ልዩ መርሐ ግብር በእንግሊዝ አገር፣ ሊድስ ከተማ

 

መስከረም  18 ቀን 2006 ዓ.ም.

በሰሜን ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት የሊድስ ደብረ ስብሐት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን እና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ማኅበረ ቅዱሳን ትብብር ገቢው ለአብነት ት/ቤቶች መርጃ የሚውል ልዩ መርሐ ግብር ሊዘጋጅ ነው።

”በእንተ ስማ ለማርያም” በሚል መሪ ቃል የተሰየመው ይህ መርሐ ግብር ቅዳሜ መስከረም ፳፭ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም (5 Oct 2013) እንደሚካሄድ ከዝግጅቱ አስተባባሪዎች የተገለጸ ሲሆን መርሐ ግብሩም በሊድስ ደብረ ስብሐት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ከቅዳሴ አገልግሎት በኋላ እንደሚካሄድ ለመረዳት ተችሏል።

በመርሐ ግብሩም ትምህርተ ወንጌል፣ ያሬዳዊ ዝማሬዎች፣ መንፈሳዊ ተውኔት፣የሕጻናት ጭውውቶች፣ እንዲሁም ጨረታና የገንዘብ ልገሳ መርሐ ግብራት የተካተቱበት ሲሆን በተለይም ”ስለ ገዳማት እና አብነት ትምህርት ቤቶች ምንነት፤ ስላሉባቸው ፈተናዎች እንዲሁም ከእኛስ ምን ይጠበቃል” በሚሉ ጉዳዮች ዙሪያ ሰፋ ያሉ ውይይቶች ከተሳታፊ ምዕመናን ጋር እንደሚደረጉ ተገልጿል።

የሊድስ ደብረ ስብሐት መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ መልአከ ገነት ቀሲስ ከፍያለው አስቻለውን ጨምሮ ካህናት አባቶችና ምዕመናን እንዲሁም ከሊድስ ከተማ አጎራባች ከተሞች የሚገኙ ካህናት አባቶች እና በርካታ ምዕመናን ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የሊድስ ደብረ ስብሐት መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ መልአከ ገነት ቀሲስ ከፍያለው አስቻለው ዝግጅቱን አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ የመርሐ ግብሩን ምንነት እና አስፈላጊነት እንዲሁም ለአብነት ትምህርት ቤቶች ተጠናክሮ መቀጠል ያለውን ጠቀሜታ በመግለጽ ምዕመናን በዚህ መርሐ ግብር ላይ በእለቱ ተገኝተው እንደ ቤተ ክርስቲያን ልጅነታቸው የሚጠበቅባቸውን ድርሻ መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ከዚህ በፊት ”በእንተ ስማ ለማርያም” በሚል ተመሳሳይ መርሐ ግብራት በኢትዮጵያ እና ከኢትዮጵያ ውጪ ባሉ በተወሰኑ ሀገራት ተዘጋጅተው ለአብነት ትምህርት ቤቶቹ በመጠኑም ቢሆን አብነት ሊሆን የሚችል ስራ መስራት እንደ ተቻለ ሁሉ ከዚህም መርሐ ግብር ጥሩ ውጤት እንደሚገኝ ተስፋ ይደረጋል።

ወስብሐት  ለእግዚአብሔር