የጀርመን ንዑስ ማእከል አራተኛውን የሐዊረ ሕይወት አካሄደ

በጀርመን ንዑስ ማእከል

ሰኔ 20 ቀን 2009 ዓ.ም.

የጀርመን ንኡስ ማእከል ከመጋቢት ፲፯ እስከ መጋቢት ፲፱ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም አራተኛውን የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር በጀርመን የግብፅ አቡነ እንጦንስ ገዳም አካሄደ፡፡ በዚህ ሐዊረ ሕይወት ከጀርመን እና ከሌሎች አውሮፓ ሀገራት የተውጣጡ ካህናት፣ ዲያቆናት እና ምዕመናን የተሳተፉ ሲሆን በጠቅላላ የተጓዦች ብዛት 250 ነበር።  የጕዞ መነሻውን መጋቢት ፲፯ ከቀኑ 11 ሰዓት ከፍራንክፈርት ዋናው ባቡር ጣቢያ በማድረግ ወደ ገዳሙ የአንድ ሰዓት ተኩል ጉዞ በባቡርና ከዛም የቻለ በእግር  የ30 ደቂቃ መንገድ በመጓዝ ወደ ገዳሙ ተደርሷል። በተዘጋጀው መርሐ ግብር መሠረት ዓርብ ምሽት በመጋቤ ሐዲስ ቀሲስ አባተ “የሕይወት ጉዞ” በሚል ርዕስ ትምህርት ለመእመናን ተሰጥቷል። በመቀጠልም ቅዳሜ ጠዋት 11፡30 ኪዳንና ቅዳሴ እንደሚኖር ማሳሰቢያ ከተሰጠ በኋላ የዕለቱ መርሐ ግብር በጸሎት ተዘግቷል።

ቅዳሜ ጠዋት ቅዳሴው በመልአከ ኃይል ቆሞስ አባ ዘድንግል በጀርመን የዳርምሽታት ሐመረ ኖኅ ኪዳነ ምሕረት ቤ/ክ አስተዳዳሪ እና በደ/ምዕ/ምሥ/አውሮፓ ሀገረ ስብከት የሰ/ት/ቤቶች ማ/መምሪያ ኃላፊ መሪነት በቅዱስ እንጦንስ ቤተ ክርስቲያን ተካሂዷል። ከቅዳሴው መልስ የንዑስ ማእከሉ መዘምራን መዝሙር አቅርበው፣ የዕለቱ የክፍል አንድ ትምህርት በ“ነገረ ቅዱሳን” ላይ ሰፋ ያለ ትምህርት በቆሞስ አባ ዘድንግል ተስጥቷል።

17499328_1396233957081546_4273810476738406398_n

ከምሳ በኋላ ክፍል ሁለት ትምህርት በ“ነገረ ክርስቶስ” ላይ መጋቤ ሐዲስ ቀሲስ አባተ ሰጥተዋል። መምህሩ ነገረ ክርስቶስን በአራት ንዑስ ክፍሎች ማለትም:- የክርስቶስ አምላክነት፣ ነገረ ተዋሕዶ፣ በነገረ ክርስቶስ ላይ ለተነሱ መናፍቃን መልስ የሰጡ ሊቃውንት፣ እና  መናፍቃን በሳቱባቸው ጥቀሶችና መልሶቻቸው ላይ ሰፋ ያለ ትምህርት ሰጥተዋል።

17553618_1396236083748000_1193940756168687786_n

17632211_1398649536839988_4059797751435315387_oበመቀጠልም ምእመናንን ያስደመመ፣ ያሳዘነ ደስም ያሰኘ ማኅበረ ቅዱሳን በስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ መርሐ ግብሩ ያከናወናቸው ተግባራት ዘገባ ከምስል ቅንብር ጋር በዶ/ር ወርቁ ዘውዴ የጀርመን ንዑስ ማዕከል ሰብሳቢ ቀርቧል። ተሳተፊ ምእመናንም አገልግሎቱን ለመደገፍ የበኩላቸውን ገንዘብ አስተዋጽኦ አድርገዋል። ከእራት መርሐ ግብር በኋላ ከተሳታፊ ምእመናን የተነሱ ጥያቄዎች በአባቶች ምላሽ ተሰጥቷል። በመጨረሻም በቀሲስ ዶክተር ያብባል የአውሮፓ ማዕከል ሰብሳቢ “አንዳንድ ዘመናዊ አስተሳሰቦች እና ክርስትናችን” በሚል ርዕስ ጽሑፍ ቀርቧል። በዚህም ርዕስ ላይ አንዳንድ የዓለም ጠበብት ያነሷቸውን እና አሁንም እየተንጸባረቁ የሚገኙ አስተሳሰቦችን በማንሳት ወላጆች የዘመኑን አስተሳሰብ በመረዳት ልጆቻቸውን የሃይማኖት ትምህርት እንዲያስተምሩ በጥብቅ አሳስበዋል።

እሑድ ጠዋት የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ጋር ቅዳሴ በመሳተፍ ቁርስ ተበልቶ ሁሉም ወደ መጣበት “የዓመት ሰው ይበለን” እየተባባለ የሐዊረ ሕይወት ጉዞው ፍፃሜ ሆኗል።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!