ሐዊረ ሕይወት በሀገረ ጀርመን ተካሄደ

ጀርመን ቀጣና ማከል

ግንቦት 15 ቀን 2006 ዓ.ም.

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ማኅበረ ቅዱሳን አውሮፓ ማእከል የጀርመን ቀጣና ማከል በአውሮፓ የመጀመሪያውን የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር ከግንቦት 8-10, 2006 በክሩፈልባክህ (Kroeffelbach) በሚገኘው የኮፕቲክ ቅዱስ እንጦንስ ገዳም (Sankt-Antonius Kloster) በደማቅ ሁኔታ አካሄደ። በዚህ ከ80 በላይ ምእመናን  በተሳተፉበት መርሐ ግብር ላይ ሰፊ ትምህርት የተሰጠ ሲሆን በተለይ ነገረ ድኅነት እና መንፈሳዊ አገልግሎት ላይ የተሰጡት ጥልቅ ትምህርቶች ተሳታፊዎች በጉዳዮቹ ላይ የነበራቸውን እውቀት በከፍተኛ ሁኔታ ያሳደጉ እና ታዳሚው ሐዊረ ሕይወት በቅርቡ ይደገምልን የሚል ጥያቄን እንዲሰነዝር ያነሳሱ ነበሩ። በተጨማሪም መዝሙራት በዘማርያንና በሕብረት የቀረቡ ሲሆን ማኅበረ ቅዱሳን በሀገር ቤት ስብከተ ወንጌልን ለማስፋፋት በተለይም በተመረጡ ጠረፍና ገጠር አብያተክርስቲያናት ላይ አቅዶ እያከናወነው ስላለው የስብከት ወንጌል ማስፋፊያ ፕሮግራም ገለጻ ተደርጓል

HH p3

ወደ ጀርመን ሀገር የሚመጡ አዳዲስ ስደተኞችን ከቅድስት ቤተክርስቲያን ለማስኮብለል የሚደረገው የተቀናጀ ዘመቻም ትኩረት ተሰጥቶ ውይይት የተደረገበት ሲሆን ይህንንም ለመከላከል ቀጣና ማከሉ ከሀገረ ስብከቱ፣ ከሌሎች አገልጋዮች እና ከእመናን ጋር በመተባበር የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ከተሳታፊዎች ማሳሰቢያ ተሰጥቷል።

 

Photo Abune

አርብ ምሽት እራት በመብላትና አንድ ትምህርት በመስማት የተጀመረው መርሐ ግብር ቅዳሜ እስከ ምሽቱ 5 ሰዓት ድረስ በትምህርት፣ መዝሙርና ውይይት ከቀጠለ በኋላ ፍጻሜውን ያገኘው እሁድ ከግብፃውያን አባቶች ጋር ቅዳሴ በመሳተፍ ነበር።

በስደት አገር ይህንን የመሰለ ትልቅ ገዳም ሰርተው ይህንን የተሟላ ሊባል የሚችል ማረፊያ ቦታቸውን በነፃ የሰጡን የግብፃውያን ትጋት ለቦታው አዲስ የሆኑ ታዳሚዎችን ያስደመመ ሲሆን የሊቀ ጳጳሱ አቡነ ሚካኤል ደግነትና ትህትናም በቀላሉ የሚረሳ አይሆንም። መርሐ ግብሩ እሁድ ከምሳ በኋላ የተፈጸመ ሲሆን ሁለተኛ የምንገናኘው መቼነው የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ሆኖ ይቆያል

ቀጣና ማእከሉ ለዝግጅቱ መሳካት የተለያዩ ድጋፍ ያደረጉ ምእመናንን፣ በአገልግሎቱ የተሳተፉ መምህራንንና በገዳሙ በነጻ መጠቀም እንድንችል ለፈቀዱልን ለብፁዕ አቡነ ሚካኤል ከፍተኛ ምስጋናውን ያቀርባል