ጽጌ አስተርአየ በውስተ ምድርነ ጊዜ ገሚድ በጽሐ
በ ዲ/ን አረጋ ጌታነህ
ጥቅምት 25 ቀን 2009 ዓ.ም
“ጽጌ አስተርአየ በውስተ ምድርነ ጊዜ ገሚድ በጽሐ ፤ አበባ በምድራችን ታየ የመከርም ጊዜ ደረሰ” መኃ ፪፥፪
በቤተ ክርስቲያናችን የዘመን አቆጣጠር መሠረት አሁን ያለንበት ወቅት ዘመነ መፀው ይባላል። አንዳንዶች በስሕተት ፀደይ ሲሉት ይሰማሉ። ዓመቱን ለዐራት የሚካፈሉት ወቅቶች በሐዲስ ኪዳን በዐራቱ ወንጌላውያን የሚመሰሉ ሲሆኑ ሁልጊዜም በ፳፮ ይጀምራሉ በ ፳፭ ደግሞ የሚፈጽሙ ሦስት ወራትን ይይዛሉ። ስለሆነም አሁን የያዝነው መፀው መስከረም ፳፮ ገብቶ ታኅሣሥ ፳፭ ለሐጋይ (ለበጋ) ያስረክባል ማለት ነው። ይህ የመፀው ወቅት በቤተ ክርስቲያን አምስት ወይም ስድስት ሳምንታት የሚኖሯትን ወርኃ ጽጌን ይይዛል። ጽጌም መስከረም ፳፮ ገብታ ጽጌም ኅዳር አምስት ትፈጸማለች። በማግስቱ ሕዳር ፮ ደግሞ እመቤታችን ከነልጇ በደብረ ቍስቋም ማደሯን እናስባልን። ይህ የአበባ ወቅት ልዩ ልዩ አበቦች መዓዛቸውን ስለሚሰጡ ባለው ምሳሌዊ ትምህርት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መስላ የዘመነ ጽጌን ሥርዓት ሰርታለች። ይህም እመቤታችን ወደ ግብጽ የተሰደደችውን ስደትና የደረሰባትን መከራ እያሰብን ጥልቅና እጅግ አስደናቂ የነገረ ሥጋዌና ነገረ ማርያም የነገረ ድኅነትን ትምህርት የምንማርበትና የምናስተምርበት ጊዜ ነው።
ጥንተ ነገር
ቤተ ክርስቲያን ስለ ድንግል ማርያም አብዝታ መናገሯን የማታቋርጠው ነገረ ድኅነትንም ይሁን ነገረ ሥጋዌን ከእምቤታችን ነጥለን ለመጓዝ መሞከር በጨለማ እንደመደናበርነው። ስለእመቤታችን ስንናገር ስለክርስቶስ ፣ ስለነገረ ሥጋዌ ፣ ስለነገረ ድኅነት ማውራታችን እና መናገራችን መሆኑ የታወቀ ነው። ሊቁ አባ ጽጌ ድንግል በድርሰቱ “በጌጋየ አዳም ወሔዋን ሱራፊ ዘአፀዋ እንበለ በፍቅርኪ(በጽድቅኪ)(ጽጌኪ) መኑ ለአንቀጸ ገነት ዘአርኃዋ ተፈስሒ ድንግል መያጢተ አዳም እምፄዋ በተአምርኪ ውስተ ምድረ ጽጌ አቲዋ ከመ ጣዕዋ አንፈርዓፀት ሔዋ” እንዳለ። ልብ አድርጉ ሊቁ የሚነግረን በአዳምና በሔዋን በደል ምክንያት ገነት በሱራፊ መጠበቋንና የሰው ልጅ ለአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ገነትን ያህል ቦታ ጥንተ ርስቱን አጥቶ በግብርናተ ዲያብሎስ መያዙን ነፍሱ በሲኦል ሥጋው ደግሞ በመቃብር የደረሰብትን ስቃይና የመርገመ ኃጢአትን ገፈት እየቀመሰ እንደነበረ እንረዳለን። አዳምም እግዚአብሔር ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃልሁ ያለውን ተስፋ ይዞ ልቅሶውን ማሰማቱን ያም ይሆን ዘንድ ያንቺ እውነት (ጽድቅ አንድም ልጅሽ) ካንቺ የተገኘ ክርስቶስ እንጂ ያንን