ሕይወት በባዕድ ምድር (፪ጴጥ. ፪፥፰)

በዚህ በባዕድ አገር ያለዉ ሁናቴ ኢትዮጵያ ዉስጥ ካለዉ የተለየ መሆኑ፤ ግለኝነት የተንሰራፋበት እና ለመንፈሳዊዉ ነገር ደንታቢስ የሆነዉ ሕዝብ ቁጥር መብዛት በመንፈሳዊ ሕይወት እንዳንጎለምስ፣ በጾም፣ በጸሎት እና በአገልግሎት ሌሎች ትሩፋቶችንም በማብዛት እንዳንተጋ ጫና ሊያሳድርብን ይችል ይሆናል። ሆኖም ግን ከላይ ከፍ ብሎ የተመለከትናቸዉ ቁም ነገሮች ከፊት ይልቅ እንድንተጋ የሚያደርጉ፣ የጊዜዉን ሁናቴ እንድንመረምር እና ቃለ ወንጌልን እንድናስታዉስ የሚያስገድዱን ናቸዉ። ከሀገር መዉጣታችን ፍሬ እንድናፈራ መሆኑን ከተቀበልነዉ በጸሎትና በመንፈሳዊ አገልግሎት መትጋት ወደ መካከል መምጣትም ይገባናል። በምክረ ካህን የምንኖር፣ በንስሓ ሕይወት የምንመላለስ ከሆነንና ሕይወታችንን በቅዱስ ሥጋዉ እና በክቡር ደሙ ያተምን ከሆነ የሚገጥመንን ፈተና ሁሉ ረድኤተ እግዚአብሔርን አጋዥ በማድረግ በአሸናፊነት ለመወጣት አያዳግትም፣ በእኛ የሚሠራ እርሱ አምላካችን ከአሸናፊዎች ሁሉ በላይ ነዉና። አኗኗራችን እንዲህ ከሆነ ለከተማዋ የታዘዘ ጥፋት ቢመጣ እንኳ እግዚአብሔር አምላካችን ከጥፋት ሊያድን የታመነ አምላክ መሆኑን ጻድቅ ሎጥና ቤተ ሰዎቹን ለማዳን መላእክቱን በመላክ አሳይቶናል። ከአብርሃም እና ከሎጥ ጋር የነበረ እግዚአብሔር ዛሬም ያዉ ነው፣ ፍቅሩ በዘመን ብዛት የሚቀንስ የማዳን እጁንም የሚያጥፍ አይደለም። በድንቅ አጠራሩ የጠራን በቸርነቱ ጥላ ከልሎ እድሜ ለንስሓ የሰጠን፣ በፍቅሩ ከጥፋት እስከ አሁን የጠበቀን ቅዱስ እግዚአብሔር ቀሪ ሕይወታችንን እንዲያስተካክልልን፣ አገልግሎታችንን እንዲያሰፋልን፣ የመንግሥቱ ወራሾችም እንዲያደርገን ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን። የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም የእናትነት ፍቅርና ርኅራኄ፣ የቅዱሳን ጸሎት እና ምልጃ አይለየን፤ አሜን።