ነሥታችሁ (ወስዳችሁ) ለዚያ ለባለ ዐራቱና ለባለ ዐሥሩ ደርቡለት! እርሱን ግን አውጡት የሚል ነው። ምክንያቱም ከበጎ ምግባር የተለየች እምነት የሞተች እንደሆነ ተጽፏልና።
ዛሬም እያንዳንዳችን በዓቅማችን መጠን መክሊት ተሰጥቶናል። ነገር ግን መክሊቱን እንደቀበረው እንደዚያ ሰው የተሰጠንን ቀብረን ለወቀሳና ለፍርድ እንዳንሰጥ በአገልግሎታችን ልንተጋ ይገባናል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህንኑ ሲገልጥ “ወዘሂ ይትለአክ በመልእክቱ፤ ወዘሂ ይሜህር በትምህርቱ. . .፤ አገልግሎት ቢሆን በአገልግሎታችን እንትጋ የሚያስተምርም በማስተማሩ ይትጋ የሚሰጥም በልግሥና ይስጥ” (ሮሜ. ፲፪፥፯) በማለት ተናግሯል።
ለመሆኑ አሁን ባለንበት የስግብግብነት ወቅት ዛሬ ‹‹አንተ በጎ ታማኝ አገልጋይ…›› ተብሎ በእግዚአብሔር ሊመሰገን የሚችል ሰው ማን ይሆን? በእውነት እንዲህ ተብሎ የሚመሰገን በጎና ታማኝ ካህን በጎና ታማኝ መምህር በጎና ታማኝ ምእመን ታማኝ ሰባኪና ታማኝ ዘማሪ ማግኘት ይቻል ይሆንን? ትልቅ መሠረታዊ ሊሆን የሚገባው ጥያቄ ቢኖር ይህ ነው። ምክንያቱም ይህ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት ስለታማኝነት የሁላችንንም ሕይወት የሚዳስስና ሁላችንንም የሚመለከት ነውና። ነገር ግን መቼም አምላካችን ቸር ነውና በየዘመናቱ አንዳንድ ታማኝ አባቶችን እንደማያሳጣን ተስፋ አለን።
ምክንያቱም ዛሬም ቢሆን እንደአባቶቻችን እንደቅዱሳን ሐዋርያት በእምነት፣ በትዕግሥት በፍቅር በተጋድሎ በየውሐት በትሕርምት በጸሊዓ ንዋይ በትሕትናና በትጋት በማገልገል የተሰጣቸውን መክሊት የሚያበዙ አገልጋዮች አሉ። የእነዚህ ክብራቸው በምድርም በሰማይም እጅግ የበዛና ራሳቸውን አስመስለው በትምህርት የወለዷቸው ልጆቻቸውም ለቤተ ክርስቲያን የተወደዱ የተከበሩ ልጆች ናቸው።
ለምሳሌ ነቢየ እግዚአብሔር ሙሴ ነቢየ እግዚአብሔር ኢያሱን፤ ቅዱስ ጴጥሮስ ቀሌምንጦስን፣ ቅዱስ ጳውሎስም ቅዱስ ጢሞቴዎስን ለቤተ ክርስቲያን አበርክተዋል። ሌሎችም አበው ቅዱሳን በወንጌል ቃል መንፈሳውያንና ትጉሃን የሆኑ ምእመናንን በሚገባ አፍርተዋል። ያላመኑትንም አሳምነው ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመመለስ ለዘለዓለማዊ ክብር የበቁ እንዲሆኑ አስችለዋቸዋል። በተሰጣቸው ጸጋም አትርፈው አትረፍርፈው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በሀብተ መንፈስ ቅዱስ እንድትጎበኝ አድርገዋል። የእነርሱም በረከታቸው ረድኤታቸው ቃል ኪዳናቸው ለሌሎች እንዲተርፍ ሆኖላቸዋል።
በመሆኑም ክርስቶስ በደሙ የከፈለውን ወደር የሌለውን ዋጋ ዓለም አምኖና አውቆ ተቀብሎ በክርስትና ሃይማኖት እንዲድንበትና እንዲጠቀምበት በማድረግ እንዲሁም በታማኝነትና በበጎነት አገልግሎታቸው ጥንትም ዛሬም ላለችዋና ወደፊትም ለምትኖረዋ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ድምቀትም ውበትም የሆኑት ቅዱሳን አበው ሊገኙ የቻሉት ከእግዚአብሔር ይልቅ ሰውን ደስ ለማሰኘት በመድከማቸው ሳይሆን የተጠሩበትን ዓላማና የጠራቸውን እርሱን በሚገባ አውቀውና ከልብ ተረድተው ለዘለዓለማዊ ሕይወት ተግተው በመሥራታቸው ነው።
“ወይእዜሰ ለሰብእኑ ነአምን ወአኮ ለእግዚአብሔር ወእምሰኬ እፈቅድ ለሰብእ አድሉ ኢኮንኩ ገብሮ ለክርስቶስ፤ አሁንስ ለእግዚአብሔር ያይደለ ለሰው ብለን እናመናለን፤ ለሰው የማደላ ከሆንኩስ፣ የክርስቶስ ባሪያ /አገልጋይ/ አይደለሁም” /ገላ. ፩፥፲/ በማለት ያስተማረው ለዚህ ነው። ከዚህ ቃል በመነሣት በተለይ ደግሞ በክህነት አገልግሎት ውስጥ ያለ ሰው ከምንም በላይ በከፍተኛ መንፈሳዊ ሓላፊነት ላይ ያለ እንደመሆኑ መጠን በሃይማኖትም በሥነ ምግባርም ለሌላው አርአያ በመሆን እንደ እርሱ ሃይማኖትን ከምግባር ጋር አስተባብረው የያዙ ምእመናንን ማፍራት ማብዛት አለበት። ይህ ሲሆን ብቻ ነው አንተ በጎ ታማኝ አገልጋይ በጥቂቱ ታምነሃልና ወደ ጌታህ ደስታ ግባ ልንባል የምንችለው።