የተዘጋ በር ማን ከፈተው? ስለዚህ ድንግል ሆይ! አዳምን ከምርኮ የመለሽው ሔዋንንም ገነት ስትመለስ እንደእንቦሳ እንድትቦርቅ ያደረግሻት ሆይ! ደስታ ይገባሻል በማለት በቅዱስ ገብርኤል ምስጋና ደስ ይበልሽ ማለቱን ልብ ይሏል። አሕዛብ በእርሷ ተቀድሰዋል ስድባቸው እርቆላቸዋል አባታችን አብርሃምም ለእግዚአብሔር ልጅነት መለያ ይሆነው ዘንድ የግዝረቱ ምልክት የሆነችለት አብርሃም ልጁን ይሰዋው ዘንድ እግዚአብሔር በጠየቀው ጊዜ በእምነት ልጁን ሊሰዋው በተዘጋጀ ጊዜ ለቤዛ ይስሐቅ የተሰጠውን በድንግልና የወለደችውን በግዕ ክርስቶስን አስገኝታልናለችና “ማርያም ዕፀ ሳቤቅ ወምስራቅ ዘያዕቆብ ወላዲቱ ለስርግው ኮከብ “ እንላታለን። በቤተ ያዕቆብ ለዘላለሙ ይነግሣል የተባለ አማናዊ ኮከብ ፀሐየ ጽድቅ ክርስቶስን ወልዳልናለችና። እመቤታችን ክርስቶስን ለመውለድ የተገባች ሁና ተገኝታለችና ከመንፈስ ቅዱስ ግብር የተነሣ ለወላዲተ አምላክነት ተመረጠች። ይልቁንም እርሷ ትንቢት የተነገረላትንና መሲሕ ክርስቶስን ትወልዳለች የተባለችውን ድንግል ሴት ደርሸባት ለማገልገል በታደልኩ እያለች ትመኝ ነበር። በዚህም ያለበደልና በንጽሕና በመገኘቷ ሰባቱን መስተቃርናን አንድ ያደረገውን የሁላችንንም ደስታና መድኃኒት ክርስቶስን ለመውለድ በቃች።
በአይሁድ እና በሄሮድስ ያደረ ጥንተ ጠላት ዲያብሎስ መከራ ያበዛባት ዘንድ ከበፊቱ ይልቅ አሁን ዝናሩን ታጠቀ። ሄሮድስ የክርስቶስን መወለድ ከነገደ ስምዖን (ጸሐፍት) ኋላም ከሰብአ ሰገል ጠይቆ በተረዳ ጊዜ በቤተልሔም አውራጃ ያሉ ሕፃናትን አስፈጃቸው ማቴ ፪፥፲፫። ቍንጽል ሄሮድስ ክርስቶስን ሊገድል መፈለጉን አስቀድሞ እንደምትወልድ ያበሠራት መልአክ ለአረጋዊ ዮሴፍ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ ግብጽ ሽሽ አለው። ይህም ልጄን ወደ ግብጽ ጠራሁት ተብሎ በኢሳይያስ ነቢይ የተነገረው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ግብጽም በኪደተ እግሩ እንድትባረክ የግብጽ ጣዖታትም እንዲሰባበሩ ለስዱዳንና ለመናንያነ ዓለም ስደትን ዋጋ ያገኙበት ዘንድ ሊባርካቸው ቃሉ የታመነ መሆኑ እንጂ አኃዜ ዓለም በእራኁ ኵሉ እኁዝ ውስተ እዴሁ የተባለ በደመናት ጀርባ ላይ የሚራመድ ብርሃናትን የሚያመላልስ መለኮታዊ ቃል ለከንቱ አልተሰደደም። ይህንንም ሊቁ “ እፎ ጐየይኪ እምፍርሐተ ቀትል እምገጸ ሄሮድስ ቍንጽል ወለተ አናብስት እለ ይጥኅሩ በኃይል ኢፈቀድኪዮ በምድር ለመንግሥተ ዓለም ወብዕል እስመ ልማዱ ትሕትና ለፍሬ ከርስኪ ልዑል ከማሁ ግዕዝኪ በምግባር ወቃል” ብሏታል። በአናብስት የተመሰሉ ነቢያት ዘመዶቿ በመንፈስ ኃይል ትንቢት መናገራቸውን በማስታወስ ለምድራዊ ምቾት ራሷን ያላዘጋጀች መሆኗንም አስቀምጧል። ለዛ ነበር