በአውሮፓ ተወልደው ላደጉ የአብነት ተማሪዎች ሢመተ ዲቁና ተሰጠ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በስዊድንና ስካንዴኒቪያን ሀገረ ስብከት የኦስሎ መካነ ቅዱሳን ቅዱስ ገብርኤል ወአቡነ ተክለሃይማኖት ቤተክርስቲያን በአውሮፓ ተወልደው ላደጉ ሰባት የአብነት ተማሪዎች ዲቁና ተሰጠ።
ለ 4 ዓመታት የአብነት ትምህርታቸውን ሲከተታሉ ለነበሩት ሰባት አዳጊ የአብነት ተማሪዎች ኅዳር 28 ቀን 2012 ዓ.ም. በሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ በብጹዕ አቡነ ኤልያስ ማዕርገ ዲቁና ተሰጥቷል፡፡
የኢጣሊያና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሕርያቆስም እ.ኤ.አ ከ2015 ዓ.ም. ጀምሮ በደብሩ የአብነት ትምህርት ቤትን በማቋቋም፣ የአብነት ትምህርቱንም በማስተማር፤ ተተኪው ትውልድ በትክክል እንዲቀረጽ እና የነገዋ ቤተ ክርስቲያን ተረካቢ እንዲሆን፣ በደብሩ የሚገኙት አዳጊ ወጣቶችም በፈሪሃ እግዚአብሔር፣ በፍቅረ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንዲያድጉና ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በሚገባ እንዲያውቋት በማድረግ ረገድ፡ በአጥቢያው የሚገኙትን ማኅበረ ምእመናን በማስተባበር አባታዊ ሓላፊነታቸውን በመወጣት ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡
በአሁኑ ጊዜ በደብሩ ከአንድ መቶ በላይ ተማሪዎች የአብነት ትምህርት በመከታተል ላይ የሚገኙ ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ ሕጻናት እና ወጣት ሴቶችን ለማበረታታት መዝሙረ ዳዊት ላይ የደረሱ እንዲሁም ውዳሴ ማርያም በመጨረስ ላይ ያሉ ሁለት ሴት ተማሪዎች በብጹዕ አቡነ ሕርያቆስ የተዘጋጀላቸውን የማበረታቻ ሥጦታ ከብጹዕ አቡነ ኤልያስ እጅ ተቀብለዋል። በተጨማሪም በዲቁና ሲያገለግሉ የነበሩ አንድ አገልጋይም በዕለቱ ማዕርገ ቅስና ተቀብለዋል፡፡
በማኅበረ ቅዱሳን አውሮፓ ማእከል የኖርዌይ ንዑስ ማእከል አባላትም የአብነት ትምህርቱ እንዲጠናከር በማስተማር እና በማስተባበር የበኩላቸውን አስተዋጾ በማበርከት ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