በፓሪስ የደ/ም/ቅ/ማርያም ቤተክርስቲያን የምሥረታ በዓል ብጹዕ አቡነ ዮሴፍ በተገኙበት ተከበረ

በፈረንሳይ ግንኙነት ጣቢያ

ግንቦት 27 ቀን 2007 ዓ.ም.

በፈረንሳይ ሀገር የመጀመሪያ የሆነችው በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የደ/ም/ቅ/ማርያም ቤ/ክ ፲ኛ ዓመት የምሥረታ ክብረ በዓል እና የንግሥ በዓል ከግንቦት ፳፩ እስከ ፳፫ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. በድምቀት ተከበረ። በመጀመሪያ ጥቂት ምእመናን በእመቤታችን በቅድስት ማርያም ሥም በጽዋ ማኀበር ተሰባስበው ለብዙ ዓመታት ከቆዩ በኋላ በ፲፱፻፺፯ ዓ.ም. ግንቦት ወር በወቅቱ የአውሮፓ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በነበሩት አቡነ ዮሴፍ መልካም ፍቃድ ደብረ ምጥማቅ ቅድስት ማርያም በመባል ቤተክርስቲያኗ ተመሠረተች፡፡

paris-10-1

በዚህ የምሥረታ በዓልም ከላይ በተጠቀሱት ዕለታት ልዩ የሕዝብ ጉባኤ ተካሂዷል፡፡ በመርሐ ግብሩም ብጹዕ አቡነ ዮሴፍ የባሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል እንዲሁም መጋቤ ሐዲስ እሸቱ ዓለማየሁ በመምህርነት ከኢትዮጵያ ተጋብዘው አገልግሎት ሰጥተዋል፡፡ በተጨማሪም ከተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት በተለይም ከሆላንድና ከቤልጄም ካህናትና ምእመናን ተግኝተዋል ።

በዓርብ መርሐ ግብር መጋቤ ሐዲስ እሸቱ ዓለማየሁ «ሰው» በሚል ርእስ ሰፊ ትምህርት ሰጥተዋል፡፡ በመልአከ ሕይወት ቆሞስ አባ ዘድንግል ኑርበገን በፓሪስ የመካነ ሕይወት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ አስተዳዳሪ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን በቤተክርስቲያን አገልግሎት ያላቸውን ከፍተኛ ድርሻ እና የማይተካ ሚና በተመለከተ ትምህርት ሰጥተዋል ። አባ ዘድንግል ቤተ ክርስቲያኗ ስትመሰረት ታቦተ ማርያምን ከማምጣት ጀምሮ የመጀመሪያው አስተዳዳሪና መሥራች አገልጋይ በመሆን ለአራት ዓመታት አገልግለዋል፡፡ ቀጣዩን አራት ዓመታትም መልአከ ጽዮን አባ ወልደ ትንሣኤ ጫኔ የቤተክርስቲያኗ አስተዳዳሪ ሆነው ማገልገላቸው ይታወሳል ።

ቅዳሜ እለት በነበረውም የምሽት መርሐ ግብር ስብከተ ወንጌል እና መዝሙር በሰንበት ተማሪዎችና ዲያቆናት የቀረበ ሲሆን የጥያቄና መልስ መርሐ ግብርም ተካሂዷል። በመጨረሻም ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ ዘመኑ ስለሚጠይቀው ሰማዕትነት እና ስለ ሰማዕታተ ሊቢያ ትምህርት ሰጥተው የእለቱ መርሐ ግብር ፍጻሜ ሆኗል፡፡

paris-10-2

በእለተ እሑድ ከቅዳሴ በኋላም የተለያዩ መርሐ ግብራት የተካሄዱ ሲሆን ቤተክርስቲያኗ ስላላት ካፒታል እና ሕንጻ ቤተክርስቲያን ለመግዛት ስለሚደረገው እንቅስቃሴ ለሕዝቡ የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ሕይወት ፍስሐ ድንበሩ ገለጻ አድርገዋል፡፡ ቀሲስ ዶክተር መዝገቡ የቤልጄም አቡነ ተክለሃይማኖት ቤ/ክ አስተዳዳሪ እንድንገለገልበት ቤተክርስቲያን በውሰት የሰጡንን አካላት በማመስገን ለነገ በዘላቂነት የራሳችን ሕንጻ ቤተክርስቲያን እንደሚያስፈልግ እና ምእመናን የውዴታ ግዴታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል። በመጨረሻም ታቦተ ሕጉ ከመንበረ ክብሩ ወጥቶ በቤተክርስቲያኗ ዑደት ካደረገ በኋላ በብጹዕ አቡነ ዮሴፍ ቡራኬ እና ቃለ ምእዳን ሠርሆተ ሕዝብ ተደርጓል።