“ዘይሁብ መርሐ ርቱዐ ለቤተ ክርስቲያን – ለቤተ ክርስቲያን ቅን መሪ የሚሰጥ”
(ጸሎተ ኪዳን – ዘሠርክ)
በዲያቆን ያረጋል አበጋዝ
ቤተ ክርስቲያን የምንላት ወልድ ዋሕድ ኢየሱስ ክርስቶስ ከፍጹምና ከማይነገር ፍቅሩ የተነሣ ሰው እስከ መሆን፣ ሰው ሆኖም በዚህ ዓለም ከኃጢአት በስተቀር እንደ ሰው መኖርን፣ ከዚያም በቀራንዮ ቅዱስ ሥጋውን እስኪቆርስላትና ክቡር ደሙን እስኪያፈስላት ድረስ የደረሰላትና የመሠረታት የምእመናን አንድነት (ጉባኤ) ናት። “ወነአምን በአሐቲ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንተ ላእለ ኩሉ ጉባኤ ዘሐዋርያት” የምንለው ለዚህ ነው። ቤተ ክርስቲያን በወንጌል መሠረትነት በኢየሱስ ክርስቶስ ራስነት በምእመናን አካልነት የተመሠረተች ጉባኤ ናት።