ደብረ ዘይት

                                          በአባ ዘሚካኤል ደሬሳ

 

 

የዓለሙ ፍጻሜ ምልክቱ ምንድ ነው?/ማቴ. 24፣3/

 

በዓቢይ ጾም ውስጥ ካሉት ሳምንታት ደብረ ዘይት 5ኛው ሳምንት ላይ ይውላል፡፡ ደብረ ዘይት ትርጉሙ የወይራ ዛፍ ተራራ ማለት ሲሆን፣ ይህም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኢየሩሳሌም በሚገኘው በደብረ ዘይት ተራራ ቅዱሳን ሐዋርያት” የዓለሙ ፍጻሜስ ምልክቱ ምንድነው?”/ማቴ. 24፣3/ ብለው ጠይቀውት እርሱም የማይቀረውን የዓለም ፍጻሜና አስቀድመው የሚፈጸሙ ምልክቶችን አስረድቷቸዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያንም ይህንኑ በደብረ ዘይት ሳምንት ታስበዋለች፤ ለምእመናኑም ከዘመኑ ሁኔታ አንጻር በመጻሕፍት የተጠቀሱትን የትንቢት ምልክቶቹን ከተግባራዊ የዓለም ክንዋኔዎች አንጻር በማገናዘብ ታስተምራለች፡፡ በመሆኑም በቤተ ክርስቲያናችን በደብረ ዘይት ሳምንት ምጽአትን አስመልክቶ የሚነገሩ ምስጢራት እጅግ ሰፊ ናቸው፡፡ ነገር ግን በዚህ ጽሑፍ በመጠኑ የምናየው ከቅዱሳት መጻሕፍት አንጻር በዓለም እየተከሰቱ ካሉ ወቅታዊ ምልክቶች ጋር በማገናዘብ ይሆናል፡፡

 

 

የሰው ልጅ ከሥነ ፍጥረት መነሻ ጀምሮ ስለ ራሱ መጨረሻና ስለ ዓለም ፍጻሜ ምንነት ማወቅን እንደሚሻ ቅዱሳት መጻሕፍት ያስረዱናል፡፡ ከነዚህም በተለይ ቤተ ክርስቲያን በደብረ ዘይት እለት የምታስተምረው፤ ቅዱሳን ሐዋርያት’ የዓለሙ ፍሳሜስ ምልክቱ ምንድነው?/ማቴ. 24፥3/’ በማለት የጠየቁት ጥያቄ ቅድሚያ ይሰጠዋል፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያት ከመለሰላቸው ዋናውና ቀዳሚው የምጽአቱ ምልክት የሐሳዊ መሲህ መምጣት ነው፡፡ ሐሳዊ መሲሕ ማለት በቀጥታ ትርጉሙ ሐሰተኛ የሆነ በስሙ ማለትም በኢየሱስ፣ በክርስቶስ፣ በአምላክ ስም የሚመጣ የክርስቶስ ተቃዋሚ ማለት ነው፡፡ ትርጉሙን አስፍተን ስናየው፣ ደግሞ ከሃይማኖት ጋር ተያያዥ የሆኑና ያልሆኑ በዓለም እየተካሄዱ ያሉ ሐሰተኛ ጉዳዮችንና የጥፋት መንገዶችን ያጠቃልላል፡፡ የሐሳዊ መሲሕ የጥፋት ሥራዎች ሳያውቁም ሆነ በተለይ ሆን ብለው በዓለማውያንና በክፉ መናፍስት ተከታዮች እየተፈለሰፉ በሚከሰቱ ሁኔታዎች የሚካሄዱ ናቸው፡፡ ከእግዚአብሔር የተገኙ የሃይማኖት የሥነ ተፈጥሮ የጋብቻና የመሳሰሉ ድንበሮች ማፍለስን ዓላማ ያደረጉ፤ እንዲሁም መንፈሳዊ ባህል፣ ሰብአዊ ክብርና የእድሜ፣ የቅደም ተከተል ትስስርና ክብር እንዲጠፋ የሚሠሩ ሁሉ ከሐሳዊ መሲሕ መደብና ከዓለም ፍጻሜ ምልክትአንጻር የሚታዩ ናቸው፡፡ በዝርዝር ለማየት የሚከተሉትን ነጥቦች እንመልከት፣

 

1. የሃይማኖት ድንበርን ማፍለስ፡- ”አባቶችህ ያኖሩትን /የሠሩትን/ የቀድሞውን የድንበር ምልክት አታፍርስ” ምሳ.22፥28፣ 23፥10 አፈጻጸሙ ሰዎች የእግዚአብሔርን ማንነት እንዳያውቁ ከማድረግ ይጀምራል፡፡ከዚህም አንዱ ሐሳዊ መሲሕ በእግዚአብሔር ስም በተለያየ ሁኔታና መንገድ መገለጥ ነው፡፡ ”እስመ ብዙሃን ይመጽኡ በስምየ እንዘ ይብሉ አነ ውእቱ ክርስቶስ፤ እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ ብዙ ሰዎች በኔ ስም ይነሣሉና” /ማቴ. 24፣5/፡፡ ይህም እንደ መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርትና የቅዱሳን ሐዋርያት ስብከት መሠረት፣ ከክርስቶስ ወደ ሰማይ ማረግ በኋላ የሚመጣ፣ ክርስቶስን የእግዚአብሔር የባሕርይ ልጁ ነው ብሎ የማይሰብክ ሁሉ፤ ሌላ አምላክን የሚሰብክ ሁሉ መደቡ ከሐሳዊ መሲሕ ትምህርት ይመደባል፡፡ በመሆኑም ከዚህ በፊት ያለፉ፣ አምላክ ነን ብለው የተነሡ እንደ ቴዎዳስ ዘግብጽና ይሁዳ ዘገሊላ /ሐዋ. ሥራ. 5፣36-37/ የመሰሉ ሁሉ ከዚያም በኋላ በየጊዜው የተነሡና በዚህም ወቅት የዋሁን ሕዝብ ”ኢየሱስ ነኝ፣ ኢየሱስ በኛ ዘንድ አለ” እያሉ የሚያጭበረብሩ ሁሉ ሐሳውያነ መሲሖች ናቸው፡፡ ከዚህም ሌላ ክርስቶስን ከአብ የሚያሳንሱ፣ ”ሎቱ ስብሐት” ነቢይ ነው ብለው የሚያምኑ፣ በመናፍስት አሠራር የሚጠነቁሉ፣ በማቴሪያሊስት /ቁሳውያን/ ወይም በኢቮሉሽን /በዝግመተ ለውጥ/ ትምህርት አምነው አምላክ የለም የሚሉ ሁሉ፣ ወዘተ የሐሳዊው መሲሕ አካላት ናቸው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ በመልእክቱ ”ኢየሱስ ክርስቶስም በሥጋ እንደ መጣ የማይታመን መንፈስ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም፤ ይህም የክርስቶስ ተቃዋሚው መንፈስ ነው፤ ይህም እንደማመጣ ሰምታችኋል፥ አሁንም እንኳ በዓለም አለ።” /1ዮሐ. 4፣3/ በማለት ይመሰክርባቸዋል፡፡

 

ቅዱስ ዮሐንስ አሁንም በመልእክቱ ”ልጆች ሆይ፥ መጨረሻው ሰዓት ነው፥ የክርስቶስም ተቃዋሚ ይመጣ ዘንድ እንደ ሰማችሁ አሁን እንኳ ብዙዎች የክርስቶስ ተቃዋሚዎች ተነሥተዋል፤ ስለዚህም መጨረሻው ሰዓት እንደ ሆነ እናውቃለን።” /1ዮሐ. 2፥18/ ይለናል፡፡ ከዚህ የምንረዳው የክርስቶስ ተቃዋሚ መምጣት የምጽአት ጊዜው መቃረብ ምልክት መሆኑን የማያሻማ ሀሳብ ያደርገዋል፡፡ በተጨማሪም የምጽአትን መቅረብ የሚያመለክቱ፣ ስለ ሐሳዊው መሲሕ እና ከርሱ ጋር ተያያዥ ስለሆኑ ወቅታዊ ጉዳዮች ተዛማጅ የሆኑትን የሚከተሉትን ትንቢቶች እንመልከት፣

ሀ. ”የአውሬው ምስል ሊናገር እንኳ ለአውሬውም ምስል የማይሰግዱለትን ሁሉ ሊያስገድላቸው፥ ለአውሬው ምስል ትንፋሽ እንዲሰጠው ተሰጠው። ታናናሾችና ታላላቆችም ባለ ጠጋዎችና ድሆችም ጌታዎችና ባሪያዎችም ሁሉ በቀኝ እጃቸው ወይም በግምባራቸው ምልክትን እንዲቀበሉ፥ የአውሬውም ስም ወይም የስሙ ቍጥር ያለው ምልክት የሌለበት ማንም ሊገዛ ወይም ሊሸጥ እንዳይችል ያደርጋል። ጥበብ በዚህ አለ። አእምሮ ያለው የአውሬውን ቍጥር ይቍጠረው፤ ቍጥሩ የሰው ቍጥር ነውና፥ ቍጥሩም ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት ነው።” /ራእ. ዮሐ. 13፥16-18/ የሚለው የቅዱስ ዮሐንስ ራእይን ሊፈታ ከሚችልበት ትርጉም አንዲት ቅንጣት ብቻ ከዘመኑ አንጻር ብናይ ’የሚናገር የአውሬው ምስል’ ማለትም ለሱ ያልተገዙትን ወይም ቁጥሩን ያልያዙትን የሚናገርባቸው፤ ምልክቱን ያልተቀበሉትን ሊገዙና ሊሸጡ እንዳይችሉ ያደርግል ማለት መኖር፣ መሥራት፣ መሸጥ፣ መለወጥ ወዘተ የሚያግዳቸው ሲል አሁን ባለን ወቅታዊ የዚህ ዓለም አኗኗር አንጻር ሲታይ ተመሳሳይ ጉዳዮች አሉ፡፡ ለምሳሌ፣ መታወቂያ ወረቀት፣ ፓስፖርት፣ ቪዛ፣ የመኖሪያ ፈቃድ ወዘተ በዓለም አጠቃላይ አሠራር እና ባንድ ሰው የመኖር ማንነት ሚና ላይ ተጽእኖ የሚያደርጉ ነገሮች ናቸው፡፡ እነዚህ መታወቂያ ወረቀቶች የሌሉት ሰው ካለበት የትም መንቀሳቀስ አይችልም፡፡ ከዚህም በላይ ጉዳዩን ስናሰፋው በሰለጠኑት ዓለማት አሠራር የእያንዳንዱ ሰው የጣት አሻራ ኮምፒውተራይዝድ በሆነ መንገድ የተደራጀ በመሆኑ፣ እዚያ አደረጃጀት ውስጥ ካልተካተተ በቀር እዚያ ሀገር ሊኖር፣ ሊዘዋወር፣ ሊሠራ፣ ሊነግድ ወዘተ አይችልም፡፡ ለምሳሌ፣ አንድ እዚህ የኮምፒውተር ድር አደረጃጀት ውስጥ ያለ ሰው የትም ዓለም ቢሄድ በጣቱ አሻራ ይታውቃል፡፡ በትንቢቱ” አእምሮ ያለው የአውሬውን ቍጥር ይቍጠረው፤ ቍጥሩ የሰው ቍጥር ነውና፥ ቍጥሩም ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት ነው።”  የሚለው ይህን የሚያደራጀው ጉዳዩን የሚያስተሳስረው ሌላ አካል ሳይሆን ሰው መሆኑን የሚያመለክት ነው፡፡ ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት የሚለው ቁጥር የሰው ልጅ የጅማት ቁጥር ነውና፡፡