መልአኩ ወንድ ልጅን ትልጇለሽ ሲላት “እንዘ ኢየአምር ብእሴ” ያለችው። ሴቶች የሚያስቡትን ዓይነት ምድራዊ አላፊ ጠፊ አሳብ አልነበራትም። የማሕጸንሽ ፍሬ ክርስቶስ የትሕትና አባት አንቺም ትሑት እና ንጽሐ ሥጋ ወነፍስ የተባበሩልሽ ነሽ ያላትም ለዚህ ነው። እመቤታችን በግብጽ ፵፪ ወራት (ሦስት ዓመት ከስድስት ወራት) ተንከራታለች። እመቤታችንን ካገኛት ስቃይ መከራና ልቅሶ አንጻር ዓመቱን ሁሉ ብናስባትም የሚበቃ አልነበረም። ሰይጣን መከራውን ያፀናባት ዘንድ ያላደረገው ተንኮል ያልሞከረው ክፋት አልነበረም።ሴቲቱን ግን አልቻላትም ተብሎ እንደተጻፈ (ራዕ ፲፪ ) እመቤታችን የድል ምልክት የመስቀል መገኛ ዕፀ ሳቤቅ ለመሆን በቃች። ስለዚህ ስደቷን በማኅሌት በቅዳሴ በጾም በጸሎት በቃለ እግዚአብሔር እንዘክረዋለን። ኋላም የሄሮድስን ሞት ሰምታ እመቤታችን ስትመለስ በደብረ ቍስቋም እረፍት ማድረጋቸውን እናስባለን። “ምንተ እነግር ወምንተ እዜኑ በእንተ ዝንቱ ምስጢር እስመ ኀደረ ልዑል ውስተ ደብረ ቍስቋም ወምስለ ማርያም ድንግል” እንዲል ሊቅ። ከላይ ከአርያም የሆነ ኃይልና ፅንዕ ድንቅ መካር የማይጠፋ የሕይወት ብርሃን እንደ ደካማ የሚያርፍበትን ቦታ ፈለገ። ደብረ ቍስቋም የመመለስ (ጠብቆ) የምስጢር የድል አድራጊነት የማሸነፍ የአዲስ ሕይወት ጅማሮ መሠረት ተደረገች። መላእክቱም በቤተልሐም የነበራቸውን ግብር አስተባበሩ። እናትና ልጁን ጋረዷቸው አንድም በደብረ ቍስቋም መኖራቸው ለሰው ልጅ ሁሉ በገሐድ (በግልጥ) ታየ ተረዳ ምስጋና በሰማይ ሰላምም በምድር ይሁን በማለት ዘመሩ።
ከላይ ለማየት እንደሞከርነው ቤተ ክርስቲያን እንዲህ የተሰናሰለ የዘመነ ጽጌ ሥርዓትን ለምእመናን እየሰጠች ምእመናንም እየተቀበሉ ክርስቶስም እየተሰበከ የማይቋረጠውን ቃል ኪዳን በማስቀጠል ሕያው አገልግሎቷን ትሰጣለች። ይህ እንግዲህ የቤተ ክርስቲያን ሕይወት መንፈስ ቅዱስ በቤተ ክርስቲያን አባቶች ላይ አድሮ ያስተማረው የገለጠው አበውም ያስቀጠሉት እኛም የተረከብነው እጅግ ውብና ማራኪ ትውፊት እና ሥርዓተ አምልኮ ነው። ይህም ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን በጎላና በተረዳ መልኩ እየተገበረችው ያለው መንፈሳዊ አገልግሎት በብሉይ ኪዳን በነበሩ አባቶችም በምሳሌ ትምህርት በትንቢትና በተስፋ ኋላም በክርስቶስና በእናቱ የተፈጸመ ሐዋርያት የስተማሩት ሊቃውንት ሥርዓት ያበጁለት ግሩም ሥጦታ ነው። ሰሎሞን ክረምቱ አለፈ ዝናብም አልፎ ሄደ ጽጌ አስተርአየ በውስተ ምድርነ አበቦች በምድር ላይ ታዩ በማለት በምሳሌ ትምህርት በጥልቅ አገላለጥ አዝማንን ተፈጥሮን አካልን በማስተሳሰር ድንቅ ምስጢር አስተላልፎበታል። እመቤታችንን በአበባ ልጇን ደግሞ በፍሬው ለመመሰል የሚመች ወቅት ከወርኃ ጽጌ ሌላ ባለመሮሩ ነገሮችን በምስጢር ማሰናሰል የሆነላቸው ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ይህንን ጊዜ ከጥንት ዘመን ጀምረው ያመሰጥሩበታል። የዚህ ወቅት ትምህርታቸውም በአበባና በፍሬ ቢመስሉትም በምስጢር ደግሞ ክርስቶስና ሙሽራዋ ድንግል ማርያምን ሙሽራው ክርስቶስንና ቤተ ክርስቲያንን እንዲሁም ሙሽራዋ ወንጌልን ይሰብኩበታል። ይህ ወቅት የአበባ ብቻ ሳይሆን ፍሬም የሚያፈሩ አዝርዕት እና እፅዋት በመኖራቸው መኸርንም ሲጠራው ጊዜ ገሚድ በጽሐ የመኸር ጊዜ ደረሰ ብሎናል። መኸር ምርት ከገለባው ጥሩ ምርት ጥሩ ካልሆነ ግርድ የሚለይበት እንክርዳዱም ተነቅሎ የሚጣልበት ከዚህም አልፎ በወንጌል እንደተጻፈው ወደ እሳት የሚወረወርበት አጫጆች ማጭዳቸውንና ምሳራቸውን የመከሩ ባለቤትም መንሹን የሚያዘጋጅበት እረፍት የሌለው የመጨረሻ የልፋቱን ዋጋው ምርት የሚያገኝበት ጎበዝ ገበሬ የሚደሰትበት ሰነፍ ደግሞ ቁርጡን የሚያውቅበት አዕዋፋት አራዊትም ቢሆኑ የራሳቸውን ድርሻ ለመውሰድ የሚሯሯጡበት አስደናቂ ወቅት ነው። እርግጥ ነው እንደ ክረምት አስፈሪነት ከባድነት ርጡብነት ጎርፍና ማእበል ብዛት የአበባ የፍሬ የእሸት የመኸር ጊዜ ባይመጣ ሕይወት ከባድ አስፈሪም ትሆን ነበር። ከፈጠረ ዘንድ መመገብ ልማዱ የሆነ የሠራዊት ጌታ ልዑል እግዚአብሔር ግን ነገሩን ድንቅ አድርጎ በሥነ ፍጥረት እንድንገረም አደረገን። የእኛም ድርሻ በቤቱ በመኖር የታዘዝነውን እየፈጸመን እግዚአብሔር ቸር እንደሆነ ቅመሱት እንደተባልን እንድንኖር ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ሠራችልን። ከገበሬውና ከግብርና ጋር አያይዘን የገለጥናቸውን ነገሮች በምስጢር ካየናቸው ደግሞ የመከሩ ባለቤት ክርስቶስ አጫጆች መላእክት ፍሬ ማፍራት ያለብንና እንድናፈራ የሚጠበቅብን ምእመናን መንሽ የተባለው የእግዚአብሔር ፍትሕ ርትዕ ሁሉ አይቀሬዎች ናቸው። ጥበበኛው ሰሎሞን ደረቅ በሆነ ትንቢት ጊዜ ገሚድ በጽሐ ብሎናል።
እርግጥ ነው በዚህ በተበታተነ በተዘበራረቀና የኅሊና እረፍት በሌለበት ወቅት ለምንገኝ ክርስቲያኖች የመኸር ጊዜ ደረሰ የሚለው አስደሳች አይመስልም። ለመመለስ በቀጠሮ ጊዜ ለምናባክን በቤቱም አለን የምንል የተዘራብንን የማናበቅል ቢበቅልም በቶሎ የሚጠወልግብን ጎስቋሎች ወደ ቤቱ ለመመለስ ማሳሰቢያ ወቅት ነው። ዘመነ መገለጥን የሚያበስረው የመኸርን መድረስ የሚያመለክተን ይህ ወቅት ምንኛ አስደናቂ ነው? ዘመነ መገለጥ ሲመጣ በመገለጡ ለመጠቀም የሚያበቃውን እምነትና ታማኝነት ቅን ልቡና ይዘን መገለጡን እንድንታደም በቤቱ በአካል ብቻ ሳይሆን በሕይወትም እንድንኖር በምስጢራት በመታጀብ ኅብረታችንን ከፊት ይልቅ አሁን ልናጠናክረው በሚያስፈልገን ወቅትና ቦታ እንገኛለን።