ሀገረ ስብከቱ ፬ኛ ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤውን አካሄደ።
በጀርመን ንዑስ ማእከል
መስከረም 3 ቀን 2010 ዓ.ም.
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በምሥራቅ፣ ምዕራብና ደቡብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት ፬ኛ ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤውን ዓርብ ነሐሴ 26 እና ቅዳሜ ነሐሴ 27 ቀን 2009 ዓ/ም የሀገረ ስብከቱ መቀመጫ በሆነችው በጀርመኗ ሮሰልስሀይም ከተማ አካሄደ። በዚህ ዓመታዊ ጉባኤ የሀገረ ስብከቱ ልዩ ልዩ ሓላፊዎች፣ የአድባራት አስተዳዳሪዎችና የሰበካ ጉባኤ ተወካዮች የተገኙ ሲሆን ጉባኤው በዋናነት በሀገረ ስብከቱ፣ በአጥቢያዎች እንዲሁም በማኅበረ ቅዱሳን የአውሮፓ ማእከል የሥራ ክንውን፣ የሂሳብ ዘገባ እና የ2010 ዓ/ም የሥራ ዕቅድ ላይ ሰፊ ውይይት አድርጓል። የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሙሴ በስልክ አባታዊ ቃለ ምዕዳን እና መመሪያ ያስተላለፉ ሲሆን ብፁዕነታቸው በአካል ባልተገኙባቸው ባለፉት ጥቂት ወራት ውስጥ አድባራቱ በተለይም የሀገረ ስብከቱ ሓላፊዎች የተጣለባቸውን ኃላፊነትና አደራ ለመወጣት ያደረጉትን ጥረት አድንቀው አሁንም ለቤተክርስቲያን ዕድገትና ሰላም ተግተው እንደሚሠሩ ያላቸውን ሙሉ እምነት በመግለጽ አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል። በተጨማሪም ጉባኤው በሀገረ ስብከቱ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ሰፊ ውይይት በማድረግ የአቋም መግለጫ አውጥቷል።
በየዓመቱ እንደሚደረገው ሁሉ በዚህ ዓመትም የተሻለ አፈጻጸም ያሳዩ እና አርአያነት ያለው የአገልግሎት ፍሬ ያፈሩ አጥቢያዎች የተለዩ ሲሆን የሮም ደብረ ከነዓን ቅድስትሥላሴ፣ የፓሪስ ደብረ ምጥማቅ ቅድስት ማርያም እና የፍራንክፈርት ደብረ ፀሐይ ቅድስት ማርያም አብያተ ክርስቲያናት እንደቅደም ተከተላቸው ከ 1ኛ እስከ 3ኛ ድረስ ያለውን ደረጃ በመያዝ የተዘጋጀላቸውን ሽልማቶች ተቀብለዋል።
በመጨረሻም የሀገረ ስብከቱ ም/ሥራ አስኪያጅ መጋቤ ምሥጢር ኅሩይ ኤርምያስ ስብከተ ወንጌልን ለማስፋፋት፣ የሕገወጥ አጥማቂዎች እና የተሐድሶ መናፍቃንን እንቅስቃሴን ለመግታት እንዲሁም ለሁለንተናዊ የቤተክርስቲያን እድገት የተጀመረው ተመካክሮና የቤተ ክርስቲያኒቱን ሕግና ሥርዓት ተከትሎ የመሥራቱ ልምድ እንዲቀጥል ጥሪያቸውን አስተላልፈው ጉባኤው በጸሎት ተፈጽሟል።