ለ. ሌላው የምጽአት መቃረብ ምልክት የሐሳዊው መሲሕ ዘመቻን አውቀው በድፍረት፣ ላላወቁት በረቀቀ መንገድ እግዚአብሔርን ያመለኩ አስመስሎ የእግዚአብሔርን ስም፣ እመቤታችንን ቅድስት ድንግል ማርያምን፣ ቅዱሳንን፣ ባጠቃላይ በሰማይ የሚያድሩትን መስደብ ነው፡፡ እነዚህም ተግባራት በተለያዩ ዘመናት ሲፈጸሙ የቆዩ ናቸው ዛሬም ተጠናክረው እየተፈጸሙ ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ፣ ሩቅ ሳንሔድ ዛሬ ቤተ ክርስቲያናችንን እየተፈታተነ ያለው የተሐድሶ ሤራ ዋናው ተቃውሞው የወልድን አምላክነት፣ የድንግል ማርያምን ክብርና አማላጅነት፣ የታቦትንና የመስቀልን ክብር፣ የቅዱሳንን ክብርና አማላጅነት ነው፡፡ በመሆኑም ተሐድሶ በሥራው የአውሬው መንፈስ አራማጅና መንገድ ጠራጊ መሆኑን ቅዱስ ዮሐንስ በራእዩ እንዲህ በማለት ያረጋግጥልናል፡፡ ”ለዘንዶውም ሰገዱለት፥ ለአውሬው ሥልጣንን ሰጥቶታልና፤ ለአውሬውም፡- አውሬውን ማን ይመስለዋል፥ እርሱንስ ሊዋጋ ማን ይችላል? እያሉ ሰገዱለት። ታላቅንም ነገርና ስድብን የሚናገርበት አፍ ተሰጠው፥ በአርባ ሁለት ወርም እንዲሠራ ሥልጣን ተሰጠው። እግዚአብሔርንም ለመሳደብ ስሙንና ማደሪያውንም በሰማይም የሚያድሩትን ሊሳደብ አፉን ከፈተ። ቅዱሳንንም ይዋጋ ዘንድ ድልም ያደርጋቸው ዘንድ ተሰጠው፥ በነገድና በወገንም በቋንቋም በሕዝብም ሁሉ ላይ ሥልጣን ተሰጠው። ከዓለምም ፍጥረት ጀምሮ በታረደው በግ ሕይወት መጽሐፍ ስሞቻቸው ያልተጻፉ በምድር የሚኖሩ ሁሉ ይሰግዱለታል።” /ራእ. ዮሐ. 13፣4.8/ እንዲል፡፡

ሐ. ሌላው በዓለም ላይ የሚታየው በሰዎች ዘንድ ክብር፣ ዝናና ታዋቂነትን ለማግኘት ሲባል ራስን ከፍ ማድረግና እንደ አማልክት መቁጠር ከሐሳዊው መሲሕ ያስመድባል፡፡ ከዚህ በተመሳሳይ ሊቀ ነቢያት ሙሴ እንደገለጸው የሰናዖር ሰዎችን ኀጢአት ስናሰተውል የተነሡበት ዋናው ነጥብ ’ስማችንን እናስጠራ’ የሚለው ነበር፡፡” ኑ ለእኛ ከተማና ራሱ ወደ ሰማይ የሚደርስ ግንብ እንሥራ፤ በምድር ላይ ሳንበተንም ስማችንን እናስጠራው አሉ።” /ዘፍ. 11፥4/ ነው የሚለን፣ በዚህ እኩይ አሳብ ምክንያት እግዚአብሔር ቋንቋቸውን ደባለቀባቸው፡፡ የሰናዖር ሰዎች ያሰቡትናየተመኙት ትውልዱ እግዚአብሔርን ማድነቅ ትቶ፣ ለዘለዓለም ስማቸውን ሲጠራቸው፣ ሲያደንቃቸው መኖርን ነበር፡፡ ዛሬም ብዙዎቹ ይህንን የሰናዖርን ኀጢአትና የጥፋት ጉዞ እንደ ዓላማ ይዘው በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ፡፡

2. የሥነ ተፈጥሮ ሕግ ድንበር መጣስ አንዱ የጊዜው መቃረብ ምልክት ነው፡፡ እግዚአብሔር የፈጠረው ፍጥረት ፍጹም በመሆኑ፣ ይህ ቀረህ፣ ይህ ይጨመርልህ የሚባል አይደለም፡፡ ነገር ግን በዚህ ወቅት፣ ሰው ለተለያየ ጥቅም በሚል ሰበብ ዝርያቸው የተለያዩ የሆኑትን ፍጥረታት ማዳቀልንና ማደበላለቅን ተያይዞታል፡፡እንስሳትና ተክሎችን ለማባዛት የማያደርገው ጥረትና  የማዳቀል ዘዴ የለም፡፡ በተቃራኒውም የሰውን ቁጥር ለመቀነስ የማያደርገው ሩጫ የለም፡፡ በመሆኑም ውጤቱ የሰውን ቁጥር ለመቀነስ ሲባል በሚደረጉ ሕክምናዎች ሰዎች ለተለያዩ በሽታዎች ተዳርገዋል፡፡ በሚደረገውም ማበረታታት በሠለጠኑት ዓለም ብዙዎቹ የግብረ ሰዶም ፈጻሚና አስፈጻሚ ሆነዋል፡፡ ይህ አሠራር አምላክ የሠራውን የፍጥረት ሕግ በማጣጣል ሰው ላሻሽል ወደሚል ያዘነበለ በመሆኑ የሰውን ልጅ ቅጥ ያጣ ድፍረት ያሳያል፡፡ እግዚአብሔር ግን ሥነ ፍጥረቱን እንዲያደባልቁበት አይፈልግም፡፡እግዚአብሔር ለሊቀ ነቢያት ሙሴ ”ሥርዓቴን ጠብቁ። እንስሳህ ከሌላ ዓይነት ጋር አይደባለቅ፤ በእርሻህም ሁለት ዓይነት ዘር አትዝራ” /ዘሌ. 19፣ 19፤/ ማናቸውም ሰው ከሴት ጋር እንደሚተኛ ከወንድ ጋር ቢተኛ ሁለቱ ጸያፍ ነገር አድርገዋል፤ ፈጽመው ይገደሉ፤ ደማቸው በላያቸው ነው።” /ዘሌ 20፣ 13/ በማለት ያሰተምረናል፡፡

3.    በጋብቻ ላይ የሚደረግ ርኩሰትን ስንመለከትም በየትኛውም ዓለም የፍርድ ቤቶች ትልቁ ሥራ ማፋታት ሆኗል፡፡ ምክንያቱም ተጋቢዎች ባንድ ላይ እንዳይኖሩ አውሬው /አስማንድዮስ/ የጋብቻ ጠላት በመሆን ስለነገሠ ፈተናውን መቋቋም አልቻሉምና ነው፡፡ ስለዚህ አስማንድዮስ ከዛ ይልቅ ግብረ ሰዶምን እያበረታታ በአንዳንድ ሀገሮች እንደሚታየው ወንድ ከወንድ፣ ሴት ከሴት ጋር እያቆራኘ በቤተ ክርስቲያኖቻቸው” ጋብቻ እስከ መፈጸም አድርሷቸዋል፡፡ ስለዚህም ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ይላል፣” ስለዚህ እርስ በርሳቸው ሥጋቸውን ሊያዋርዱ እግዚአብሔር በልባቸው ፍትወት ወደ ርኵሰት አሳልፎ ሰጣቸው፤ ይህም የእግዚአብሔርን እውነት በውሸት ስለ ለወጡ በፈጣሪም ፈንታ የተፈጠረውን ስላመለኩና ስላገለገሉ ነው፤ እርሱም ለዘላለም የተባረከ ነው፤ አሜን። ስለዚህ እግዚአብሔር ለሚያስነውር ምኞት አሳልፎ ሰጣቸው፤ ሴቶቻቸውም ለባሕርያቸው የሚገባውን ሥራ ለባሕርያቸው በማይገባው ለወጡ፤ እንዲሁም ወንዶች ደግሞ ለባሕርያቸው የሚገባውን ሴቶችን መገናኘት ትተው እርስ በርሳቸው በፍትወታቸው ተቃጠሉ፤ ወንዶችም በወንዶች ነውር አድርገው በስሕተታቸው የሚገባውን ብድራት በራሳቸው ተቀበሉ። እግዚአብሔርን ለማወቅ ባልወደዱት መጠን እግዚአብሔር የማይገባውን ያደርጉ ዘንድ ለማይረባ አእምሮ አሳልፎ ሰጣቸው፤ ዓመፃ ሁሉ፥ ግፍ፥ መመኘት፥ ክፋት ሞላባቸው፤ ቅናትን፥ ነፍስ መግደልን፥ ክርክርን፥ ተንኰልን፥ ክፉ ጠባይን ተሞሉ፤ የሚያሾከሹኩ፥ ሐሜተኞች፥ አምላክን የሚጠሉ፥ የሚያንገላቱ፥ ትዕቢተኞች፥ ትምክህተኞች፥ ክፋትን የሚፈላለጉ፥ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፥ የማያስተውሉ፥ ውል የሚያፈርሱ፥ ፍቅር የሌላቸው፥ ምሕረት ያጡ ናቸው፤ እንደነዚህ ለሚያደርጉት ሞት ይገባቸዋል የሚለውን የእግዚአብሔርን ሕግ እያወቁ እነዚህን ከሚያደርጉ ጋር ይስማማሉ እንጂ አድራጊዎች ብቻ አይደሉም።” /ሮሜ.1፥24-ፍጻሜ

