ትንሣኤ

በዲ/ን ብሩክ አሸናፊ

ሚያዚያ 23 ቀን 2008 ..

የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ሲነገር አብሮ የሚነሣው በዕለተ ዓርብ ስለኛ ብሎ የተቀበለው ሞቱ ነው። አባታችን አዳም እና እናታችን ሔዋን በፈጸሙት በደል ምክንያት የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸው ሳለ በበደላቸው ንስሐ ገብተው አምላካችንን በመለመናቸው፥ እርሱም የሰው ፍቅር አገብሮት በዕለተ አርብ በመስቀል ላይ ሞቶ ሶስት መዓልት እና ሶስት ሌሊት በከርሰ መቃብር አድሮ ሞትን ድል አድርጎ ተነሳ። ነገር ግን ተነሣ የሚለውን ለማመን ሞተ የሚለውን ማመን ስለሚቀድም፥ ጌታችን በዕለተ አርብ መሞቱን የቅዱሳት መጻህፍትን ምስክርነት በማስቀደም እንጀምራለን።

ጌታችን በዕለተ ዓርብ በመስቀል ላይ በተሰቀለበት ሰዓት የቤተ መቅደስ መጋረጃ ለሁለት ሲቀደድ፥ ምድር ስትናወጥ፥ ዓለቶች ሲሰነጠቁ፥ ሙታን ሲነሱ፥ ፀሐይ ብርሃኗን ስትከለክል፥ ጨረቃ ደም ስትሆን፥ ከዋክብት ሲረግፉ ያዩት የመቶ አለቃው እና አብረው ጌታን ይጠብቁ የነበሩት ”ይህ በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነው” ብለው እጅግ ፈሩ (ማቴ 27፥51-54)። ትንኝን የምታጠሩ ግመልንም የምትውጡ ብሎ ጌታችን ሲያስተምር የዘለፋቸው አይሁድ ትልቁን ኃጢአት ፈጽመው ሰንበት እየገባ ስለነበር ሰንበትን ላለመሻር ሥጋቸው በሰንበት በመስቀል ላይ እንዳያድር፥ ጭናቸውን ሰብረው እንዲያወርዱአቸው ጲላጦስን ለመኑት (ዮሐንስ 19፥31)። ጭናቸውን የሚሰብሩበት ምክንያት ተንጠልጥለው በልብ ድካም እና ሰውነታቸው ውስጥ ያለው ወዝ ፈሶ ቶሎ እንዲሞቱ ለማድረግ ነው። ጭፍሮቹም በጌታችን ግራና ቀኝ የተሰቀሉትን የሁለቱን ወንበዴዎች ጭኖችቻቸውን ሰብረው ወደ ጌታችን በመጡ ጊዜ ግን እርሱ ፈጽሞ እንደ ሞተ አይተው ጭኑን አልሰበሩም (ዮሐ 19፥32-36)።

በጎና ጻድቅ ሰው የሸንጎ አማካሪም የሆነ፥ በምክራቸውና በሥራቸው ከአይሁድ ጋር ያልተባበረ፥ የአርማትያሱ ዮሴፍ ወደ ጲላጦስ ቀርቦ የኢየሱስን ሥጋ ለመነው (ዮሐንስ 19፥38)። ጲላጦስም አሁኑን እንዴት ሞተ ብሎ ተደነቀ፥ የመቶ አለቃውንም ጠርቶ ከሞተ ቆይቶአልን? ብሎ ጠየቀውና (ማርቆስ 15፥44) ከመቶ አለቃው እንደሞተ ተረድቶ የጌታችንን ቅዱስ ሥጋ ይቀብር ዘንድ ለዮሴፍ ፈቀደለት ። እንግዲህ ሞቱን ያረጋገጡትና ሞቱን ፈልገው እንዲሞት የሰቀሉት ጠላቶቹ መሆናቸው በእርግጥ መሞቱን ተአማኒነት እንዲኖረው ያደርገዋል። ስለዚህ አይሁድም ሆኑ በኋላ የሚነሱ መናፍቃን አልሞተም ነበር ብለው ትንሣኤውን እንዳይክዱ ምክንያት አይኖራቸውም። አስቀድሞ በሌሊት ወደ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሄዶ የተማረው ኒቆዲሞስ እና ዮሴፍ የጌታችንን ሥጋ ወስደው እንደ አይሁድ አገናነዝ ልማድ ከሽቱ ጋር በተልባ እግር ልብስ ከፈኑት። በተሰቀለበትም ስፍራ አትክልት ነበረ፥ በአትክልቱም ማንም ገና ያልተቀበረበት ከአለት የተወቀረ አዲስ መቃብር ነበረ። ሰንበት እየገባ ስለነበር የጌታችንን ቅዱስ ሥጋ ቅርብ በነበረው በዚህ መቃብር አኖሩት (ዮሐንስ 19፥36-42)። ሰው ተቀብሮበት የነበረ ቢሆን ኖሮ በኤልሳዕ መቃብር ላይ ያረፈው አስክሬን ነፍስ ዘርቶ እንደተነሣ (2ኛ ነገ 13፥20-21) እንዲሁ ጌታም የተነሳው በራሱ አስነሺነት ሳይሆን ቀድሞ በተቀበረው ሰው ቅድስና ነው የሚሉ መናፍቃን እንዳይነሱ በአዲስ መቃብር አኖሩት። የመቃብሩንም ደጃፍ በታላቅ ድንጋይ ዘጉት። ከገሊላም ከእርሱ ጋር የመጡት ሴቶች ተከትለው መቃብሩን ሥጋውንም እንዴት እንዳኖሩት አዩ ተመልሰውም ሽቱና ቅባት አዘጋጁ (ሉቃስ 23፥55-56)። የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን ወደ ጲላጦስ ተሰበሰቡና ያ አሳች (ሎቱ ስብሐት) በሕይወቱ ገና ሳለ ከሦስት ቀን በኋላ እነሣለሁ እንዳለ ትዝ አለን ደቀ መዛሙርቱ መጥተው በሌሊት እንዳይሰርቁት ለሕዝቡም ከሙታን ተነሣ እንዳይሉ፥ የኋለኛይቱ ስሕተት ከፊተኛይቱ ይልቅ የከፋች ትሆናለችና መቃብሩ እስከ ሦስተኛ ቀን ድረስ እንዲጠበቅ እዘዝ አሉት። ፈቅዶላቸውም ሄደው ከጠባቆች ጋር ድንጋዩን በንጉሡ ማህተም አትመው መቃብሩን በአይሁድ ጭፍሮችና በሮም ወታደሮች አስጠበቁ (ማቴ 27፥62-66)።

የጌታችን ትንሣኤከሳምንቱ በፊተኛው ቀን እሑድ ማለዳ ጨለማ ሳለ ማርያም መግደላዊት እና ቁጥራቸው ከ36ቱ ቅዱሳት አንስት የሆኑ ሌሎች ሴቶች የጌታችንን ቅዱስ ሥጋ ለመቀባት ያዘጋጁትን ሽቱ ይዘው ወደ መቃብሩ ሲሄዱ ድንጋዩን ከመቃብሩ ደጃፍ ማን ያንከባልልልናል? ይባባሉ ነበር (ማርቆስ 16፥1-3)። የጌታ መልአክም ድንጋዩን አንከባሎ ስለጠበቃቸው ማን ያንከባልልልናል? የሚለው ጭንቀታቸው ተወግዶ ወደ ውስጥ ቢገቡ የጌታን ቅዱስ ሥጋ አላገኙትም፤ ሁለት መላእክትም የሚያንጸባርቅ ልብስ ለብሰው ወደ እነርሱ ቀረቡ: ሴቶቹም ፈርተው ፊታቸውን ወደ ምድር አቀርቅረው ሳሉ፥ እንዲህ አሉአቸው፦ ሕያውን ከሙታን መካከል ስለ ምን ትፈልጋላችሁ? ተነሥቶአል እንጂ በዚህ የለም የሰው ልጅ በኃጢአተኞች እጅ አልፎ ሊሰጥና ሊሰቀል በሦስተኛውም ቀን ሊነሣ ግድ ነው እያለ ገና በገሊላ ሳለ ለእናንተ እንደ ተናገረ አስቡ (ሉቃ 24፥4-7) ። እንደተናገረ ተነስቶአልና በዚህ የለም የተኛበትንም ስፍራ ኑና እዩ። ፈጥናችሁም ሂዱና ከሙታን ተነሣ እነሆም ወደ ገሊላ ይቀድማችኋል በዚያም ታዩታላችሁ ብላችሁ ለደቀመዛሙርቱ ንገሯቸው አሏቸው (ማቴ 28፥6-7)። ከመቃብሩም ተመልሰው ይህን ሁሉ ለአሥራ አንዱና ለሌሎች ሁሉ ሊነግሩአቸው ሄዱ።

ከጠባቆቹ አንዳንድ ወደ ከተማ መጥተው የሆነውን ሁሉ ለካህናት አለቆች አወሩ:፡ ከሽማግሎች ጋርም ተሰብስበው ተማከሩና ለጭፍሮች ብዙ ገንዘብ ሰጥተዋቸው እኛ ተኝተን ሳለን ደቀ መዛሙርቱ በሌሊት መጥተው ሰረቁት ብለው እንዲዋሹ ነገሯቸው። እነርሱም ገንዘቡን ተቀብለው እንደ አስተማሩአቸው አደረጉ። ይህም ነገር በአይሁድ ዘንድ እስከ ዛሬ ድረስ ሲወራ ይኖራል(ማቴ 28፥11-15)። ይህ የአይሁድ ውሸት ግን ተአማኒነት የጎደለው ነበር። ምክንያቱም ሐዋርያት ሰረቁት እንዳይባል ሐዋርያት የአይሁድ ጭፍሮችን እና የሮም ወታደሮችን አሸንፎ የጌታችንን ቅዱስ ሥጋ የሚያሰርቅ አቅምም ድፍረትም አልነበራቸውም፥ ሌላው ደግሞ የተልባ እግሩ ልብስ እና በራሱ የነበረው ጨርቅ በሥርዓት በቦታው ተቀምጦ መገኘቱ (ዮሐንስ 20፥7) የጌታችን ሥጋ ላለመሰረቁ ምልክት ነው፤ ምክንያቱም ሌባ ካሁን ካሁን መጡብኝ እያለ አዘበራርቆ ይሄዳል እንጂ በሥርዓት አያስቀምጥም። ጲላጦስም በመረመራቸው ጊዜ የአራቱም የጭፍሮች አለቆች ቃላቸው ተለያየ፤ አንዱ አሥራ አንዱ ደቀመዛሙርት ወሰዱት ሲል፥ ሌላው መቶ ሃያው ቤተሰብ ሲል፥ ደግሞ ሌላው ዮሰፍና ኒቆዲሞስ ሲል፥ ሌላኛው ደግሞ አላየሁም ተኝቼ ነበር ሲል (የማቴዎስ ወንገል አንድምታ) ጲላጦስ ጌታ በእውነት ተነስቷል ብሎ አመነ፤ የጌታን ትንሣኤም መስካሪ ሆነ(ግብረ ሕማማት)።

