ጥምቀት እና በዓለ ጥምቀት

በዲ.ን ዶ.ር አለማየሁ ኢሳይያስ

ጥር 8 ቀን 2007 ዓ.ም.

ጥምቀት

ጥምቀት የሚለው ቃል አጥመቀ (አጠመቀ ወይም ነከረ) ከሚለው የግእዝ ሥርወ ቃል የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም መጠመቅ ፣ መነከር ፣ መደፈቅ ፣ ውኃ ውስጥ ብቅ ጥልቅ ማለት ነው ። ጥምቀት ከሌሎቹ ምሥጢራተ ቤተክርስቲያን በመጀመሪያ ላይ የሚፈጸም ምሥጢር ሲሆን ያለ ጥምቀት ከሌሎቹ ምሥጢራተ ቤተክርስቲያን መሳተፍ አይቻልም ። (ዮሐ. ፪፥፩-፵፩) በጥምቀት ከእግዚአብሔር በመንፈስ እንወለዳለን፤የልጅነት ፀጋንም እናገኛለን። የነፍስ ድኅነትን ለማግኘትም በጥምቀት የእግዚአብሔርን ልጅነት ማግኘት ግድ ነው ።(ማር ፲፮፥፲፮ ፤ ዮሐ ፫፥፭) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተጠመቀበትን እለት በታላቅ ድምቀት በየዓመቱ ጥር ፲፩ ቀን እንደምታከብር ይታወቃል። የጥምቀት በዓል አከባበር የሚጀምረው ጥር ፲ ቀን በጾም ሲሆን ይህም እለት ገሀድ በመባል ይታወቃል።ትርጉሙም መገለጥ ማለት ነው። ምክንያቱም ወልድ የተባለ ኢየሱስ ክርስቶስ ቅድመ ዓለም ያለ እናት ከአብ ፣ በኋለኛው ዘመን ደግሞ ያለ አባት ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍስዋ ነፍስ ነስቶ፣ ከሁለት አካል አንድ አካል፣ ከሁለት ባሕርይ አንድ ባሕርይ ሆኖ ተዋሕዶ ስለተገለጠልን እና በ፴ ዓመቱ በባሕረ ዮርዳኖስ በእደ ዮሐንስ ተጠምቆ ክብሩንና ጌትነቱን ስለገለጠልን ነው።

ጌታ የተጠመቀው በ፭ሺ፭፻፴ ዓ.ዓ በዘመነ ሉቃስ በእለተ ማክሰኞ ጥር ፲ ለ ፲፩አጥቢያ ከሌሊቱ በ፲ኛው ሰዓት በመጥምቁ ዮሐንስ እጅ በዮርዳኖስ ባሕር በ፴ ዓመት ከ ፲፫ ቀኑ ነው። የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት እንግዳ ደራሽ እንደ ውኃ ፈሳሽ የተፈጸመ አይደለም ፤ አስቀድሞ ትንቢት ተነግሮለታልና። ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት በትንቢት መነፅር ተመልክቶ “ባሕር አየች፤ ሸሸችም ፤ ዮርዳኖስም ወደኋላው ተመለሰ።” (መዝ ፻፲፫፥፫) በማለት ስለ ጌታ ጥምቀት ትንቢት ተናግሯል። ዳግመኛም “አቤቱ ውኆች አዩህ፤ ውኆችም አይተውህ ፈሩ፤ ጥልቆችም ተነዋወጡ ውኆችም ጮሁ ።” (መዝ ፸፯፤፲፮) በማለት ዘምሯል። ነቢዩ ሕዝቅኤልም (ሕዝ ፴፮፥፳፮) ስለ ጥምቀት እንዲህ ብሏል። “ጥሩ ውኃንም እረጭባችኋለሁ፤ እናንተም ትጠራላችሁ አዲስም ልብ እሰጣችኋለሁ።” በትንቢተ ሚክያስ ምዕ. ፯ ቁ ፲፱ ላይም “ ተመልሶ ይምረናል ፤ ክፋታችንንም ይቀጠቅጣል፤ ኃጢአታችንንም በባሕሩ ጥልቅ ይጥለዋል ። ” የሚል ተጽፎ እናገኛለን።

ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በ፴ ዘመኑ የተጠመቀው የሰው ልጆች ሁሉ አባት የሆነው አዳም የ፴ ዓመት ጎልማሳ ሆኖ በ፵ ቀኑ አግኝቶ በኋላ ያጣትን ልጅነት ለማስመለስ ነው። እርሱ አምላክ ሲሆን በእደ ዮሐንስ መጠመቁ ደግሞ ትህትናውን ለመግለጥ ነው። ጌታ ወደ ዮሐንስ ሄዶ መጠመቁ ለእኛ ለምእመናን ሥርዓት ሊያስተምረን ስለወደደ ነው። ቅዱስ ቃሉ ከሚነገርባት፣ ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ ከሚፈተትባት፣ የክርስቶስ ማደሪያ ከሆነች ከቅድስት ቤተክርስቲያን ሄዳችሁ ተጠመቁ ሲለን ነው። ይህ ሥርዓት ባይሠራልን ኖሮ በየዘመኑ የሚነሱ መኳንንትና መሣፍንት አባቶች ካህናትን ቤታችን መጥታችሁ አጥምቁን ብለው በጠየቁ ነበር። ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተጠመቀው ሁሉም ሰው በቀላሉ ማግኘት በሚችለው በውኃ ነው፤ ምክንያቱም ጥምቀት መዳንን ለሚሻ ለሁሉ የተሰጠች ናትና።

በተጨማሪም ጌታ ከሌሎች ውኆች ይልቅ የዮርዳኖስን ባሕር የመረጠበት ምክንያት አለው። ዲያብሎስ አዳምንና ሔዋንን በጨለማ መጋረጃ ጋርዶ ለእኔ መገዛታችሁን ማረጋገጫ ጽፋችሁ ስጡኝ ብሎ በጠየቃቸው መሰረት “አዳም ገብሩ ለዲያብሎስ” እና “ሔዋን አመቱ ለዲያብሎስ” የሚል ጽፈው ሰጥተውት ነበር። ዲያብሎስም ይህንን በሁለት እብነ ሩካም ቀርጾ አንዱን በዮርዳኖስ ሁለተኛውን በሲኦል ጥሎታል። ጌታ በዮርዳኖስ ሲጠመቅ ክብር ምስጋና ለእርሱ ይሁንና በዮርዳኖስ የተጣለውን የእዳ ደብዳቤያችንን እንደ ሰውነቱ ረግጦ እንደ አምላክነቱ አቅልጦ አጥፍቶልናል (ፊል. ፪፥፲፪)። ጌታ ጥምቀቱን ከሌሊቱ ፲ ሰዓት ላይ ያደረገበትም ምክንያት ምሥጢረ መንግሥቱን (አንድነቱን ሥስትነቱን) ለመግለጥ ነው። ጌታ በዮሐንስ እጅ ተጠምቆ ሲወጣ አብ በደመና ሆኖ “ የምወደው ልጄ ይህ ነው እርሱን ስሙት” ብሎ የእግዚአብሐር አብ የባሕርይ ልጅ መሆኑን መስክሮለታል። መንፈስ ቅዱስም በነጭ ርግብ አምሳል ወርዶ በራሱ ላይ አርፎበታል (ማቴ. ፫፥ ፲፫-፲፯)። ጌታ ጥምቀቱን በቀን ያላደረገበትም ምክንያት አለው። ጥምቀቱን በቀን ቢያደርገው ኖሮ አይሁድ ይህ የወረደው መንፈስ ቅዱስ ሳይሆን መናኛ ርግብ ነው ይሉ ነበር ብለው የቤተክርስቲያን አባቶች ያስተምራሉ።