4.    መንፈሳዊ ባህል፣  የክህነት ክብር፣ ሰብአዊ ክብርና የእድሜ፣ የቅደም ተከተል ትስስርና  ክብር እንዲጠፋ የሚሠሩ፣ በሚለው ዙሪያ ስንመለከት በቀላሉ ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ ያለውን ማየት እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡ነገር ግን በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን እንዲመጣ ይህን እወቅ። ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉና፥ ገንዘብን የሚወዱ፥ ትምክህተኞች፥ ትዕቢተኞች፥ ተሳዳቢዎች፥ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፥ የማያመሰግኑ፥ ቅድስና የሌላቸው፥ ፍቅር የሌላቸው፥ ዕርቅን የማይሰሙ፥ ሐሜተኞች፥ ራሳቸውን የማይገዙ፥ ጨካኞች፥ መልካም የሆነውን የማይወዱ፥ ከዳተኞች፥ ችኩሎች፥ በትዕቢት የተነፉ፥ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ፤ የአምልኮት መልክ አላቸው ኃይሉን ግን ክደዋል፤ እነዚህ ደግሞ ራቅ። ወደ ቤቶች ሾልከው እየገቡ፥ ኃጢአታቸው የተከመረባቸውን በልዩ ልዩ ምኞትንም የሚወሰዱትን ሁል ጊዜም እየተማሩ እውነትን ወደ ማወቅ ሊደርሱ ከቶ የማይችሉትን ሞኞችን ሴቶች የሚማርኩ፥ ከእነዚህ ዘንድ ናቸውና። ኢያኔስና ኢያንበሬስም ሙሴን እንደተቃወሙት፥ እንዲሁ እነዚህ ደግሞ አእምሮአቸው የጠፋባቸው ስለ እምነትም የተጣሉ ሰዎች ሆነው፥ እውነትን ይቃወማሉ። ዳሩ ግን የእነዚያ ሞኝነት ደግሞ ግልጥ እንደሆነ፥ ሞኝነታቸው ለሁሉ ይገለጣልና ከፊት ይልቅ አይቀናላቸውም።” / 2ጢሞ. 3፥1.7/ በማለት በመጨረሻው ዘመን የሚነሡ ሰዎችን ፀባይን ይነግረናል፡፡ ይህንን ትምህርተ ጥቅስ ለማገናዘብ  እግዚአብሔርን የማያምነውን ህዝብ ትተን፣ አሁን በዓለም ሁሉ ካለው የቤተ ክርስቲያንዋ አማኞች ብቻ አንጻር በመጠኑ እንይ ደግሞ፤

ሀ. መንፈሳዊ ባህል ማፍረስን ስንመለከት፣ የሁሉንም ባይሆን፣ የአንዳንዶቹ አማኞች ሰዎች ጸባይ ቅ. ጳውሎስ ”ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ፤ የአምልኮት መልክ አላቸው ኃይሉን ግን ክደዋል” የሚያሰኝ ሕይወት የያዙ እንደሆነ ያስረግጥልናል፡፡ እንደ አማኝ ቤተ ክርስቲያን የሚገኙ፣ ነገር ግን መንፈሳዊ አምልኮ የማይፈጽሙና የራሳቸውን አሳብ ቤተ ክርስቲያን ላይ ሊጭኑ የሚፈልጉትን ነው ’የአምልኮት መልክ አላቸው ኃይሉን ግን ክደዋል’ ያላቸው፡፡ የእግዚአብሔር ቤት መታዘዝ፣ መከባበርና ሰላም የነገሠበት መሆን ነው ያለበት፡፡ ነገር ግን በአንዳንድ ቦታ እንደሚስተዋለው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ብዙዎቹ በመንፈሳዊው ባህል የጠነከሩ እንዳሉ ሁሉ አንዳንዶቹ ሥራ ፈቶች ሆነው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ፖለቲካ፣ዘረኝነት፣አሉባልታ፣ ወዘተ በማምጣት ቤተ ክርስቲያንን ሲያውኩአት ይታያል፡፡ ቅ. ሉቃስ በተመሳሳይ አይሁድ ቀንተው በቤተ ክርስቲያን ላይ ያደረጉትን ”አንዳንዶቹ ተረድተው ከሚያመልኩም ከግሪክ ሰዎች ብዙ ከከበሩትም ሴቶች ጥቂቶች ያይደሉ፥ ከጳውሎስና ከሲላስ ጋር ተባበሩ።  አይሁድ ግን ቀንተው ከሥራ ፈቶች ክፉ ሰዎችን አመጡ ሕዝብንም ሰብስበው ከተማውን አወኩ፥” /የሐዋ. ሥራ 17፣ 5/ በማለት እንደገለጸው ያሉ ናቸው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም ”ወደ ቤቶች ሾልከው እየገቡ፥ ኃጢአታቸው የተከመረባቸውን በልዩ ልዩ ምኞትንም የሚወሰዱትን ሁልጊዜም እየተማሩ እውነትን ወደ ማወቅ ሊደርሱ ከቶ የማይችሉትን ሞኞችን ሴቶች የሚማርኩ፥ ከእነዚህ ዘንድ ናቸውና።” ይላቸዋል፡፡

ለ. የክህነት ክብርን ማፍረስ በተመለከተ፣ ቅ. ጳውሎስ ”ኢያኔስና ኢያንበሬስም ሙሴን እንደ ተቃወሙት፥ እንዲሁ እነዚህ ደግሞ አእምሮአቸው የጠፋባቸው ስለ እምነትም የተጣሉ ሰዎች ሆነው፥ እውነትን ይቃወማሉ። ዳሩ ግን የእነዚያ ሞኝነት ደግሞ ግልጥ እንደ ሆነ፥ ሞኝነታቸው ለሁሉ ይገለጣልና ከፊት ይልቅ አይቀናላቸውም።” እንዳለው ሁሉ ካህናት ነን ከሚሉት ጀምሮ እስከ ምእመናን ድረስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያት ሰጥቷቸው በአንብሮተ እድ እየተሾሙ ሲወርድ መጥቶ ለኛ የደረሰውን ታላቁን የድኅነት መፈጸሚያ ክህነት እንደ ኢያኔስና ኢያንበሬስ ዛሬ በብዙዎች ተንቆና ተዋርዶ ይገኛል፡፡ ለምሳሌ ከሚፈጸሙ ስህተቶች ጥቂቶቹን ቀጥለን እንመለከት፣

  • ቅዱስ ማቴዎስ ”በዚያን ዘመን ብዙዎች ይሰናከላሉ፣ እርስ በርሳቸውም አሳልፈው ይሰጣጣሉ፣ እርስ በርሳቸው ይጣላሉ” /ማቴ. 24፣10/ እንዳለው ሁሉ፤ለዘመናት በአንድነት የኖረችውን ቤተክርስቲያን ”ከዓመጻም ብዛት የተነሣ የብዙዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች” እንዲል፣ በዚህ ዘመን በድፍረት አስተዳደሩዋን በመከፋፈል ”ኢያኔስና ኢያንበሬስም ሙሴን እንደ ተቃወሙት” እንዲሁ አሳድጋ፣ አስተምራ፣ ክህነት የሰጠቻቸውን እናታቸውን ቤተ ክርስቲያን እስከ ማውገዝ የድፍረት ኀጢአት የተደረሰበት ዘመን ነው፡፡በመወጋገዙ ሂደት ያለው ጉዳትን ማን አስተዋለው? እግዚአብሔር ይማረን እንጂ እንደ ሰውኛው ከሆነ፣ በጭካኔ፣ ውስጥ ያለው ውጪውን፣ ውጭ ያለው ደጋግሞ ውስጥ ያለውን አውግዞትአንዲት ነፍስ ወደ እግዚአብሔር እንዳትደርስ ተቆላልፎ ቁጭ ብሏል፡፡ ነገር ግን ኢያኔስና ኢያንበሬስ ሙሴን ቢቃወሙትም ሙሴ ክህነቱ ከእግዚአብሔር በመሆኑ የእግዚአብሔር ክብር በርሱ ላይ ተገልጦ እግዚአብሔርን የተቃወሙት በደላቸው እንደ ተገለጠ ሁሉ፣ ዘለዓለማዊዋ ቤተ ክርስቲያን ክህነታዊ ክብርዋ በእግዚአብሔር ዘንድ ክቡር ነው፡፡  ”ሁሉ ለንጹሖች ንጹሕ ነው፤ ለርኵሳንና ለማያምኑ ግን ንጹሕ የሆነ ምንም የለም፥ ነገር ግን አእምሮአቸውም ሕሊናቸውም ረክሶአል።  እግዚአብሔርን እንዲያውቁ በግልጥ ይናገራሉ፥ ዳሩ ግን የሚያስጸይፉና የማይታዘዙ ለበጎ ሥራም ሁሉ የማይበቁ ስለ ሆኑ፥ በሥራቸው ይክዱታል።” / ቲቶ. 1፥15/ እንዳለ፡፡
  • ” ሰለስቱ ምእት በኒቂያ ጉባኤ ’ያለ ኢጲስ ቆጶስ ፈቃድ ቤተ ክርስቲያንን የመሠረተ ከክህነቱ ይሻር’ብለው ደንግገዋል፡፡ ነገር ግን በተለይ በውጭ አገር እየተለመደ የመጣው ጉዳይ የትኛውንም ኤጲስቆጶስ ሳያስፈቅድ አንድ ካህን፣ ከዚያም አልፎ በሚገርም ሁኔታ ዲያቆን ወይም ምእመን ከፈለገ ቦርድ አቋቋምኩ እያለ ቤተ ክርስቲያን አስተምራ አጥምቃ ያሳደገችውን ምእመን ከሥርዓተ ቤተክርስቲያን በማውጣት እንደ ማንኛውም ድርጅት ቤተ ክርስቲያን ከፈትኩ የሚባልበት የድፍረት ኀጢአት በጠራራ ፀሐይ ከሚፈጸምበት ዘመን ደርሰናል፡፡ በተጨማሪም በዚህ ዓይነት ለተቋቋሙ ሁሉ የሚገለገሉበት ታቦት ከየት መጣ? ሜሮን ከየት ተገኘ? የሚሉ ጥያቄዎች ምላሽ የላቸውም፡፡ ”ብዙዎች ይስታሉ” እንደተባለ በድፈረትና በስሕተት መሠረት ላይ የስሕተትና የድፍረትን ግድግዳ ማቆም፣ የስሕተትና የድፍረት ጣሪያንም ማዋቀር እንደ ሕጋዊ ሥራ ከተቆጠረ ሰነባበተ፡፡
  • የጥፋት ርኩሰት በተቀደሰው ስፍራ ቆሞ ስታዩ አንባቢው ያስተውል” /ማቴ 24፣15/ በየአጥቢያው የሚሰማውን ክፉ ወሬ ስናስተውል የዚህ ትንቢት ተፈጻሚነት እንዳገኘ ያረጋግጥልናል፡፡ የተሐድሶ ሴራ፣ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚፈጠሩት ጭቅጭቆች፣ በመነኮሳትና በካህናት የሚነሱ ሐሜቶች፣ ሙሰኝነት፣ዘረኝነት ምን ይነግሩናል?በውጭ አገር በየቦታው አቋቋምን የሚሉት ሰበካ ጉባኤ ሳይሆን ራስ ገዝ የቦርዶቹ አስተዳደር ግፍ ደግሞ በሚገርም ሁኔታ የሚያገለግለው ካህንን የሚያዩት እንደ እግዚአብሔር ካህን ሳይሆን ከአንድ ቅጥር ሠራተኛቸው በታች ነው፡፡ ስለ አስተዳደሩ እንዲያውቅ አይፈልጉም፣ እነሱ ያዘዙትን ብቻ ይሰብካል/ ይናገራል፣ ካህኑም ሲፈልጉ የሚያኖሩት ሲፈልጉ የሚያባርሩት ሆኗል፡፡ ይህን አሠራር ለዘመናት ቤተ ክርስቲያን ከኖረችበት አንጻር ስናየው እጅግ የራቀና አስጸያፊ የሚባል ነው፡፡ ጌታችን ቤተ ክርስቲያንን የመሠረተው በሥልጣነ ክህነት እንድትተዳደር ሲሆን ይህኛው በተቃራኒ የቆመ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ምእመኑን አስተምራ አጥምቃ አሳድጋ እንደገና በተንኮለኞች ሤራ ልጆቹዋን ቀስጠው በስዋ ላይ እንዲያምጹ ማድረግ የጥፋት ርኩሰት መሆኑን ስንቱ ተረድቶት ይሆን?፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ”ማንም ልዩ ትምህርት የሚያስተምር ከጌታችንም ከኢየሱስ ክርስቶስ በሆነው ጤናማ ቃልና እግዚአብሔርን ለመምሰል በሚስማማ ትምህርት የማይጠጋ ቢሆን፥ በትዕቢት ተነፍቶአል አንዳችም አያውቅም፥ ነገር ግን ምርመራን በቃልም መዋጋትን እንደ በሽተኛ ይናፍቃል፤ ከእነዚህም ቅንዓትና ክርክር ስድብም ክፉ አሳብም እርስ በርስ መናደድም ይወጣሉ፥ አእምሮአቸውም በጠፋባቸው እውነትንም በተቀሙ፥ እግዚአብሔርን መምሰል ማትረፊያ የሚሆን በመሰላቸው ሰዎች ይገኛሉ። እንደነዚህ ካሉት ራቅ።” /1 ጢሞ.6፥3-5/ እንዳለ፡፡