ደቀመዛሙርቱም የሴቶቹ ቃል ቅዠት መስሎ ታያቸውና አላመኑአቸውም፤ ጴጥሮስና ዮሐንስ ግን ወጥተው ወደ መቃብሩ ሮጡ። የተልባ እግሩን ልብስ በመቃብሩ እግርጌ፥ በራሱ የነበረው ጨርቅ ደግሞ ለብቻው በራስጌ ተቀምጦ አይተው ጌታ በእውነት መነሳቱን አመኑ፤ ወደ ቤታቸውም ተመለሱ (ዮሐ 20፥3-7)። ማርያም ግን እያለቀሰች ከመቃብሩ በስተ ውጭ ቆማ ነበር። ስታለቅስም ወደ መቃብር ዝቅ ብላ ተመለከተች፤ ሁለት መላእክትም ነጭ ልብስ ለብሰው የጌታችን ቅዱስ ሥጋ ተኝቶበት በነበረው አንዱ በራስጌ ሌላውም በእግርጌ ተቀምጠው አየች። እነርሱም አንቺ ሴት፥ ስለ ምን ታለቅሻለሽ? አሉአት። እርስዋም፦ ጌታዬን ወስደውታል ወዴትም እንዳኖሩት አላውቅም አለቻቸው። ይህንም ብላ ወደ ኋላ ዘወር ስትል ኢየሱስን ቆሞ አየችው፤ ኢየሱስም እንደ ሆነ አላወቀችም። አንቺ ሴት፥ ስለ ምን ታለቅሻለሽ? ማንንስ ትፈልጊያለሽ? አላት። እርስዋም የአትክልት ጠባቂ መስሎአት:- ጌታ ሆይ፥ አንተ ወስደኸው እንደ ሆንህ ወዴት እንዳኖርኸው ንገረኝ እኔም እወስደዋለሁ አለችው። ኢየሱስም፦ ማርያም አላት፤ እርስዋም ዘወር ብላ በዕብራይስጥ ረቡኒ አለችው፤ ትርጓሜውም መምህር ሆይ ማለት ነው። ለደቀመዛሙርቱም መጥታ ጌታችንን እንዳየችው ነገረቻቸው (ዮሐ 20፥11-16)።

በዚያ ቀን ከኢየሩሳሌም ስድሳ ምዕራፍ ያህል ወደሚርቅ ኤማሁስ ወደሚባል መንደር ይሄዱ የነበሩት ሁለቱ ደቀመዛሙርት (ሉቃስና ኒቆዲሞስ) ስለሆነው ሁሉ ሲነጋገሩ ጌታችን ራሱ ቀርቦ ከእነርሱ ጋር ሲሄድ ስለምን እንደሚያወሩ በጠየቃቸው ጊዜ በጥያቄው ተገርመው ስለራሱ ስለጌታችን እንዲህ እያሉ ነገሩት፦ እስራኤልን እንዲቤዥ ያለው እርሱ እንደ ሆነ ተስፋ አድርገን ነበር፤ ደግሞም ከዚህ ሁሉ ጋር ይህ ከሆነ ዛሬ ሦስተኛው ቀን ነው ደግሞም ከእኛ ውስጥ ማልደው ከመቃብሩ ዘንድ የነበሩት አንዳንድ ሴቶች አስገረሙን፤ ሥጋውንም ባጡ ጊዜ ሕያው ነው የሚሉ የመላእክትን ራእይ ደግሞ አየን ሲሉ መጥተው ነበር። ከእኛም ጋር ከነበሩት ወደ መቃብር ሄደው ሴቶች እንደ ተናገሩት ሆኖ አገኙት፥ እርሱን ግን አላዩትም። እርሱም፦ እናንተ የማታስተውሉ ብሎ ከሙሴና ከነቢያት ሁሉ ጀምሮ ስለ እርሱ በመጻሕፍት ሁሉ የተጻፈውን ተርጉሞ ካስተማራቸው በኋላ ከእነርሱም ጋር በቤታቸው በማዕድ ተቀምጦ ሳለ እንጀራውን አንሥቶ ባርኮ በሰጣቸው ጊዜ ዓይናቸው ተከፍቶ አወቁት። በዚያችም ሰዓት ተነሥተው ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፥ አሥራ አንዱና ከእነርሱ ጋር የነበሩትም ጌታ በእውነት ተነሥቶአል ለስምዖንም ታይቶአል እያሉ በአንድነት ተሰብስበው አገኙአቸው። እነርሱም በመንገድ የሆነውን እንጀራውንም በቈረሰ ጊዜ እንዴት እንደ ታወቀላቸው ተረኩላቸው። ሉቃ 24፥13-35። ያም ቀን እርሱም ከሳምንቱ ፊተኛው በመሸ ጊዜ፥ ደቀ መዛሙርቱ ተሰብስበው በነበሩበት፥ አይሁድን ስለ ፈሩ ደጆቹ ተዘግተው ሳሉ፥ በተዘጋ ቤት ኢየሱስ መጣ፤ በመካከላቸውም ቆሞ ሰላም ለእናንተ ይሁን አላቸው። ይህንም ብሎ እጆቹንም ጎኑንም አሳያቸው፤ ደቀ መዛሙርቱም ጌታን ባዩ ጊዜ ደስ አላቸው (ዮሐ 20፥19-20)።

ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልዩ ከሆነች ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በኅቱም ድንግልና ያለ ተፈትሆ ማህፀን እንደተወለደ እንዲሁ በተዘጋ መቃብር ተነሥቷል (ማቴ 28፥2)። ለሐዋርያትም በተዘጋ ቤት ተገልጦ አረጋግቷቸዋል (ዮሐ 20፥19፤20፥26)። በተዘጋ ቤት ሲገባ መንፈስም ያዩ በመሰላቸው ጊዜ እኔ ራሴ እንደ ሆንሁ እጆቼንና እግሮቼን እዩ፤ በእኔ እንደምታዩት፥ መንፈስ ሥጋና አጥንት የለውምና እኔን ዳስሳችሁ እዩ አላቸው። ይህንም ብሎ እጆቹንና እግሮቹን አሳያቸው። እነርሱም ከደስታ የተነሣ ገና ስላላመኑ ሲደነቁ ሳሉ በዚህ አንዳች የሚበላ አላችሁን? አላቸው እነርሱም ከተጠበሰ ዓሣ አንድ ቁራጭ፥ ከማር ወለላም ሰጡት፤ ተቀብሎም በፊታቸው በላ (ሉቃስ 24፥36-43)። እንግዲህ ይሄ ሁሉ የሚያሳየው ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከትንሣኤውም በኋላ በተዋሕዶ የከበረ መሆኑን ነው። ሥጋ ግዙፍ ስለሆነ የተዘጋን ነገር ማለፍ አይችልም፤ መለኮት ደግሞ ረቂቅ ስለሆነ አይዳሰስም፥ አይበላም፥ አይጠጣም እርሱ ግን በተዘጋ ቤት ገብቶ፥ ዳሰውት፥ በልቶ እና ጠጥቶ በተዋሕዶ መነሳቱን ገለጠልን።

የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ

  1. ለዘላለማዊ ሕይወታችን ማረጋገጫ ሆነልን፦ ጌታችን የትንሣኤያችን በኩር ሆኖ በመነሣቱ እኛም ሞተን፥ በስብሰን እንደማንቀር ዳግመኛ እንደምንነሣ በትንሣኤው አረጋገጠልን። የአምላካችን ትንሣኤ እንደእነ አልአዛር ትንሣኤ አይደለም። አልአዛር በሞተ በአራተኛው ቀን ቢነሣም ዳግመኛ ግን ሞቶአል ትንሣኤውም አስነሺ ነበረው፤ የአምላካችን ትንሣኤ ግን ዳግመኛ ሞት አይከተለውም፥ እንደሌሎቹም አስነሺ ሳይፈልግ በራሱ ስልጣን እንደሞተ በራሱ ስልጣን ተነሥቶአል፤ የትንሣኤያችን በኩር ሆኖ ተነሣ ያልነው በዚህ ምክንያት ነው። “ክርስቶስ ከሙታን ተነሥቶ ወደ ፊት እንዳይሞት ሞትም ወደ ፊት እንዳይገዛው እናውቃለንና”( ሮሜ 6፥9)። ክርስትናን ያለ ትንሣኤ ሙታን ማሰብ ከባድ ነው፤ ስለዚህም ነው ትንሣኤውን ካረጋገጡ እና ካመኑ በኋላ ሐዋርያትን ሂዱና አሕዛብን አስተምሩ ያላቸው። “ትንሣኤ ሙታንስ ከሌለ ክርስቶስ አልተነሣማ ክርስቶስም ካልተነሣ እምነታችሁ ከንቱ ናት… ክርስቶስ ላንቀላፉት በኩራት ሆኖ ከሙታን ተነሥቶአል…ሙታንስ ከቶ የማይነሡ ከሆነ እኛስ ዘወትር በሚያስፈራ ኑሮ የምንኖር ስለ ምንድር ነው?” 1ኛ ቆሮ 15፥13-30። ቤተክርስቲያናችንም ይህንን በማሰብ ነው ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታንን ለእምነታችን መሠረት ከሆኑት ከአምስቱ አዕማደ ምሥጢራት ውስጥ ያስገባችው።
  2. በተስፋ እንድንኖር አደረገን፦ ተስፋ የሌለው ሰው ሕይወቱ ጎስቋላ፥ ሐሳቡም ምድራዊ ነው። እኛ ክርስቲያኖች ግን የክርስቶስ ትንሣኤ በሰጠን ተስፋ ዘላለማዊ ሕይወታችንን ከእርሱ ጋር ለመኖር በምድራዊ ሕይወታችን የሚገጥመንን ችግር ሁሉ እያለፍን ዋላ ወደ ውኃ ምንጭ እንደሚናፍቅ እንዲሁ ተስፋ መንግሥተ ሰማያትን ከፊታችን አድርገን እያየን የጽድቅን ሥራ በመሥራት እንኖራለን። ወዳጆቻችን ቢሞቱብን እንኳን ተስፋ እንደሌላቸው አሕዛብ አናዝንም። “ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ተስፋ እንደሌላቸው እንደ ሌሎች ደግሞ እንዳታዝኑ፥ አንቀላፍተው ስላሉቱ ታውቁ ዘንድ እንወዳለን። ኢየሱስ እንደ ሞተና እንደ ተነሣ ካመንን፥ እንዲሁም በኢየሱስ ያንቀላፉቱን እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ያመጣቸዋልና” (1ኛ ተሰ 4፥13-14)።
  3. ነፃነታችንን አስገኘልን፦ አዳም ከነልጆቹ በበደሉ ምክንያት የገነት ደጅ ተዘግቶበት፥ በዲያብሎስ የጭካኔ አገዛዝ ስር ወድቆ፥ ሞት ሠልጥኖበት፥ ነፃነት አጥቶ ለ5500 ዘመን ሲኖር፥ በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ የገነት ደጅ ተከፍቶለት፥ የዲያብሎስ አገዛዙ ተገርስሶ ኃይሉ ደክሞ ከእግሩ በታች ወድቆለት፥ የሞት ስልጣን ተሽሮለት፥ ነፃነትን አግኝቶ የነፃነትን አየር እያጣጣመ “ሞት ሆይ መውጊያህ የት አለ? ሲኦል ሆይ ድል መንሳትህ የት አለ?” እያለ ባርያ አድርገው ይዘውት በነበሩት ሞት እና ሲኦል ላይ ከሠለጠነ እነሆ 1971 ዓመታት ተቆጥረዋል። 1ኛ ቆሮ 15፥55። አባቶች የክርስቶስን ትንሣኤ ሲናገሩ የባቢሎን ሰዎች ያመልኩት የነበረ ዘንዶ ዳንኤል ያዘጋጀለትን መብል በተቀበለ ጊዜ ከሁለት እንደተከፈለ አንዲሁ ሞት የጌታን ሥጋ በዋጠ ጊዜ ድል ተነሣ፤ ጌታም ሕያው ሆኖ ከሙታን ተለይቶ ተነሣ ብለዋል። ዳን 12፥22-26 (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ) ታዲያ የሰጠንን ነጻነት አሳልፈን ሰጥተን ባርነትን በድጋሚ እንደሸማ እንዳንለብስ ቅዱስ ጳውሎስ አስጠንቅቆናል። “በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻነት አወጣን፤ እንግዲህ ጸንታችሁ ቁሙ እንደ ገናም በባርነት ቀንበር አትያዙ።” ገላ 5፥1
  4. ሰላማችንን አስገኘልን፦ በዘመነ ትንሣኤ ክርስቲያኖች ሲገናኙ “ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን … በዐቢይ ኃይል ወስልጣን … አሠሮ ለሰይጣን … አግአዞ ለአዳም … ሰላም … እም ይእዜሰ … ኮነ … ፍስሐ ወሰላም ” እያሉ ሰላም የሚባባሉት በጌታችን ትንሣኤ ያገኘነውን ዘላለማዊ ሰላም ለመመስከር ነው። ጌታችንም ለሐዋርያት ሲገለጥላቸው “ሰላም ለእናንተ ይሁን” ነው ያላቸው። ዮሐ 20፥19። “አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል” (ፊል 4፥7)።
  5. የማይተኛ እረኛ እንዳለን ማረጋገጫ ሆኖናል፦ ሐዋርያት አምላካቸው፥ መምህራቸው እና እረኛቸው ክርስቶስ በጨካኞች አይሁድ ከተያዘ በኋላ በፍርሃት ተውጠው ሳሉ በመካከላቸው ተገኝቶ ተበትነው እንዳይቀሩ ሰላምን ሰብኮላቸው ሞት ድል የማያደርገው እረኛ እንደሆነ አረጋግጦላቸዋል። እንዲያውም ለዘላለም የማይለያቸው እረኛ መሆኑን “እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” ብሎ ብርታት ሆኗቸዋል። ማቴ 28፥20። ”እነሆ፥ እስራኤልን የሚጠብቅ አይተኛም አያንቀላፋምም” (መዝ 121፥4)።

