ዐቢይ ጾም ለሕጻናት
በልደት አስፋው
መጋቢት ፩ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም
እንደምን ሰነበታችሁ ልጆች? ባለፈው ሳምንት ስለ ነቢዩ ዮናስ እና ስለ ነነዌ ሰዎች የጻፍንላችሁን ታሪክ አነበባችሁት? ጎበዞች፡፡ ከታሪኩ ውስጥ ያልገባችሁ ትምህርት ካለ ከቤተ ክርስቲያን መምህራን በመጠየቅ መረዳት ትችላላችሁ፡፡ በዛሬው ዝግጅታችን ደግሞ ስለ ዐቢይ ጾም አጭር ትምህርት ይዘንላችሁ ቀርበናል፤
ልጆች! ‹‹ዐቢይ ጾም›› ማለት ታላቅ ጾም ማለት ነው፡፡ ዐቢይ ጾም በቤተ ክርስቲያናችን በዐዋጅ እንዲጾሙ ከታወጁ ከሰባቱ አጽዋማት መካከል አንዱ እና ዋነኛው ነው፡፡ ጾሙ ታላቅ የተባለበት ምክንያትም ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጾመው ጾም በመኾኑ ነው፡፡
ልጆች! ይኽንን ጾም ዕድሜአቸው ሰባት ዓመት ከኾናቸው ሕፃናት ጀምሮ ዅሉም የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አማኞች እንዲጾሙት የቤተ ክርስቲያናችን ሕግ ያዝዛል፡፡ እንዴት ነው ታዲያ ሰባት ዓመትና ከዚያ በላይ የኾናችሁ ሕፃናት አጽዋማትን እየጾማችሁ ነው አይደል? እየጾማችሁ ከኾነ በጣም ጎበዞች ናችሁ ማለት ነው፤ በዚሁ ቀጥሉ፡፡
ዕድሜአችሁ ለመጾም ደርሶ መጾም ያልጀመራችሁ ካላችሁ ደግሞ ከቤተሰቦቻችሁ ጋር ተመካክራችሁ እስከምትችሉበት ሰዓት ድረስ በመጾም ጾምን ከልጅነታችሁ ጀምራችሁ ተለማመዱ፤ የጾሙ ተሳታፊዎችም ኹኑ እሺ? በሕመም ምክንያት መድኀኒት የምትወስዱ ከኾነ ግን መድኀኒታችሁን ስትጨርሱ ትጾማላችሁ፡፡
ልጆች! የዘንድሮው (የ፳፻፱ ዓ.ም) ዐቢይ ጾም የሚጀመረው መቼ እንደ ኾነ ታውቃላችሁ? የካቲት ፲፫ ቀን ነው፡፡ የሚፈታው ማለትም የሚፈሰከው ደግሞ ከአምሳ አምስት ቀናት በኋላ ሚያዝያ ፰ ቀን ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ ዓመት የፋሲካ በዓል ሚያዝያ ፰ ቀን ይውላል ማለት ነው፡፡
በዐቢይ ጾም ውስጥ የሚገኙት አምሳ አምስቱ ቀናት በስምንት ሳምንታት (እሑዶች) የተከፋፈሉ ናቸው፡፡ የእያንዳንዱ ሳምንት ወይም እሑድ መጠሪያ ስሞችም የሚከተሉት ናቸው፤
የመጀመሪያው ሳምንት (እሑድ) – ዘወረደ
ሁለተኛው ሳምንት (እሑድ) – ቅድስት
ሦስተኛው ሳምንት (እሑድ) – ምኵራብ
አራተኛው ሳምንት (እሑድ) – መጻጕዕ
አምስተኛው ሳምንት (እሑድ) – ደብረ ዘይት
ስድስተኛው ሳምንት (እሑድ) – ገብር ኄር
ሰባተኛው ሳምንት (እሑድ) – ኒቆዲሞስ
ስምንተኛው ሳምንት (እሑድ) – ሆሣዕና
ተብለው ይጠራሉ፡፡
የፋሲካ በዓል የሚከበርበት የመጨረሻው የዐቢይ ጾም እሑድ ደግሞ ትንሣኤ ወይም ፋሲካ ይባላል፡፡
ልጆች! እንደ እግዚአብሔር መልካም ፈቃድ እነዚህን ሳምንታት (እሑዶች) የሚመለከት ትምህርት በየሳምንቱ እናቀርብላችኋለን፡፡ እስከዚያው ድረስ ከቤተ ክርስቲያን መምህራን ወይም ደግሞ ከወላጆቻችሁ ጠይቃችሁ ሰባቱ አጽዋማት የሚባሉት ማን ማን እንደ ኾኑ አጥንታችሁ ጠብቁን እሺ?
በሉ እንግዲህ ልጆች በሌላ ዝግጅት እስከምንገናኝ ድረስ ሰላመ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይኹን፡፡
ይቆየን