ሀገረ ስብከቱ የመጀመሪያውን ልዩ የትምህርተ ወንጌል ጉባኤና ዐውደ ጥናት እንደሚያካሂድ አሳወቀ፡፡

በወርቁ ዘውዴ

ነሐሴ 19 ቀን 2007 ዓ.ም.

በኢ/ኦ/ተ/ቤተ ክርስቲያን የደቡብ፣ ምሥራቅና ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት ከነሐሴ ፴ እስከ ጷጉሜን ፩ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት በሚገኝበት በጀርመኗ ሮሰልሳይም ከተማ የትምህርተ ወንጌል ጉባኤ እና ዐውደ ጥናት ለማካሄድ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን አሳወቀ፡፡ ሀገረ ስብከቱ በአዲስ መልኩ ተዋቅሮ የመንበረ ጵጵስና መቀመጫውን በጀርመን ካደረገበት ጊዜ አንስቶ አስተዳደራዊ መዋቅሩን በማጠናከር የቤተ ክርስቲያኗን መንፈሳዊ አገልግሎት የሚደግፍና የሚያግዝ ጠቃሚ ተግባራትን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ከሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት የተገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡

አሁን በተዘጋጀው የሁለት ቀን ጉባኤ ላይ በመላው ጀርመን የሚኖሩ ምዕመናን እና ለሀገረ ስብከቱ ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔ የሚመጡ የአድባራት አስተዳደሪዎችና የሰ/ጉባኤ ተወካዮች እንደሚሳተፉበት ይጠበቃል። በጉባኤው ከኢትዮጵያ በመጡ መምህራን ትምህርተ ወንጌል፣ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የተደረጉ የጥናት ወረቀቶች የሚቀርቡ ሲሆን በሰ/ት/ቤት መዘምራን መዝሙር ይቀርባል። የሀገረ ስብከቱን አገልግሎት ለማጠናከር እገዛ የሚያደርግ የገቢ ማሰባሰብ ሥራ የሚሰራ ሲሆን ኢየሩሳሌም ደርሶ መልስ እና ሌሎች ዕጣዎችን ያካተተ ልዩ ቶምቦለ ተዘጋጅቶ በመሸጥ ላይ እንደሆነ ተገልጿል።

ከትምህርታዊ ጉባኤው ቀደም ብሎም የሀገረ ስብከቱ ጠቅላላ ጉባኤ እንደሚካሄድ፤ በጉባኤውም የሀገረ ስብከቱን፣ የወረዳ ቤተ ክህነቶችና የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናትን የሥራ ክንውንና የሒሳብ ረፖረቶች አዳምጦ ተገቢውን ዉሳኔ ማሳለፍ፤ በሥራ ዘመኑ ባጋጠሙ ችግሮችና መፍትሔዎቻቸው ተወያይቶ መወሰንና በሀገረ ስብከቱ የቀጣይ የሥራ ዘመን የሥራ እቅድ መርምሮ ማጽደቅ የጉባኤው ዋና ዋና ጉዳዮች እንደሆነ ከሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።