ማኅበረ ቅዱሳን ማን ነው?

ማኅበረ ቅዱሳን ማን ነው? ምንስ እየሠራ ነው?

 

የተዛባ አመለካከት የማይጋርደው ገሐድ እውነታ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሊቃውንት ብራና ዳምጠው፤ ቀለም በጥብጠው፣ ብዕር ቀርጸው በየአብያተ ክርስቲያናቱ የመቃብር ቤቶች ውስጥ በማስተማር ትውልዱ የሀገር መሪ፣ የቤተክርስቲያን አለኝታ፣ የእግዚአብሔር ቅን አገልጋይ እንዲሆን ያበረከቱት አገልግሎት ከዘመን ዘመን እየተሸጋገረ ለትውልድ ሲተላለፍ የኖረና የሚኖር ነው፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ለሀገራችን ሥልጣኔ በር ከፋች ሆና የኖረች ከመሆኗም በላይ ዛሬ ላለው ዘመናዊ ሥልጣኔም መሠረት የጣለች ባለውለታ ናት፡፡ ቀደምት የቤተክርስቲያን አበው ደከመን፣ ሰለቸን ሳይሉ ዐረፍተ ዘመን እስከገታቸው ድረስ ሲያገለግሉ ኖረው ቤተክርስቲያኒቱ አሁን ከምትገኝበት የዕድገት ደረጃ አድርሰዋታል፡፡ በዚህ ዘመንም የሚገኙ የቤተክርስቲያኒቱ ልጆች ሁሉ

ይህን ከአበው የተማሩትን ሃይማኖትና ሥርዓት ጠብቀውና አስጠብቀው ለሚመጣው ትውልድ የማቆየት ሓላፊነት ያለባቸው መሆኑ ግልጽ ነው፡፡

በመሆኑም ይሔንን አባቶች ወዛቸውን አንጠፍጥፈው፣ ዐይናቸውን አፍዘው፣ ደማቸውን አፍስሰውና አጥንታቸውን ከስክሰው በሰማዕትነትና በተጋድሎ ያቆዩትን ሃይማኖት ለማስጠበቅና ለቀጣዩም ትውልድ በተመቻቸ ሁኔታ ለማስተላለፍ በእግዚአብሔር ፈቃድ በቅዱስ ሲኖዶስ ሙሉ ድጋፍና ዕውቅና የተመሠረተው ማኅበረ ቅዱሳን በውጪ በአጽራረ ቤተክርስቲያንና በአሕዛብ፣ በውስጥ ዓላማውን ባልተረዱ፣ ዓላማውን ተረድተው የኑፋቄ ትምህርታቸውን እንደልብ በቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ ለማስረግ ሌት ተቀን በሚተጉ አንዳንድ ግለሰቦችና ቡድኖች ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ እየተከሰሰ እየተወቀሰና ያለ ስሙ ስም እየተሰጠው ይገኛል፡፡

እነዚህ በውስጥና በውጭ የሚገኙት የቤተክርስቲያን ጠላቶች ቤተክርስቲያን ላይ በየዘመኑ በሚነሳው ፈተና እየተጠቀሙና በምክንያት እየተሳቡ ለቤተክርስቲያን ወዳጅ መስለው እየቀረቡና እያስቀረቡ ማኅበረ ቅዱሳንን ቢቻላቸው እንዲፈርስ፣ ባይቻላቸው ደግሞ የቤተክርስቲያኒቱን ሥርዓት ለማፍረስ በገንዘብ፣ በቁሳቁስ የሚያስታጥቋቸው መናፍቃን ሴራና ዓላማ እንዳይጋለጥ እና በቤተክርስቲያኒቱ ላይ እንደፈለጋቸው እንዲሆኑ ማኅበሩ አገልግሎቱ ተገድቦ እንዲዋቀር ለማስደረግና ለማድረግ የጥፋት ዘመቻዎችን በመክፈት ላይ ናቸው፡፡

እነዚህ የቤተክርስቲያን ጠላት ወዳጆች በማኅበረ ቅዱሳን ላይ ጊዜ በሰጣቸው ጊዜ ሁሉ በመጠቀም ማኅበሩን ለማሳጣትና ለማጥላላት የሚጠቀሙባቸው ስልቶች በርካቶች ናቸው፡፡

ከብዙ በጥቂቱ ለመጥቀስ ያህል «ማኅበረ ቅዱሳን ሲኖዶስ ከሰጠው ደንብና መመሪያ ውጪ እየሠራ የሚገኝ፣ ፖለቲካዊ ዓላማ ያለውና ገቢና ወጪው የማይታወቅ ማኅብረ» እንደሆነ አድርገው» ሚያናፍሱት አሉባልታ ከብዙ በጥቂቱ የሚጠቀስ ነው፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን ግን ባለፉት 17 ዓመታት እነዚህ የውስጥና የውጪ የቤተክርስቲያን ጠላቶች በየጊዜው ማኅበሩ ላይ የሚያናፍሱትን ወሬ ችላ በማለት ከወሬ ሥራ ይቀድማል በማለት ከቅዱስ ሲኖዶስ የተቀበለውን ዓላማ በዓይን በሚታይ፣ በእጅ በሚዳሰስ መልኩ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ ነገር ግን «ውሸት ሲደጋገም እውነት ይመስላል» እንዲሉ ማኅበረ ቅዱሳን ማን ነው? እንዴትስ ተመሠረተ? ዓላማውስ ምንድን ነው? ቅዱስ ሲኖዶስ የሰጠውን ሓላፊነት እንዴት እየተወጣ ነው? ለ17 ዓመታትስ ምን ሠራ? የሚሉትን ጥያቄዎት በስፋት ማቅረቡ አስፈላጊ መሆኑን ለምእመናን መግለጽ ግድ ብሎናል፡፡