ሐ. ሰብአዊ ክብርና የዕድሜ፣ የቅደም ተከተል ትስስርና  ክብር እንዲጠፋ የሚሠሩ ለሚለው ሌላ ብዙ ከማለት ይልቅ ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ ”ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉና፥ ገንዘብን የሚወዱ፥ ትምክህተኞች፥ ትዕቢተኞች፥ ተሳዳቢዎች፥ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፥ የማያመሰግኑ፥ ቅድስና የሌላቸው፥ ፍቅር የሌላቸው፥ ዕርቅን የማይሰሙ፥ ሐሜተኞች፥ ራሳቸውን የማይገዙ፥ ጨካኞች፥ መልካም የሆነውን የማይወዱ፥  ከዳተኞች፥ ችኩሎች፥ በትዕቢት የተነፉ” በማለት የዘረዘረው ለርእሰ ጉዳዩ ተስማሚና በቂ ነው፡፡/1ጢሞ.3፥1-3/

ባጠቃላይም የምጽአት ምልክቶች የሚያሳዩት ሁኔታዎች ከመንፈሳዊው እስከ ዓለማዊው፣ ከተማረው እስከ መሀይሙ፣ ከትልቅ እስከ ትንሽ፣ ያላገባው፣ ያገባው፣ መነኩሴው ሳይቀር ሁሉም ሁሉም ባንድ ላይ ከቅድስና ርቀት፣ ከጥፋት ርኩሰት፣ ከመከራ ሕይወት፣ ተቋደሽ መሆናቸውን ነው የሚያሳየው፡፡ ነገር ግን ቅዱሳት መጻሕፍት ተባብረው እንደመሰከሩልን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ድንገት ይመጣል አይዘገይም፡፡ ቅዱስ ዳዊት ”ከክብሩ ውበት ከጽዮን እግዚአብሔር ግልጥ ሆኖ ይመጣል።  አምላካችን ይመጣል ዝምም አይልም፤ እሳት በፊቱ ይቃጠላል፥ በዙሪያውም ብዙ ዐውሎ አለ።” /መዝ.49፥2-3/ ብሎ እንደተናገረው፡፡ ከላይ እንደተዘረዘረው የሰው ልጆች ሁለ ጊዜ ከመንፈሳውያን እስከ ዓለማውያን ድረስ በተጠመዱበት የዓለማዊ ሥራ እንደ ተወጠሩ ነው ያሉት፡፡ ከዚህም በኋላ የበለጠ በሥጋ ሥራ እየተወጠሩ ይሄዳሉ እንጂ መንፈሳዊ ወደ ሆነው የተጋድሎ ሕይወት የሚያዘነብል ይኖራል ለማለት ያስቸግራል፡፡ እንዲያውም በዐመጽ እየበረታ እስከ መቅደስ ድፍረቱን ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ይገልጸዋል፤”ማንም በማናቸውም መንገድ አያስታችሁ፤ ክህደቱ አስቀድሞ ሳይመጣና የዓመፅ ሰው እርሱም የጥፋት ልጅ ሳይገለጥ፥ አይደርስምና። እኔ እግዚአብሔር ነኝ ብሎ አዋጅ እየነገረ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እስኪቀመጥ ድረስ፥ አምላክ ከተባለው ሁሉ፥ ሰዎችም ከሚያመልኩት ሁሉ በላይ ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርገው ተቃዋሚ እርሱ ነው።” /2ተሰ.2፥3-4/ ይለናል፡፡ ነገር ግን ክርስቲያኖች ነን የምንል ሁሉ የጥፋት ትንቢቱ እኛ ላይ እንዳይፈጸም አሁኑኑ ሳናመነታ ንስሐ መግባትና በትንቢት ከተገለጡት ርኩሰቶች ጨክነን መራቅ ይገባናል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር አሜን፡፡

ኪዳነ ምሕረት

%e1%8a%aa%e1%8b%b3%e1%8a%95

በዲያቆን ኃይለ ኢየሱስ ቢያ

የካቲት ፲፭ ቀን ፳፻፲፬ .

‹‹ኪዳን›› የሚለው ቃል ‹‹ተካየደ – ተዋዋለ፤ ቃል ኪዳን ተጋባ፤ ተማማለ›› ከሚለው የግእዝ ግስ የተገኘ ሲኾን፣ ትርጕሙም ኪዳን፣ ውል፣ መሐላ፣ ቃል ኪዳን፣ የውል ቃል ማለት ነው /ዘዳ.፳፱፥፩፤ ኤር.፴፩፥፴፩-፴፫፤ መዝ.፹፰፥፫/፡፡ በሌላ በኩል ኪዳን የጸሎት ስም ሲኾን፣ ጌታችን ሞትን ድል አድርጎ ከተነሣ በኋላ፣ ከማረጉ በፊት ለሐዋርያት ያስተማራቸው ጸሎት ኪዳን ይባላል፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከልጇ ከወዳጇ ከጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የምሕረት ቃል ኪዳን (ውል፣ ስምምነት) የተቀበለችበት ዕለት (የክብረ በዓል ስም) ደግሞ ኪዳነ ምሕረት ይባላል፡፡

በየዓመቱ የካቲት ፲፮ ቀን የምናከብረው ይህ በዓል እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በጎልጎታ በልጇ በመቃብር ላይ ኾና ‹‹ኦ ወልድየ ወፍቁርየ እስእለከ በእንተ ዘተሰባእከ እምኔየ ወበማኅፀንየ ዘጾረተከ፤ ልጄ ወዳጃ ሆይ ከሥጋዬ ሥጋ፣ ከነፍሴ ነፍስ ነሥተህ ሰው ስለመኾንህ፤ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን ስለቻለችህ ማኅፀኔ፤ ከአንተ ጋር ከአገር ወደ አገር ስለመሰደዴ መጥተህ ልመናዬን ትሰማኝ ዘንድ እለምንሃለሁ››እያለች ስትጸልይ ጌታ እልፍ አእላፍ መላእክቱን አስከትሎ ወደእርሷ መጥቶ ‹‹ሰላም ለኪ ማርያም እምየ፤ እናቴ ማርያም ሰላም ላንቺ ይኹን! እንዳደርግልሽ የምትለምኚኝ ምንድን ነው?›› አላት፡፡ እመቤታችንም በስሟ የሚማጸኑትንና መታሰቢያዋን የሚያደርጉትን፣ ለችግረኛ የሚራሩትን፣ ቤተ ክርስቲያን የሚያንጹትን፤ ዕጣን ዘይትና መብአ ለቤተ ክርስቲያን የሚሰጡትን፤ ለእመቤታችንና ለሃይማኖታቸው ካላቸው ፍቅር የተነሣ ልጆቻቸውን በስሟ የሰየሙትን ዅሉ እንዲምርላትና ከሞተ ነፍስ እንዲያድንላት ጠየቀችው፡፡

ጌታችንም ‹‹ይህን ዅሉ እንዳደርግልሽ መሐልኩ ለኪ በርእስየ ወበአቡየ ወበመንፈስ ቅዱስ ሕያው፤ በራሴ፣ በአባቴ እና በመንፈስ ቅዱስ ማልኩልሽ›› ብሎ ቃል ኪዳን ገብቶላት ወደ ሰማይ ዐርጓል፡፡ ለዚህም ነው ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ በቅዳሴው ‹‹… ዳግመኛም በእናትህ በማርያም ተማፅነናል፤ ይህችውም አንተን በመውለድ እመቤታችንና የባሕርያችን መመኪያ ናት፡፡ አንተ ‹መታሰቢያሽን ያደረገ፣ ስምሽንም የጠራ፣ የዘለዓለም ድኅነትን ይድናል› ብለሃታልና …፤›› በማለት የሚማጸነው፡፡

በተአምረ ማርያም መጽሐፍ እንደተመዘገበው በዚህ ዕለት የሚታሰቡ ሁለት ተአምራት አሉ፤ ከእነዚህም አንደኛው የስምዖን ታሪክ ነው፡፡ ስምዖን የሚባል እንግዳ ተቀባይ ደግ ሰው ነበር፡፡ ሰይጣን ለምቀኝነት አያፍርምና ከዕለታት አንድ ቀን በእንግድነት ከቤቱ ገብቶ ‹‹ልጅህን አርደህ ካላበላኸኝ ሌላ ምግብአልበላም›› አለው፡፡ በዚህ ጊዜ ስምዖን ሲያወጣና ሲያወርድ ቆየና ‹‹አብርሃም ልጁን ሰውቶ ነው የእግዚአብሔር ሰው የተባለው›› በማለት፣ ‹‹የእግዚአብሔርን እንግዳ›› ላለማሳዘን ሲል ልጁን አርዶ አቀረበለት፡፡ እንግዳ መሰሉ ሰይጣንም ሥጋውን ቅመስልኝ ብሎ ግድ አለው፡፡ ስምዖንም (በላዔ ሰብእ) አርዶ ያዘጋጀውን የልጁን ሥጋ በቀምሰ ጊዜ ሰይጣን ስላደረበት (ስለተዋሐደው) ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ቤተሰቦቹን፣ ጎረቤቶቹንና መንገደኛውን ዅሉ ይበላ ጀመር፡፡ በአጠቃላይ ፸፰ ሰዎችን ከበላ በኋላ አንድ በቍስል የተመታ ሰው አገኘና ሊበላው ሲል ‹‹ውኃአጠጣኝ›› ብሎ በሥላሴ፣ በቅዱስ ሚካኤል፣ በቅዱስ ገብርኤል ስም ለመነው፤ እርሱም ዝም አለው፡፡

