ሕይወት በባዕድ ምድር (፪ጴጥ. ፪፥፰)

የርዕሳችን መነሻ የሆነው በ፪ኛ ጴጥሮስ ምዕራፍ ፪ ላይ የምናገኘው ታሪክ ነው። “ጻድቅ ሎጥም እያየና እየሰማ፣ አብሮአቸውም እየኖረ በክፉ ሥራቸው ዕለት ዕለት ጻድቅት ነፍሱን ያስጨንቃት ነበር።” ፪ጴጥ. ፪፥፰

ሎጥ ኃጢአትን የዕለት ከዕለት ተግባራቸው ካደረጉ ሰዎች ጋር ለመኖር የተገደደው በዘፍ ፲፫ ላይ እንደምናነበው ከአጎቱ ከአብርሃም ጋር ይኖርበት የነበረው ቦታ ስለጠበባቸው በእረኞቻቸው መካከልም እየተፈጠረ የነበረው ጥላቻ ወደ እነርሱ እንዳይጋባ ራቅ ወዳለ ቦታ መሄድ ስለነበረበት ነበር። ለመለያየት ሲወስኑም ለሎጥ እንዲመርጥ ዕድል በተሰጠው ጊዜ የመረጣት ውሃ የሞላባትን ለምለሟን ሰዶምን ነበር። ሎጥ ግን በጎረቤቶቹ መካከል እየኖረ ዕለት ዕለት የሚሠሩትን ሥራ እያየና እየሰማ

ይጨነቅ ነበር። ጎረቤቶቹ ግን ማንኛውንም ኃጢአት ከመስራት ወደ ኋላ የማይሉ ነበሩ። ከእግዚአብሔር ዘንድ ተልከው የመጡ መላእክትን እንኳን ሳይቀር በግብር ለማወቅ ከሎጥ ጋር ግብግብ ሲገጥሙ በዘፍ ፲፱:፬-፲፩ ላይ እናነባለን።

በተለያየ ምክንያት ከሀገራችን ወጥተን በስደት ሕይወትን ለመግፋት ግድ የሆነብን ሰዎች

ዛሬ ከአባታችን ከሎጥ የምንማረው ብዙ ነገር አለ። ፈተና የክብር ማግኛ መንገድ ነዉ። ስለሆነም ደጋግ አባቶቻችን ፈተና ሲርቅላቸዉ አይወዱም ነበር፤ ከቅዱስ እግዚአብሔር ጋር ለመሆናቸዉ አንዱ ማረጋገጫቸው በፈተና መጎሸማቸዉ ስለሆነ። ጻድቅ ሎጥ አስጸያፊ የሆነ ግብረ ሰዶም በሚፈጸምባት ከተማ እየኖረ ከእግዚአብሔር አልተለየም ነበር፤ ነፍሱን በብዙ ያስጨንቃት ነበር እንጂ። አበ ብዙሃን የተባለ አብርሃም ስለነዚያ ሰዎች ድኅነት ልመና ቢያቀርብም በከተማዋ 10 ደጋግ ሰዎች ባለመገኘታቸዉ ቅዱስ እግዚአብሔር ከተማዋን ሊያጠፋት በወሰነ ጊዜ ከነዚያ ሰዎች ኃጢአት ተሳታፊ ያልነበረ ጻድቅ ሎጥ እና ቤተ ሰዎቹን ለማውጣት መላእክት ተልከዋል።

ጻድቅ ሎጥ በመጀመሪያ የአካባቢዉን ልምላሜ እና ለከብቶቹ ምቹ መሆኑን እንጂ የነዋሪዎቹን ክፋት አልመረመረም። በመሆኑም የነዚያን ሰዎች ገደብ የለሽ የኃጢአት ሕይወት በማየትና በመስማት እየተጨነቀ መኖር ግድ ሆነበት። ለእግዚአብሔር ሰዉ የሰዶም ሰዎች ሕይወት የተጠላ ነዉና። በየአዝማናቱ በክፉ መንገድ የሚጓዘው ሰዉ በቁጥር አያሌ ነው። ቅዱሳን ሰዎች የቅድስና እና የብጽእና ክብር የተቀዳጁት ከነዚህ ሰዎች ጋር እየኖሩ በክፉ ሥራቸው ሳይተባበሩ ራሳቸውን ጠብቀዉ በመኖራቸዉና ፈተናዉን በማሸነፋቸው ነዉ። ሁሉ በደለኛ ነዉ እኔ እንዴት ብቻየን መኖር ይቻለኛል? የሚል አዕምሮ የለባቸዉም። እንዲህስ ቢሆን ጽድቃቸዉ ግዘፍ ነስቶ ባልተናገረ ነበር።

ኖኅ በጽድቁ ዓለምን ኮነነ የተባለዉ ሰብአ ትካት (የጥንት ሰዎች) ሲበድሉ በአምልኮተ እግዚአብሔር ጸንቶ በመገኘቱ ነዉ። ለሎጥስ የግብረ ሰዶምን አስከፊነት ማን ነገረዉ፣ በዚያን ጊዜ የጽሑፍ ሕግ አልነበረምና። ዛሬ ግብረ ሰዶም በዓለም ተንሰራፍቶ እንዲያዉም በመንግሥታት ሳይቀር ሕግ እየወጣለት ነዉ፤ ወንድ ከወንድ፣ ሴትም ከሴት መጋባት ተጀምሯል። እጅግ የሚገርመዉ በእንስሳቱም እኮ ይሕ ይፈጸማል በማለት የሚናገሩ መኖራቸዉ ነዉ። ዓለም በቴክኖሎጂ፣ በዕዉቀት፣ በስልጣኔ እና በመሳሰሉት መጥቆ ሄዷል እየተባለ እንደገና ሰዉ ራሱን አዋርዶ ከእንስሳት ለመማር መዳዳቱ የጊዜዉን አስከፊነት ፍንትዉ አድርጎ የሚያሳይ ነዉ። ቆነጃጅቱ ራቁታቸዉን ሲሄዱ፣ በየመንገዱ እንደዉሻ ሲላላሱ፣ ዝሙቱንም ያለ ሃፍረት ሲፈጽሙ እነሆ እናያቸዋለን። በአንዳንድ አካባቢዎች ሰዎች ራቁታቸዉን ሆነዉ የሚታዩበት ቦታ የተከለለላቸዉ መሆኑ ይነገራል። ወንድ ከወንድ ጋር ጋብቻ እንዳይከለከል በፍርድ ቤት ቀርበዉ ሲከራከሩ ከተፈጥሮ ሕግ ወጣን ብለዉ ቅንጣት ታክል እንኳን አይደነግጡም። ታዲያ ከሎጥ ዘመን፣ ከሰብአ ትካት የተሻሉት በምን ይሆን? ሰዉ እንስሳትን መምሰል ብቻ አይደለም ከእንስሳትም አንሷል። እንሰሳት እና አራዊት እንኳ የየራሳቸዉን ግብር ይዘዉ ይኖራሉ፤ ሰይጣንም እንኳ ስለሚበላዉና ስለሚጠጣዉ ተጨንቆ አያዉቅም። ለዚህም ነዉ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ አንተ ማስተዋል ከሌላቸዉ ዲዳ አራዊት እንስሳት ከሰይጣንም የምታንስ ስለሆነ ምን ብዬ ልጥራህ? እያለ ለመናግር የደረሰዉ።