በቅድስት ቤተ ክርስቲያን እየደረሰ ያለውን ጥቃት በመቃወም በተለያዩ የአውሮፓ አገራት ሰላማዊ ሰልፍ ተደረገ፡፡

መንግሥት የዜጎችን ደኅንነት የማስጠበቅ ግዴታ ያለበት በመሆኑ በአገር ቤት በምትገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እና በልጆቿ ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃት የኢትዮጵያ መንግሥት እንዲያስቆም፣ አብያተ ክርስቲያነቱን ያቃጠሉ በልጆቿ ላይም ግፍን ያደረጉ ሰዎችን ለፍርድ እንዲያቀርብ ለመጠየቅ በአውሮፓ በሚገኙ ሦስቱ አህጉረ ስብከት (የስዊድንና የስካንዴኒቪያን ሀገረ ስብከት ፣ ጀርመንና አካባቢው ሀገረ ስብከት እና የጣልያንና አካባቢው ሀገረ ስብከት) አስተባባሪነት በተለያዩ የአውሮፓ ከተሞች ሰላማዊ ሰልፍ  ተካሂዷል፡፡

ሰላማዊ ሰልፎቹ በ ጣልያን ሮም፣ ቤልጅየም ብራስልስ፣ ጀርመን በርሊን፣ ሆላንድ ዘሄግ፣ ስዊዘርላንድ ጄኔቫ.፣ ስዊድን ስቶክሆልም እና በ ኦስትሪያ ቪዬና ኅዳር 26 ቀን 2012 ዓ.ም. ተካሄደዋል፡፡ በተጨማሪም በፈረንሳይ ፓሪስ ኅዳር 25 ቀን 2012 ዓ.ም. ተካሂዷል፡፡ በሰልፎቹም ላይ የጀርመን እና አካባቢው አገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ዲዮናስዮስ፣ የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ፣ የየአድባራት አስተዳዳሪዎችና አገልጋይ ካህናት፣ የሰ/ት/ቤት ወጣቶች እና ምእመናን ተገኝተዋል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ በሌሎቹም አገራት የየአህጉረ ስብከት ተወካዮች፣ የየአድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ካህናት፣ የሰ/ት/ቤት ወጣቶች እና ምእመናን በተገኙበት በታላቅ ድምቀት ተከናውኗል፡፡

ሰልፉ በሁሉም ሥፍራ በጸሎተ ወንጌል የተጀመረ ሲሆን፡ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን እየደረሰ ያለው መገፋትን እግዚአብሔር እንዲመለከትም ጸሎተ ምሕላ ደርሷል፡፡ በሰልፉ ላይ የተገኙት አባቶችም “ጩኸታችንን ለዓለም ሕዝብ በማሰማት ብቻ እንዳይገታ ይልቁንም ከፊት ይልቅ ይበልጥ ወደ እግዚአብሔር በመቅረብ ስለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን እና እግዚአብሔርን ስለ ምትወድደው አገራችን በፍጹም ኀዘን ልናሳስብ ይገባል” በማለት መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ ሰላማዊ ሰልፎቹ የተካሄዱበት ዓላማም በቤተ ክርስቲያን ላይ እየደረሰ ያለውን ግፍና መከራ ለማውገዝ፣ እንዲቆም ለመጠየቅ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ሚዲያዎች ተገቢውን ሽፋን ሊሰጡት ስላልቻሉ የተለያዩ ሚዲያዎች እና የዓለሙ ማኅበረሰብ እንዲያውቀው እና ይህን ችግር እየፈጠሩ ያሉ አካላት ላይም ሆነ የኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ጫና እንዲፈጥሩ ለማድረግ መሆኑን በሰልፉ ላይ የተገኙ አባቶችና አስተባባሪዎች ተናግረዋል፡፡

 በክርስቲያኖች ላይ የተቃጣውን ጥቃት የዓለሙ ማኅበረሰብ እንዲያውቀውና እንዲያወግዘው ለማድረግ ታስቦ የተደረገው ሰልፍ፡ በየአህጉረ ስብከቶቹ ሊቃነ ጳጳሳት በየሀገራቱ ቋንቋዎች የተጻፉት የአቤቱታ ደብዳቤዎች በሮማ ለፓርላማው ጽ/ቤት፣ በበርሊን ለጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ዴስክ፣ በጀርመን ለአውሮፓ ህብረት ጽ/ቤት፣ ለፈረንሳይ እና አሜሪካ ኢምባሲዎች፣ በዘሄግ ለኢትዮጵያ ኤምባሲ፣ በስቶክሆልም ለስዊድን ገዢ ፓርቲ፣ በጽሑፍ ቀርበዋል፡፡ አባቶችና የምእመናን ተወካዮችም ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የየሀገራቱ ተዋካዮች ጋር በመነጋገር ለተጨማሪ ውይይት ቀጠሮ ማስያዛቸው ታውቋል፡፡ በሆላንድም እንዲሁ የኢትዮጵያው አምባሰደር የሰልፉን ተወካዮች በቢሮአቸው በመቀበል አነጋግረዋቸዋል፡፡

በሰላማዊ ሰልፉ ላይ ከተላለፉት መልእክታት እና መፈክሮች መካከል ሀገር ከነድንበሩ፣ ነጻነትን ከነክብሩ፣ ፊደልን ከነቁጥሩ ያስረከበች ቅድስት ቤተክርስቲያን ይህ አይገባትም፤ የቤተ ክርስቲያን ጩኸትና አቤቱታ ይሰማ፤ አክራሪ ብሔርተኞችና ጽንፈኞች እጃቸውን ከቤተክርስቲያን ላይ ያንሡ፤ ቤተክርስቲያንን ያቃጠሉ፣ ካህናትንና ምዕመናንን የገደሉ በሕግ ይጠየቁልን፤ የሚሉ እና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡

ሰልፉ ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መንገድ በተያዘላቸው መርሐ ግብራት መሠረት የተከናወኑ ሲሆን፤ በሥራ ቀን የተደረገ ቢሆንም የተገኙት የምእመናን ቁጥር ከፍተኛ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በሮም የተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑና የ የታላቋ ብሪታንያ እና አየርላንድ ሀገረ ስብከትም ከወራት በፊት በተመሳሳይ መልኩ በለንደን ከተማ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረጉና በለንደን ከኢትዮጵያ ኢምባሲ ጋርም ውይይት ማካሄዱ ይታወሳል፡፡

ከየከተማዎቹ የተወጣጡ የተወሰኑ ፎቶዎች

ሮም ፤ ጣልያን
ጀርመን ፤ በርሊን
ስዊድን ፤ ስቶክሆልም
ሆላንድ ዘሄግ በ ኢትዮጵያ ኤምባሲ ውስጥ