በመጨረሻም ‹‹በድንግል ማርያም ስም›› አለው፡፡ ስምዖን የእመቤታችንን ስም በሰማ ጊዜም ወደ ልቡናው ተመልሶ ‹‹እስኪ ቃሉን ድገመው›› አለው፤ በሽተኛውም መልሶ ‹‹ስለ ድንግል ማርያም ውኃአጠጣኝ›› ብሎ ለመነው፡፡ ያን ጊዜ ‹‹ይህችስእንደምታስምር በልጅነቴ ሰምቻለሁ›› ብሎ ጥቂት ውኃ ሰጠው፤ ውኃው ጕሮሮውን እንኳን ሳያርስለት ‹‹ጨረስህብኝ›› ብሎ ነጥቆት ሔደ፡፡ በሌላ ቦታም አንድ ገበሬ አግኝቶ ሊበላ ሲል ገበሬው ‹‹በላዔ ሰብየምትባል አንተ ነህ?›› ባለው ጊዜ ‹‹ለካስ አመሌን ሰውዅሉ አውቆብኛል›› ብሎ ዋሻ ገብቶ በመጸጸት በዚያው ሞተ፡፡ ነፍሱንም መላእክተ ጽልመት መጥተው ሲወስዷት እመቤታችን ‹‹ልጄ በማይታበል ቃልህ ይህችን ነፍስ ማርልኝ?›› አለችው፡፡ ጌታችንም ‹‹ሰባስምንት ነፍስ ያጠፋ፣ ፈጣሪውን የካደ ሰው ይማራልን?›› አላት፡፡ እመቤታችንም ‹‹በስሜየተጠማውን ውኃ አጥጥቶ የለምን?›› ብላ ስምዖንን (በላዔ ሰብእን) አስምራዋለች፡፡ ነፍሱንም መላእክተ ብርሃን መጥተው ወደ ገነት አስገብተዋታል፡፡

ሁለተኛው ተአምር ደግሞ ከብሮ ከኖረ በኋላ ለድህነት በተጋለጠ አንድ ምእመን ላይ የተደረገ ነው፤ ከክርስቲያን ወገን የኾነ ሀብት አግኝቶ ያጣ አንድ ሰው ነበር፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን ‹‹ከብሬ በኖርኹበት አገር ተዋርጄአልኖርም›› ብሎ ጓዙን ጠቅልሎ ከአገሩ ወጥቶ ሲሔድ ሰይጣን ያዘነ ሰው መስሎ ደንጊያውን በምትሐት ወርቅ አስመስሎ ‹‹ሥላሴን፣ ጻድቃንን፣ ሰማዕታትንን፣መላእክትን ካድልኝና ይህን ወርቅ እሰጥሃለሁ›› አለው፡፡ ዅሉንም ካደለትና ወርቁን ተቀብሎ ዞር ሲል ‹‹ምእመናን የሚመኩባት ድንግል ማርያምየአምላክእናት አይደለችም› ብለህ ካድልኝ›› አለው፡፡ ሰወየውም ‹‹እርሷንስ አልክድም›› ስላው በደንጊያ ቀጥቅጦ ገደለው፡፡ መላእክተ ጽልመት የሟቹን ነፍስ ሊወስዱ ሲሉ መላእክተ ብርሃንም አብረው ቀረቡ፡፡ እመቤታችንም ጌታችንን ‹‹ልጄ ይህችን ነፍስማርልኝ?›› አለችው፡፡ እርሱም ‹‹ከልብኑ ይትመሐርእምየ፤ እናቴ፣ ውሻ ይማራልን?›› አላት፡፡ እመቤታችንም፡- ‹‹‹ስምሽን የጠራውን፣ መታሰቢያሽንያደረገውን እምርልሻለሁ› ያልኸው ቃል ይታበላልን?››አለችው፡፡ በዚህ ጊዜ ‹‹ምሬልሻለሁ›› አላት፡፡

እግዚአብሔር አምላካችን ‹‹ከመረጥኳቸው ጋር ቃል ኪዳን አደረግሁ›› ባለው መሠረት ከቅዱሳን ጋር ያደረጋቸው ቃል ኪዳኖች ብዙዎች ናቸው፡፡ ከእነዚህም መካከል ከላይ በተአምራቱ እንደተመለከትነው አንዱ ለእመቤታችን የሰጠው የአማላጅነት ኪዳን ነው፡፡ ማማለድ ማለት ስለሌላው መጸለይ፣ መለመን፣ የደረሰውን ችግር እንዲወገድ ማድረግ፣ ማስማር (ይቅርታ ማሰጠት) ማለት ነው፡፡ በዚሁ መሠረት ከእግዚአብሔር በታች ከቅዱሳን ዅሉ በላይ ከፍ ከፍ ያለችና የከበረች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከእግዚአብሔር በተሰጣት የማማለድ ሥልጣን ‹‹ሰአሊ ለነ ቅድስት፤ ቅድስት ሆይ ለምኚልን›› እያሉ ለሚለምኗት ዅሉ ከእግዚአብሔር እያማለደችና እየለመነች ምሕረትን እንደምታሰጥ ቀናውንና የተመሰገነውን ሃይማኖት የምንከተል ምእመናን ዅሉ እናምናለን፡፡ ምክንያቱም ቅድስት ድንግል ማርያም የእግዚአብሔር እናትና አገልጋይ እንደመኾኗ ከዅሉም ቅዱሳን በበለጠ ለእግዚአብሔር ቅርብ ናትና፡፡ በእግዚአብሔር ዘንድም ኾነ በሰው ዘንድ ባለሟልነትን ማግኘት ወይም ቅርብ መኾን ደግሞ አንድን ጉዳይ በቀላሉ ለማስፈጸም ይጠቅማል፡፡ ለምሳሌ፡-

  • መልአኩ ቅዱስ ገብርአል በእግዚአብሔር ፊት የሚቆም ባለሟል በመኾኑ የድኅነትን ምሥጢር አብሣሪ ኾኗል /ሉቃ. ፩፥፲፱-፳፮/፡፡
  • አስቴር የንጉሡ አርጤክስስ ሚስት በመኾኗ በወገኖቿ አይሁድ የታወጀውን የሞት አዋጅ አስለውጣለች /መጽሐፈ አስቴር ፫፥፲/፡፡
  • ነቢዩ ሙሴ በእግዚአብሔር ፊት ባለሟል በመኾኑ ‹‹ይህንን ኀጢአታቸውን ይቅር በላቸው፤ ያለዚያ ግንእኔን ከጻፍከው መጽሐፍህ እባክህ ደምስሰኝ?›› በማለት ለእስራኤላውያን ምሕረትን አሰጥቷል /ዘፀ.፴፪፥፲፬/፡፡

ስለዚህ የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነትም እንደ ፀሐይ የበራ ሐቅ ነው፡፡ ይህንን እውነት ቅዱስ ያሬድ ሲመሰክር፡- ‹‹ወታስተሠርዪ ኀጢአተ ሕዝብኪ ተበውሀለኪ እምአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ወከመ ትኩኒተንከተመ ለውሉደ ሰብእ ለሕይወት ዘለዓለም፤ ለሕዝብሽ፣ ለወገኖችሽ የኃጢአት ይቅርታን ታሰጪዘንድ፤ ዘለዓለማዊ ሕይወትንም ለሚወርሱ ዅሉመሸጋገሪያ ድልድይ ትኾኚ ዘንድ ከአብ ከወልድከመንፈስ ቅዱስ ዘንድ ሥልጣን አግኝተሻል›› በማለት አመስግኗታል /አንቀጸ ብርሃን/፡፡ አባ ጽጌ ድንግልም በማኅሌተ ጽጌ ድርሰታቸው፡- ‹‹ሶበሰ ኪዳንኪ ምክንያተ ድኂን ኢሀሎ ፈለገ እሳት ወደይን እም አሰጠመ ኩሎ፤ የድኅነት ምክንያት ቃል ኪዳንሽ ባይኖር ኖሮ የጥፋት እሳት፣ መርገም (ኀጢአት) ባጠፋን ነበር›› ብለዋል፡፡ አባ ሕርያቆስም በቅዳሴው፡‹‹ጥፋትን ያይደለ ይቅርታን አሳስቢ፡፡ መዓትን ያይደለ ምሕረትን አሳስቢ፡፡ ለጻድቃን ያይደለ ለኀጥአን አሳስቢ፡፡ ለንጹሐን ያይደለ ለተዳደፉት አሶስቢ፤›› ሲሉ ይማጸኗታል /ቅዳሴ ማርያም ቍ.፻፷፭-፻፸፩/፡፡

ስለዚህም ዘወትር በሥርዓተ ቅደሴአችን፡- ‹‹ድኅነትንየምንለምንሽ ክብርን የተመላሽ ቅድስት ሆይ ደስይበልሽ፡፡ ዅል ጊዜ ድንግል የምትኾኚ አምላክንየወለድነሽ የክርስቶስ እናት ሆይ ኀጢአታችንንያስተሠርይልን ዘንድ ወደ ልጅሽ ወደ ወዳጅሽ ወደ ላይጸሎታችንን አሰርጊልን፡፡ በእውነት የጽድቅ ብርሃንየሚሆን አምላካችንን ክርስቶስን የወለድሽልን ንጽሕትሆይ ደስ ይበልሽ፡፡ ንጽሕት ድንግል ሆይ ለነፍሳችንይቅርታን ያደርግ ዘንድ፤ ኀጢአታችንንም ያስተሠርይልንዘንድ ወደ ጌታችን ለምኚልን፡፡ በእውነት ለሰው ወገንአማላጅ የምትሆኝ አምላክን የወለድሽ ንጽሕትቅድስት ድንግል ማርያም ሆይ ደስ ይበልሽ፡፡ የኀጢአታችንን ሥርየት ይሰጠን ዘንድ በልጅሽበክርስቶስ ፊት ለምኝልን፡፡ በእውነት ንግሥትየምትኾኚ ንጽሕት ድንግል ሆይ ደስ ይበልሽ፡፡ የባሕርያችን መመኪያ ሆይ ደስ ይበልሽ፡፡ አምላካችንአማኑኤልን የወለድሽልን ሆይ ደስ ይበልሽ፡፡ በጌታችንበኢየሱስ ክርስቶስ ፊት እውነተኛ አስታራቂ ሆነሽታስቢን ዘንድ እንለምንሻለን፡፡ ለነፍሳችን ይቅርታንያደርግልን ዘንድ ኀጢአታችንንም ያስተሰርይልንዘንድ፤›› በማለት እመቤታችንን እንማጸናታለን፡፡

በአጠቃላይ ‹‹ኪዳነ ተካየድኩ ምስለ ኅሩያንየ፤ ከመረጥኋቸው ጋር ቃል ኪዳን አደረግሁ፤›› በማለት በነቢዩ ቅዱስ ዳዊት አድሮ ራሱ እግዚአብሔር ከመረጣቸው አበው ነቢያት፣ ጻድቃን፣ ቅዱሳንና ሰማዕታት ጋር ቃል ኪዳን እንደ ገባ፣ እንደሚገባ ተናግሯል /መዝ.፹፰፥፫/፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ‹‹እንግዲህ እርሱ ራሱ ካጸደቀ እግዚአብሔር የመረጣቸውን ሰዎች የሚቃወማቸው ማን ነው?›› በማለት እግዚአብሔር ሰዎችን እንደሚጠራ፣ እንደሚያከብር፣ እንደሚቀድስና ቃል ኪዳን እንደሚሰጥ ነግሮናል /ሮሜ.፰፥፴፫/፡፡ ቅዱስ ዳዊት ‹‹ነኪር ነገሩ በእንቲአኪ ሀገረ እግዚአብሔር፤ የእግዚአብሔር ከተማ ሆይ ስለ አንቺ የተነገረው ነገር ድንቅ ነው፤›› /መዝ.፹፮፥፫/ በማለት እንደተናገረው እግዚአብሔር አምላካችን ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም የገባው ቃል ኪዳን ከቅዱሳን ቃል ኪዳን ዅሉ ልዩ ነው፡፡ ይህም እንደምን ነው ቢሉ፡-

  • ለአምላክ እናትነት የተመረጠች ልዩ እናት በመኾኗ፤
  • አምላክ ከሥጋዋ ሥጋ፣ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ ከእርሷ በመወለዱ፤
  • ከመለለዷ በፊት፣ በወለደች ጊዜ፣ ከወለደች በኋላ ምን ጊዜም ድንግል በመኾኗ፤
  • በሁለቱም ወገን (በአሳብም በገቢርም) ድንግል በመኾኗ፤
  • አማላጅነቷ የወዳጅነት ሳይኾን የእናትነት በመኾኑ፤
  • ዓለም ይድን ዘንድ የድኅነት ምክንያት አድርጎ አምላክ ስለመረጣት ነው፡፡

ስለዚህ ብዙ ከንቱ አሳቦችን ትተን፣ እንደበላዔ ሰብእ በቃል ኪዳኗ ተጠቅመን፣ ንስሐ ገብተን፣ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ተቀብለን፣ የስሙ ቀዳሽ፣ የመንግሥቱ ወራሽ ለመኾን ያብቃን፡፡ የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የእመቤታችን አማላጅነት፣ የቅዱሳን ተራዳዒነት አይለየን፡፡

ዋቢ መጻሕፍት፡-

  • መጽሐፈ ስንክሳር
  • መዝገበ ታሪክ
  • ተአምረ ማርያም
  • አማርኛ መዝገበ ቃላት
  • ክብረ ቅዱሳን

ብሥራታዊዉ መልአክ

ክፍል ሦስት

ከማርታ ታከለ

የካቲት ፲፫ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

 

እንደምን ሰነበታችሁ ልጆች? ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችሁም ጋር ይሁን!

 

ባለፉት ክፍላት ስለ ቅዱሳን መላእክት አፈጣጠር፥ ቅዱስ ገብርኤል እውነተኛ አጽናኝ እና አረጋጊ መልአክ እንደሆነ፥ ስለ አዳምና ሔዋን አፈጣጠር፥ አዳምና ሔዋን የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ ስለማፍረሳቸውና ይኖሩባት ከነበረችው ከመልካሟ ስፍራ ከገነት እንደተባረሩ ተነጋግረናል። በመጨረሻም አዳምና ሔዋን በሱባኤና በጸሎት እግዚአብሔርን ይቅርታ ሲለምኑ ከአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን በኋላ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ የሚል ቃል ኪዳን እንዳገኙ አይተናል።

በዛሬው ክፍልም በርእሳችን ያነሳነው ብስራታዊው መልአክ ቅዱስ ገብርኤል  አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ሲፈጸም እግዚአብሔር ለአዳም የገባውን ቃል አስቦ የምስራች ቃሉን አስይዞ ወደምድር እንደላከው እንነጋገራለን። ልጆች! ለመሆኑ እግዚአብሔር የላከው ይህ የደስታ ቃል ምን ነበር? ቅዱስ ገብርኤልንስ ወደማን ላከው?

የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ አምላክ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ሊወለድ ፈቃዱ ሆነ፡፡ይህንንም የየምስራች ቃል ለቅዱስ ገብርኤል አስይዞ ወደ እርሷ ላከው። በዘመኑ ብዙ ደናግል መሲሑን/ አዳናችንን/ እንወልደዋለን ብለው ድንግልናቸውን ጠብቀው ይኖሩ ነበር።፡፡ የቅዱስ ገብርኤል ብሥራት ከእነዚህ ደናግላን ለአንዲቱ የተነገረ ቢሆን ኖሮ ምኞታቸው እንደተፈጸመላቸው ይቆጥሩት ነበር፡፡ እመቤታችን ግን በንጽሕና እና በቅድስና ከቤተመቅደስ ስትኖር ለዚህ ክብር ራስዋን አስባ አታውቅም፡፡ በአምላክ ዘንድ ግን በንጽህናዋ፥ በቅድስናዋ እና በትህትናዋ ተመርጣ ነበር። ነገር ግን እግዚአብሔር የሰውን ነጻ ፈቃድ የሚያከብር ነውና ሊወለድ እንደወደደ በራሱ ፈቃድ ብቻ ልወለድ ሳይል ወደ ድንግል ማርያም  መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልን ላከ፡፡

ቅዱስ ገብርኤልም በፍጹም ትህትና ከፍጥረት ሁሉ የከበረች ድንግልን አደግድጎ አመስግኖ እና አክብሮ ‘ደስ ይበልሽ ጸጋን የሞላብሽ ሆይ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው ፣ አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ’ አላት፡፡

የእመቤታችን አስተዳደጓ በቤተ መቅደስ በመላእክቱ እቅፍ ነው፡፡ሦስት ዓመት ሲሆናት እናትና አባቷ ለቤተመቅደስ ከሰጧት በኋላ የእግዚአብሔር መልአክ በአንድ ክንፉ አቅፎ በአንድ ክንፉ ደግፎ ሰማያዊ ምግብ እየመገበ አሳድጓታል።ስለዚህ ከእርሷ በፊትም ሆነ ከእርሷ በኋላ ያሉ ሰዎች የእግዚአብሔርን መልአክ ማየት አላስደነገጣትም። ነገር ግን የሰላምታው ቃል አስደነገጣት።እመቤታችን ሔዋንን ያሳተው የዲያቢሎስ ሽንገላ ወደ እርስዋ የመጣ ስለመሰላት ከመልአኩ የቀረበላት ሰላምታ አስደነገጣት፡፡ ‘ከሴቶች ሁሉ የተባረክሽ’ ያላትን ምስጋናም በደስታ አልተቀበለችውም፡፡ ‘እንዲህ ያለውን ሰላምታ እንደምን ይቀበሉታል’ ብላ አሰበች፡፡ ቅዱስ ገብርኤልም ‘ማርያም ሆይ! በእግዚአብሔር ፊት ጸጋ አግኝተሻልና አትፍሪ’ በማለት አረጋጋት። ከዚያም ‘እነሆም ትፀንሻለሽ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፥ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ እርሱ ታላቅ ይሆናል የልዑል ልጅም ይባላል፥ ጌታ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤ በያዕቆብ ቤትም ላይ ለዘለላም ይነግሣል፥ ለመንግሥቱም መጨረሻ የለውም’ በማለት አዳምና ልጆቹ ለአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ሲጠብቁት የነበረውን ምስራች አበሰራት።

እመቤታችን ግን አሁንም ጥያቄ ነበራት። ‘ወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ይሆናል?’ ብላ ጠየቀች።

ቅዱስ ገብርኤል ወደእመቤታችን ከመላኩ ከስድስት ወር በፊት ወደ ካህኑ ወደዘካርያስ ልጅ እንደሚወልድ እንዲነግረው ተልኮ መጥቶ ሲነግረው ዘካርያስ አላመነውም ነበር። ይህ ነገር እንዴት ይሆናል ብሎ ነበር። ቅዱስ ገብርኤልም ‘ቃሌን ስላላመንህ ይህ ነገር እስከሚሆን ድረስ ዲዳ ትሆናለህ’ ብሎ የካህኑን የዘካርያስን አንደበት ዘግቶት ነበር። በእመቤታችን ፊት ግን የአምላኩ እናት ለመሆን ተመርጣለችና የተግሣጽን ቃል እንኳን አልተናገረም፡፡ ‘መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፥ የልዑልም ኃይል ይጸልልሻል ስለዚህ ደግሞ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል።እነሆ ኤልሳቤጥ ካንቺ ወገን የምትሆን ከሸመገለች ካረጀች በኋላ ጸነሰች። እነሆም ይህ ስድስት ወር ሆነ።ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለም’ አላት፡፡ እርሷም ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር እንደሌለ ስለምታምን ከዚህ በኋላ አልተከራከረችውም። በታላቅ ትህትና ሆና ‘እነሆኝ የጌታ ባሪያ እንደቃልህ ይደረግልኝ’ በማለት ፈቃደኝነቷን ገለጸች።አምላክም በማኅጸንዋ አደረ፡፡

የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ገብርኤልም ለአዳም ልጆች ለሁላችንም ከዚያ በፊት ያልተሰማ ከዚያ በኋላም የሚስተካከለው የማይኖር ድንቅ የደስታ ዜናን አብሳሪ ሆነ።

ልጆች! ይህ ቅዱስ መልአክ ዘወትር በእግዚአብሔር ፊት ስለሚቆም ለምድራችን አሁንም የደስታ የሰላም ብስራት እንዲያሰማት፥ እናንተንም በጥበብና በሞገስ በሃይማኖታችሁ ጸንታችሁ በእግዚአብሔር ቤት እንድታድጉ እንዲረዳችሁ ለምኑት!እኛን ሁላችንን ይረዱን ዘንድ መላእክትን ዘወትር በፊታችን እንዲሄዱ ያደረገ እግዚአብሔር ይመስገን። አሜን።

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር!

 

 

ምንጭ ፥  መጽሐፍ ቅዱስ፥ አክሲማሮስ፥ ገድለ አዳም፥ ድርሳነ ገብርኤል

 

 

ብሥራታዊዉ መልአክ

ክፍል ሁለት

ከማርታ ታከለ

የካቲት ፫ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

        እንደምን አላችሁ ልጆች? ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችሁም ጋር ይሁን!

 

ዛሬ በክፍል አንድ መጨረሻ ላይ ያነሳናቸውን ጥያቄዎች በመመለስ እንጀምራለን።

 

ቅዱስ ገብርኤልና ሌሎችም ቅዱሳን መላእክት እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ለቁጣም ሆነ ለምህረት ወደሚልካቸው ቦታ እየተላላኩ መኖር ጀመሩ።ለቁጣም ሆነ ለምህረት የሚልካቸው በምድር ወደሚኖሩ ሰዎች ዘንድ ነበር።እነዚህ በምድር የሚኖሩ ሰዎች ማን ፈጠራቸው? ከየት መጡ?ለምንስ በጨለማና በሞት ጥላ ውስጥ ይኖሩ ነበር አልን?

