በቱሉዝ ፈረንሳይ የቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ቅዳሴ ቤቱ ተከበረ፡፡
በቀሲስ አለባቸው በላይ ከፈረንሳይ ግንኙነት ጣቢያ
በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ን የኢጣልያና አካባቢው ሀ/ስብከት በደቡብ ፈረንሳይ ቱሉዝ ከተማ የቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ በተገኙበት ቅዳሴ ቤቱ ተከበረ፡፡ ወደ አጥቢያ ቤተክርስቲያንነት ከማደጉ በፊት ‘የቱሉዝና አካባቢው ቅዱስ ሚካኤል ማኅበር’ በሚል ስያሜ የቆየ ሲሆን፤ አመሠራረቱም በመስከረም ወር 2008 ዓ.ም አሁን ነዋሪነቱን በአሜሪካን ሀገር ያደረገ ዶ/ር ኢንጅነር ኃይሉ በላይ የሚባል የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ለወራት ሥልጠና ወደ ከተማዋ በመጣበት አጋጣሚ ኢትዮጵያዊያንን ፈልጎ በማግኘትና በማስተባበር ነበር፡፡ ከ2 ወራት በኋላ ኅዳር ወር 2008 ዓ.ም ከፓሪስ መልአከ ጽዮን ቆሞስ አባ ወልደ ትንሳኤን በማምጣት የመጀመሪያው የቅዳሴ አገልግሎት ተከናውኗል፡፡ በተጨማሪም ክፍላትን በማዋቀር ማኅበሩ ቅርፅ እንዲኖረው የተደረገ ሲሆን፤ ከማኅበረ ቅዱሳን የፈረንሳይ ግንኙነት ጣቢያ ጋር በመተባበር ለአገልጋዮችም ተከታታይ ሥልጠናዎችን በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች በመስጠት አቅም የማጎልበት ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ ላለፉት አራት ዓመታት በየወሩ የቅዳሴ አገለግሎት በማከናወን፣ ሕጻናትን ክርስትና በማንሳት፣ ብዙ ምእመናን የምስጢራት ተካፋይ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡ አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችን ለሀ/ስብከቱ በማሳየት በብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ መልካም ፈቃድ በቀን 15/06/2012 ዓ.ም የቅዱስ ሚካኤል ጽላት ገብቶ ማኅበሩ ወደ ቤተ ክርስቲያነት አድጓል፡፡
በበዓሉ ዋዜማ ብዙ ቁጥር ያላቸው ምእመናን እና ካህናት ለሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ በቱሉዝ (Blagnac) ኤርፖርት ተገኝተው ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡ በብክብረ በዓሉ የማኅሌት፣ የትምህርትና እንዲሁም የቅዳሴ አገልግሎት በሊቀ ጳጳሱ መሪነት ተከናውኗል፡፡ ከቅዳሴ በኋላ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ “አስቀድማችሁ መንግስቱንና ጽድቁን ፈልጉ” (ማቴ6፡33) በሚል ርዕስ መነሻነት በሰጡት ሰፋ ያለ ትምህርት፤ የምእመናኑን መጠናከርና እዚህ ደረጃ መድረስ በማውሳት በቀጣይም ለበለጠእ የጽድቅ ሥራ መበርታት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ በመጨረሻም ተተኪን ከማፍራት እና የተደራጀ አገልግሎት ከመፈጸም አንጻር በኖርዌይ እሳቸው በበላይ ጠባቂነት የሚመሩትን ደብር ተሞክሮ አነስተው፤ ተተኪ ካህናትን ማፍራት ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ አባታዊ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡ በመጨረሻም በብፁዕነታቸው ጸሎተ ምዕዳን የበዓሉ ፍጻሜ ሆኗል፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