መንፈሳዊ ሕይወትና ስደት

3.ጾምና ጸሎት፦ ጸሎት ማለት ከእግዚአብሔር ጋር መነጋገር፤ እግዚአብሔርን ማመስገን፣ መለመን፣ መጠየቅ መማጸን ማለት ነው። እንዲሁም ሰው አሳቡን ለእግዚአብሔር የሚገልጥበት፣ እግዚአብሔር የሰውን ልመና ተቀብሎ ፍቃዱን የሚፈፅምበት ረቂቅ ምስጢር ነው። ጾምና ጸሎት ሁለቱ የማይለያዩ የእግዚአብሔር የበረከት ስጦታዎች ናቸው። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌ በምድር በነበረበት ጊዜ ከፈፀማቸው አበይት ተግባራት መካከል ጾምና ጸሎት ይገኙበታል። እርሱ የዲያብሎስን ፈተና በጾምና በጸሎት ድል እንደምንነሳው በገዳመ ቆሮንቶስ ለ40 ቀንና ለ40 ሌሊት ጾሞና ጸልዮ አሳይቶናል። ማቴ 4፡1_ ስለጾም ኢትዮጵያዊ ቅዱስ ያሬድ “ንጹም ጾም ወናፈቅር ቢጸነ፣ ወንትፋቀር በበይናቲነ፣ ዓይን ይጹም እምርእየ ሕሱም፣ ዕዝን ይጹም እምሰሚዓ ሕሱም፣  ልሳንኒ ይጹም እምተናግሮ ሕሱም ትርጉም ጾምን እንጹም፣ ባልንጀራችንን እንውደድ እርስ በርሳችን እንዋደድ፣ ዓይን ክፉ ከማየት ጀሮ ክፉ ከመስማት፣ አንደበትም ክፉ ከመናገር ይጹም”  በማለት እንዴት መጾም እንዳለብን በሚገባ ገልጾልናል። 

አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያት “ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉና  ፀልዩ” ማቴ 26፡41  ፈተና እንዳይገጥማችሁ ተግታችሁ ፀልዩ ብሎ እንዳስተማራቸው እኛም ወደ ፈተና እንዳንገባ በጸሎት መትጋት ያስፈልጋል።  ጾምና ጸሎት ወደ ፈተና እንዳንገባ የምንጠበቅበትና ከፈተናም የምንወጣበት ታላቅ መሳሪያ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ያስረዳናል። “ይህ ዓይነት ግን ከጸሎትና ከጾም በቀር አይወጣም” ማቴ 17፡21ሰይጣንን ልታስወጡ የምትችሉት፣ በፈተና ውስጥ ብትሆኑ ከገባችሁበት ፈተናና ችግር ልትወጡ፣ ልትፈወሱ የምትችሉት በጸሎትና በጾም ብቻ ነው ሲል ጌታችን በሐዋርያት አማካኝነት ገልጾልናል። እኛም ካልጾምን ካልጸለይን ወደ ፈተና እንገባለን ከገባንም አንወጣም። ጾምና ጸሎት ከፈተና የምንወጣበትና የምንጠበቅበት ብቻም ሳይሆን የሚያስፈልገንን ሥጋዊ ነገርም እንድናገኝ አማላካችን በቸርነቱ እንዲጎበኘን ይረዳናል። “ለምኑ ይሰጣችኋል፤  ፈልጉ ታገኙማላችሁ፤ መዝጊያ አንኳኩ ይከፈትላችሁማል” ማቴ 7፡7 እያለ ቅዱስ ወንጌል የምንፈልገውን ነገር እግዚአብሔር አምላክን በጾምና በጸሎት ከለመንነው በሚስፈልገን ስዓትና ጊዜ እንደሚሰጠን ያስረዳናል። ስለዚህ እኛ ወደፈተና እንዳንገባ፣ ከገባንም ከፈተና እንድንወጣና የሚያስፈልገንን ነገር ሁሉ እንድናገኝ የስደትን ኑሮ፣ ባህልና የአየር ጠባይ ለውጥ ምክንያት ሳናደርግ እንደ አባቶቻችን እግዚአብሔርን በጸሎትና በጾም መለመን መማጸን አስፈላጊ ነው። 

