የዚህን ዓለም ጣዕም ናቁ
በዲን. ብርሃኑ ታደሰ
ጥቅምት 03 ቀን 2005 ዓ.ም.
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ’ዓለም’ የሚለውን ቃል በተለያየ አገባብ እናገኘዋለን። ለምሳሌ፦ ፍጥረትን፥ ሰማይንና ምድርን የሚወክልበት ጊዜ አለ፦ “ዓለም ሳይፈጠር በፊት ቅዱሳንና ነውር የሌለን በፍቅር እንሆን ዘንድ በክርስቶስ መረጠን።”(ኤፌ 1፥4) “ምድርና ሞላዋ ለእግዚአብሔር ናት፥ ዓለምም በእርስዋም የሚኖሩ ሁሉ።” እንዲል። (መዝ 24፥1) በሌላም ስፍራ “ከዚህም በኋላ ዓለም አያየኝም፤ እናንተ ግን ታዩኛላችሁ፤” (ዮሐ 14፥19) እንዲሁም “. . . በኵርነቱን እንደ ሸጠ እንደ ዔሳው ለዚህ ዓለም የሚመች ሰው እንዳይሆን ተጠንቀቁ።” (ዕብ 12፥16) ሲል ደግሞ ውክልናው ከእግዚአብሔር ሐሳብ ጋር የማይስማማው ሁሉ ለሥጋ ሐሳብ ያደላውን ሁሉ ይሆናል።
ሰው ሁሉ በዚህ ዓለም ሲኖር የእግዚአብሔርን ሕግ ቢጠብቀውና ቢንከባከበው ኖሮ የዚህ ዓለም ኑሮ መልካም ይሆን ነበር። በዚህም ላይ የህሊናውን ዳኝነት ተከትሎ መልካም በመሥራት ቢጸና፣ ወይም እግዚአብሔር በደብረ ሲና የሰጠውን ሕግ ቢተገብር ማለትም ባልንጀራውን ባይበድል፤ ከዚያም በኋላ የተሰጠችውን ፍጽምት ሕግ ሕገ ወንጌልን ቢከተል፣ ይኸውም ባልንጀራውን ብቻ ሳይሆን ጠላቱንም መውደድ ቢችል፣ ዓለም ለኑሮ እንዴት የተመቸችና የተደላደለች ትሆን ነበር!? በሐሰት አትመስክር፥ ሐሰት አትናገር የምትለውን ሕግ ማክበር ቢችል፤ ሰው ለኑሮው የሚሆነውን ይገዛ ዘንድ ገበያ ገብቶ፣ የሚያታልለኝ አለ ብሎ ባያስብ፣ ጉዳይ ለማስፈጸም ወጥቶ እውነትን ብቻ ይዞ የሚያናግረው እንደሚያገኝ አምኖ ቢመላለስ እርሱም እንዲሁ ቢያደርግ፤ ለሕሊናው እንዴት የተመቸ እንደሚሆን ግልጽ ነው። እንግዲያውስ ሁሉንም ብንፈጽም ዓለም እንዴት ሰላማዊ ትሆን ነበር!? ነገር ግን ሁሉም ይህንን መፈጸም ስላልቻለ የዚህች ዓለም ኑሮ ውጣ ውረድ የበዛበት ሆነ። ይልቁንም እነዚህን ለመፈጸምና ፈቃደ ሥጋውን ለማሸነፍ የሚታገል በታላቅ ሰልፍ ውስጥ ይገባል።
አይደለም እንጂ ሁሉ በፈቃደ እግዚአብሔር የሚኖር ቢሆንና ይህችም ምድር ለመኖር የተመቸች ብትሆን እንኳን ዘላለማዊ አይደለችም፤ ታልፋለች። ጥቂት ጊዜ ነው ያለን ስለዚህም እንደ ልባችንና እንደ ፈቃዳችን እንሁን፤ ከልካይ አይኑርብን ብንልም በሕይወት እስካለን ድረስ የሚዘልቅ ሀሴትን ማግኘት በዚህች ምድር አይቻልም። ፀሐይ የምትወጣው ለጥቂት ጊዜ ነውና ጨለማውም ይመጣል፣ መስከረም ብለን ስንጀምር ነሐሴ ሩቅ ይመስለናል፤ ነገር ግን ቀንና ወራቱ ይቀየራል ርቀቱ ሲጀምሩት እንደነበረ አይደለም፣ በእርሷም (በዚህች ዓለም) ደስታ ብቻ አይደለም ያለው ሐዘንም አለና። ስለዚህም እርሷም ፈቃዷም አላፊና ጠፊ ናቸው።
