በጀርመን ሀምቡርግ ከተማ ዐውደ ርእይ ተካሄደ

በጀርመን ቀጣና ማእከል

ሰኔ 3 ቀን 2007 ዓ.ም.

በጀርመን ሀገር በሀምቡርግ ከተማ ግንቦት ፳፱ እና ፴ ፳፻፯ ዓ.ም. ”ለሁለንተናዊ የቤተክርስቲያን እድገት የድርሻችንን እንወጣ” በሚል መሪ ቃል የዐውደ ርእይ እና የስብከተ ወንጌል መርሐግብር ተካሄደ። ዐውደ ርእዩን በማኅበረ ቅዱሳን የአውሮፓ ማእከል ከሀምቡርግ ደብረ መድኃኒት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ሲሆን መርሐግብሩን የከፈቱት የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ገነት ቆሞስ አባ ብርሃነ መስቀል ተድላ ናቸው።

Hamburg-2

 

ዐውደ ርእዩ ”ፍኖተ ቤተክርስቲያን”፣ ”ገዳማት እና የአብነት ትምህርት ቤቶች” እንዲሁም ”ማኅበረ ቅዱሳን” የሚሉ ሦስት ትዕይንቶች ነበሩት። በተለይም የኢትዮጵያ ገዳማትና የአብነት ትምህርት ቤቶች ለእምነት፣ ለትውፊት፣ ለታሪክ፣ ለዕውቀት እና ለባሕል መጠበቅ እንዲሁም ከትውልድ ወደ ትውልድ መሸጋገር ያበረከቱትና እያበረከቱት ያለው አስተዋጽኦ እና አሁን ያሉባቸው ወቅታዊ ችግሮቻቸው ከማኅበረ ቅዱሳን ዋናው ማእከል በመጡ ልዑካን በሰፊው ተገልጿል። ከዐውደ ርእዩ በተጨማሪም ከማኅበረ ቅዱሳን ዋናው ማእከል የመጡት መምህር ዲ/ን ዶ/ር ቴዎድሮስ በለጠ በሁለቱም ቀናት ሰፊ ትምህርት የሰጡ ሲሆን በመርሐ ግብሩም ብዙ ምእመናን ተሳታፊ ሆነዋል።

Hamburg-3

ከሁለቱ ቀናት የዐውደ ርእይ ገለጻ እና ትምህርት በኋላ የውይይት መድረክ የተከፈተ ሲሆን ምእመናኑ በማስረጃ እና በፎቶ የተደገፈውን የቤተክርስቲያንን ረጅም እና ታሪካዊ ጉዞ በማየታቸው ብዙ መማራቸውን እና እጅግ መደሰታቸውን በአንጻሩም ገዳማትና የአብነት ትምህርት ቤቶች ያሉባቸውን ችግሮችን ሲረዱ ማዘናቸውን ገለፀዋል። ምእመናኑ በማኅበረ ቅዱሳን አስተባባሪነት እየተሰሩ ባሉ ገዳማትን እና የአብነት ትምህርት ቤቶችን የመርዳት አበረታች ጅምሮች እኛም የድርሳችንን ልንወጣ ይገባናል በማለት በቋሚነት አንድ የአብነት ትምህርት ቤት ወይም የአንድ ገዳም ፕሮጀክት ለመርዳት ቃል የገቡ ሲሆን በእለቱ በነበረው የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐግብር ላይም በንቃት ተሳትፈዋል።

Hamburg-1

በመርሐ ግብሩ ማጠቃለያ ላይ ንግግር ያደረጉት በማኅበረ ቅዱሳን የጀርመን ቀጣና ማእከል ሰብሳቢ ዲ/ን ዶ/ር ያብባል መሉዓለም መርሐግብሩ በተሳካ ሁኔታ እንዲካሄድ ከቅድመ ዝግጅት ጀምረው ከፍተኛ ክትትል እና ድጋፍ ላደረጉት ለመልአከ ገነት ቆሞስ አባ ብርሃነ መስቀል ተድላ፣ ምእመናንን በማስተባባር ለተሳታፊዎች መስተንግዶ በማቅረብ ገቢ እንዲሰበሰብ ላደረገው እና ተስማሚ አዳራሽ በማመቻቸት ከፍተኛ ሥራ ለሠራው ለደብሩ ሰበካ ጉባኤ እንዲሁም እንግዶችን በማስተናገድ እና በዝግጅቶቹ ላይ በመሳተፍ ልዩ ፍቅር ላሳዩት የአጥቢያው ምእመናን ከፍተኛ ምሥጋና አቅርበዋል።

በመጨረሻም መልአከ ገነት ቆሞስ አባ ብርሃነ መስቀል ተድላ ዐውደ ርእዩን ያዘጋጀውን የማኅበረ ቅዱሳን የአውሮፓ ማእከል ፣ ከኢትዮጵያ የመጡትን እንግዶች እና ለዝግጅቱ የተራዱትን ምእመናን ሁሉ አመስግነው የገዳማትና የአብነት ትምህርት ቤቶች ጉዳይ የቤተክርስቲያን ልጆች ሁሉ ጉዳይ ሰለሆነ የሀምቡርግ ምእመናንም ዛሬ ያሳየነውን ተነሳሽነት አጠናክረን በገባነው ቃል መሠረት በቋሚነት አንድ ገዳም ወይም የአብነት ትምህርት ቤት ልንረዳ ይገባናል በማለት መርሐ ግብሩን በጸሎት ዘግተዋል።

በቀጣይም ተመሳሳይ የዐውደ ርእይ ዝግጅቶችና ለገዳማትና የአብነት ት/ቤቶች ማጠናከሪያና ማቋቋሚያ ድጋፍ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብራት በጀርመን ኮሎኝ እና ፍራንክፈርት እንዲሁም በስዊዘርላንድ፣ ግሪክ፣ ስዊድን፣ ዴንማርክ፣ ጣሊያን፣ ፊንላንድ፣ ቤልጄምና እንግሊዝ እንደሚካሔድ ከማእከሉ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።