ብስራታዊው መልአክ
ከማርታ ታከለ
ጥር ፳፮ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም
ክፍል አንድ
እንደምን አላችሁ ልጆች? የእግዚአብሔር ሰላም ከሁላችሁም ጋር ይሁን!
ዛሬ ስለ አንድ ቅዱስ የእግዚአብሔር መልአክ ታሪክ እነግራችኋለሁ።ይህ መልአክ ብስራታዊው መልአክ ይባላል። ብስራት ማለት ምስራች ወይም ደስ የሚል ዜና ማለት ነው።ብስራታዊ ማለት ደግሞ ባለምስራች ወይም ደስ የሚያሰኝ ዜና የሚናገር የሚያሰማ ማለት ነው።የዚህ ቅዱስ መልአክ ስሙ ገብርኤል ይባላል።ልጆች! ታዲያ ቅዱስ ገብርኤል ምን ደስ የሚያሰኝ ዜና አሰምቶ ብስራታዊ ተባለ?
ከላይ ያነሳነውን ጥያቄ ከመመለሳችን በፊት ስለዚህ ቅዱስ መልአክ እና ስለሌሎች መላእክት አፈጣጠር በአጭሩ ልንገራችሁ፥
መላእክት በመጀመሪያው ቀን በዕለተ እሁድ ተፈጥረዋል። በተፈጠሩም ጊዜ ብርሃን አልነበረም። አንዱ መልአክ ሌላውን በሚነካው ጊዜ ሁሉም ማን ፈጠረን? የሚለውን ጥያቄ መጠየቅ ጀመሩ። በዚህ ጊዜ ከሁሉም በላይ የነበረው መልአክ ሳጥናኤል ነበር። ከበላዩ ማንም እንደሌለ ሲረዳና ሁሉም እሱ ከነበረበት በታች እንደሆኑ ሲያውቅ አንድ ነገር ተናገረ። ‘የፈጠርኳችሁ እኔ ነኝ’ አላቸው።የመጀመሪያውንም ሀሰት ተናጋሪ ሆነ።እሱ እንዳልፈጠራቸው እያወቀ ሁሉም ማን እንደፈጠራቸው አለማወቃቸውን ተመልክቶ ሀሰትን ከራሱ አመንጭቶ ተናገረ።
በዚህ ጊዜ ዛሬ ታሪኩን የምነግራችሁ ቅዱሱ መልአክ ገብርኤል ‘የፈጠረንን እስክናውቅ ድረስ በያለንበት ጸንተን እንቁም’ በማለት ሌሎች መላእክትን እንዲጸኑና ተረጋግተው የፈጠራቸው እስኪገለጥ እንዲጠብቁ ተናገረ። በዚህ ጊዜ ሳጥናኤልን ያመኑና የተከተሉ መላእክት አሉ። ገብርኤልን ሰምተው የፈጠራቸው እስኪገለጥ ጸንተው የቆሙ መላእክት አሉ። በመኻል ደግሞ መወሰን ሳይችሉ ቀርተው እየዋለሉ ያሉ መላእክት ነበሩ።
ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ‘ብርሃን ይሁን!’ አለ። ብርሃንም ሆነ። መላእክትም ፈጣሪያቸውን አወቁ። ሳጥናኤልም የመላእክት ሳይሆን የሀሰት ፈጣሪ መሆኑ ተጋለጠ። በሰራው ስህተት ጸጸት የማያውቅ አመጸኛ በመሆኑ የራሱን ሠራዊት ይዞ ከገብርኤልና ከሚካኤል ከሌሎችም የመላእክት አለቆችና ሠራዊቶቻቸው ጋር ተዋጋ። እነርሱም ሳጥናኤልን አሸነፉት። ሳጥናኤልን ያመኑትና መወሰን አቅቷቸው ሲወላውሉ የነበሩት መላእክት ሁሉ ከሰማይ ተጣሉ። ከክብራቸውም ተዋርደው ተባረሩ። ቅዱስ ገብርኤልና ሌሎች ቅዱሳን መላእክት ግን ከነክብራቸው የፈጠራቸውን እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ለመኖር ቻሉ።
ልጆች ቅዱስ ገብርኤልን ብስራታዊ መልአክ የምንለው ከላይ ባየነው ታሪክ ይመስላችኋል? አይደለም። ከላይ ባየነው ታሪክ ውስጥ መለእክትን እንዲጸኑና እንዲረጋጉ አድርጓል። በዚህም ሌሎች መላእክት ሳጥናኤልን ሰምተው ከክብራቸው ከመዋረድና ከመላእክት ዓለም ከመባረር አድኗቸዋል። ታዲያ ብስራታዊ ለምን ተባለ?
ከብዙ ዘመን በኋላ ቅዱስ ገብርኤል ከእግዚአብሔር አብ ዘንድ ወደ ምድር ተላከ። ታላቅ የምስራች፥ ታላቅ የደስታ ዜናም ይዞ ነበር።የሰው ልጆች ሁሉ ለዘመናት በተስፋ ሲጠብቁት የነበረውን ዜና የምስራች ይዞ ከሰማይ ወረደ።በጨለማ በሞት ጥላ ውስጥ ይኖሩ ለነበሩት የሰው ልጆች ወደ ህይወት የሚያመጣ ወደ ብርሃን የሚያወጣ የምስራች ዜና ይዞ ከሰማይ አየሩን በክንፎቹ እያማታ ወደምድር ወረደ።
ልጆች! በዛሬው ክፍል ጥያቄ እጠይቃችኋለሁ። ቅዱስ ገብርኤል ከተፈጠረ ከብዙ ጊዜ በኋላ የምስራች ይዞ ወደ ምድር መጣ ብለናል። ምስራቹን ከማምጣቱ በፊት ምን ይሠራ ነበር? ምስራቹን ያመጣላቸው የሰው ልጆች እነማን ናቸው?ለምንስ በጨለማና በሞት ጥላ ውስጥ ይኖሩ ነበር አልን? ቅዱስ ገብርኤልን ብስራታዊ ያሰኘው የብስራት መልእክትስ ምን ይሆን?
በቀጣይ ክፍል መልሱን እናገኛለን!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር!