የአውሮፓ ማዕከል በአጭሩ ሲቃኝ

ማኅበረ ቅዱሳን እግዚአብሔር ያከበራቸዉ የነቢያት፣ የሐዋርያት፣ የጻድቃን፣ የሰማዕታት፣ በአጠቃላይ የቅዱሳን ገድል፣ ትሩፋትና አማላጅነት የሚዘከርበት ማኅበር ነው። በ1977 ዓ.ም. በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሲማሩ የነበሩ ጥቂት የቤተ ክርስቲያን ወጣቶች በጽዋ ማኅበር ስም በመሰባሰብ ትምህርተ ሃይማኖትን መማማር ጀመሩ። ይህ እንቅስቃሴ በየዓመቱ የክረምት ወራት በዝዋይ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ካህናት ማሰልጠኛ ይሰጥ በነበረው ስልጠና ተጠናክሮ ቀጠለ። ከዚያም በ1983 ዓ.ም በተለያዩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ይማሩ የነበሩ ተማሪዎች ወደ ብላቴ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ተቋም እንዲገቡ በመንግሥት በታዘዘ ወቅት በተቋሙ የገቡ ኦርቶዶክሳዊ ተዋሕዶ ወጣቶች በኅብረት ሲጸልዩና ትምህርተ ሃይማኖትን ሲማማሩ ቆዩ። ከብላቴ መልስ በተለያዩ የጽዋ ማኅበራት የነበረው መሰባሰብ ቀጥሎ በ1984 ዓ.ም. በቅዱስ ሲኖዶስ ፈቃድ መተዳደሪያ ደንብ ጸድቆለት ማኅበረ ቅዱሳን ለመመሥረት በቃ።

ማኅበሩ ከምሥረታው ጀምሮ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሥር ተዋቅሮ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ አገልግሎቱን እያከናወነ ይገኛል። ማኅበሩ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትምህርታቸውን የሚከታተሉ የቤተ ክርስቲያን ልጆችን በማሰባሰብና በማስተማር የጀመረው አገልግሎት በዓይነትና በቦታ ሽፋን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቶ በአሁኑ ወቅት አገልግሎቱን በ300 ግቢ ጉባኤያት (ከመቶ ሺህ በላይ ተማሪዎችን በማስተማር)፤ በ44 የአገር ውስጥ እና በ4 የውጭ ማዕከላት በማከናወን ላይ ይገኛል።

ማኅበረ ቅዱሳን በአገር ውስጥና ከአገር ውጭ ባሉት መዋቅራቱ አማካኝነት በርካታ የቤተ ክርስቲያኒቱን መንፈሳዊ አገልግሎቶች እያበረከተ የሚገኝ ሲሆን፤ ዋና ዋናዎቹም፥ (1) ሥርዓተ ትምህርት በመቅረጽ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገኙ ተማሪዎችን ትምህርተ ሃይማኖትን ማስተማር (2) ሐዋርያዊ ጉዞ በማዘጋጀት፣ ሰባክያነ ወንጌል በማሰማራት፣ ልዩ ልዩ ኅትመቶችን በማዘጋጀትና በማሰራጨት በመላው ዓለም ስብከተ ወንጌልን ማስፋፋት እና (3) የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ማፍሪያ የሆኑትን አድባራት፣ ገዳማትና የአብነት ትምህርት ቤቶችን ጊዜያዊ ዕርዳታ ከመስጠት ባሻገር ፕሮጀክቶችን በመቅረጽና በጎ አድራጊዎችን አስተባብሮ በመተግበር በዘለቄታ በልማት ራሳቸውን ማስቻል ናቸው።

ከአገር ውጭ ማዕከላት አንዱ የሆነው የአውሮፓ ማዕከል የተመሠረተው በታኅሣሥ ወር 1993 ዓ.ም. ለትምህርት ከኢትዮጵያ በመጡ እና በአውሮፓ ነዋሪ በነበሩ የማኅበሩ አባላት ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት በ5 ቀጣና ማዕከላትና በ7 ግንኙነት ጣቢያዎች በተለያዩ የአውሮፓ አገራት አገልግሎቱን እየፈጸመ ይገኛል።

ማኅበረ ቅዱሳን በአውሮፓ ከሐምሌ ወር 2002 ዓ.ም. ጀምሮ በጀርመን አገር በኮሎኝ ከተማ በሕጋዊ ለትርፍ ያልተቋቋመ ማኅበርነት ተመዝግቧል።