ይህችን ዓለም ከንቱ የምታሰኝ ግን ሌላ ዓለም አለች፤ ሰማያዊት እየሩሳሌም። ይህች አንዴ ከተሰጠች በኋላ አታልፍም። በእርሷም ዘንድ ፀሐይ አትጠልቅም፣ ልቅሶና ሐዘን የለባትም፤ ደስታ እንጂ፣ በዚያ ምስጋና ብቻ ነው ሰልፍም የለም። (ራእ 21፥22፣ኢሳ 60፥9) ዴማስ ይህቺን ዓለም ወዷልና ከንቱ ናት ብሎ ሊንቃት ፈቃዷንም ሊተው አልወደደምና ያችን ዓለም አያገኛትም። ነገር ግን ከሐዋርያው ጋር – “ለእኛም ይገለጥ ዘንድ ካለው ክብር ጋር ቢመዛዘን የአሁኑ ዘመን ሥቃይ ምንም እንዳይደለ አስባለሁ።” ብለው ለሚታገሱ የምትሰጥ ናት። (ሮሜ 8፥18) ስለዚህች ዓለም ጣዕም ከንቱነት ግን፦ ጠቢቡ ሰሎሞን – “ከንቱ፥ ከንቱ፥ የከንቱ ከንቱ ሁሉ ከንቱ ነው” ይላል። (መክ 1፥2) በቅዳሴ ጸሎት ላይም ዲያቆኑ የቅዱስ ዮሐንስን ስብከት ይዞ – “ወንድሞቼ ይህን ዓለም አትውደዱ በዓለሙ ውስጥ ያለውንም። ዓለሙም አላፊ ነው፥ ፈቃዱም አላፊ ነው፥ ሁሉም አላፊ ነውና።” ይላል። (1ኛ ዮሐ 2፥15)
ዔሳውስ የሳተው ምንድን ነው? ለማደን ወደ ዱር ገባ የሚያጠምደውም አጣ ስለዚህ ደክሞት ተመለሰ፤ ያዕቆብንም ካዘጋጀው ምግብ እንዲሰጠው ለመነው፣ ያዕቆብ ግን በምስር ወጡ ፋንታ ብኩርናኽን ስጠኝ አለው፤ ዔሳውም ”እነሆ እኔ ልሞት ነኝ ብኩርናዬ ለምኔ ናት?” አለ። ከምስር ወጡም ወሰደ፤ በላም ብኩርናውንም ተዋት። እነዚህን ጥያቄዎች እስቲ እንመርምራቸው፦ ዔሳው ከአደን አግኝቶ ቢመለስ ኑሮ ማዕድ ማዘጋጀት ምን ያህል ጊዜ ይፈልግበት ነበር? ወይንስ ያደነውን እንኳን ለማዘጋጀት አቅም አልነበረውም? በዚያውስ ላይ ያዕቆብን በምስር ወጡ ፋንታ አቻውን እሰጥሃለሁ ለምን አላለውም? በዚህስ ነገር ባይስማማ ያዕቆብ ወንድሙ ምግቡን ከልክሎት በረሀብ እስኪሞት ድረስ ይጨክንበታልን? እናቱ ርብቃስ አባቱ ይስሐቅስ በረሀብ እስኪሞት ዝም ይላሉን? በቤቱ ከሞላ ከተረፈ ሀብት ውስጥ ዔሳው አድኖ ከሚያመጣው ውጪ እንዲመገብ አይፈቀድለትምን? አባቱ ይስሐቅ ዔሳው ከሚያመጣው አደን ይመገብ እንደነበር ታሪኩ ይነግረናል። ስለዚህ ይስሐቅም የሚመገበው የለውም ማለት ነውን? አይደለም። ነገር ግን ዔሳው ለብኩርናው የሰጣት ግምት ምን ያህል እንደሆነ ዳግመኛም መታገስን ትንሽ መራብን ስላልፈለገ አሳልፎ ሰጣት። የምግብ ጣዕም አታለለው(ዘፍ25፥27) ። ለእኛ ግን የሐዋርያት አለቃ ቅዱስ ጴጥሮስ፦ “. . . የጸጋ ሁሉ አምላክ ለጥቂት ጊዜ መከራን ከተቀበላችሁ በኋላ ራሱ ፍጹማን ያደርጋችኋል ያጸናችሁማል ያበረታችሁማል።” (1ኛ ጴጥ 5፥10) ይለናል።
ነብየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት ፍልስጥኤማውያን የተወለደበትን ክፍለ ሀገር ቤተ ልሔምን ይዘዋት በነበረ ጊዜ፣ በልጅነቱ ይጠጣ የነበረውን የምንጭ ውኃ ይጠጣ ዘንድ ወደደ። የጦር አለቆቹንም፡- ከቤተ ልሔም ምንጭ ውኃን ማን ያመጣልኛል? አላቸው። እነርሱም ታጥቀው በጠላት ሰፈር ዘምተው ሊጠጣ የፈለገውን አመጡለት። ንጉሥ ለእርሱ ብለው ሰውነታቸውን ለሞት አሳልፈው ሰጥተው እንዳመጡለት አይቶ ከውኃው አልጠጣም አፈሰሰው፤ በነፍሳቸው የደፈሩትን የእነዚህን ሰዎች ደም እጠጣታለሁን!? ብሎ (1ኛ ዜና 10፥16-19)። ንጉሥ ዳዊት ስለሠራዊቱ ብሎ የውኃውን ጣዕም ሳይቀምስ አፈሰሰው፤ ሠራዊቱም ለእርሱ ያላቸውን ታዛዥነት በገለጡበት መጠን እርሱም እንዲሁ የሚወደውን አሳልፎ በመስጠት ፍቅሩን ገለጠው። ይህንን ታሪክ ለሰማዕታት ሁሉ በመስጠት ሶርያዊው ቅዱስ ኤፍሬም በውዳሴ ማርያም ድርሰቱ ላይ፦ “ሰማዕታት የዚችን ዓለም ጣዕም በእውነት ናቁ ደማቸውንም ስለ እግዚአብሔር አፈሰሱ ስለ መንግስተ ሰማያት መራራ ሞትን ታገሱ” ብሏል።
እኛም የእንቅልፍን ጣዕም ትተን ቅዳሴ ማስቀደስ ከቻልን፣ ስንፍናውን ትተን ትንሽ የእግዚአብሔርን ቃል ማጥናትና በአዕምሮ መያዝ ከቻልን፣ መዝሙሩን በቃል አጥንተን ለመዘመር የቻልን እንደሆን፣ ለየትኛውም ኑሮ አስተዋጽዎ የሌላቸውን እና ጊዜያችንን እንዲሁ የሚወስዱብንን ነገሮች መቀነስ ከቻልን፣ ከገንዘባችን ከፍለን ለድሃ መስጠት እንዲሁም ለመንፈሳዊ አገልግሎት ለማዋል ከጨከንን፣ ከዘፈኑ ከካካታው መራቅ ከቻልን፣ በዓለሙ የምናየውና የምንሰማው የምናነበውም እንደዋዛ ስቦ የማይወስደን ከሆነ፣ ኃጢያታችንን ቸል ሳንላት ንስሐ የምንቀበልባት ከሆነ፣ ቅድሚያ የምንሰጠው የሚበልጥብን መንፈሳዊ ነገር ከሆነ፣ የጣዕመ ዓለም እና የጣዕመ አምልኮ እግዚአብሔር ልዩነታቸው ተረድቶናል፤ ካልሆነም ልብ እንበል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ፍቅር በመላበትና በርኅራኄ ቃል እንዲህ ይለናል፦ “ሰውነታችሁን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝና ሕያው ቅዱስም መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ርኅራኄ እለምናችኋለሁ፥” (ሮሜ 12፥1)። ማለትም በኃጢያት ምውት ያልሆነ፦ ሕያው፣ ከዓለም ጣዕም የተለየ፣ ቅዱስ መስዋዕት እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘዋል። ስለዚህም ራሳችንን በዚህ መልክ በማዘጋጀት ብናቀርብ እግዚአብሔርን ደስ እንደምናሰኘው የታመነ ነው።
ጣዕመ ዓለምን ንቀው መንግስቱን ከወረሱ ጋር የሚያስደምር ሕሊና ያድለን። አሜን።