ኢትዮጵያዊዉ ጃንደረባ
በዓለም የክርስትና ታሪክ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ቀዳሚውን ስፍራ የያዘችና ሐዋርያዊት ለመሆንዋ ምስክር ከሚሆኑ ታላላቅ የቤተ ክርስቲያን አባቶች መካከል ባኮስ ቀዳማዊ ነው። ኢትዮጵያውያን ከዘመነ ብሉይ ጀምሮ ሕዝበ እግዚአብሔር ከሚባሉ እስራኤል ጋር በአምልኮተ እግዚአብሔር የሚኖሩ ሕዝብ ስለመሆናቸው ቅዱስ መጽሐፍ ይመሰክራል። አያሌ የታሪክ መዛግብትና የአርኪዮሎጂ ምርምር ውጤቶችም ይህንን እውነት ያረጋግጣሉ። እኛም በዚህ የቅዱሳን ታሪክ ዓምድ፣ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ”በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሰወር አይቻላትም” ማቴ፭፥፲፬ እንዳለ፤ በረከቱና አርአያነቱ ለትውልድ ይተርፋል በማለት የኢትዮጵያዊውን ጃንደረባ ታሪክ ይዘን ቀርበናል። የቅዱሳን አማላጅነትና በረከት ከሁላችን ጋር ይሁን፤ አሜን።
ከጥንት ዘመን ጀምሮ ኢትዮጵያውያን እንደ እስራኤላውያን ልማድ በየዓመቱ ለበዓለ ፋሲካ ወደ ኢየሩሳሌም ይወጡ ነበር።ጃንደረባውም ወደ ኢየሩሳሌም ሊሰግድ የመጣው ይህን የአባቶች ሥርዓት መሠረት በማድረግ ነው። የዚያ ዘመን ጉዞ ከኢትዮጵያ ወደ ኢየሩሳሌም ለመድረስ ፬ሺ/፵፻ ማይልስ መጓዝን ግድ ይል ነበር። የኢትዮጵያ ንግሥት የሕንደኬ የገንዘብዋ ሁሉ ኃላፊ (በጅሮንድ) የነበረ ይህ ባኮስ የፋሲካን በዓል አክብሮ ወደ ሀገሩ ሲመለስ፣ የበረሃው ሙቀት ሳያሰቅቀው በሠረገላው ውስጥ ሆኖ የነቢዩ የኢሳይያስን መጽሐፍ ያነብ ነበር። ይህም ኢትዮጵያውያን መቼም ቢሆን ከእግዚአብሔር መለየት የማይወዱና የነቢያትን መጻሕፍት የሚከተሉ እንደነበሩ የሚያሳይ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምስክር ነው ሐዋ፰፥፳፮-፴፰።
በወቅቱ ጃንደረባው የሚያነበው የትንቢት ቃል ምስጢሩ ስለረቀቀበት የተሠወረውን መግለጥ ልማዱ የሆነው እግዚአብሔር ሐዋርያው ፊልጶስን ለጃንደረባው ላከለት። ፊልጶስም “እንደ በግ ወደ መታረድ ተነዳ፣ የበግ ጠቦትም በሸላቹ ፊት ዝም እንደሚል እንዲሁ አፉን አልከፈተም። በውርደቱ ፍርዱ ተወገደ። ሕይወቱ ከምድር ተወግዳለችና። ትውሉዱንስ ማን ይናገራል።” ኢሳ፶፫፥፯ የሚለውን የትንቢት ቃል አሰምቶ ሲያነብ አገኘው። ”በውኑ የምታነበውን ታስተውለዋለህን?” ሲልም ጠየቀው። ጃንደረባውም በተለመደው የኢትዮጵያውያን ትሕትና “የሚመራኝ ሳይኖር ይህ እንዴት ይቻለኛል?” ሲል መለሰለት። ወደ ሠረገላው እንዲወጣና አብሮት እንዲቀመጥም ፊልጶስን ጋበዘው።
ፊልጶስ ከመነሻ እስከ መድረሻ ዘርዝሮ ወንጌልን ሰበከለት። ጃንደረባውም አመነ። ወደ ወንዝ በደረሱም ጊዜ ጃንደረባው እነሆ በውኃ እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ማን ነው? ሲል ጠየቀ፤ ፊልጶስም “በፍጹም ልብህ ብታምን ተፈቅዶልሃል” አለው። በዘመኑ ለብዙዎች ለማመን ያስቸገራቸውን ንጹህ እምነት ያዘ ፤ “ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ አምናለሁ” ሲልም መሠከረ። ከኢየሩሳሌም ፳ ማይልስ ርቀት ላይ ከምትገኘው፣ በቤተ ሳሮን እና በኬብሮን መካከል ካለው ኮረብታ ሥር ከምትመነጨው ወንዝ ሲደርሱም አጠመቀው።
በአንዳንድ የጥንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥራዞች “ከተጠመቀ በኋላ መንፈስ ቅዱስ በላዩ ወረደ” የሚል ሐረግ ተጽፏል። /Lives of the most Eminent Fathers of the church P. 87/ ቅዱስ ጄሮም (የሮም) የተባለው አባት “የኢትዮጵያ ሐዋርያ” በማለት ይጠራዋል። ጃንደረባው ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሰ በኋላ የወንጌልን ቃል በማስተማሩ፤ አስቀድማ ንግሥት ሕንደኬ፣ በኋላም የቤተመንግሥቱ ሰዎች ተጠመቁ። ከአክሱም ቀጥሎ ወደ የመን ከዚያም አልፎ ወደ ፐርሽያ ተጓዘ። በእነዚህም ሀገሮች ወንጌልን ከሰበከ በኋላ ወደ ሕንድ ተሻገረ የመጨረሻ ሀገረ ስብከቱ ጥንት ታፕሮባና /Taprobona/ ዛሬ ሲሎን የምትባለው ደሴት ናት። በዚያም ወንጌልን ሲያስተምር ቆይቶ በአረማውያን እጅ በሰማዕትነት ዐረፈ። የቅዱስ ባኮስ አማላጅነትና በረከት ከሁላችን ጋር ይሁን፤ አሜን።