 

እግዚአብሔር አምላክ  ከዕለተ እሁድ አንስቶ እስከ ዕለተ አርብ ድረስ ሰማይንና ምድርን የሚታየውንና የማይታየውን ሁሉ ፈጠረ። በስድስተኛው ቀን ሁሉን ፈጥሮ ካዘጋጀ በኋላ ‘ ሰውን እንደመልካችን እንደምሳሌያችን እንፍጠር’ ብሎ ከሌሎቹ ፍጥረታት በተለየ መልኩ አዳምንና ሔዋንን ፈጥሮ የብርሃን ልብስ አልብሶ በገነት አስቀመጣቸው። ሌሎች ፍጥረታት ሁሉ እንዲገዙላቸው አደረገ። ልምላሜዋ ካማረ እና ብዙ ፍሬዎች ካሉባት ገነት ሲያስቀምጣቸው ግን አንድ ትዕዛዝ አዘዛቸው።በገነት ካሉት እጽዋት ሁሉ እንዲበሉ ነገር ግን በገነት መኻከል ካለችው ከዕፀ በለስ ፍሬ እንዳይበሉ አዘዛቸው። እነርሱም ትዕዛዙን አክብረው በደስታና በሐሴት በገነት መኖር ጀመሩ።

 

በዚህ ጊዜ በክፍል አንድ ታሪኩን ያየነው ሀሰተኛው መልአክ ሳጥናኤል በአዳም ላይ ቂም ያዘበት። እግዚአብሔር በእርሱ ምትክ እንደፈጠረውና ብዙ ክብር እንደሰጠው በማየቱ አዳምንና ሔዋንን ከእግዚአብሔር ጋር የሚያጣላበትን ጊዜ ሲጠብቅ ኖረ።ከዕለታት በአንዱ ቀንም እባብ ሌሎች እንስሳት እንደሚያደርጉት አዳምንና ሔዋንን እጅ ለመንሳት ወይም ስም ሳይወጣለት ቆይቶ ኖሮ አዳም ለሌሎቹ እንስሳት ሁሉ ስም እንዳወጣላቸው ስም እንዲያወጣለት ወደ ገነት ሲሄድ ሳጥናኤል ያገኘዋል።ወዴት እንደሚሄድ ይጠይቀውና እሱም ወደዛው ስለሚሄድ አብረው ጉዟቸውን ይቀጥላሉ። ትንሽ እንደተጓዙ ‘ይህች ወደገነት የምታደርስ መንገድ አድካሚ ናት በየተራ እየተዛዘልን እንሂድ’ብሎ ሳጥናኤል እባብን ይጠይቀዋል በነገሩ ስለተስማማ ቀድሞ እሱ ይሸከመዋል። ትንሽ ከሄዱ በኋላ ያወርደውና በተራው እባብ ላይ ወጥቶ ይታዘልበታል። በዛውም ተፈጥሮው ረቂቅ መንፈስ ስለሆን በሰውነቱ ይገባል።

 

እባብም በገነት ፈሳሾችና አትክልቶች መኻከል ተቀምጣ ወደነበረችው ወደ ሔዋን መጣ። ‘ንግስተ ሰማይ ወምድር  ሆይ ሰላም ላንቺ ይሁን’ ብሎ ሰላምታ አቀረበላት። ሔዋንም ንግስተ ምድር እንጂ ንግስተ ሰማይ አይደለሁም ብላ በማስተካከል ፈንታ እባብ ባቀረበላት በዚህ አዲስ ሰላምታ ደስ ተሰኘች።እባብም  በውኑ እግዚአብሔር ከገነት ዛፍ ሁሉ እንዳትበሉ አዝዞአልን? አላት። ሔዋንም ለእባቡ ‘በገነት ካለው ከዛፍ ፍሬ እንበላለን፤ ነገር ግን በገነት መካከል ካለው ከዛፉ ፍሬ፥ እንዳትሞቱ ከእርሱ አትብሉ አትንኩትም’ ብሎ እግዚአብሔር እንዳዘዛቸው ነገረችው።  እባብም ‘ሞትን አትሞቱም፤ ከእርስዋ በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ እንዲከፈቱ እንደ እግዚአብሔርም መልካምንና ክፉን የምታውቁ እንድትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው እንጂ’ አላት ።

 

በዚህ ጌዜ ሔዋን ዛፉ ለመብላት ያማረ እንደ ሆነ፥ ለዓይንም እንደሚያስጎመጅ አየች ከፍሬውም ወሰደችና በላች። ለአዳምም ደግሞ ሰጠችው እርሱም ከእርስዋ ጋር በላ።

 

በዚህ ጊዜ የሁለቱም ዓይኖች ተከፈቱ። ዕራቁታቸውን እንደ ሆኑ አወቁ። የበለስንም ቅጠሎች ሰፍተው ለራሳቸው ግልድም አደረጉ።ቀኑ በመሸ ጊዜ የእግዚአብሔርን ድምፅ ከገነት ውስጥ ሲመላለስ ሰሙ። አዳምና ሚስቱም ከእግዚአብሔር ፊት በገነት ዛፎች መካከል ተሸሸጉ። እግዚአብሔር አምላክም አዳምን ጠርቶ ‘ወዴት ነህ?’ አለው። እርሱም ‘በገነት ድምፅህን ሰማሁ፤ ዕራቁቴንም ስለ ሆንሁ ፈራሁ፥ ተሸሸግሁም።’ ብሎ መለሰ እግዚአብሔርም ‘ዕራቁትህን እንደ ሆንህ ማን ነገረህ? ከእርሱ እንዳትበላ ካዘዝሁህ ዛፍ በውኑ በላህን?’ ብሎ ጠየቀው አዳምም አለ ‘ከእኔ ጋር እንድትሆን የሰጠኸኝ ሴት እርስዋ ከዛፉ ሰጠችኝና በላሁ።’ አለ። እግዚአብሔር አምላክም ሴቲቱን ‘ይህ ያደረግሽው ምንድር ነው?’ አላት። ሴቲቱም ‘እባብ አሳተኝና በላሁ።’ አለች።

 

እግዚአብሔር አምላክም እባቡን ‘ይህን ስላደረግህ ከእንስሳት ከምድር አራዊትም ሁሉ ተለይተህ አንተ የተረገምህ ትሆናለህ፤ በሆድህም ትሄዳለህ፥ አፈርንም በሕይወትህ ዘመን ሁሉ ትበላለህ። በአንተና በሴቲቱ መካከል፥ በዘርህና በዘርዋም መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፥ አንተም ሰኰናውን ትቀጠቅጣለህ’ አለው።ለሴቲቱም ‘በፀነስሽ ጊዜ ጭንቅሽን እጅግ አበዛለሁ፤ በጭንቅ ትወልጃለሽ፤ ፈቃድሽም ወደ ባልሽ ይሆናል፥ እርሱም ገዥሽ ይሆናል’ አላት።አዳምንም ‘የሚስትህን ቃል ሰምተሃልና፥ ከእርሱ እንዳትበላ ካዘዝሁህ ዛፍም በልተሃልና ምድር ከአንተ የተነሣ የተረገመች ትሁን፤ በሕይወት ዘመንህም ሁሉ በድካም ከእርስዋ ትበላለህ።እሾህንና አሜከላን ታበቅልብሃለች፤ የምድርንም ቡቃያ ትበላለህ። ወደ ወጣህበት መሬት እስክትመለስ ድረስ በፊትህ ወዝ እንጀራን ትበላለህ፤ አፈር ነህና፥ ወደ አፈርም ትመለሳለህ’ አለው። እግዚአብሔርም አዳምንና ሔዋንን ትዕዛዙን አላከበሩምና ከገነት አስወጣቸው፥ ወደ ሕይወት ዛፍ የሚወስደውንም መንገድ ለመጠበቅ ኪሩቤልንና የምትገለባበጥ የነበልባል ሰይፍን በዔድን ገነት ምሥራቅ አስቀመጠ።

 

ከዚህ በኋላ አዳምና ሔዋን በተድላና ደስታ ይኖሩባት ከነበረችው ከገነት ተባረው ከገነት ፍጹም ከተለየችው ምድር ላይ ራሳቸውን አገኙ። በዚያም በጣም በሀዘንና በለቅሶ መኖር ጀመሩ። አዳምም ራሱን እስኪስትና በድን እስኪሆን ጊዜ ድረስ ደረቱን እየመታና እያለቀሰ ከእግዚአብሔር ይቅርታን ይለምን ነበር። ሔዋንም በእኔ ምክንያት ይህ ሁሉ ቅጣት መጣብን እግዚአብሔርን አሳዘንን።እግዚአብሔርን ያህል ጌታ ገነትን ያህል ቦታ አጣን እያሉ። ብዙ ሱባኤና ጸሎት ያዙ። እግዚአብሔርም አጥብቀው ይቅርታውን ስለፈለጉ፥ ‘ከ5500 ዘመን በኋላ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ’ በማለት ቃል ኪዳን ገባላቸው። እነርሱም ልጆች ወልደውና ብዙ ሆነው የማዳኑን ቀን ሲጠባበቁ ኖሩ።

 

ስለዚህ አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ሲፈጸም በጨለማና በሞት ጥላ ሲኖሩ ለቆዩት የአዳም ልጆች ቅዱስ ገብርኤል የምስራች ዜና ይዞ እንዲወርድ ከእግዚአብሔር ዘንድ ተላከ።

 

ልጆች ቅዱስ ገብርኤል የምስራቹን ሊናገር የመጣው ወይም የተላከው ወደማን እንደሆነ ታውቃላችሁ? ይህንን በቀጣይ ክፍል እንመለከተዋለን።

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክብር!

ብስራታዊው መልአክ

ከማርታ ታከለ

ጥር ፳፮ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

ክፍል አንድ

 

እንደምን አላችሁ ልጆች? የእግዚአብሔር ሰላም ከሁላችሁም ጋር ይሁን!

 

ዛሬ ስለ አንድ ቅዱስ የእግዚአብሔር መልአክ ታሪክ እነግራችኋለሁ።ይህ መልአክ ብስራታዊው መልአክ ይባላል። ብስራት ማለት ምስራች ወይም ደስ የሚል ዜና ማለት ነው።ብስራታዊ ማለት ደግሞ ባለምስራች ወይም ደስ የሚያሰኝ ዜና የሚናገር የሚያሰማ ማለት ነው።የዚህ ቅዱስ መልአክ ስሙ ገብርኤል ይባላል።ልጆች! ታዲያ ቅዱስ ገብርኤል ምን ደስ የሚያሰኝ ዜና አሰምቶ ብስራታዊ ተባለ?