አሁን ባለንበት ወቅት በጎና ታማኝ አገልጋይ መሆን እንዳንችል ብዙ ችግሮች አሉ። የችግሮቹም መሠረታዊ ምንጭ በተጠሩበት ጸንቶ መቆም ፈጽሞ አለመቻልና ለሥጋዊ ጥቅም ብቻ በማድላት ሓላፊነትን መዘንጋት ናቸው። በሥጋዊ አምሮት ፍላጎትና ምርጫ ውስጥ ደግሞ መንፈሳዊ ጸጋንና በረከትን ለማግኘት የሚያስችለንን የታማኝነት ሥራን መሥራት አይቻልምና በታማኝነት ከምናድነው ሰው ይልቅ መክሊታችንን በመቅበር ባለመታመን መሰናክል የምንሆንበት ሰው ሊበዛ እንደሚችል አያጠራጥርም።
በመሆኑም ከእርሱ ዘንድ እንደ ዓቅማችን የተሰጠንን መንፈሳዊ ዕውቀት ሀብትና አገልግሎት ለሌላው በማድረስ መክሊታችንን ልናበዛ የምንችለውና አገልግሎታችን ወይም ክርስትናችን ውጤታማ የሚሆነው ምርጫችንን አውቀን እንደቃሉ ሆነንና ጸንተን ስንገኝ ብቻ ነው። ይህ ባለመሆኑ ነው ዛሬ ብዙዎቻችን በሕይወታችን ሌላውን ማትረፍ አቅቶን በእግዚአብሔርና በሰውም ዘንድ በሚያስወቅስ የስንፍና መንገድ ላይ ቆመን የምንገኘው። ስለዚህም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው “ጌታችሁ በምን ሰዓት እንዲመጣ አታውቁምና እንግዲህ ንቁ”(ማቴ. ፳፬፥፵፪) ብሎናል።
ቃሉን የሰማንና የምናውቅ ሁላችን በሞቱ ላዳነን፣ በልጅነት ጸጋም ላከበረን፣ በትንሣኤውም ላረጋጋን፣ በመስቀሉ ጥልን ገድሎ ከራሱ ጋር ላስታረቀን፣ በውኂዘ ደሙም ሕይወትን፣ ሰላምን፣ ፍቅርን፣ በረከትንና ዘለዓለማዊ ደስታን ለሰጠን አምላካችን በመታዘዝ አቅማችን በሚፈቅደው አገልግሎት ጸንቶ መገኘት ተገቢ ነው። በአገልግሎት የመጽናት ምልክቱ ደግሞ አትራፊነት ነው። ቅዱሳን ነቢያት፣ ቅዱሳን ሐዋርያት፣ ቅዱሳን ሊቃውንት በቤተ ክርስቲያናችን ታሪክ በአትራፊነት ይታወቃሉ። ለማትረፍ ግን ራሳቸውን ለእውነት ለአገልግሎት ለመከራ አሳልፈው በመስጠት ነው፤ በትንሹ መታመን ሲባል የእኛ አገልግሎት ከፈጣሪ ቸርነት ጋር ስለማይመጣጠን ነው፤ በብዙ እሾምሃለሁ ማለቱም በመንግሥተ ሰማያት ለዘለዓለም ከብሮ መኖርን ነው።
ከቅዱሳን ነቢያትም ሐዋርያትም ሰብአ አርድእትም ሊቃውንትም የሰማነውና ያየነው እውነት ምንጊዜም ትጉህ ሠራተኛ የሚሠራው መልካም ሥራ ሁሉ ለቤተ ክርስቲያንም ለሀገርም የሚሰጠው ጥቅም እጅግ ከፍተኛ መሆኑን ነው። በመሆኑም በዚህ ዘመን ልዑል እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንን፤ ምእመናንን፤ ሀገርንና ሕዝብን ለመምራት የጠራንና የመረጠን፤ በአገልግሎት ዐደባባይ ያስቀመጠን ሰዎች እጅግ ዕድለኞች ነን፤ ምክንያቱም የሕዝብን ችግርና አቤቱታ ሰምቶ ተቀብሎ መፍትሔ መስጠት ትርፋማነት ነውና፤ ትርፋማነት ደግሞ ወደ ትልቁ የሹመት መሰላል መውጣት ነው፤ ይህ ሳይሆን ቀርቶ አገልግሎታችን ተደናቅፎ የሕዝባችን ችግር ሳይፈታ ቀርቶ የአገልግሎታችን ተቆጣጣሪ አምላካችን ቢጎበኘን “አንተ ሰነፍ አገልጋይ” ተብለን ወደ ውርደት አዘቅት እንዳንላክ መጠንቀቁ አይከፋም። የመሾም የመሻር የማሳደግና የማውረድ ሥልጣን የእግዚአብሔር ነውና። “ከእናንተ መካከል አንዱን እንኳ እንዳናስቸግር ቀንም ሌሊትም እንሠራ ነበር” /፩ኛ ተሰ. ፪፥፱/ በጎና ታማኝ አገልጋዮች ሆነን እንድንገኝ ጠንክረን ልንሠራ ይገባናል።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!
[ከዋናው ማእከል ድረ-ገጽ መጋቢት 10 ቀን 2007 ዓ.ም. ከተለጠፈው የተወሰደ ]