እንደተናገረ ተነሥቷል (ማቴ28፥5)
እንኳን ለጌታችን፣ ለአምላካችንና ለመድኃኔታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ ትንሣኤ በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን።
በአባ ወልደትንሣኤ ጫኔ
ሚያዚያ 26፣ 2005ዓ.ም.
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ በከብቶች በረት ከተወለደበት ሰዓት ጀምሮ ለሰው ልጅ ድህነት ሲል ጽኑ መከራና ስቃይን ተቀብሏል። በተለይ በመጨረሻው ሰዓት ከሰው ልጅ አዕምሮ በላይ የሆነ ስቃይ፣ መከራ፣ እንግልትና ግርፋትን ተቀብሎ፤ በጲላጦስ ካለበደሉ ከወንበዴዎች ጋር ተፈርዶበት፤ በቀራንዮ አደባባይ በዕለተ አርብ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ፤ ነፍሱን በፈቃዱ ሰጥቶ አዳምንና ዘሩን ከሞት ወደ ሕይወት፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን መልሶ በሦስተኛው ቀን መቃብር ክፈቱልኝ፣ መግነዝ ፍቱልኝ ሳይል ብርሃንን ተጎናጽፎ በታላቅ ኃይልና ስልጣን በክብር ተነስቷል።
“እነሆም የጌታ መልአክ ከሰማይ ወረደ፣ ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፣ እናንተስ አትፍሩ የተሰቀለውን ኢየሱስን እንድትሹ አውቃለሁና። እንደ ተናገረው ተነስቷልና በዚህ የለም ኑና እዩ አላቸው።” (ማቴ 28፥5)። የጌታ መልአክ ለእናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አምላክን እንደምትወልድ እንዳበሰራት ሁሉ እነሆ ጌታም ሞቶ በተቀበረ በሦስተኛው ቀን የትንሣኤውን ብስራት በሌሊት ወደ መቃብሩ ስፍራ ለመጡ የገሊላ ሰዎች ተናገረ። ስለ አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ አስቀድመው ነቢያት በትንቢታቸው ተንብየዋል። ራሱ ጌታችንም በዘመነ ሥጋዌው በምሳሌ አስተምሯል። በመጨረሻም እንደተናገረ በተግባር ከመቃብር ተነስቷል። ሐዋርያት በስብከታቸው እና በመጽሐፋቸው ስለ ትንሣኤው ምስክርነት በመስጠት አረጋግጠው አስፍተውና አምልተው አስተምረዋል፤ ጽፈዋል። (ማቴ 28፣ ማር 16፣ ሉቃ 24፣ ዮሐ 20)። ነገር ግን ስለ ጌታችን ትንሣኤ በቅዱሳት መጻሕፍትም ሆነ ጌታችን ራሱ በትምህርቱ ግልጽ አድርጎ ቢናገርም ሰዱቃውያንና ሌሎች ብዙ ሰዎች ለማመን ያዳግታቸው ነበር። ከሐዋርያትም መካከል የሆነው ቅዱስ ቶማስ እንኳ ጌታችን በዝግ ቤት ሰላም ለእናንተ ይሁን ብሎ የተወጋውን ጎኑን አሳይቶ በክብር መነሣቱን እስከሚያረጋግጥለት ድረስ የጌታችንን ትንሣኤ ለማመን እንደተቸገረ ቅዱስ መጽሐፍ ይነግረናል። በተጨማሪም የጌታን ትንሣኤ እና ትንሣኤ ሙታንን በአጠቃላይ ለመቀበል የተቸገሩ ብዙዎች እንደነበሩ ከቅዱሳት መጻሕፍት እንረዳለን።