እንደ ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያናችን አባቶች አስተምህሮ በብሉይ ኪዳን ዘመን ለአማናዊው የሐዲስ ኪዳን ጥምቀት ምሳሌ ሆነው የሚጠቀሱት የሚከተሉት ናቸው።፩ኛ) አበ ብዙኅን አብርሃም የአሕዛብን ነገሥታት ድል አድርጎ ሲመለስ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ለማቅረብ ዮርዳኖስን መሻገሩ ነው (ዘፍ. ፲፬፥ ፲፯-፳፫)። አብርሃም የምእመናን ምሳሌ ሲሆን ዮርዳኖስን መሻገሩ ደግሞ ለምእመናን ጥምቀት ምሳሌ ነው። ፪ኛ) ነቢዩ ኤልያስ ዮርዳኖስን ተሻግሮ ወደ ብሔረ ሕያዋን ማረጉ (፪ኛ ነገ. ፪፥፮) ሲሆን ዮርዳኖስን ተሻግሮ ማረጉ ምእመናን በጥምቀት ለመዳናቸው ምሳሌ ሆኖ ይጠቀሳል። ፫ኛ) የሶርያው ንእማን በዮርዳኖስ ውኃ ተጠምቆ ከደዌ ሥጋው መፈወሱ ከለምጹ መንጻቱ (፪ኛ ነገ. ፭፥፲፬) ፣ ምእመናን በጥምቀት አማካኝነት ከደዌ ኃጢአት እንደሚድኑ ምሳሌ ነው። ፬ኛ) ኖህና ቤተሰቡ በእምነት መርከብ ሰርተው ከጥፋት ውኃ መዳናቸው (፩ኛ ጴጥ. ፫፥ ፳፳፩)፣ ፭ኛ) በኦሪት የነበረው የግዝረት ሕግ (ዘፍ ፲፯፥ ፱፲፬፤ ቆላ. ፪፥፲፲፪)፤ ፮ኛ) እስራኤል ቀይ ባሕርን መሻገራቸው (ዘጸ. ፲፬፥ ፳፪) እና ፯ኛ) የመጥምቁ ዮሐንስ ጥምቀት (ማቴ. ፫፥፩) በዋናነት ይጠቀሳሉ።

በዓለ ጥምቀት

በግሪክ “ኤጲፋንያ” ማለት ፣ በግእዝ “አስተርእዮ” እንዲሁም በአማርኛ “መገለጥ” የሚል ትርጉም ይሰጠዋል። ከበዓለ ልደት ጀምሮ እስከ ጾመ ነነዌ መግቢያ ያለው ጊዜም በዚሁ ምክንያት ዘመነ አስተርእዮ ይባላል። በዘመነ አስተርእዮ አምላክ ሰው ሆኖ በሥጋ መገለጡን፣ በእደ ዮሐንስ በዮርዳኖስ በተጠመቀ ጊዜ የአንድነትና የሦስትነት ምሥጢር መታወቁን (ማቴ. ፫፥፲፮-፲፯) እና በቃና ዘገሊላ በተደረገው ሠርግ ላይ በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት በሠርግ ቤት የመጀመሪያው ተአምር መፈጸሙን (ዮሐ. ፪፥፩-፲፩) ቤተክርስቲያን ለምእመናን ታስተምራለች፤ ለፈጣሪዋም ምስጋናን ታቀርባለች።

ጥር ፲ በከተራ እለት ኢየሱስ ክርስቶስ ከገሊላ ወደ መጥምቁ ዮሐንስ ሄዶ በዮርዳኖስ ባሕር መጠመቁን ለማስረዳት ታቦታት ከመንበራቸው ወርደው እና በካህናት አባቶች ከብረው በዓሉ ወደሚከበርበት ቦታ በያሬዳዊ ዝማሬ፣ በእልልታ እና በሆታ ታጅበው ይጓዛሉ። በገጠር ላሉት አብያተክርስቲያናት ታቦታቱ በወንዝ ዳር፣ እንዲሁም በከተማ ደግሞ ለከተራ በተዘጋጀላቸው ጊዜያዊ ማረፊያዎቸ እንዲያርፉ ይደረጋል። ሌሊቱን ካህናቱ በቅኔ ማህሌት ሲያገለግሉ አድረው ጠዋት ላይ የቅዳሴው ሥርዓት በካህናት አባቶች መሪነት ይከናወናል። የቅዳሴው ሥርዓት እንደተጠናቀቀ የተከተራው ወኃ (መጠመቂያው ውኃ) በካህናት አባቶች ከተባረከ በኋላ ሕዝቡ ተረጭቶ ከበረከቱ ይሳተፋል። በዓሉን በተመለከተም ትምህርት ሲሰጥ ቆይቶ ታቦታቱ ካረፉበት ድንኳን ተነስተው በመጡበት አኳኋን በያሬዳዊ ዝማሬ፣ በሽብሸባ እና በእልልታ ታጅበው ወደየአጥቢያቸው ይመለሳሉ። በዚህ እለት ሊቃውንተ ቤተክርስቲያንና የሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን ”ተጠምቀ ሰማያዊ በእደ መሬታዊ” ትርጉሙም “ሰማያዊው በመሬታዊው እጅ ተጠመቀ” በሚለው ያሬዳዊ ዝማሬ እና ለበዓሉ በተዘጋጁ ሌሎች የቤተክርስቲያን መዝሙሮችም በዓሉን ሲያደምቁት ይውላሉ።

