የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ ክርስቲያን መዝሙራት ከየት ወዴት በሚል ለሦስተኛ ጊዜ የተዘጋጀ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሐግብር በእንግሊዝ ለንደን ከተማ ተካሄደ።

በእንግሊዝ ንዑስ ማእከል

ሰኔ 16 ቀን 2009 ዓ.ም.

በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ ክርስቲያን ስም የሚወጡ መዝሙራት ቁጥር እየተበራከቱ ቢሄዱም በተለይ በቅርብ ጊዜ የወጡ አንዳንድ መዝሙራት ግን ከያሬዳዊ ዜማ ይልቅ ለዓለማዊ ዘፈን ያደሉ መሆናቸዉን ተከትሎ ማኅበረ ቅዱሳን ባካሄደዉ ጥናት እየታዩ ያሉትን ችግሮችና የመፍትሔ ሐሳቦችን በመረጃ በማስደገፍ አቅርቦ ነበር። የዚህ ጥናት ዉጤት በተለያዩ የሀገር ዉስጥና የዉጭ ሀገራት ጉባኤያት ላይ የቀረቡ ሲሆን በማኅበረ ቅዱሳን የዩኬ (እንግሊዝ) ንዑስ ማእከል ከሚመለከታቸዉ የቤተ ክርስቲያን አካላት ጋር በመተባበር በ2008 ዓ.ም በበርሚንግሃም እና በኖቲንግሃም ከተሞች በእያንዳንዳቸዉ የተሳካ መርሐ ግብር ተካሂዶ ነበር። ንዑስ ማእከሉ በ2009 ዓ.ም በያዘዉ ዕቅድ መሠረት በለንደን ከተማ በሚገኙ ሦስት አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ከመንፈሳዊ ሰበካ ጉባኤያት ጋር በመተባበር በእያንዳንዳቸዉ ለግማሽ ቀን የቆየ መርሐግብር ተካሂዷል። በዚህም መሠረት መጋቢት 17 ቀን 2009 ዓ.ም በለንደን ደ/ገነት ቅድሥት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን፤ ሚያዝያ 22 ቀን 2009 ዓ.ም በለንደን ደ/ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን፤ ግንቦት 20 ቀን 2009 ዓ.ም በርዕሰ አድባራት ለንደን ደ/ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን በእያንዳንዳቸዉ በፕሮጀክተር፣ በድምጽና በምስል የታገዘ ገለጻ ተሰጥቷል።

Mezmurat keyet wedet_London_Pict 3 Mezmurat keyet wedet_London_Pict 1

መርሐ ግብሩ በሦስት ክፍሎች ተከፋፍሎ የተሰጠ ሲሆን የመርሐግብሩ አንዱ አካል በሆነዉ የጥያቄና መልስ መርሐ ግብር በርካታ ጥያቄዎች ተነስተዉ ሰፊ ዉይይት ተደርገዉባቸዋል። በመርሐግብሩ ከተዳሰሱት አበይት ነጥቦች መካከል የአማርኛ መዝሙራትና የቅዱስ ያሬድ ዜማ ሥጋቶች፤ በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ ክርስቲያን ስም የተዘመሩ መዝሙራት እና የዓለማዊ ዘፈን ወይም የፕሮቴስታንት መዝሙራት ተመሳሳይነት፣ የመፍትሔ ሐሳቦች (ምን እናድርግ) ወዘተ ይገኙበታል። መርሐ ግብሩን የተከታተሉ አንዳንድ ተሳታፊዎች ከሰጡት አስተያየት መካከል መርሐግብሩ ከጠበቁት በላይ ግንዛቤ እንዳስጨበጣቸዉና በመዝሙራት ዙሪያ ባዩት እና በሰሙት ጉዳይ ቁጭት እንዳደረባቸዉ፤ ተመሳሳይ መርሐ ግብራት ወደፊትም ቢቀጥሉ፣ የሚመለከታቸዉ የቤተ ክርስቲያኒቱ አካላት ለጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት ቢሰጡ ለሁሉም አካላት መልካም እንደሆነ አሳስበዋል። ዲ/ን መኮንን ግርማ፣ መጋቤ ሠናይ ሳምሶን ሰይፈ፣ ኤፍሬም ደምሴ እና ኃይሉ አብርሃም በሦስቱም አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት በመገኘት መርሐግብሩን በተሳካ ሁኔታ አቅርበዋል።

Mezmurat keyet wedet_London_Pict 2
በነዚህ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሐግብራት ላይ ካህናት አባቶች፣ ዲያቆናት፣ የሰ/ት/ቤት አባላትና በርካታ ምዕመናን የተገኙ ሲሆን የዩኬ ንዑስ ማእከል ጽ/ቤት መርሐ ግብሩ በተሳካ ሁኔታ እንዲካሄድ ከፍተኛ አስተዋጸኦ ላደረጉት የየአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት አስተዳዳሪዎች እና የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤያት እንዲሁም የሰ/ት/ ቤቶች ከፍ ያለ ምስጋና በእግዚአብሔር ስም አቅርቧል።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!