ወወሃብኮሙ ትእምርት ለእለ ይፈርሁከ፣ለሚፈሩህ ምልክትን ሰጠሃቸው (መዝ 59፡4)
በመምህር ሰሎሞን መኩሪያ
መስከረም 16 ቀን 2006 ዓ.ም.
ይህንን የተናገረ ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት ነው፡፡ ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት ከተሰጡት 7ት ሃብታት አንዱ ሃብተ ትንቢት ነው። በዚተሰጠው ሃብተ ትንቢት የራቀው ቀርቦለታል፣ የቀረበው ተከናውኖለታል፣የረቀቀው ጐልቶለታል። ስለዚህም ከእርሱ በፊት የተደረገውን፣ በእርሱ ዘመን የሆነውን፣ ከእርሱም በኋላ እስከ እለተ ምፅአት የሚደረገውን ሁሉ ልዑል እግዚአብሔር ገልፆለት ብዙ ነገር ተንብይዋል። ከትንቢቶቹም መካከል አንዱ የመስቀሉ ነገር ነው፡፡
ቅዱስ መስቀል እንደ እንግዳ ደራሽ እንደ ውሃ ፈሳሽ ሳይሆን ትንቢት ሲነገርለት ምሳሌ ሲመሰልለት የኖረና በኃላም በከበረ በክርስቶስ ደም ተቀድሶ የመለኮት ዙፋን ሆኖ የተመረጠ ለክርስቲያኖች ኃይልና መመኪያ እንዲሁም አጋንንትን ድል መንሻ ነው፡፡
ስለ ቅዱስ መስቀሉ የተመሰለ ምሳሌ
በመጽሐፍ ቅዱስ የተመሰሉ ምሳሌዎች ምስጢራዊ ትርጉም አላቸው። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ቅዱስ ወንጌልን በብዙ ምሳሌ እየመሰለ ለህዝቡ በሚገባቸው መልኩ ያስተምራቸው ነበር፡፡ ከትምህርቱ በኃላም ቅዱሳን ሐዋርያት ለብቻቸው ሲሆኑ ምሳሌውን ተርጉምልን ይሉት ነበር፤ እርሱም ምሳሌውን ይተረጉምላቸው ነበር፡፡ ‹መስማት በሚችሉበት መጠን እነዚህን በሚመስል በብዙ ምሳሌ ቃሉን ነግራቸው፤ ያለምሳሌ ግን አልነገራቸውም። ለብቻቸውም ሲሆኑ ነገሩን ሁሉ ለገዛ ደቀመዛሙርቱ ይፈታላቸው /ይተረጉምላቸው/ ነበር› (ማር 4፡33 , 34) እንዲል;; ለመግቢያ ያህል ስለምሳሌ ይህንን ካልን ስለ ቅዱስ መስቀሉ የተመሰለ ምሳሌ ከብሉይ ኪዳን የሚከተለውን ምሳሌ እንመለከታለን።
ለህዝበ እስራኤል ድህነት የሆነው አርዌ ብርት
እስራኤል ዘሥጋ በግብፅ ምድር ለ430 ዓመት በባርነት ከኖሩ በኋላ በእግዚአብሔር ቸርነት በአባታቸው በእነ አብርሃም ቃል ኪዳን በሙሴ መሪነት በቅዱስ ሚካኤል ተራዳኢነት ባህር ተከፍሎላቸው፣ ጠላት ጠፍቶላቸው፣ መና ከደመና እየወረደላቸው፣ ውሃ ከአለት እየፈለቀላቸው፣ ቀን በአምደ ደመና ሌሊት በአምደ ብርሃን እየተጓዙ በምድረ በዳ 40 ዓመት ኑረዋል፡፡ በጉዟቸውም ላይ ሳሉ በልባቸው እግዚአብሔርን አሙት፤ እንዲህም አሉ ‹አሁን እግዚአብሔር መና አወረድኩላችሁ የሚለን ይህ ያለንበት አካባቢ ደጋ ስለሆነ ውርጭ /ጤዛ/ ያወጣውን ያንን እያረጋ መና አወረድኩላችሁ ይለናል ‹ይክልኑ እግዚአብሔር ስሪአ ማዕድ በገዳም› ‹እግዚአብሔር በምድረ በዳ /በቆላ/ መና ማውረድ ይችላልን? (መዝ 77፡20) አሉ። በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር ሙሴን ህዝቡን ይዘህ ወደ ቆላ አውርዳቸው አለው በዚያም የፈለጉትን ሰጣቸው፤ ነገር ግን የሚበሉት በአፋቸው ሳለ ሁለት መንታ ምላስ ያለው እባብ እየነደፈ ህዝቡን አስጨነቃቸው። በዚህ ጊዜ ህዝቡ ሁሉ ወደ ሙሴ ቀርበው በእግዚአብሔር እና በአንተ ፊት በድለናል፣ እባቦችን ከእኛ ያርቅልን ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ፀልይልን አሉት። ሙሴም ስለ ህዝቡ ወደ እግዚአብሔር ፀለየ። እግዚአብሔርም ፀሎቱን ተቀብሎ ለሙሴ እንዲህ አለው፤ ከጥሩ ናስ እባብን ሰርተህ በዓላማ ላይ ስቀል የተነደፈውም ሁሉ ሲያዩት በህይወት ይኖራል አለው። ሙሴም የናሱን እባብ ሰርቶ በዓላማ ላይ ሰቀለ፣ እባብም የነደፋቸው ሰው ሁሉ የናሱን እባብ ባየ ጊዜ ዳነ፡፡ (ዘኁ 21፡7-9) ይላል፡፡ ይህ እንግዲህ ስለ ቅዱስ መስቀሉ መድኅኒትነት ህይወትነት አስቀድሞ የነበረ ምሳሌ ነው። አባቶቻችን ሊተረጉሙት ሕዝበ እስራኤል የእስራኤል ዘነፍስ የክርስቲያኖች ምሳሌ ናቸው። በምድረ በዳ ያስጨነቃቸው /የነደፋቸው/ መርዘኛዋ እባብ የጥንት ጠላታችን የዲያብሎስ ምሳሌ ነው። እርሱም 5500 ዘመን የሰው ልጆችን በሲኦል እያስጨነቀ ለመኖሩ ምሳሌ ነው። የህዝቡ ሁሉ ጩኽት የአበው ቀደምትን፣ የነቢያትንና የካህናትን ሱባኤ መስዋዕትነት ያመለክታል። እነርሱም በመስዋዕታቸው በሱባኤያቸው እግዚአብሔር እንዲያድናቸው አጥብቀው ለመለመናቸው ምሳሌ ነው፡፡ (ኢሳ 64፡1) ‹ሰማዮችን ቀድደህ ምነው ብትወርድ› እንዲል።እግዚአብሔርም ልመናቸውን ሰምቶ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በህቱም ድንግልና ተፀንሶ, በህቱም ድንግልና ተወልዶ፣ በ30 ዘመኑ ተጠምቆ፣ ዞሮ አስተምሮ፣ በኋላም ስለ ድህነተ ዓለም በመልዕልተ መስቀል ተሰቅሎ ለማዳኑ ምሳሌ ነው። የናሱ እባብ የክርስቶስ ምሳሌ ነው፤ በዚያ መርዝ እንደሌለበት ለእርሱም ክብር ይግባውና ኃጢአት የለበትም። ዓላማውም የመስቀሉ ምሳሌ ነው። ለሙሴ ህዝቡ ሁሉ ሲያየው ይዳን ብሎ ለህዝቡ የሚድኑበትን ምልክት እንደሰጠው ሁሉ በወልድ ውሉደ እግዚአብሔር በክርስቶስ ክርስቲያን የተባሉ ምዕመናንም የክርስቶስን መስቀል ተሳልመው እንዲሚባረኩ ፣ ተማጽነው እንደሚድኑ የእግዚአብሔር ፈቃዱ እንደሆነ የሚያሳይ ምሳሌ ነው። ይህ ምሳሌም እውነተኛ እንደሆነ ጌታችን አምላካችን መድኅኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ወንጌል ሲገልፅ እንዲህ ብሏል ‹ሙሴም በምድረ በዳ እባብን እንደሰቀለ እንዲሁ በእርሱ የማያምን ሁሉ የዘለዓለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ የሰው ልጅ ክርስቶስ ይሰቀል ዘንድ ይገባዋል፡፡› (ዮሐ 3፡14, 15) ብሏል፡፡ እንግዲህ ስለቅዱስ መስቀሉ ከተመሰሉ ብዙ ምሳሌዎች መካከል አንዱን ይህንን ብቻ ወስደን ለትምህርታችን ተመለከትን እንጂ ብዙ ተነግሮለታል፡፡ በመቀጠልም መስቀሉ ለክርስቲያኖች የተሰጠበትን ምክንያት እንመለከታለን፡፡
ሀ. መስቀሉ ለክርስቲያኖች ምልክት ነው
ምልክት መለያ መታወቂያ ነው፡፡ መስቀልም ክርስቲያኖች ከኢ-አማንያን /ከአህዛብ/ የሚለዩበት ከእግዚአብሔር ዘንድ የተሰጠ ምልክት ነው፤ ‹ለሚፈሩህ ምልክትን ሰጠሃቸው› (መዝ59፡4) እንዲል። እስራኤል ዘሥጋ በግብፅ ሳሉ ከቀሳፊ መልአክ እንዲድኑ የበጉን ደም ምልክት በቤታቸው በመቃኑና በመድረኩ እንዲረጩ በእግዚአብሔር ታዘው ነበር፡፡ በዚህም የደም ምልክት ከቀሳፊ መላእክ ተጠብቀዋል፡፡ (ዘፀ 12፡13) ክርስቲያኖችም በክርስቶስ ደም መዳናቸውን የሚያበስር የመስቀሉ ምልክትነት ነው፡፡
