ሀገረ ስብከቱ የመጀመርያውን ሥልጠና ሰጠ

በጀርመን ቀጣና ማዕከል

መጋቢት 4 ቀን 2007 ዓ.ም.

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የደቡብ፣ ደቡብ ምሥራቅና ደቡብ ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት በአይነቱ ልዩ የሆነ እና የሰበካ ጉባዔ አባላትን አቅም ለማሳደግ የታለመ ሥልጠና በሀገረ ጀርመን በፍራንክፈርት ዙርያ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ መቀመጫ በሆነው በሩሰልስሀይም ከተማ የካቲት ፳፰ ቀን ፳፻፯ዓ.ም ሰጠ::

dicesec training2ሥልጠና መርሐግብሩን በጸሎትና በቡራኬ የከፈቱት ብፁዕ አቡኑ ሙሴ የሀገረ ስብከቱ ሊቀጳጳስ ሲሆኑ የስልጠናውን ወቅታዊነት እና አስፈላጊነት አበክረው ተናግረዋል:: በመቀጠልም የሀገረ ስብከቱ ጸሐፊና የስልጠናው ዋና አስተባባሪ የሆኑት መጋቤ ምሥጢር ኅሩይ ኤርሚያስ የእለቱን መርሐግብር በዝርዝር በማስተዋወቅ እና ጥሪውን አክብረው የመጡ ሰልጣኞችን በማመስገን ስልጠናውን አስጀምረዋል::

በተያዘለት ሰዓት መሠረት የመጀመሪያው ርዕስ ሆነውን “የሰበካ ጉባኤ አመሰራረትና አጠቃላይ የአስተዳደር መዋቅር” የሚለውን ሥልጠና የሰጡት ሊቀ ብርሃናት አባ ገብረ ሕይወት ፍሥሐ በጀርመን ሙኒክ የደብረ ብስራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ ሲሆኑ የቤተክርስቲያናችንን አስተዳደርና አወቃቀር ሰፋ ባለ እና አጥጋቢ በሆነ መልኩ አቅርበዋል::

dicesec training1በመቀጠልም ከሻይ እረፍት በኋላ ከፈረንሳይ በመጡት በመልአከ ሕይወት አባ ዘድንግል ኑርበገን በፓሪስ የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ አማካኝነት “የሂሳብ አያያዝና የገንዘብ አሰባሰብ ገቢና ወጪ ሥርዓትና ደንብ” በሚል ርዕስ ሰፊ እና ቁልፍ ጉዳዮችን ያስጨበጠ ሥልጠና የተሰጠ ሲሆን “የምእመናን እና ንዋየተ ቅድሳት ምዝገባ፣ ቆጠራና ሪፖርት” የሚል ሥልጠናም በቀሲስ ግሩም ታየ ቀርቧል።

ለምሳ በተደረገው እረፍት የሁሉም ተሳታፊዎች ጭውውት ትምህርቱን በተመለከተ መሆኑ የሚሰጡት ትምህርቶች ጠቃሚ እና አጓጊ እንደነበሩ አንዱ ማሳያ ሊሆን ይችላል። ከምሳ በኋላ በፈረንሳይ ፓሪስ ከተማ የደብረ ምጥማቅ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ በሆኑት በመልአከ ሕይወት ቀሲስ ፍሥሐ ድንበሩ የቀረበው “የአገልግሎትና አስተዳደር ሥራ አፈጻጸም” ሁሉንም ከላይ የተነሱትን ርእሶች በሚያዳብርና በሚያጠናክር መልኩ የቀረበ ሲሆን ለተነሱ ጥያቄዎችም መልስ እየሰጠ ያልፍ ነበር::

የመጨረሻው ርእስ “የሰንበት ትምህርት ቤቶችና የጽዋ ማኅበራት አደረጃጀት እና ሚና” የሚል ሲሆን የቀረበው በዲያቆን ዶክተር ያብባል መሉዓለም በማኅበረ ቅዱሳን የጀርመን ቀጣና ማዕከል ሰብሳቢ ነበር። ከዚህ በመቀጠል የነበረው መርሐግበር ውይይት ሲሆን በተደረጉት ገለጻዎች ላይ ተሳታፊዎቹ ያሏቸውን ጥያቄዎች አቅርበው ሰፊ ማብራሪያ በብፁዕ አቡኑ ሙሴ እና በሌሎች አባቶች ተሰጥቷቸዋል:: ተሳታፊዎቹ በሰጡት አስተያየት ስልጠናው ስለ ቤተክርስቲያናችን አወቃቀርና አደረጃጀት ያላወቅነውን ያወቅንበት እና ያላስተዋልነውን ያስተዋልንበት ነው ያሉ ሲሆን በተለይም ደግሞ ብጹዕ አባታችን በመካከላችን በመገኘት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ የጠመመውን በማቅናት በመዋላቸው ፍጹም ደስተኞች ነን ብለዋል።

ብፁዕ አቡኑ ሙሴ “አሐተ ሰአልክዎ ለእግዚአብሔር ወኪያሃ አኀሥሥ ከመ አሀድር ቤቶ ለእግዚአብሔር በኵሉ መዋዕለ ሕይወትየ – እግዚአብሔርን አንዲት ነገር ለመንሁት ፤ እርሷንም እሻለሁ፤ በሕይወቴ ዘመን ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት እኖር ዘንድ” (መዝ፳፮፥ ፬) በሚል ርዕስ ተነስተው ያስተማሩ ሲሆን የቤተ ክርስቲያን ልጆች ባንድ ላይ ተሰባስበው ሲማማሩ እና ሲወያዩ መዋላቸው ለቤተክርስቲያን እድገት እና መስፋፋት እጅግ ጠቃሚ በመሆኑ በጣም ደስ መሰኘታቸውን ገልጸዋል። በመጨረሻም ብፁዕነታቸው ለዚህ ጉባኤ መሳካት አስተዋጽዎ ያደረጉትን፣ ስልጠናውን ያስተባበሩትን፣ ያስተማሩትን፣ ጥሪውን አክብረው በሥልጠናው የተሳተፉትን እንዲሁም በመስተንግዶ ያገለገሉትን የሮሰልሳይምና ራውንሃይም አካባቢ ነዋሪ ምእመናንን አመስግነው መርሐግበሩን በጸሎት ዘግተዋል::

በዚህ ስልጠና ላይ ከ ፵ በላይ ሰልጣኞች የተሳተፉ ሲሆን በጀርመን ሀገር ከሚገኙ ፲፪ አብያተክርስቲያናት ውስጥ የ፱ኙ አብያተክርስቲያናት አስተዳዳሪዎችና የሰበካ ጉባዔ አመራር አባላት እንደተገኙ ታውቋል።