ኒቆዲሞስ

፩ መግቢያ

በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት መሠረት የእምነቱ ተከታዮች ሁሉ እንዲጾሟቸው መጀመሪያቸውና መጨረሻቸው ተቀምሮ ጊዜና ወቅት ተወስኖላቸው የተደነገጉ ሰባት የዐዋጅ አጽዋማት አሉ።

እነዚህም አጽዋማት በሐዋርያት ሲጾሙ የቆዩና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በቀኖና መጻሕፍት የአጿጿም ሥርዓታቸውን የሠሩላቸው ናቸው። ከእነዚህም ሰባት አጽዋማት አንዱና ዋናዉ ዐቢይ ጾም ነው። ይህ ጾም ክብር ምሥጋና ይግባዉና ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተጠመቀ በኋላ ፵ መዓልትና ፵ ሌሊት ከቆመ ሳያርፍ ከዘረጋ ሳያጥፍ በትኅርምት የጾመዉ ጾም በመሆኑ ዐቢይ ተብሏል። ማቴ ፬፥፩። እኛም አምላካችን የጾመዉን ጾም ለማስታወስ፥ በረከቱን ለማግኘት፥ እርሱን አርዓያ አድርገን የሥጋ ፈቃዳችንን ለነፍስ ፈቃዳችን ለማስገዛት እንጾመዋለን። በዚህ ጾም ከተድላና ከደስታ ወገን ማናቸውንም ማድረግ እንዳይገባና ሁሉም ጿሚ ከሥጋዊ ነገር መጠበቅና መጠንቀቅ እንደሚገባዉ ተጽፏል። ዐቢይ ጾም አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ድኅነተ ዓለም የተቀበለዉን መከራ በማሰብ የምናዝንበት፥ በቸርነቱ በሰጠን ኃይል መንፈሳዊ ከሰይጣንና ከፈቃደ ሥጋ ጋር የምንጋደልበት፥ እኛ በበደልን እርሱ ክሦ እንዳዳነን በማዘከር ደግሞ ወደ ኃጢአት ላለመመለስ ቃል የምንገባበት፥ አብነት ሊሆነን ከኖረልን ሕይወትና ከሠራልን ሕግ የምንማርበትና ለቅዱስ ቁርባን የምንዘጋጅበት እጅግ የከበረ ወቅት ነው። እነዚህ የጾም ዕለታት ለሌሎች ጊዜያት ስንቅ የምንይዝባቸውና ተኩላ ከሆነው ሰይጣን የምንጠነቀቅባቸዉ መሆናችዉም በዓመቱ ዉስጥ ከሚኖሩት ቀናት ሁሉ ልዩ ያደርጋቸዋል።

ቅዱስ ያሬድ በጾመ ድጓው በዐቢይ ጾም ለሚገኙት ሰንበታት ሁሉ የተለየ መዝሙር ሠርቶላቸዋል። ሰንበታቱም በመዝሙሩ ስም ዘወረደ፥ ቅድስት፥ ምኩራብ፥ መጻጉዕ፥ ደብረ ዘይት፥ ገብር ኄር፥ ኒቆዲሞስና ሆሳዕና በመባል ይጠራሉ። እነዚህም የዕረፍትና የበረከት ዕለታት በመሆናቸው ከኃጢያት ሥራ ተለይተን በእግዚአብሔር ቃል በጸሎትና በዝማሬ ተግተን ለቅዱስ እግዚአብሔር ምሥጋና የምናቀርብባቸዉ ናቸው። በዚህ ሳምንት የሚገኘው እሑድ ኒቆዲሞስ ይባላል። ስለዚህም በዚህ ጽሑፍ ስለ ኒቆዲሞስ ከብዙው ከፍለን፤ ከረጅሙ አሳጥረን ለማየት እንሞክራለን። እርሱም የዐቢይ ጾም ሰባተኛ ሳምንት ሲሆን በዕለቱ የሚነበበዉ የወንጌል ክፍል ዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ሦስት ነዉ።

፪ ኒቆዲሞስ ማን ነዉ?