 

ከላይ ያነሳነውን ጥያቄ ከመመለሳችን በፊት ስለዚህ ቅዱስ መልአክ እና ስለሌሎች መላእክት አፈጣጠር በአጭሩ ልንገራችሁ፥

 

መላእክት በመጀመሪያው ቀን በዕለተ እሁድ ተፈጥረዋል። በተፈጠሩም ጊዜ ብርሃን አልነበረም። አንዱ መልአክ ሌላውን በሚነካው ጊዜ ሁሉም  ማን ፈጠረን? የሚለውን ጥያቄ መጠየቅ ጀመሩ። በዚህ ጊዜ ከሁሉም በላይ የነበረው መልአክ ሳጥናኤል ነበር። ከበላዩ ማንም እንደሌለ ሲረዳና ሁሉም እሱ ከነበረበት በታች እንደሆኑ ሲያውቅ አንድ ነገር ተናገረ። ‘የፈጠርኳችሁ እኔ ነኝ’ አላቸው።የመጀመሪያውንም ሀሰት ተናጋሪ ሆነ።እሱ እንዳልፈጠራቸው እያወቀ ሁሉም ማን እንደፈጠራቸው አለማወቃቸውን ተመልክቶ ሀሰትን ከራሱ አመንጭቶ ተናገረ።

 

በዚህ ጊዜ ዛሬ ታሪኩን የምነግራችሁ ቅዱሱ መልአክ ገብርኤል ‘የፈጠረንን እስክናውቅ ድረስ በያለንበት ጸንተን እንቁም’ በማለት ሌሎች መላእክትን እንዲጸኑና ተረጋግተው የፈጠራቸው እስኪገለጥ እንዲጠብቁ ተናገረ። በዚህ ጊዜ ሳጥናኤልን ያመኑና የተከተሉ መላእክት አሉ። ገብርኤልን ሰምተው የፈጠራቸው እስኪገለጥ ጸንተው የቆሙ መላእክት አሉ። በመኻል ደግሞ መወሰን ሳይችሉ ቀርተው እየዋለሉ ያሉ መላእክት ነበሩ።

 

ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ‘ብርሃን ይሁን!’ አለ። ብርሃንም ሆነ። መላእክትም ፈጣሪያቸውን አወቁ። ሳጥናኤልም የመላእክት ሳይሆን የሀሰት ፈጣሪ መሆኑ ተጋለጠ። በሰራው ስህተት ጸጸት የማያውቅ አመጸኛ በመሆኑ የራሱን ሠራዊት ይዞ ከገብርኤልና ከሚካኤል ከሌሎችም የመላእክት አለቆችና ሠራዊቶቻቸው ጋር ተዋጋ። እነርሱም ሳጥናኤልን አሸነፉት። ሳጥናኤልን ያመኑትና መወሰን አቅቷቸው ሲወላውሉ የነበሩት መላእክት ሁሉ ከሰማይ ተጣሉ። ከክብራቸውም ተዋርደው ተባረሩ። ቅዱስ ገብርኤልና ሌሎች ቅዱሳን መላእክት ግን ከነክብራቸው የፈጠራቸውን እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ለመኖር ቻሉ።

 

ልጆች ቅዱስ ገብርኤልን ብስራታዊ መልአክ የምንለው ከላይ ባየነው ታሪክ ይመስላችኋል? አይደለም። ከላይ ባየነው ታሪክ ውስጥ መለእክትን እንዲጸኑና እንዲረጋጉ አድርጓል። በዚህም ሌሎች መላእክት ሳጥናኤልን ሰምተው ከክብራቸው ከመዋረድና ከመላእክት ዓለም ከመባረር አድኗቸዋል። ታዲያ ብስራታዊ ለምን ተባለ?

 

ከብዙ ዘመን በኋላ ቅዱስ ገብርኤል ከእግዚአብሔር አብ ዘንድ ወደ ምድር ተላከ። ታላቅ የምስራች፥ ታላቅ የደስታ ዜናም ይዞ ነበር።የሰው ልጆች ሁሉ ለዘመናት በተስፋ ሲጠብቁት የነበረውን ዜና የምስራች ይዞ ከሰማይ ወረደ።በጨለማ በሞት ጥላ ውስጥ ይኖሩ ለነበሩት የሰው ልጆች ወደ ህይወት የሚያመጣ ወደ ብርሃን የሚያወጣ የምስራች ዜና ይዞ ከሰማይ አየሩን በክንፎቹ እያማታ ወደምድር ወረደ።

 

ልጆች! በዛሬው ክፍል ጥያቄ እጠይቃችኋለሁ። ቅዱስ ገብርኤል ከተፈጠረ ከብዙ ጊዜ በኋላ የምስራች ይዞ ወደ ምድር መጣ ብለናል። ምስራቹን ከማምጣቱ በፊት ምን ይሠራ ነበር? ምስራቹን ያመጣላቸው የሰው ልጆች እነማን ናቸው?ለምንስ በጨለማና በሞት ጥላ ውስጥ ይኖሩ ነበር አልን? ቅዱስ ገብርኤልን ብስራታዊ ያሰኘው የብስራት መልእክትስ ምን ይሆን?

 

በቀጣይ ክፍል መልሱን እናገኛለን!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ወለወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር!

የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር ከሀገረ ዴንማርክ(ኮፐንሃገን) ወደ ሀገረ ስዊድን (ሉንድ)

ከዴንማርክ ኮፐንሃገን ደብረ ምሕረት ቅዱስ አማኑኤል ቤተ ክርስቲያን በመነሳት ወደ ስዊድን፣ ሉንድ ደብረምጥማቅ ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ነሐሴ 16/2013 . (Aug.22/2021) የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር ተካሄደ።

ሐዊረ ሕይወቱን ያዘጋጅው የዴንማርክ ግንኝነት ጣቢያ ከደ/// አማኑኤል እና ከሉንድ /// ማርያም /ሰበካ ጉባኤያት ጋር በመተባበር ነው። በዚህ መርሐ ግብር ላይ የሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት ምእመናን እናበአጎራባች የሚገኙ አጥቢያዎች፣ አጠቃላይ 200 በላይ የሚሆኑ ምእመናን ተሳተፈዋል። የሁለቱም አጥቢያዎችአስተዳዳሪ መልአከ ምሕረት ቆሞስ አባ ዘሚካኤል ደሬሳ፥ መጋቤ ሃይማኖት ቀሲስ ኃይለ ማርያም አያሌው እናመልአከ መዊእ ቀሲስ ሃይለ ጊዮርጊስ አሰፋ ተገኝተው ቃለ እግዚአብሔር እና ምክር ሰጥተዋል።  

መርሐ ግብሩ እሐድ ጠዋት 06:00 ላይ ከኮፐሃገን ///አማኑኤል ቤተክርስቲያን በመነሳት ወደ ሉንድ /// ማርያም ቤተ ክርስቲያን ተደርጓል። በደብረ ምጥማቅም የኪዳን ጸሎት፥ የቅዳሴ ጸሎት በኋላ የሐዊረ ሕይወቱየመጀመሪያው ክፍል በጸሎተ ወንጌል ተጀምሮ በኮፐንሃገን የተስፋ ምሕረት //ቤት ዘማሪያን ያሬዳዊዝማሬያት እና የበገና መዝሙር አቅርበዋል።

ከዚያ በማስቀጠል በመልአከ ምሕረት ቆሞስ አባ ዘሚካኤልከመረጥኹት፣ጋራ ቃል ኪዳኔን አደረግኹ መዝ883″ በሚል ርእስ ትምህርተ ወንጌል ሰጥተዋል። በማያያዝም የደ/ምጥማቅ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያንየአጥቢያው ምእመናን 30 ዓመታት በላይ ይጠቀሙበት የነበረውን ሕንጻ ኮንትራት፣ ለቀጣይ 100 ዓመታትመራዘሙን ምክንያት በማድረግ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑን ለሰጡት የስዊድን ቤተክርስቲያን እና ላስተባበሩትየሰብካ ጉባኤ አባላት ምስጋና በማቅረብ ሊሠራ ስለታቀደው ደጀ ሰላም ገለጻ ተደርጓል፡፡ ደጀ ሰላሙ በአውሮፓያሉ ምእመናን በፍልሰታና በሌሎች ጊዜያት መጥተው ሱባኤ ሊይዙበት የሚችሉ በመሆኑ እቅዱ እንዲሳካየምእመናን ሁለንተናዊ ትብብር እንዲደረግለት ሰበካ ጉባኤው ጥሪውን አስተላልፏል።  


የሐዊረ
ሕይወት 2 ክፍል የሆነው ምክረ አበው  በመጋቢ ሃይማኖት ቀሲስ ሃይለ ማርያም እና በመልአከ መዊእቀሲስ ሃይለ ጊዮርጊስ አማካኝነት 2ሰዓት ያክል ተከናውኗል። በምክረ አበውም ምእመናን ጥሩ ግንዛቤአግኝተውበታል። በተጨማሪም  የተስፋ ምሕረት / ተማሪዎች የተለያዪ ሥነ ጹሑፎችን በኅብረት አቅርበዋል።

በመጨረሻም ሰለ ማኅበረ ቅዱሳን ማንነት፥ ሰለአመሠራረቱ እና ስለሚከናውናቸው መንፈሳዊ መርሐ ግብራትከተገለጸ በኋላ፣ ይህን ሐዊረ ሕይወት በማዘጋጀት ለተሳትፉ ባለድርሻ አካላት ሁሉ በእግዚአብሔር ስም ምስጋናበማቅረብ በደ/// ማርያም ቤተ ክርስቲያን አውደ ምሕረት ውስጥ የነበረው መርሐ ግብር ተጠናቋል፡፡ ሐዊረሕይወቱ የዴንማርክ /// አማኑኤል ቤተ ክርስቲያን አባላት ከሉንድ ///ማርያም ቤተክርስቲያን ወደኮፐንሃገን //ቅዱስ አማኑኤል ቤተ ክርስቲያን ባደረጉት በዝማሬ የታጀበ የመልስ ጉዞ ተፈጽሟል።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር።

ግቢ ጉባኤ

ቨርችዋል ግቢ ጉባኤ በአውሮፖ በዚህ ይመዝገቡ:-
https://docs.google.com/forms/u/1/d/1kwZcBbi7PrnK1m-Iz6E8Njpdmy-sMURA8wf2pDWrR_k/viewform?edit_requested=true&pli=1 

ቡሄ

የአውሮፓ ማዕከል በአጭሩ ሲቃኝ

ማኅበረ ቅዱሳን እግዚአብሔር ያከበራቸዉ የነቢያት፣ የሐዋርያት፣ የጻድቃን፣ የሰማዕታት፣ በአጠቃላይ የቅዱሳን ገድል፣ ትሩፋትና አማላጅነት የሚዘከርበት ማኅበር ነው። በ1977 ዓ.ም. በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሲማሩ የነበሩ ጥቂት የቤተ ክርስቲያን ወጣቶች በጽዋ ማኅበር ስም በመሰባሰብ ትምህርተ ሃይማኖትን መማማር ጀመሩ። ይህ እንቅስቃሴ በየዓመቱ የክረምት ወራት በዝዋይ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ካህናት ማሰልጠኛ ይሰጥ በነበረው ስልጠና ተጠናክሮ ቀጠለ። ከዚያም በ1983 ዓ.ም በተለያዩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ይማሩ የነበሩ ተማሪዎች ወደ ብላቴ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ተቋም እንዲገቡ በመንግሥት በታዘዘ ወቅት በተቋሙ የገቡ ኦርቶዶክሳዊ ተዋሕዶ ወጣቶች በኅብረት ሲጸልዩና ትምህርተ ሃይማኖትን ሲማማሩ ቆዩ። ከብላቴ መልስ በተለያዩ የጽዋ ማኅበራት የነበረው መሰባሰብ ቀጥሎ በ1984 ዓ.ም. በቅዱስ ሲኖዶስ ፈቃድ መተዳደሪያ ደንብ ጸድቆለት ማኅበረ ቅዱሳን ለመመሥረት በቃ።

Read more