በኖርዌይ ንዑስ ማእከል የመጀመሪያው ሐዊረ ሕይወት ተካሄደ
በኖርዌይ ንዑስ ማእከል
ሰኔ 20 ቀን 2009 ዓ.ም.
በማኅበረ ቅዱሳን አውሮፓ ማእከል፣ የኖርዌይ ንዑስ ማእከል ከክርስቲያንሳንድ ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ጋር በመተባበር በሀገረ ኖርዌይ የመጀመሪያውን የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር በክርስቲያንሳንድ ከተማ መጋቢት ፳፫ እና ፳፬ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም አካሔደ። በሐዊረ ሕይወቱ ላይ ከክርስቲያንሳንድ ከተማ እና በአቅራቢያው ከሚገኙ ሌሎች ከተሞች የተሰባሰቡ ቁጥራቸው ከ40 እስከ 50 የሚደርሱ ምእመናን ተሳትፈዋል።
መርሐ ግብሩ የፈረንሳይ ፓሪስ ደብረ ምጥማቅ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ በሆኑት በመልአከ ሕይወት ቀሲስ ፍሰሐ ድንበሩ የኪዳን ጸሎት የተጀመረ ሲሆን፣ በማስከተል ማኅበረ ቅዱሳን በገዳማት እና አብነት ት/ቤቶች ዙሪያ እየሠራው ስላለው ሥራ አጭር መግለጫ ተስጥቷል፡፡ በመቀጠልም የነገረ ክርስቶስ ትምህርት በስታቫንገር መድኃኔዓለምና ኪዳነ ምሕረት ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ በሆኑት በመጋቤ ምስጢር ቆሞስ አባ ቴዎድሮስ አካሉ ተሰጥቷል፡፡ ከሰዓት በኋላ በነበረው መርሐ ግብር ላይ ከምእመናን ለቀረቡ ጥያቄዎች መጋቤ ምስጢር ቆሞስ አባ ቴዎድሮስ አካሉ እና መልአከ ሕይወት ቀሲስ ፍሰሐ ድንበሩ ሰፊ ማብራሪያ እና ምላሽ ሰጥተዋል።
በቀጣዩ ቀን ከሰዓት በኋላ መርሐ ግብር በመልአከ ሕይወት ቀሲስ ፍሰሐ ድንበሩ የነገረ ቅዱሳን ትምህርት በሰፊው ተሰጥቷል። በድጋሜም ከምእመናን ለቀረቡ ጥያቄዎች ሰፊ ማብራሪያ እና ምላሽ ተሰጥቶ የሐዊረ ሕይወቱ ፍፃሜ ሆኗል።