4.ትዕግሥትሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንደተናገረው ትዕግሥት ከመንፈስ ፍሬዎች አንዱ ነው። ገላ 5፡22_23 የመንፈስ ፍሬ ብሎ የዘረዘራቸው ምግባረ ሰናያት እርስ በእርሳቸው ግንኙነት አላቸው። ዕምነት ያለው ሰው የውሃት፣ ቸርነት፣ በጎነት ሊኖረው ይገባል፤ ፍቅር ያለው ሰው ደስታ፣ ሰላም ከእነዚህም ጋር ትዕግሥትም አለው። ፍቅርና ዕምነት ያለው ሰው እራሱን መግዛት ይችላል። ፍቅር ይታገሳል እንዲል 1ቆሮ 13፡4። ትዕግሥት ቻይ፣ ልበ ሰፊ፣ ትሁትና መሀሪ የሆነ ሰው ጠባይ መለያ ነው። ትዕግሥት ዘርፈ ብዙ ነው። በአገልግሎት፣ በጸሎት፣ በማህበራዊ ትዕግሥት አስፈላጊ ነው። ትዕግሥት የሌለው ሰው በቀላሉ ይጨነቃል፣ ይረበሻል፣ ይበሳጫል ምክንያቱም ለምን አሁን የምፈልገው ነገር አልሆነም ብሎ ስለማይረጋጋና ስለሚቸኩል ነው። በተለይ በስደት ዓለም ስንኖር የምናያቸው፣ የምንሰማቸው እና የምናገኛቸው ነገሮች በአብዛኛው ትዕግሥትን የሚፈታተኑ ስለሆኑ ትዕግሥት ከመቸውም በበለጠ ያስፈልጋል። 

ጠቢቡ ሰሎሞን “ለሁሉም ጊዜ አለው” መክ 3፡1  እንዳለ ጸሎታችን ልመናችን መልስ የሚያገኝበት፣ የሚያስፈልገን ሥጋዊ ነገር የምንናገኝበት፣ እጅግ አስቸጋሪ መስሎ የሚታየን የብቸኝነት የስደት ኑሮ የሚያበቃበት ጊዜ አለና ይህን በትዕግሥት መጠበቅ ይኖርብናል። “ቢዘገይም በእርግጥ ይመጣልና ታገሰው እርሱ አይዘገይም” ዕን 2፡3  እግዚአብሔርን እናውቀውና እናከብረው ዘንድ ልመናችን ሊዘገይ ይችላል። ነገር ግን እግዚአብሔር የእኛን ልመና አስፈላጊ ሆኖ ካገኘው በሚያስፈልገን ሰዓት እንደ አባታችን ኢዮብ ትዕግሥትን አለማምዶ ቢዘገይም ይሰጠናል። ትዕግሥት ባለማወቅም እንኳ ቢፈጽሙት ፍሬው እጅግ ታላቅና ጽድቅንም ያፈራል። “በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፤ እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና።  ለመቀጣት ታገሡ፤ እግዚአብሔር እንደ ልጆች ያደርችኋልና፤ አባቱ የማይቀጣው ልጅ ማን ነው? ነገር ግን ቅጣት ሁሉ ለጊዜው የሚያሳዝን እንጂ ደስ የሚያሰኝ አይመስልም፥ ዳሩ ግን በኋላ ለለመዱት የሰላምን ፍሬ እርሱም ጽድቅን ያፈራላቸዋል።” ዕብ 12፡2_11  እንዲሁም አባታችን ኢዮብ “እነሆ ቢገድለኝ ስንኳ እርሱን በትዕግሥት እጠብቃለው ነገር ግን መንገዴን በፊቱ አጸናለው” ኢዮ 13፡15 በማለት ይህ የመጣብኝ ሥጋዊ ፈተና ለሞት ቢዳርገኝም እንኳ በትዕግሥት ሞቴን እጠብቃለው እንጂ እምነቴን በሥጋዊ ፈተና ምክንያት ከእምነቴ ወደ ኋላ አልልም እንዳለ እኛም እንደ  አባቶቻችን የመጣብንን ፈተና  ሁሉ ታግሰን፣ የጽድቅን ፍሬ እንበላ ዘንድ ትዕግሥትን ገንዘብ ማድረግ ያስፈልጋል። 

