በፍራንክፈርት ከተማ ዐውደ ርእይ ተካሄደ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን በአውሮፓ ማእከል የጀርመን ንኡስ ማእከል አዘጋጅነት “ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን አስተምህሮዋን እንጠንቅቅ፤ ድርሻችንን እንወቅ” በሚል መሪ ቃል ኅዳር 28 ቀን 2012 ዓ.ም. በፍራንክፈርት ምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ዐውደ ርእይ ተካሄደ::

ዐውደ ርእዩን የጀርመን እና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅና የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ መዊዕ ልሳነ ወርቅ ውቤ በጸሎት የከፈቱት ሲሆን፤ የደብሩ ካህናት እና ከ100 በላይ ምዕመናን ተመልክተውታል። ዐውደ ርእዩ በዋናነትም በአራት ክፍሎች ተደራጅቶ፤ ስለ ቤተ ክርስቲያናችን መሠረተ እምነት፣ ስለ ሐዋርያዊ አገልግሎት ምንነትና እና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የሐዋርያዊ አገልግሎት ጉዞ፣ በዓለምና በኢትዮጵያ በተለያዩ ክፍላተ ዘመን ስለነበረው የቤተ ክርስቲያን ተጋድሎ፣ እና ወቅታዊው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተጋድሎ (በተለይም ከአክራሪዎች እና ከፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ጋር ያለው ተጋድሎ) በድምጽ ወምስል የታገዘ ገለጻ በዝርዝር ቀርቧል፡፡

በመጨረሻም ማኅበረ ቅዱሳን ባለፉት ዓመታት ውስጥ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን የነበረውን የአግልግሎት ሱታፌ እና አስተዋጽኦ በተንቀሳቃሽ ምስል በታገዘ መልኩ የቀረበ ሲሆን የማኅበረ ቅዱሳን አመሠራረት፣ ርእይ፣ እና የአገልግሎት መስኮች እንዲሁም በአውሮፓ ማዕከል እና በጀርመን ንዑስ ማዕከል ስላለው እንቅስቃሴ በሊቀ ትጉኃን ቀሲስ አብርሃም አሰፋ ሰፊ ገለጻ ተደርጓል፡፡ 

ዐውደ ርእዩን ከተመለከቱ ካህናት እና ምዕመናን ጋር ስለ ወቅታዊ የቤተ ክርስቲያን ፈተናዎች በተለይም እየከፋ ስለሄደው የአብያተ ክርስቲያናት መቃጠል፣ የምዕመናን መገደል እና መፈናቀል ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡ በውይይቱ ላይ ለተነሱ ጥያቄዎችም በሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ በመልአከ መዊዕ ቀሲስ ልሳነ ወርቅ ውቤ ማብራሪያ ተሰጥቷል። 

የጀርመን ንዑስ ማዕከልም ለዝግጅቱ መሳካት ከጅማሬ እስከ ፍጻሜ ከፍተኛ ትብብር ያደረጉትን የደብሩን አስተዳዳሪ እና ሰበካ ጉባኤ፣ ዐውደ ርእዩ ላይ በገላጭነት የተሳተፉትን የደብሩን ሰንበት ትምህርት ቤት አባላት፣ ለዝግጅቱ መሳካት በተለያየ መልኩ እገዛ ያደረጉትን እንዲሁም ረጅም ሰዓት ወስደው ዐውደ ርእዩን የጎብኙትን ምዕመናን በሙሉ አመስግኖ ይህ ቀና ትብብር ለወደፊትም እንደማይለየው ያለውን ጽኑ እምነት ገልጿል። 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መዋቅራዊ አንድነቷን መመለስ ተከትሎ፣ ማኅበረ ቅዱሳን በነበረው የአስተዳደር ልዩነት ምክንያት አገልግሎቱን ሳይሰጥ በቆየባቸው አጥቢያዎች አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኝ የማኅበረ ቅዱሳን ተወካይ መልአከ ሣህል ቀሲስ ያብባል ሙሉዓለም ገልጸዋል። ይህ ዐውደ ርእይም ማኅበረ ቅዱሳን ብዙ ካህናት እና ምዕመናን ባሉት፣ የራሱ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ባለቤት በሆነው፣ እንዲሁም ከሕጻናት እስከ አዋቂዎች ሰፊ አገልግሎት በሚሰጥበት በፍራንክፈርት ምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ያካሄደው የመጀመሪያ አገልግሎቱ ነው፡፡

በመጨረሻም መልአከ መዊዕ ቀሲስ ልሳነ ወርቅ ውቤ ዐውደ ርእዩ እንዲሳካ ድጋፍ ያደረጉትን ሁሉ አመስግነው ከምንጊዜውም በላይ ለቤተክርስቲያን ኅልውና በጋራ የምንቆምበት ጊዜ በመሆኑ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ለመደገፍ ሁላችንም የበኩላችንን አስተዋጽዖ ልናደርግ እንደሚገባ በማሳሰብ መርሐ ግብሩን በጸሎት ዘግተዋል፡፡