ለአብነት ያክልም የሚከተሉትን እንመልከት:-
ክርስቶስ ስለትንሣኤው ለሐዋርያት በምሳሌ “ይህንንን ቤተ መቅደስ አፍርሱት በሦስተኛው ቀን አስነሣዋለሁ” (ዮሐ 2፥19)። ብሎ ቢነግራቸውም እነርሱ ግን የተረዱትና ያመኑት ከትንሣኤው በኋላ ነበር። በሌላም ስፍራ ጌታችን በሚያስተምርበት ጊዜ ትንሣኤ ሙታን የለም የሚሉ ሰዱቃውያን ጌታችንን ምላሽ ለማሳጣትና የእነርሱን የውሸት ትምህርት ይደግፍልናል የሚሉትን ጥያቄ እየጠየቁ ጌታችንን ይፈታተኑት ነበር። (ማቴ 22፥23-33)። ዛሬም እንደሰዱቃውያን ትንሣኤ ሙታንን የማያምኑ ሰዎች የራሳቸውን የክህደት ትምህርት የሚደግፉላቸውን የተለያዩ ትምህርቶችን በማዘጋጀት የሚያስተምሩና የሚጽፉ ብዙ ናቸው። ከዚህም የተነሳ የመጨረሻው የፍርድ ቀን ደርሶ ራሳቸው ተነሥተው በክርስቶስ የፍርድ ዙፋን እስከሚቆሙ ድርስ በአለማመን ጸንተው የሚኖሩ ብዙ ሰዎች አሉ። “አንተ ግን በተማርህበትና በተረዳህበት ነገር ጸንተህ ኑር፥ ከማን እንደ ተማርከው ታውቃለህና።” (2ኛ ጢሞ 3፥14)። ብሎ ቅዱስ ጳውሎስ ለመንፈስ ልጁ ለጢሞቴዎስ እንደ ተናገረው እኛም ከማን እንደተማርነው እናውቃለንና የጌታን ትንሣኤ በፍጹም ልብ አምነን ለእኛ ትንሣኤ መዘጋጀት ይገባናል።
ከላይ እንደጠቀስነው ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስም የተቸነከሩትን እጆቹንና እግሮቹን፣ በጦር የተውጋውን ጎኑን ካላየሁ፣ ካልዳሰስሁ የክርስቶስን መነሣት አላምንም ብሎ ነበር። ነገር ግን ጌታችን በዝግ ቤት ተገልጾ የተወጋ ጎኑን፣ የተቸነከሩ እጆቹን እና እግሮቹን በአይኖቹ እንዲያይ፤ በእጆቹም እንዲዳስስ አድርጎ ትንሣኤውን አረጋግጦለታል (ዮሐ 20፥24)። እኛ ክርስቲያኖች የቅዱስ ቶማስን ዓይኖች ዓይኖቻችን አድርገን፤ የእርሱን ጆሮዎች ጆሮቻችን አድረገን፤ የእርሱን እጆች እጆቻችን አድርገን ትንሣኤውን በፍጹም ልባችን አምነን መኖር ይገባናል። እንዲሁም ጌታችን ለቶማስ ሳያዩ የሚያምኑ ብጹዓን ናቸው ብሎ እንደ ተናገረ እኛም ትንሣኤውን በመንፈስ የተረዳን ሁሉ ከትንሣኤው ብርሃን በረከትን ለማግኘት የጌታችንን ትንሣኤ ላልተረዱ ሁሉ እነርሱም እንደኛ የትንሣኤውን ብርሃን እንዲያዩ ልንመሰክርላቸው ይገባል።
ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ትንሣኤ በአቴና ከተማ ሲያስተምር ትምህርቱን ባለመረዳት እንዳፌዙበት ሁሉ በአሁኑም ወቅት የሙታን ትንሣኤ ሲነገር የሚቀልዱና የሚዘብቱ ብዙዎች አሉ። (የሐዋ 17፥32)። ቅዱስ ጳውሎስ የአቴና ሰዎችን ከአምልኮተ ጣኦት ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር እንዲመለሱ፣ በጌታችን ትንሣኤ አምነው በትንሣኤው ክብርን