የጀርመን እና አካባቢው ሀገረ ስብከት ጠቅላላ ጉባኤውን አካሄደ
ታኅሣሥ 18 ቀን 2011 ዓ.ም
በጀርመን ንዑስ ማዕከል
በጥቅምት ወር 2011 ዓ.ም. በተደረገው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ላይ ለዐራት ተከፍለው በአዲስ መልክ ከተዋቀሩት የአውሮፓ አህጉረ ስብከት አንዱ የሆነው እና በብፅዕ አቡነ ዲዮናስዮስ የሚመራው የጀርመን እና አካባቢው ሀገረ ስብከት የምሥረታ ጠቅላላ ጉባኤውን በፍራንክፈርት ከተማ በሚገኘው በምስካዬ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ታህሳስ 6 ቀን 2011 ዓ.ም. አካሄደ። ይህ ጀርመንን፣ ስዊዘርላንድን፣ ኦስትሪያን እና ሆላንድን የሚያጠቃልለው ሀገረ ስብከት በቁጥር ከ 30 በላይ የሚሆኑ አጥቢያዎችን የሚያስተዳድር ሲሆን ለዚህ ጉባኤ ከአብዛኛዎቹ አጥቢያዎች የመጡ የአድባራት አስተዳዳሪዎች እንዲሁም የሰበካ ጉባኤ፣ የካህናት እና የሰንበት ትምህርት ቤት ተወካዮች በአጠቃላይ ከ 90 በላይ ተሳታፊዎች ተገኝተውበታል።
ጉባኤው በጸሎት ከተከፈተ በኋላ የአስተናጋጁ የፍራንክፈርት ምስካዬ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ መልአከ መዊዕ ቀሲስ ልሳነወርቅ ውቤ አጭር የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን በመቀጠልም ብፁዕ አቡነ ዲዮናስዮስ “መሰባሰባችንን አንተው“ (ዕብ 10÷ 24-25) በሚል ርእስ ተነስተው ስለሀገረ ስብከቱ አወቃቀር እና በመዋቅር ማገልገል ስላለው ጠቀሜታ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል። “የቤተከርስቲያን አንድነት ከመጣ በኋላ የምናደርገው ጉባኤ በመሆኑ በታላቅ ደስታ እንደመጣችሁ አምናለሁ“ ያሉት ብፁዕነታቸው ይህንን አንድነት ለማጽናት በፍቅርና በአንድነት ልናገለግል እንዲሁም ሀገረ ስብከታችንንም ልናጠናክር ይገባል የሚል መልእክት በአጽንዖት አስተላልፈዋል።
በመቀጠል የነበረው መርሐ ግብር የተሰናባቹ የምሥራቅ፣ ምዕራብ እና ደቡብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት አስተዳደር ጉባኤ አጭር የሥራ ዘገባ ሲሆን ይህንንም ዘገባ ያቀረቡት የሀገረ ስብከቱ ምክትል ሥራ አስኪያጅ መጋቤ ምሥጢር ኅሩይ ኤርምያስ ናቸው። አስተዳደር ጉባኤው ከተመረጠበት ከነሐሴ 2005 ዓ.ም. ወዲህ ተሰርተው በም/ሥራ አስኪያጁ ከተዘረዘሩት በርካታ ዐበይት ተግባራት መካከል የቅዱስ ሲኖዶስን እና የጠቅላይ ቤተ ክህነትን መመሪያዎች መፈጸም እና ማስፈጸም፤ የስምንት አዳዲስ አጥቢያዎች መመሥረት፤ የስዊዘርላንድ አጥቢያዎችን ወደ ሀገረ ስብከቱ ማምጣት፤ ኤፍራታ በተባለች ዓመታዊ መጽሔቱ እና በፌስቡክ ገጹ ስብከተ ወንጌለን ማስፋፋት፤ በአድባራት መካካል እና በአድባራት ውስጥ የተከሰቱ አላመግባባቶችን መፍታት፤ ሁለት ዙር የረዳት ሰባክያን ሥልጠና መስጠት፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ድርቅ በተከሠተ ጊዜ ከ 20 ሺህ ዩሮ በላይ አሰባስቦ መላክ እና ለጠቅላይ ቤተ ክህነት ዓመታዊ ፈሰስ ማድረግ የሚሉት ተጠቃሽ ክንውኖች ናቸው። በሌላ በኩል ከሀገር ውጭ በነበረው ሲኖዶስ ሥር የነበረው የመላው አውሮፓ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ መልአከ መዊዕ ቀሲስ ልሳነወርቅ ውቤ ሀገረ ስብከቱ ሲሰራቸው የነበሩትን ዋና ዋና ተግባራት ጠቅለል አድርገው ያቀረቡ ሲሆን ከተለመዱት አድባራትን የመትከል እና ስብከተ ወንጌልን የማስፋፋ ሥራዎች በተጨማሪ በተለይም ከ 5 በላይ አጥቢያዎች የራሳቸው ህንጻ ቤተ ክርስቲያን ባለቤቶች ሆነዋል ብለው ያቀረቡት ክንውን የጉባኤውን ትኩረት የሳበ ስኬት ነበር።
በሦስተኛነት የተያዘው አጀንዳ ሀገረ ስብከቱን የሚመሩ የአስተዳደር ጉባኤ አባላትን ማስመረጥ ሲሆን ለዚህም በመጀመሪያ የምርጫው ሂደት ምን መሆን እንዳለበት ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል። በተለይም የአስተዳደር ጉባኤ አባላቱ ከዐራቱም ሀገራት የተወጣጡ እንዲሆኑ፤ ቀድሞ የሀገር ውስጥ እና የሀገር ውጭ ሲኖዶስ ይባሉ በነበሩት አህጉረ ስብከት ሥር የነበሩትን እንዲሁም ገለልተኛ ይባሉ የነበሩትን አጥቢያዎች ውክልና የሚሰጥ እንዲሆን፤ እንዲሁም ከካህናት በተጨማሪ የምእመናን ተዋጾኦ እንዲኖርበት የሚሉት ቁልፍ ጉዳዮች ላይ ስምምነት ከተደረሰ በኋላ አምስት አባላት ያሉት አስመራጭ ኮሚቴ ተቋቁሞ የምሳ እረፍት ተደርጓል። ከምሳ እረፍት በኋላ አስመራጭ ኮሚቴው 18 እጩዎችን ያቀረበ ሲሆን ጉባኤው 9 የአስተዳደር ጉባኤ አባላትን በድምጽ ብልጫ መርጧል። ከእነዚህ ውስጥም የፍራንክፈርት ምስካዬ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ መልአከ መዊዕ ቀሲስ ልሳነወርቅ የሀገረ ስብከቱ ምክትል ሥራ አስኪያጅ እንዲሁም የፍራንክፈርት ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ቆሞስ አባ ስብሐት ለአብ የሀገረ ስብከቱ ዋና ጸሐፊ በመሆን ተመርጠዋል።
የሀገረ ስብከቱ እና የወረዳ ቤተ ክህነቶች ግንኙነት ምን ይምሰል? የሚለው አጀንዳ ሌላው ጉባኤውን ብዙ ያወያየ አጀንዳ ሲሆን ከአጥቢያዎቹ ቁጥር ማነስ እና የሀገራቱን መልክዐ ምድራዊ አቀማመጥ ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ወረዳ ቤተ ክህነት ማቋቋም ሀብትን እና የሰው ሃይልን ከማባከን እና የአሰራር ሰንሰለቱን ከማርዘም የዘለለ ብዙ ጥቅም የለውም ያለው ጠቅላላ ጉባኤው ወረዳ ቤተ ክህነት ማቋቋም ሳያስፈልግ አጥቢያዎች በቀጥታ ከሀገረ ስብከቱ ጋር ይገናኙ በማለት ወስኗል።
በመጨረሻም ለተሰናባች የሀገረ ስብከት አስተዳደር ጉባኤ አባላት የምስጋና የምስክር ወረቀት ተሰጥቶ እና ቃለ ጉባኤው ተነቦ ከጸደቀ በኋላ ብፅዕ አቡነ ዲዮናስዮስ የጉባኤውን ተሳታፊዎች እንዲሁም የአስተናጋጁ የፍራንክፈርት ምስካዬ ኅዙናን መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያንን አስተዳዳሪ እና ምእመናንን አመስግነው ጉባኤውን በጸሎት ዘግተዋል።