ቤተ ክርስቲያንና የፓትርያርክ ምርጫ
በዲ/ን ብርሃኑ አድማስ
ቤተ ክርስቲያን አንዲት፣ ቅድስት፣ ኩላዊትና ሐዋርያዊት መሆኗን ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያን ሁሉ ይቀበላሉ፤ በመሠረተ እምነታቸው ውስጥም አካትተው በጸሎትና በአስተምህሮ ይጠቀሙበታል፡፡የዚህ መሠረታዊ ምክንያቱ ደግሞ ከዘመነ ሐዋርያት ጀምሮ ይህ ትምህርት ቢኖርም ነገር ግን መልእክቱን በአግባቡ ካለመረዳት የተነሣ እነ አርዮስና መቅዶንዮስ በትውፊት ከሐዋርያት ጀምሮ የመጣውን የቅዱሳት መጻሕፍት ትርጓሜ መሠረት መቀበልን ቸል ብለው በራሳቸው መንገድ ሔደው ስለሳቱ በጉባኤ ኒቅያ በማያሻማ መንገድ ቤተ ክርስቲያን አንዲት፣ቅድስት፣ ሐዋርያዊት እና ኩላዊት መሆኗን አስቀመጡ፡፡ በኋላ በጉባኤ ቁስጥንጥንያ ደግሞ ሁላችንም እንድንጸልይበት በተዘጋጀው አንቀጸ ሃይማኖት ላይ (ጸሎተ ሃይማኖት) ‹‹ ወነአምን በአሐቲ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንተ ላዕለ ኩሉ ጉባኤ ዘሐዋርያት›› የሚለው የጸሎታችን መፈጸሚያ እንዲሆን ተደነገገ፡፡ በዚህም መሠረት እነዚህን ዓለም አቀፍ ጉባኤያት የሚቀበሉ ሁሉ የሚቀበሉትና የሚመሩበት መሠረታዊ ትምህርተ ሃይማኖት /doctrine/ ሆነ፡፡