እንዲወርሱ ቢያስተምራቸውም ብዙዎቹ ግን ድኅነትን ከመፈለግ ይልቅ ፌዝን መረጡ። ቅዱስ ጳውሎስ “ለእውነት እንዳትታዘዙ አዚም ያደረገባችሁ ማን ነው?” (ገላ 3፥1)። ብሎ እንደ ተናገረው ዛሬም የትንሣኤውን እውነት መስማትም ሆነ መናገር የማይፈልጉ ተረፈ ሰዱቃውያን አሉ፤ ወደፊትም ይኖራሉ። እንደነዚህ ስላሉት ሰዎች ቅዱስ ጴጥሮስም በመጨረሻው በዚህ ዘመን ብዙዎች ዘባቾች እንደሚመጡና ‘ሰማይና ምድር ያልፋል፤ ጌታ ይመጣል፤ ትንሣኤ ሙታን ይደረጋል፤ ያላችሁት የት አለ?’ እያሉ የሚክዱና የሚያስክዱ ሰዎች እንደሚመጡ አስቀድሞ ነግሮናል። (2ኛ ጴጥ 3፥1-18)። እንዲሁም ጌታችን በወንጌሉ “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ” (ዮሐ 11፥25)። ብሎ የሰበከውን ህያው ቃል ያልተገነዘቡ የቅዱስ ጴጥሮስንና የቅዱስ ጳውሎስን ትምህርት እንዳቃለሉና እንዳፌዙ ሁሉ ዛሬም በዘመናችን ስለትንሣኤ ሙታን፣ ስለ ዘላለማዊ ህይወት ሲነገራቸውና ሲሰበክላቸው የማያምኑ ብዙ ሰዎች መኖራቸው እንግዳ ነገር እንዳልሆነ ልንገነዘብ ይገባናል። እኛ ግን ይልቁንም ቅዱሳት መጻፍትን በማንበብና ሊቃውንተ ቤተክርስቲያንን በመጠየቅ ይበልጥ ስለትንሣኤ ልንረዳና በመጨረሻው ስዓት የክብር ትንሣኤ ባለቤት እንድንሆን መትጋት ይኖርብናል። በትንሣኤ የምናምንም የማያምኑም ለፍርድ መነሣታችን አይቀርምና።
ቅዱስ መጽሐፍ የጌታችንንና የሰው ልጆችን ሁሉ ትንሣኤ በምሳሌና በግልጽ ይነግረናል:-
ሀ. በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር ለነቢዩ ሕዝቅኤል ስለትንሣኤ ሙታን ትንቢት እንዲናገር አዝዞታል “….ጌታ እግዚአብሔር ለእነዚህ አጥንቶች እንዲህ ይላል። እነሆ፥ ትንፋሽን አገባባችኋለሁ በሕይወትም ትኖራላችሁ። ጅማትም እሰጣችኋለሁ ሥጋንም አወጣባችኋለሁ በእናንተም ላይ ቁርበትን እዘረጋለሁ ትንፋሽንም አገባባችኋለሁ በሕይወትም ትኖራላችሁ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ። እንዳዘዘኝም ትንቢት ተናገርሁ ስናገርም ድምፅ ሆነ፥ እነሆም፥ መናወጥ ሆነ፥ አጥንቶችም አጥንት ከአጥንት ጋር ተቀራረቡ። እኔም አየሁ፥ እነሆም፥ ጅማት ነበረባቸው ሥጋም ወጣ ቁርበትም በላያቸው ተዘረጋ፥ ትንፋሽ ግን አልነበረባቸውም። እርሱም፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ ትንቢት ተናገር፥ ለነፋስ ትንቢት ተናገር፥ ለነፋስም። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ነፋስ ሆይ፥ ከአራቱ ነፋሳት ዘንድ ና፥ እነዚህም የተገደሉት በሕይወት ይኖሩ ዘንድ እፍ በልባቸው በል አለኝ። እንዳዘዘኝም ትንቢት ተናገርሁ፥ ትንፋሽም ገባባቸው ሕያዋንም ሆኑ፥ እጅግም ታላቅ ሠራዊት ሆነው በእግራቸው ቆሙ።” (ሕዝ 37፥1-10)። በማለት የሙታንን ትንሣኤ በትንቢት መነጽር ተመልክቶ እንዲህ በግልጽ አስረድቶናል። በተጨማሪ የትንሣኤን መኖር የሚያስረዱ በብሉይ ኪዳን በቅዱሳን ነቢያት የተፈጸሙ ተአምራት ሌሎች ማስረጃዎች ናቸው። ነቢዩ ኤልያስ ያስነሣው የመበለቲቱ ልጅ (1ኛነገ 17፥17-24)፣ ነቢዩ ኤልሳዕ ከሞቱ እስቀድሞ የሱናማዊቱን ልጅ (2ኛ ነገ 4፥32-37)፣ ከሞተ በኋላ ደግሞ በአጽሙ ሙት ማስነሣቱ (2ኛ ነገ 13፥20-21) እንደ አብነት ሊጠቀሱ ይችላሉ።።
ለ. በሐዲስ ኪዳን በግልጽ የትንሣኤን ምንነት ያስረገጠልን ትልቁና ዋናው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ መነሣቱ ነው። ክርስቶስ እንደሞተና እንደተነሣ የሰው ዘር በሙሉ ጻድቅ ይሁን ኃጥዕሁሉም ሞቶ እንደሚነሣ አረጋግጦልናል።
ሐ. እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የአዳም ዘር ናትና በተወለደች በ64 ዓመቷ ጥር 21 ቀን ከዚህ ዓለም በክብር ዐርፋለች። ሐዋርያት ሥጋዋን በክብር ሊያሳርፉ ወደ ጌቴ ሰማኒ ይዘዋት ሲሄዱ አይሁድ ለምቀኝነት አያርፉምና እርሷም እንደልጇ ተነሣች ዐረገች እያሉ ስለሚያውኩን ሥጋዋን እናቃጥል ብለው ተነሱ። የተወደደው ልጇ የአይሁድን ክፋትና ተንኮል ተመልክቶ ዮሐንስን ለምስክርነት ጨምሮ በገነት በዕፀ ሕይወት ሥር አኑሯታል። ሐዋርያትም የእናታችንን ሁኔታ ዮሐንስ አይቶ እኛ ሳናይ ብለው ከነሐሴ 1 እስከ 14 ሱባኤ ገቡ። በ14ተኛው ቀን ይቀብሯት ዘንድ አምጥቶ ሰጣቸው። ነሐሴ 16 ቀን በዕለተ ማክሰኞ ቅዱስ ቶማስ አልነበረምና ደመና ጠቅሶ ከሀገረ ስብከቱ ሲመጣ ስታርግ አገኛት፤ ቀድሞ የልጅሽን ትንሣኤ ሳላይ አሁን ደግሞ ያንችን ትንሣኤ ሳላይ ቀረሁ ብሎ አዘነ። እርሷም ሌሎች ትንሣኤዬንና ዕርገቴን አላዩም አንተ ግን አይተሃል፤ ለሌሎችም ትናገር ዘንድ ሰበኔ (የተገነዘችበትን ጨርቅ) ለምስክርነት ይሁንህ ብላ ሰጥታው አርጋለች። ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት “አቤቱ ወደረፍትህ ተነስ አንተና የመቅደስህ ታቦት” (መዝ 131፥10)፤ “በወርቅ ልብስ ተጎናጽፋ ንግስቲቱ በቀኚህ ትቆማለች” (መዝ 44፥9)፤ ብሎ እንደተናገረው እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እንደ ልጇ ትንሣኤ ተነስታለች።
መ. ቅዱስ ጳውሎስ በስንዴ ቅንጣት ምሳሌ ትንሣኤን አስረድቶናል (1ኛ ቆሮ 15፥35-41)። የምንዘራቸው የተለያዩ አዝርዕት በምድር ከተዘሩ (ከተቀበሩ)፣ከበሰበሱ በኋላ በቅለውና (ተነሥተው) በዝተው እንደሚታዩ በአርያውና በአምሳሉ የተፈጠረ የሰው ልጅ የትንሣኤ ባለቤት እንደሚሆን ከቅዱስ ጳውሎስትምህርት መገንዘብ ይቻላል። ይህም አፈር ትቢያ ሁነን በምድር እንደማንቀርና ትንሣኤ ሙታን እንዳለን ያስረዳናል። ስንዴ ዘርተን በቆሎ፣ ገብስ ዘርተን ጤፍ እንደማይሆን ሁሉ ያለምንም መቀያየር እያንዳንዱ ሰው የራሱን አዲስ አካል ይዞ ይነሣል እንጂ መለዋወጥ አይኖርም።