ከላይ በዝርዝር እንዳየነው የጌታችን የሞቱና የትንሣኤው ነገር በሥርዓተ ቤተክርስቲያን መሠረት እንዲህ እንደዛሬው በየዓመቱ ሲታሰብ ይኖራል። ነገር ግን በዓሉን በየዓመቱ ስናከብር በመንፈሳዊ ሕይወታችን ምንም ለውጥ ሳናሳይ እንዲሁ በመብላት እና በመጠጣት ብቻ መሆን የለበትም፤ ይልቁን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ”የክርስቶስ ኢየሱስም የሆኑቱ ሥጋን ከክፉ መሻቱና ከምኞቱ ጋር ሰቀሉ” (ገላ 5፥24) እንዳለው አምላካችንን በትንሣኤው የምንመስለው ኃጢአትን እርም ብለን በመተው በፊተኛው ትንሣኤ በንስሐ፥ በሥጋ ወደሙ ወደ አምላካችን ተመልሰን ጽድቅን ፈጽመን ሁለተኛ ሞት የተባለውን የገሃነም እሳት ፍርድን በምሕረቱ አስወግዶልን መንግስተ ሰማያትን ስንወርስ ነው። “በፊተኛው ትንሣኤ ዕድል ያለው ብፁዕና ቅዱስ ነው፤ ሁለተኛው ሞት በእነርሱ ላይ ሥልጣን የለውም” (ራዕይ 20፥6)። ወደ መምህረ ንስሐዎቻችን ቀርበን ኃጢአታችንን በንስሐ አስወግደን፥ የጽድቅ ሥራ ሠርተን፥ ቅዱስ ሥጋውን በልተን፥ ክቡር ደሙን ጠጥተን፥ የመንግሥቱ ወራሾች፥ የስሙ ቀዳሾች እንዲያደርገን የቅዱሳን አምላክ እግዚአብሔር ይርዳን። “ለኃጢአት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር፥ እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ” (1ኛ ጴጥ 2፥24)።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!