5.ከክፉ ባልንጀራ መራቅ/ጓደኛን መምረጥበዚህ በምንኖርበት በስደት ዓለም ከማን ጋር መዋል፣ መነጋገር፣ መወያየትና መመካከር እንዳለብን ካለወቅን ልንነሳ በማንችልበት አወዳደቅ ልንወድቅ እንችላለን። ብዙዎች በጓደኛ ምክንያት ከእምነታቸው፣ ከባህላቸው፣ ወጥተው ማንነታቸውን ለውጠው የክፉ ጓደኛቸውን ገጸ ባህሪ ተላብሰው እናገኛቸዋለን። ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ “አትሳቱ፤ ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋልበጽድቅ ንቁ ኃጢአትንም አትሥሩ፤ እግዚአብሔርን የማያውቁ አሉና” 1ኛ ቆሮ 15፡33 እያለ ምን አይነት ጓደኛ መከተል እንዳለብን ይመክረናል። 

ክፍ ባልንጀራ የጀመርነውን መንፈሳዊ ሕይወት እስከመጨረሻው እንዳንዘልቅ እንቅፋት ይሆንብናል። እስኪ ጓደኞቻችንን እናስታውስ ስንቶች ናቸው ለመንፈሳዊ ሕይወታችን ብርታት ሊሆኑን የሚችሉ? ስንቶች ናቸው ሃይማኖታዊ ስርዓታችንን እንድንጠብቅ የሚመክሩን የሚያበረቱን? ስንቶች ናቸው ባህላችንን ማንነታችንን እንድጠብቅ የሚገፋፉን? በእርግጥ እጅግ መልካም ለመንፈሳዊ ሕይወታችን አስትዋጽኦ የሚያደርጉ ጓደኞች አሉ ይኖራሉም። አባቶቻችንና ቅዱሳን መጽሐፍት እንደ እነዚህ አይነት ሰዎችን እንድንከተል ነው የሚመክሩን። ክፉ ጓደኛ  በመጀመሪያ ሲቀርብ መልካም ቃላቶችን መርጦ እኛን ወደርሶ ሊያቀርብ በሚችልበት በደካማ ጎናችን ነው የሚቀርበን። እናታችን ሔዋንን ሰይጣን ሲቀርባት በውዳሴ ነበር የቀረባት ማንም አወድሷት የማያውቀውን የውዳሴ አይነት ነበር ያቀረበላት ፍጻሜው ግን መከራና ሞት ነው የጠበቃት። ስለዚህ እኛም የሚቀርቡንን ሰዎች ለምንና እንዴት ብለን እራሳችን መጠየቅ ያስፈልጋል አለበለዚያ ግን እንደ  ሶምሶን ጸጋችን ተገፎ መንፈሳዊነት ርቆን ከውኃ የወጣ አሳ እንሆናለን።

በአጠቃላይ ከላይ ለማየት እንደሞከርነው ከእኛ  የሚጠበቁ ነገሮችን እያደረግን፣ የቀረውን ነገር እግዚአብሔር በቸርነቱ እንዲጎበኘን በጸሎት እየለመን፣ በመንፈሳዊ ሕይወት እድንጓዝ እንቅፋት የሚሆኑ ነገሮችን ማስወገድ ይኖርብናል። በትንቢተ ሕዝቅኤል “ንስሐ ግቡ ኃጢአትም ዕንቅፋት እንዳይሆንባችሁ ከኃጢአታችሁ ሁሉ ተመለሱ። የበደላችሁትን በደል ሁሉ ከእናንተ ጣሉ አዲስ ልብና አዲስ መንፈስም ለእናንተ አድርጉ የእስራኤል ቤት ሆይ፥ ስለ ምን ትሞታላችሁ? የምዋቹን ሞት አልፈቅድምና፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር ስለዚህ ተመለሱና በሕይወት ኑሩ።” ሕዝ 18፡30_32 ተብሎ እንደተጻፈ አንዱና ትልቁ እንቅፋት ኃጢአታችን ነውና እርሱን በንስሐ ታጥበን በሕይወት እንኖር ዘንድ የቅዱሳን አምላክ እግዚአብሔር ይርዳን፤ የድንግል ማርያም፣ የቅዱሳን ምልጃና ጸሎት አይለየን አሜን።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!