ስለ ሙታን አነሣስም በነቢዩ ሕዝቅኤል ትንቢት እንደተነገረ ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግም በቅዳሴው ላይ ሦስት ጊዜ መለከት እንደሚነፋ አብራርቶ አስቀምጦታል። በመጀመሪያው መለከት አፈር ትቢያ ሁኖ በየቦታው የተበታተነው የሰው አካል የራስ ቅል በፈረሰበት ቦታ ይሰበሰባል፤ በሁለተኛው መለከት የተሰበሰበው የሰው ልጅ አካልሙሉ የሰውነት ክፍሎቹ ተሟልተውለት ፍጹም በድን ይሆናል፤ በሦስተኛው መለከት ፍጹም ትንሣኤውን አግኝቶ በክርስቶስ ፊት ለፍርድ ይቀርባል። በመጨረሻም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጻድቃንን በቀኙ ኃጥአንን በግራው አቁሞ ፍርዱን ይሰጣል፤ ጻድቃን የዘላለም ሕይወትን አግኝተው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሲገቡ፣ ኃጥአን ግን ወደ ዘለዓለም ስቃይ ይሰናበታሉ። (ማቴ 25)።
በአጠቃላይ አምላካችን እግዚአብሔር ስለ ትንሣኤ ሙታን በተለያዩ ምሳሌዎች፣ ግልጽ ትምህርቶችና ማስረጃዎች ነግሮናል። በመሆኑም የትንሣኤ ሙታንን ምሥጢር ተረድተን በክርስቲያናዊ ምግባር መኖር አለብን።
‘እንደተናገረ ተነሥቷል’ ብሎ የእግዚአብሔር መልአክ የጌታችንን ትንሣኤ እንዳበሰረን እኛም ትንሣኤውን ስናከብር:-
- የትንሣኤውን የምሥራች ላልተረዱ ወገኖች ትንሣኤውን በማብሰር፣ በምንኖርበት በስደት ዓለም በብቸኝነት የሚኖሩትን እህቶቻችንና ወንድሞቻችንን በማሰብና አብረን በጌታችን ትንሣኤ እንድንደሰት በማድረግ፣ አለማዊነቱና የምራዕቡ ዓለም ባህል በዓላትን ከማክበርና መንፈሳዊ ደስታን እንዳያገኙ መሰናክል እንዳይሆንባቸው በመምከር፣ እና ደስታችን መንፈሳዊነቱን ለቆ ወደ ዓለማዊ ደስታ እንዳይቀየር በማድረግ መሆን አለበት።
- በኋላ ስንነሣ በጌታችን ፊት እንዳናፍር በትዕዛዙና በሕጉ ጸንተን ጌታችን “ሥጋዬን የሚበላ ደሜን የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው፣ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ” (ዮሐ 6፥54)። እንዳለ የክብር ትንሣኤ አግኝተን ከምርጦቹ ጋር በቀኙ እንዲያቆመን የጌታችንን ትንሣኤ ስናከብር ንስሐ ገብተን፣ ቅዱስ ሥጋውን እና ክቡር ደሙን በመቀበል ለክብር ትንሣኤ ተዘጋጅተን ሊሆን ይገባል።
በንስሐ ታጥበን ሥጋውና ደሙን ተቀብለን፣ ተዘጋጅተን እንድንኖር የአምላካችን ቸርነት የወላዲተ አምላክ የድንግል ማርያም አማላ ጅነት አይለየን፤ አሜን!