ማኅበረ ቅዱሳን ማን ነው?
ማኅበረ ቅዱሳን ማን ነው? እንዴትስ ተመሠረተ?
ማኅበረ ቅዱሳን ማን ነው? እንዴትስ ተመሠረተ የሚለውን ጥያቄ ከመመለሳችን በፊት አጽራረ ቤተክርስቲያንና ዓላማቸውን ለማስፈጸም የሚንቀሳቀሱት ተላላኪዎቻቸው የውስጥ ዐርበኞች ማኅበረ ቅዱሳንን በሰው ውስጥ የጥላቻ መንፈስ እንዲያድር ከሚጣጣሩበት መንገድ አንዱ ማኅበሩ የሚጠራበትን ስያሜውን በማዛባት ነው የሚጀምሩት፡፡ ከዚህ አንጻር ማኅበረ ቅዱሳን ሲባል ምን ማለት ነው? የሚለውን ነገር ማብራራት ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ስያሜው ላይ አጭር ትንታኔ በመስጠት ወደ ማንነቱና አመሠራረቱ እንለፍ፡፡
የማኅበሩ ስያሜ
አንዳንድ ሰዎች ስያሜውም ግራ ያጋባቸዋል፡፡ ከላይ እንደጠቀስነው አባላቱ ለራሳቸው ያወጡት አስመስለው የሚነግሯቸው ሰዎች አሉና የዋሀኑ ግራ ቢጋቡ አያስደንቅም፡፡ ነገር ግን የማኅበሩ ስያሜ እኩያኑ ማኅበሩን ለማጥላላት ከሚጠቀሙት ፕሮጋንዳ በእጅጉ የተለየ ነው፡፡ ማኅበረ ሚካኤል «የሚካኤሎች ስብስብ»፣ ማኅበረ ማርያምም «የማርያሞች ስብስብ» ካልሆነ /እንዳልሆነ/ ማኅበረ ቅዱሳንም «የቅዱሳን ሰብስብ» አይደለም፣ ሊሆን አይችልም፤ ወይም ማኅበረ ጊዮርጊስን የመሠረቱ ሰዎች ራሳቸውን «ጊዮርጊሶች»ነን እንደማይሉት፤ እንዳልሆኑትም፣ ማኅበረ ቅዱሳንም ቅዱሳን ነን የሚሉ ሰዎች ስብስብ አይደለም፡፡ ይልቁንም ማኅበረ ማካኤል የሊቀ መላእክት የቅዱስ ሚካኤል አማላጅነት፣ ተራዳኢነት የሚታሰብበት ማኅበር እንደሆነው ሁሉ ማኅበረ ቅዱሳንም የቤተክርስቲያኒቱን ትምህርተ ሃይማኖትና ሥርዐት ከመጠበቅና ከማስተማር በተጨማሪ በቤተ ክርስቲያኒቱ ትምህርተ ሃይማኖት መሠረት የቅዱሳን ጻድቃንና ሰማዕታት እንዲሁም የቅዱሳን መላእክት ክብ ራቸው፤ ገድላቸውና ትሩፋታቸው፣ አማላጅነታቸውና በረከታቸው፤ በሰፊው እንዲታወቅና ትውልዱም የዚህ ተጠቃሚ እንዲሆን ትምህርት የሚሰጡበት ማኅበር ነው፡፡ ምእመናን በነዚህ ቅዱሳን አማላጅነትና ረድኤት እየታገዙ ለመንግሥተ ሰማያት እንዲበቁ ማድረግም ቀዳሚ ተግባሩ ነው፡፡
ከዚህ የተነሣ የእነዚያ ብዙ ማኅበራት ኅብረት የሆነው ማኅበር የነቢያት፣ የሐዋርያት፣ ጻድቃን ሰማዕታትና የቅዱሳን መላእከት ሁሉ መታሰቢያ ይሆን ዘንድ ማኅበረ ቅዱሳን ተባለ፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን እንዴትስ ተመሠረተ?
ዘመኑ የኮምዩኒዝም ርዕዮተ ዓለምና አስተሳሰብ የሰፈነበት፤ ስመ እግዚአብሔርን መጥራት አስቸጋሪ የሆነበትና ወደ ቤተ እግዚአብሔር መሔድ እንደ ኋላቀርነት የሚቆጠርበት ዘመን ነበር 1977 ዓ.ም፡፡
በተለይም በየከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ /ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች/ በሚገኙ ተማሪዎች ዘንድ ቃለ እግዚአብሔርን በግልጽ መነጋገርም ሆነ መሰማት የማይታሰብበት ወቅት ነው፡፡
ቀደም ባሉት ጊዜያት በተለይም በንጉሠ ነገሥት ዐፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት በዩኒቨርሲቲና ኮሌጆች እንዲያስተምሩ ከምዕራባውያኑ ሀገሮች መጥተው የነበሩ ሚሲዮናውያን የኑፋቄ ትምህርታቸውን ያሠራጩ የነበረውም በእነዚሁ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ነው፡፡
በዚህ ሁኔታ ትውልዱ በየአቅጣጫው በሚሲዮናውያኑ የኑፋቄ ትምህርት እንዲሁም በኮምዩኒዝም ርዕተ ዓለምና አስተሳሰብ እየተነጠቀ ከኦርቶዶከሳዊት ተዋሕዶ እምነት የኮበለለበት ከቤተክርስቲያን የራቀበት ዘመን ነበር፡፡
በዚህ ጊዜ ነው፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስድስት ኪሎ ዋናው ግቢ ከፍተኛ ትምህርታቸውን ይከታተሉ የነበሩ አምስት ወጣቶች ፈቃደ እግዚአብሔር ሆኖ በቅዱስ ገብርኤል ስም ተሰባስበው ጽዋ መጠጣት የጀመሩት፡፡ ይህ መንፈሳዊ እንቅስቀሴ በዚሁ ተወስኖ አልቀረም፡፡ በየሳምንቱ እሑድ በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ቤተክርስቲያን ግቢ በመጠለያ ሥር እየተሰባሰቡ በተደራጀ መልክ ባይሆንም መንፈሳዊ ትምህርት ይማሩ ጀመር፡፡ ከዚያም በምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም ተምሮ ማስተማር ሰንበት ትምህርት ቤት አዳራሽ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን መንፈሳዊ ትምህርት መማር ቀጠሉ፡፡
እንዲህ የተጀመረው መንፈሳዊ እንቅስቃሴ በሌሎች ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሚገኙ የቤተክርስቲያን ልጆች ዘንድ የተዳረሰበት አጋጣሚና ሁኔታ የተፈጠረው ደግሞ በዚሁ በ1977 ዓ.ም ነው፡፡ በወቅቱ በነበረው የመንግሥት ሠፈራ ፕሮግራም በሀገሪቱ ውስጥ ያሉት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች በሙሉ በመንደር ምሥረታና መልሶ ማቋቋም ዘመቻ ወደ ጋምቤላ፣ መተከል እና ፓዌ እንዲዘምቱ ተደረገ፡፡ በዘመቻው ወቅት ከተለያዩ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እየመጡ የተገናኙት የቤተክርስቲያን ልጆች ቃለ እግዚአብሔርን በመማር፣ በማኅበር ጸሎት በማድረግ እና ስለቤተክርስቲያን ጉዳይ በመወያየት ጊዜውን ተጠቀሙበት፡፡