ለ. መስቀሉ ለክርስቲያኖች ሃይል ነው
ሃይል መንፈሳዊ ሃይል ሰማያዊ የምናገኝበት ከእግዚአብሔር የተሰጠን ይህ ቅዱስ መስቀሉ ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን ሲገልፅ ‹የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነው› (1ቆሮ 1፡18) ብሏል፡፡ ‹ለሚጠፉት› ብሎ በመስቀሉ ለሚቀጠቀጡ ለአጋንነት አንድም አጋንንት አድሮባቸው በክህደት ለፀኑ ኢ-አማንያን /መናፍቃን/ የመስቀሉ ነገር ሞኝነት ይመስላል፤ ሐይማኖት አፅንተው ምግባር አቅንተው መስቀሉን መጠጊያ ላደረጉ ምዕመናን ግን ኃይል ነው ማለቱ ነው፡፡ ከዚህ ኃይለ ቃል ጋር ቅዱስ ዳዊትም ይተባበራል። (መዝ 43፡5) ‹በአንተ ጠላቶቻችንን እንወጋቸዋለን በስምህም በላያችን የቆሙትን እናዋርዳቸዋልን› ብሏል። እኛም ክርስቶስ በሰጠን በመስቀሉ ኃይል ስመ ሥላሴን በመጥራት ማለትም በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ በማለት በትምህርተ መስቀል በማማተብ በላያችን የቆሙ ማለትም ኃጢአት በማሳሰብና በማሰራት የሚታወቁ አጋንንትን ድል የምንነሳበት በቅዱስ መስቀሉ ኃይል እንደሆነ እንረዳለን፡፡
ሐ. መስቀሉ ለክርስቲያኖች መመኪያ ነው
መስቀል በጥንተ ታሪኩ የእርግማንና የኃጢአት አርማ ሆኖ መቆየቱ ቢታወቅም ዛሬ ግን የክርስቲያኖች መመኪያና አለኝታ መከታና የድል አርማ ነው፡፡
ከክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ (ገላ 6፡14) አይሁድ በመገረዝና ሕግን በመፈፀም ይመካሉ ጳውሎስ ግን በክርስቶስ የመሥዋዕትነት ሥራ ይመካል በእግዚአብሔር ክብር ተስፋ እንመካለን (ሮሜ 5፡2) መከራ ትዕግሥትን እንደሚያደርግ ትዕግሥትም ፈተናን ፈተናም ተስፋን እንደሚያደርግ እያወቅን በመከራቸውን እንመካለን (ሮሜ 5፡3) በማለት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንደተናገረው ዲያብሎስ ድል የተነሣበት እኛም የቀደመ ክብራችንን ያገኘንበት በመሆኑ መስቀል ትምክህታችን ነው፡፡
ባጠቃላይም እናታችን ቤተ ክርስቲያን በዘወትር ጸሎቷ መስቀል ኃይላችን ነው፣ መስቀል ጽንአ ነፍሳችን ነው፣ መስቀል ቤዛችን ነው፣ መስቀል የነፍሳችን መድኃኒት ነው፣ አይሁድ ክደውታል፣ እኛ ግን አመንን፣ ያመንን እኛም በመስቀሉ ኃይል ዳንን ብላ ታስተምረናለች። ይህም የክርስቶስ መስቀል ዘወትር በልብ የሚታሰብ፣ በድርጊት የሚገለጽ በመሆኑ በመስቀሉ ኃይል መድኃኒትን አደረገ ብላ ቤተ ክርስቲያን በዝማሬ ትገልጻለች። ምክንያቱም መስቀል ጥል የተገደለበት ፣ ዲያብሎስ ከመንገድ የተወገደበት ነው;; (ኤፌ 2፡16,ቆላ 2፡14)። ስለዚህ ሰይጣን ይፈራዋል ተሸንፎበታል። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደሙ የዋጀው መስቀል ኃይል ነው። ስለዚህ ነው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነው ያለው (1 ቆሮ 1፡18)፡፡
የሥላሴ ቸርነት፣የእመቤታችን አማላጅነት፣የመስቀሉ በረከት ይደርብን፡፡
አሜን!!!