በሀገረ ጀርመን በርሊን ከተማ የቅዱስ አማኑኤል ቤተ ክርስቲያን ቅዳሴ ቤት ተከበረ
ግንቦት 26 ቀን 2007 ዓ.ም.
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የደቡብ፣ምስራቅና ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት የበርሊን ቅዱስ አማኑኤል ቤተ ክርስቲያን የተገዛው ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ቅዳሴ ቤት ግንቦት 23 ቀን 2007 ዓ.ም ተከበረ፡፡
በጀርመን መናገሻ ከተማ በርሊን የሚገኘውና በምእመናኑ ትጋት የተገዛው ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ እምነት መሠረት የከበረው በብፁዕ አቡነ ሙሴ የደቡብ፣ምስራቅና ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በተመራ ሥርዓተ ጸሎት ነው፡፡ ግንቦት 23 ቀን 2007 ዓ.ም በተከበረው ቅዳሴ ቤት በሀገረ ጀርመንና አካባቢው የሚገኙ በርካታ ካህናትና ምእመናን እንደተገኙ ተመልክቷል፡፡
በከፍተኛ መንፈሳዊ ሥርዓትና ሐሴት ቅዳሴ ቤቱ የተከበረው ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን በአጠቃላይ 1329 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው ሲኾን ከቤተ መቅደሱ በተጨማሪ፣ መሰብሰቢያ አዳራሽ፣ የካህናት ቤትና ለእንግዶች ማረፊያ የሚኾኑ የተለያዩ ክፍሎች እንዳሉት የአጥቢያው አስተዳዳሪ ሕንፃው ይገዛ ዘንድ ሐሳቡን ለምእመናን ከማቅረብ ጀምሮ ከፍተኛ ጥበብና ፍቅር የተሞላበት አባታዊ የማስተባበር ሥራ የሠሩት መልአከ ገነት አባ ብርሃነ መስቀል ተድላ በበዓሉ ላይ ባቀረቡት ሪፖርት ገልጸዋል፡፡ በከተማው ከሚኖሩት ምእመናን አልፎ በመላ ጀርመን የሚገኙ ምእመናን በከፍተኛ ሁኔታ ተባብረው የገዙት ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን የራሱ ቅጽርና አስራ ሰባት መኪናዎችን የሚያቆም ቦታ እንዳለውም መልአከ ገነት አባ ብርሃነ መስቀል አክለው ገልጸዋል፡፡
በእግዚአብሔር አጋዥነትና በምእመናኑ ኅብረት የተገዛው ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ከቤተ መቅደሱ አገልግሎት ባለፈ ልዩ ልዩ መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎቶችንና ሥልጠናዎችን ለመስጠት፣ በሀገሩ ለተወለዱ ትውልደ ኢትዮጵያ ሕጻናትም መደበኛ የቋንቋና የሃይማኖት ትምህርት ለማስተማር፣ ስለ ኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ለማድረግ ለሚፈልጉ የሚያገለግል ቤተ መጽሐፍና ሥልጠና ማእከል ማቋቋም የሚያስችል እንደኾነ ተገልጿል፡፡
የበርሊኑ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን የተሳካ አጠቃላይ የግዥ ሒደትና ፍጻሜ በዝርወት የሚኖሩ ምእመናን በፍቅርና በስምምነት የሚመራቸው ካገኙ፣ እነሱም ጥቃቅን ልዩነቶቻቸውን ወደጎን ትተው ለጋራ ተጠቃሚነት አብረው ከቆሙ፤ እናት ቤተ ክርስቲያን የምትደሰትባቸው፣ እግዚአብሔርም በባዕድ ምድር የሚመሰገንባቸውና የሚከብርባቸው፣ በስደት ሀገራቸው በረከትን የሚያገኙባቸው፣ ከእግዚአብሔር መንገድ የራቁና ከትእዛዙ የተራቆቱ ነፍሳትን የሚማርኩባቸው ሥራዎችን መሥራት እንደሚችሉ ያስመሰከረ እንደኾነ በበዓሉ ሲሰጡ ከነበሩ የምእመናንና ካህናት አስተያየቶች ለመረዳት ተችሏል፡፡
የበርሊንና አካባቢው ምእመናን ያሳዩት ውጤት በተመሳሳይ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ለመግዛት እንቅስቃሴ ላይ ላሉት የሐምቡርግ፣ ካስል፣ ሙኒክና ሌሎች ምእመናን ጥሩ ትምህርት የሰጠና መነቃቃትን የፈጠረ ነው ተብሏል፡፡