ኒቆዲሞስ ቃሉ የግሪክ ሲሆን ድል ማድረግን ወይም አሸናፊነትን ያመለክታል፡: ኒቆዲሞስ ፈሪሳዊ፥ ከአይሁድ አለቆችና መምህራና አንዱ ነው። በወንጌለ ዮሐንስ ምዕራፍ ሦስት ከፈሪሳውያን ወገን የአይሁድ አለቃ የሆነ ኒቆዲሞስ የተባለ አንድ ሰው እንደነበረና እርሱም በሌሊት ወደ ጌታችን መጥቶ እንደተማረ ተጠቅሷል። (ዮሐ ፩-፪) በአይሁድ አለቆች ፊትም ”ሕጋችን አስቀድሞ ሳይሰማ የሠራውንም ሳያውቅ በሰው ይፈርዳልን?” በማለት ስለ መድኃኔዓለም ክርስቶስ የተናገረ እሱ ነው። እነርሱ ግን በክርስቶስ እግዚአብሔርነት ያመኑበት ኦሪትን የማያዉቁ ስሑታን እንደሆኑ ያስቡ ስለ ነበር ”አንተም ደግሞ ከገሊላ ነህን? ከገሊላ ነቢይ እንደማይነሳ መርምርና እይ“ አሉት እንጂ አልተቀበሉትም። ዮሐ ፯፥፵፰-፶፪። ኒቆዲሞስ የአርማትያስ ሰው ከሚሆን ከዮሴፍ ጋር በመሆን የጌታችንን ቅዱስ ሥጋ በንጹሕ በፍታ ገንዞ በአዲስ መቃብር ቀብሯል። ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ”ቀድሞ በሌሊት ወደ ጌታችን ኢየሱስ ሄዶ የነበረዉ ኒቆዲሞስም መጣ፤ ቀብተውም የሚቀበርበትን መቶ ወቄት የከርቤና የሬት ቅልቅል ሽቶ አመጣ።” እንዳለ። ዮሐ ፲፱፥፴፱። በዚህም ኒቆዲሞስ ከምክረ አይሁድ ያልተቀላቀለ መሆኑ ይታወቃል።

፫ ኒቆዲሞስ ወደ ጌታችን በሌሊት የሄደዉ ለምንድነው? ለምን በቀን አልሄደም?

ኒቆዲሞስ በሌሊት ወደ ጌታችን ከሄደባቸው ምክንያቶች አንዱ በቀን መሄድን ስለፈራ ነው። እርሱ ፈሪሳዊ፥ ከአይሁድ አለቆችም አንዱ፥ መምህረ ኦሪትም ስለነበር፤ ፍቁረ እግዚእ ቅዱስ ዮሐንስ “ከሕዝቡ አለቆችም ያመኑበት ብዙዎች ነበሩ፤ ነገር ግን ከምኩራብ አስወጥተው እንዳይሰዱአቸው በፈሪሳውያን ምክንያት አልመሰከሩለትም” በማለት እንደተናገረው አይሁድ ከምኩራብ እንዳያባርሩት ኒቆዲሞስ ወደ ጌታችን በለሊት ሄዷል። ዮሐ ፲፪፥፵፪ ። መድኃኔዓለም ክርስቶስ በአምላክነቱ ይህን ቢያውቅም ኒቆዲሞስ በሌሊት ወደ እርሱ እንዳይመጣ አልከለከለውም። በፍቅር አቅርቦ ስለ ሰማያዊ ምሥጢር በትሕትና አስተማረው እንጂ በቀን ወደ እኔ መምጣት ስለ እኔም ጌትነት መመስከር ፈርተሃልና የኔ ልትሆን አይገባህም ብሎ አልገሠጸዉም።