በመጨረሻም የጥምቀትን ምሥጢር የምናመሠጥረው ፣ በዓሉንም የምናከብረው ከላይ እንደዘረዘርነው ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን ለእኛ ለክርስቲያኖች የምትፈጽምልን የጥምቀት ሥርዓት ከክርስቶስ ጋር የሞቱም የትንሣኤውም ተካፋይ መሆናችንን የሚያስረዳ ነው። ምክንያቱም ተጠማቂው ከውኃ ውስጥ መግባቱ ከጌታ ጋር መሞቱን ያመለክታል። ይህንን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ሲገልጽ “ነገር ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የተጠመቅን እኛ ሁላችን በሞቱ እንደተጠመቅን ሁላችሁ ዕወቁ። በሞቱም እንመስለው ዘንድ ከእርሱ ጋር በጥምቀት ተቀበርን፤ እርሱ ክርስቶስ በአባቱ ጌትነት ከሙታን እንደተነሣ እኛም እንደርሱ በአዲስ ሕይወት እንኖራለን።” (ሮሜ. ፮፥፫፬) ። በሥርዓተ ቤተክርስቲያን መሠረት አጥማቂው ካህን ተጠማቂውን ሦስት ጊዜ በውኃ ውስጥ ብቅ ጥልቅ እንዲል ማድረጉ ጌታ ሥስት ቀንና ሌሌት በከርሠ መቃብር ማደሩን የሚያስረዳ ሲሆን ተጠማቂው በሦስተኛው ጊዜ ከውኃ መውጣቱ ጌታ መግነዝ ፍቱልኝ መቃብር ክፈቱልኝ ሳይል ከመቃብር ለመውጣቱ ምሳሌ ነው። እንደዚሁ እኛ በጥምቀት የእግዚአብሔርን ልጅነት ያገኘን ክርስቲያኖች ከክርስቶስ ጋር እንደምንነሣ እንደ ቅዱስ ቃሉ እናምናለን። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ስለዚህ ጉዳይ ሲጽፍልን እንዲህ ብሏል። “በሞቱ ከመሰልነው በትንሣኤውም እንመስለዋለን።” (ሮሜ. ፮፥፭) በዓሉንም ስናከብር በትንሣኤ ዘጉባዔ እርሱን መስለን በመነሣት እግዚአብሔር አምላክ እርሱ ዳግም በሚመጣበት ጊዜ ኑ የአባቴ ቡሩካን ብሎ በቀኙ ከሚያቆማቸው ወገን እንዲደምረን በማመን ነው ።

የጥምቀት በዓልንም እንደሚገባ አክብረን የበረከቱ ተካፋይ እንድንሆን እግዚአብሔር ይርዳን።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል፤ ወለመስቀሉ ክቡር ፤ አሜን።

ዋቢ መጻሕፍት

  1. ሳሙኤል ፍቃዱ ነገረ ሃይማኖት (ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ)፣ ሦስተኛ እትም ፣ 2005 ዓ.ም፣ ገጽ 154-159፣ አዲስ አበባ
  2. ኅሩይ ኤርምያስ (መምህር)፣ መዝገበ ታሪክ ክፍል ፩፣ 1998 ዓ.ም፣ ገጽ 147-151፣ አዲስ አበባ
  3. አባ አበራ በቀለ (ሊቀ ጉባኤ)፣ ትምህርተ ሃይማኖትና ክርስቲያናዊ ሕይወት፣ 1996 ዓ.ም፣ ገጽ 245- 247፣ አዲስ አበባ