ሁለቱ እንስሶች

በአስናቀች ታመነ

ምንጭ: ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ከሰኔ 16 – 30/ 2011 ዓ.ም. ዕትም

ሰላም ልጆች እንደምን አላችሁ? ደኅና ናችሁ ለዚህ ቀን ያደረሰን እግዚአብሔር ይመስገን! አሜን! ልጆች ዛሬ ከሌላው ቀናት የተለየ ታሪክ ይዘንላችሁ ቀርበናል። ጽሑፉን ከማንበባችሁ በፊት አስቀድማችሁ እስቲ ገምቱ ስለምን ይመስላችኋል፧ ስለቅዱሳን ሰዎች ካላችሁ እንደዛ አይደለም። ስለምን እንደሆነ ልንገራችሁ ስለ እንስሳት ነው። ስለየትኞቹ እንስሳት ካላችሁኝ ስለ አያ አንበሶ እና የሚጣፍጥ ማር ስለምትሰጠን ስለ ንብ ነው።

አያ አንበሶ

ከእለታት አንድ ቀን በቅድስት ማርያም ገዳም የንግሥ በዓል ይሆንና ብዙ ምእመናን በዓሉን ለማክበር ወደ እመቤታችን ቤተክርስቲያን ይመጣሉ። በንግሥ በዓሉ ላይ የተገኘው ሕዝበ ክርስቲያን ያለውን ሁሉ በደስታ ይሰጥ ጀመር። አንድአንዱ ገንዘቡን ፣ አንድአንዱ ደግሞ የአንገት ጌጡን ፣ ሌላው ደግሞ የእጅ ወርቁን ፣ ልብስ ፣ ጧፍ ፣ ሻማ ፣ ዕጣን ይሰጣል። ይህን የተመለከተ አንድ ሰው ፍቅረ ነዋይ ያድርበትና ይህን ብርና ወርቅ በኋላ ላይ መጥቼ እወስደዋለው አለ። የንግሥ በዓሉ በመዝሙርና በጸሎት ተጠናቀቀ።

እናም ይህ ክፋት ያደረበት ሰው ሁሉም ሕዝበ ክርስቲያን ወደ ቤቱ ሔዶ ሲያልቅ ወደ ቤተክርስቲያኑ ለመሔድ በልቡ አሰበ። እርሱ ያሰበው ”ሰው ሳያየኝ ሔጄ ዘርፌ ሀብታም እሆናለው” ብሎ ነበር። ነገር ግን ከሰዓት ሰው ሁሉ ከሔደ በኋላ እየተጣደፈ ከኋላው ሰው አለ የለም እያለ መገስገስ ጀመረ። ከዚያም እንደምንም ብሎ ከገዳሙ ደረሰ። ከደረሰም በኋላ በጠዋት ከሕዝበ ክርስቲያኑ ሲሰበሰብ የዋለውን ስጦታ በድፍረት ሊሰርቅ ሲል ከየት መጣ ሳይባል አያ አንበሶ ከተፍ አለና ”ለእመቤታችን የተበረከትውን ስጦታ ልትወስድ መጣህን” ብሎ በሰው ቋንቋ ሲያናግረው ሰውየው በጣም ደነገጠ።

ድንጋጤው በሦስት ምክንያት ነበር። የመጀመሪያው አያ አንበሶን ማየቱ ፣ ሁለተኛው አያ አንበሶ በሰው ቋንቋ መናገሩና ሦስተኛው ደግሞ የእራሱ ሕሊና በፈጠረበት ጭንቀት ነበር። በጣም ከመደንገጡ የተነሣ መንቀጥቀጥ እና መንዘፍዘፍ ጀመረ። አያ አንበሶ ለሁለተኛ ጊዜ ”አንተ ሰው የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር የተባለውን ቃል አስታውስ እንጂ” አለው።

ሰውየው ይበልጥ በመደንገጥ አምላኬ ይቅር በለኝ እያለ ከቅጥረ ቤተክርስቲያኑ ወጥቶ ፈረጠጠ። ልጆች እግዚአብሔር ቤቱን በእንስሳትም እንደሚጠብቅ ተመለከታችሁ። ልጆች እግዚአብሔርን እንጂ ሰውንም ሆነ ሌላውን ተደብቆ ክፋት ማድረግ ኃጥያት መሆኑን መረዳት አለባችሁ። እግዚአብሔርን ማሳዘን ጥሩ አይደለም ፣ እግዚአብሔርን የሚያሳዝኑ ሥራዎች በሙሉ መጥፎ መሆናቸውን መረዳት አለባችሁ።  

ንብ

ከእለታት አንድ ቀን የማያምኑ ሰዎች ቤተክርስቲያናችንን ለማጥፋት ያስቡና ለመስረቅ የሚመች ሰዓት እስከሚያገኙ ድረስ ይጠብቁ ነበር። ነገር ግን በቤተክርስቲያኑ አጸድ ውስጥ በሚገኝ ትልቅ ዛፍ ንቦች ይኖሩ ነበር። መጥፎ የሚያስቡ ሰዎች ካሉ ከቤተክርስቲያን ያባርራሉ። ይህን ድርጊት ማንም አያውቅም ነበር። ከዚያም ከዕለታት አንድ ቀን ቤተክርስቲያንን ለማጥፋት ተጠራርተው ቤተክርስቲያን ማፍረሻ አካፋ ፣ ዶማ እና ሌሎችም መሳሪያዎች ይዘው ወደ ቤተክርስቲያን መሔድ ጀመሩ። ወደ ቤተክርስቲያኑ ሲጠጉ ንቦቹ አንድ ጊዜ ወጥተው እየነደፉ አባረሯቸው። ንቦቹ ቅድስት ቤተክርስቲያንን ከአረማውያን ጠበቁ ማለት ነው። ልጆች ክፋትን የሚያስቡ ሰዎች በእግዚአብሔር የሚታዘዝ ቁጣ እንደሚደርስባቸው ተረዳችሁ? ወደ ቤተ እግዚአብሔር የሚመጡ በቅን ልቦና በንጹሕ ሕሊና እግዚአብሔርን የሚያስደስት ተግባር ለመፈጸም መሔድ እንዳለባቸው መረዳት ይገባችኋል።