፬ የኒቆዲሞስ ጥያቄና የጌታችን መልስ

ኒቆዲሞስ “መምህር ሆይ ልታስተምር ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደመጣህ እናውቃለን እግዚአብሔር ከርሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርገውን ይህን ተአምር ሊያደርገ የሚችል የለምና።“ በማለት ተናገረ። (ዮሐ ፫፥፪) በዚህ ጊዜ ጌታችን የገነት በር ስለሆነው ስለ ምስጢረ ጥምቀት አስፍቶና አምልቶ በምሳሌ ጭምር አስረዳው። “እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ዳግመኛ ያልተወለደ ሰው የእግዚአብሔርን መንግሥት ለማየት አይችልም” (ዮሐ ፫፥፫) በማለት መንፈሳዊ እውቀት የጎደለው መሆኑን አሳይቶ ዳግመኛ ያልተወለደ ሰው ከእግዚአብሔር መንግሥት ውጪ እንደሚሆን አስርግጦ ነገረው ። በዚህም ታላቅ ምስጢርን ሊገልጥለት ወደደ። ይህ አነጋገር ከአይሁድ አለቆች አንዱ ለሆነው ፈሪሳዊ ሰው ከባድ ነበር። ስለዚህ ኒቆዲሞስ ምሥጢሩ ቢጸንበት ጌታችንን እንዲህ በማለት ጠየቀው “ሰው ከሸመገለ በኋላ እንደምን ሊወለድ ይችላል? ዳግመኛ ይወለድ ዘንድ ወደ እናቱ ማሕጸን ተመልሶ ሊገባ ይችላልን?“። (ዮሐ ፫፥፬) ጌታችንም ለኒቆዲሞስ መልሶ የአዳም ልጆች ሁሉ ከውና ከመንፈስ ዳግም ካልተወለዱ (በመንፈስ ቅዱስ መታደስን በሚያሰጥ ጥምቀት ካልተጠመቁ) መንግሥተ ሰማያትን መውረስ እንደማይችሉ ነገረው።

የኒቆዲሞስ ጥያቄ ዛሬም ቢሆን በእምነት ያልጎለመሱ ሰዎች ዘንድ የሚነሳ ነው። እንዴት? እንደምን ይሆናል? በዚህ ጥያቄ በአንድ በኩል መጠራጠር አለ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ዳግም ልደት የሚፈጸምበትን ሁኔታ የማወቅ ፍላጎት እንዳለ ያሳያል። ኒቆዲሞስ መንፈሳዊውን ነገር በእርሱ መረዳት መጠን በሥጋዊ ልደት ወስኖ ”እንዴት?“ አለ። ዛሬም ስለ ረቂቅ መንፈሳዊት ልደት ሲነገረው የሚጠራጠርና እንደ ኒቆዲሞስ በሥጋ ልደት አንጻር የሚመለከተው ብዙ ነው። የተመሰገነ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ “ለሥጋዊ ሰው ግን የእግዚአብሔር መንፈስ ነገር ሞኝነት ይመስለዋል አይቀበለውም፤ በመንፈስም የሚመረመር ስለሆነ ሊያውቅ አይችልም።” እንዳለ ኛ ቆሮ ፩፥፲፬። ሰው በመጀመሪያ ከወላጆቹ የሚወለደው የሥጋ ልደት ነው። “ከሥጋ የተወለደም ሥጋ ነው።” ሁለተኛው (ዳግም ልደት) ሰው ከውኃና ከመንፈስ የሚወለደው ነው። በተጨማሪም ቅዱስ ጳውሎስ ከውኃና ከመንፈስ በመወለድ ውሉደ እግዚአብሔር (የእግዚአብሔር ልጆች) እንደምንባል ሲገልጽ “እንደ ምሕረቱ መጠን ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ መታደስ አዳነን።” ብሏል ። ቲቶ ፫፥፭። በመሆኑም ምስጢረ ጥምቀት አንድ ጊዜ ይፈጸማል፤ አይደገምም። እኛ እንድ ጊዜ ከእናታችን የሥጋ ልደት እንዳገኘን ሁሉ ከመንፈስ ቅዱስም አንድ ጊዜ እንወለዳለን።

እንዴት ሰው ከውኃ መወለድ ይቻለዋል? ይባል ይሆናል። ከውኃ ረቂቅ ልጅነትን ተወልዶ መዳን እንደምን ያለ ምስጢር ነው? ይህ ታላቅ ምስጢር (ጥምቀት) በነቢያት ትንቢትና ምሳሌ የተገለጠ ነው። ጌታችንም እከብር አይል ክቡር፥ እቀደስ አይል ቅዱስ አምላክ፥ እታደስ አይል ንጹሐ ባሕርይ የሆነ አምላክ ለእኛ ዳግም ልደት (ሥርዓተ ጥምቀት) ለመመስረት በባርያው በዮሐንስ እጅ ተጠምቋል። ጥምቀትን ለምን በውኃ እንዳደረገ በሰፊው መግለጽ ይቻላል። ሆኖም ግን በጥምቀት መወለድ እንደሚቻል አንጻራዊ በሆነ መልኩ እንደሚከተለው መግለጽ ይቻላል። ሰው ከመሬት አፈር ተፈጥሯል። አፈር አጥንት፥ ጅማት፥ ቆዳ፥ ወዘተ… መሆን እንዴት ቻለ? ልዩ ልዩ መልክዕና ሥራ ያላቸው የሰውነታችን ብልቶች ሳንባ፥ ልብ፣ ጉበት፥ የደም ቧንቧ፥ ጣፊያ፥ ኩላሊት ወዘተ… እንዴት ከመሬት አፈር ተገኙ? ይህ ለፈጣሪ ቀላሉ ነው። እንደዚህም በጥምቀት የሚፈጸመው አገልግሎት ይታያል፥ ልጅነቱ ሲሰጥ ግን አይታይም ረቂቅ ነውና። አለመታየቱ ግን ሊያውከን አይገባም። ነፍሳችን ረቂቅ በመሆኗ አናያትም፥ ነገር ግን ነፍስ እንዳለን እናምናለን። ጌታችንም ለኒቆዲሞስ በነፋስ መስሎ የምስጢረ ጥምቀትን ረቂቅነት አስረድቶታል። የማይታየው ልደትና ሕዳሴ የሚገኘው በጥምቀት ነው።

ጥምቀት ከቤተ ክርስቲያን ምሥጢራት የመጀመሪያ የሆነ ምሥጢር ነው። ያለ ጥምቀት ከሌሎች ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን (ሜሮን፣ ቁርባን ወዘተ…) ተሳታፊ መሆን አይቻልም። ከጥምቀት ውጪ ድኅነት የለም። ማር ፲፮፥፲፮። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንደገለጸው ሥርዓተ ጥምቀት በሚፈጸምበት መካን ቅዱሳን መላእክት በዙሪያው ከበው ይቆማሉ፥ ምስጋና ለፈጣሪያቸው ያቀርባሉ። አብ፥ ወልድ፥ መንፈስ ቅዱስ (ሥላሴ) የጸጋ ልጅነትን ይሰጣሉና። በተጨማሪም ይህ የከበረ ቅዱስ አባት እንደ ነገረን “በዐይን ከሚታየው ይልቅ እግዚአብሔር በማይታበል ቃሉ የነገረንን እንመን። በራሳቸው ሀልዎት ያልነበራቸውን ነገሮች ወደሚኖሩበት ያመጣቸው እርሱ ስለነርሳቸው ባሕርይ (ጠባይዕ) በተናገረ ጊዜ ቃሉ የታመነ ነው። ይህን ሰምቶ ለምን ውኃ የሚል ቢኖር በመጀመሪያ ሰውን ሲፈጥር መሬትን ተጠቅሞ የለምን? ለእግዚአብሔር ያለመሬት ሰውን መፍጠር ይቻለው አልነበረምን?“ እንበለው።

፭ ከጥምቀት ምን ይገኛል?

ከፍ ብሎ እንደ ተመለከትነው ያለጥምቀት ክርስትና የለም። ከቅዱስ እግዚአብሔር ጋር ላለን ግንኙነት ጥምቀት ወሳኝ ነው። በጥምቀት ከምናገኛቸው ነገሮች ለአብነት የሚከተሉትን እንመልከት።

ሀ. በጥምቀት የልጅነትን ጸጋ እናገኛለን

ከላይ በዝርዝር እንደተገለጸው፥ ጌታችን ለኒቆዲሞስ እንዳስተማረው፥ በጥምቀት ዳግም ከእግዚአብሔር እንወለዳለን። ዮሐ ፫፥፮። እንዲሁም ”ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤” ዮሐ ፩፥፲፪ እንዳለ በስሙ አምነው ለተጠመቁ ሁሉ የልጅነት ጸጋ ይሰጣቸዋል።

ለ. በጥምቀት ከክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ጋር እንተባበራለን

ስንጠመቅ ወደ ውኃ መግባታችን (መዘፈቃችን) የሞቱና የመቃብሩ ምሳሌ ሲሆን ከውኃ መውጣታችን ደግሞ የመነሣታችን ምሳሌ ነው። ለእኛ በካህኑ አማካኝነት ወደ መጠመቂያው መዘፈቅና መውጣት ቀላል እንደሆነ ለቅዱስ እግዚአብሔርም አሮጌውን ሰው መቅበርና አዲሱን ሰው ማንሣት ቀላሉ ነው። ይህም በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ሦስት ጊዜ ይፈጸማል። ቅዱስ ጳውሎስ “ሞቱን በሚመስል ሞት ከርሱ ጋር ከተባበርን ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ከርሱ ጋር እንተባበራለን።” እንዲሁም “በጥምቀት ከርሱ ጋር ተቀበራችሁ በጥምቀት ደግሞ ከሙታን ባስነሣው በእግዚአብሔር ሥራ በማመናችሁ ከእርሱ ጋር ትነሣላችሁ።” በማለት በሞቱ ከመሰልነው በትንሣኤው እንደምንመስለው ተናገረ። ሮሜ ፮፥፭፣ ቆላ ፩፥፲፪።

ሐ. በጥምቀት አዲስ ሰው እንሆናለን

በጥምቀት አዲስ ሕይወት እናገኛለን፣ ወደ እግዚአብሔር በአዲስ ተፈጥሮ እንቀርባለን፤ ሥርየተ ኃጢአትንም እናገኛለን። “እንግዲህ ክርስቶስ በአብ ክብር ከሙታን እንደተነሣ እንዲሁ እኛም በአዲስ ሕይወት እንድንመላለስ ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከርሱ ጋር ተቀበርን።” ሮሜ ፮፥፬። “አሁንም በክርስቶስ የሆነው ሁሉ አዲስ ፍጥረት ነው። የቀደመውም አለፈ፤ እነሆ ሁሉም አዲስ ሆነ።” ኛ ቆሮ ፭፥፲፯።

መ. በጥምቀት የሰማያዊ ማኅበር አባል እንሆናለን

በጥምቀት ከጌታችን ከመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር አንድነት ይኖረናል። “ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችኋል።” እንዲል። ገላ ፫፥፳፯። በጥምቀት የቤተ ክርስቲያን አባልነት መብት እናገኛለን። እንዲሁም ከጨለማ ወደ ብርሃን በመሸጋገር ለድኅነታችን ለምንጀምረው ተጋድሎ ኃይል የምናገኘው በጥምቀት ነው።

እንግዲህ በጥምቀት የሚገኘውን ጸጋና በረከት በማወቅ ልጆቻችንን ማስጠመቅና በሃይማኖት በምግባር ኮትኩቶ ማሳደግ፣ ከእምነት ውጪ የሆኑ ወገኖቻችንን ሁሉ በማስተማር የቤተ ክርስቲያን አባል የሚሆኑበትን መብት እንዲያገኙ ማድረግ ከሁላችን የሚጠበቅ ነው። እምነትን (ሃይማኖትን) በሥራ መግለጥ ያስፈልጋል። ኒቆዲሞስ ወደ ጌታችን ሄዶ እንደተማረ እኛም ወደ መምህራን በመሄድ መጠየቅና ማወቅ በተማሩትና በተረዱትም መጽናት ያስፈልገናል። ጥምቀት አንድ ምዕራፍ ነው። ከጥምቀት በኋላ ሌሎችን ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን መፈጸምና በሕገ እግዚአብሔር መኖር ይገባል። በጥምቀት ያገኙትን ልጅነት ማዳፈን አይገባም። ከጥምቀት በኋላ የተፈጸመን ኃጢያት ደግሞ ወደ አባቶቻችን ካህናት በመቅረብ መናዘዝ እና ከክፉ ስራ መከልከል ይገባል።

በሕገ እግዚአብሔር ጸንተን፣ ምግባር ትሩፋት ሠርተን “እናንተ የአባቴ ቡሩካን ኑ!” ከሚባሉት እንዲደምረን ሁሉ በእርሱ፥ ሁሉ ከእርሱና ሁሉ ስለእርሱ የሆነ አምላከ ቅዱሳን ኢየሱስ ክርስቶስ ፈቃዱ ይሁንልን። የእናታችን የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም የእናትነት ፍቅር፥ ርኅራኄና አማላጅነት አይለየን። አሜን።