ጾም በስደት ሀገር

በቀሲስ ለማ በሱፈቃድ

ሐምሌ 30 ቀን 2007 ዓ.ም.

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት መሠረት ሰባት አጽዋማት አሉ :: ከእነዚህም አንዱ ጾመ ፍልሰታ ነው:: ጾም ማለት በታወቀ ወራት ሳምንታት እና ዕለታት እስከ ጾሙ ፍጻሜ ድረስ ከተከለከሉ ጥሉላት ምግቦችና መጠጦች ወይም የእንስሳት ውጤቶች ሥጋ ወተትና ከመሳሰሉት መከልከል ሲሆን፣ ከዚያ ውጪ የሆኑ ምግቦች ለተወሰነ ሰዓት ብቻ መከልከል ነው :: ‘’ ማለፊያ እንጀራም አልበላሁም ሥጋና ጠጅም በአፌ አልገባም ሦስቱም ሳምንት እስኪፈጸም ድረስ ዘይት አልተቀባሁም’’ /ዳን .. /። ‘’ጾምሰ ተከልዖተ ብእሲ እመብልዕ በጊዜ እውቅ ‘’ /ፍትሐ ነገሥት አንቀጸ ጾም ተመልከቱ/። በሌላ መልኩ ደግሞ ጾም ማለት በዓይናችን በእጃችን በእግራችን በአንደበታችንና በመሳሰሉት የሰውነት ክፍሎቻችን ሁሉ ሳይቀር የምንጾመው ነው:: “ስንጾም አንደበታችንም ከማይገቡ ንግግሮችና ከነቀፋዎች ይጹም::’’ /.ዮሐንስ አፈ ወርቅ በእንተ ምክንያተ ሐውልታት ፫ ;.፲፪”/:: ቅዱስ ያሬድ በጾመ ድጓው «ይጹም ዐይን፥ ይጹም ልሳን፥ ዕዝንኒ ይጹም እምሰሚዐ ህሱም በተፋቅሮ፤ በፍቅር በመጽናት ዓይን ክፉ ነገርን ከማየት ይጹም፣ አንደበትም ክፉ ከመናገር ይጹም፣ ጆሮም ክፉ ከመስማት ይጹም” ብሎ ገልጾታል።

ጾም በሁለት የሚከፈል ሲሆን የአዋጅና የግል ጾም በመባል ይታወቃል :: ጾመ ፍልሰታ ከሰባቱ የአዋጅ አጽዋማት መካከል አንዱ ሲሆን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ምእመናን ዘንድ ከሊቅ እስከ ደቂቅ በየዓመቱ በተለየ መልኩ በጉጉት ይጠበቃል። ሕጻናቱ ለመቁረብ ከሌላው ጊዜ በተለየ ሁኔታ ይዘጋጃሉ:: ወጣቱ እና አረጋውያኑ ደግሞ የቻሉ በየደብሩ በየገዳማቱ ሱባኤ ይይዛሉ፣ ያልቻሉ ደግሞ በያሉበት ደብር በማስቀደስ በጉጉት ሲጠብቁ የነበረውን ጾመ ፍልሰታ ጾመው በረከት ያገኙበታል:: ይህ ሁሉ የሚሆነው የተመቻቸ ሁኔታ ባለበት በሀገር ቤት ነው:: ነገር ግን በተለያዩ ምክንያቶች ከሀገራቸው ወጥተው በስደት የሚኖሩ ኦርቶዶክሳውያን በጾም ወቅት እንዴት ማሳለፍ አለባቸው? በተለይ ቤተክርስቲያን በሌለበት፣ ቢኖርም በጣም እሩቅ ቢሆን፣ ከሥራው ጸባይ አንጻር ከቤት መውጣት ባይቻል እንዴት መጾም ይገባል?

መጀመሪያ ማንም ሰው መረዳት ያለበት ምድር መላዋ የእግዚአብሔር መሆኗን ነው።‘’ ምድርና ሞላዋ ለእግዚአብሔር ናት: ዓለምም በእርስዋ የሚኖሩ ሁሉ።‘’ /መዝ ፳፫./ ስለዚህ በየትኛውም ቦታ ሆኖ በጾም በፀሎት ከእግዚአብሔር ጋር መገናኘት ይቻላል:: ለጾም የበለጠ ትኩረት እንድንስጥበት እና ተግተን መጾም እንችል ዘንድ ከዚህ በታች ያሉትን ነጥቦች መመልከት ይገባል።

. የጾምን ጥቅምን በሚገባ መረዳት፣

ጾም ያዘነውን የምታረጋጋ፣ ትዕግስትን የምታስተምር፣ ከኃጢአት ነጻ የምታወጣ፣ ሞገስን የምትሰጥ፣ ሥጋን ለነፍስ የምታስገዛ፣ ሥጋን ቁስል የምታድን መድኃኒት ናት። በተለይ ዓለም አንድ መንደር እየሆነ በመጣ ቁጥር፣ አብረው የሚመጡ የሥጋ ፈቃዳት እጅግ ስለሚበዙ፣ ሰው የነፍስን ሥራ መሥራት ያቆማል። በዚህ ምክንያት ሰው በክብርም ሆነ በተግባር ከእንስሳት ያነሰ ይሆናል :: ”እስመ ጾም ዐቢይ በቁዔት ባቲ ታግዕዘክሙ እምኃጢአት ትሜህሮሙ ለወራዙት ጽሙና ዛቲ ጾም ቅድስት ትፈሪ ሰላመ ወተዓሥዮሙ ትፍሥሕተ” ጾም ታላቅ ጥቅም አላት፣ ነፍሳችሁን ከኃጢአት ነጻ ታወጣለች፣ ለወጣቶችም ዕርጋታንና ራስን መግዛትን ታስተምራለች። ጾም ቅድስት ናትና ሰላምን ታፈራለች። ለሚተገብራትም ሰው ደስታን ትስጠዋለች :: (የቅዱስ ያሬድ ጾመ ድጓ ዘቅድስት ዘሐሙስ/ ተብሎ እንደተጻፈው። ዓለምን መውደድ ለእግዚአብሔር ጥል እንዲሆን አታውቁምን? አንግዲህ የዓለም ወዳጅ ሊሆን የሚፈቅድ ሁሉ የእግዚአብሔር ጠላት ሆኖአል::” /ያዕ ፬./። ተብሎ እንደተፃፈ :: “ወበይእት ጾም ኤልያስ ዐርገ ውስተ ሰማያት ወዳንኤል ድኅነ እም አፈ አናብስት። በዚህች ጾም ኤልያስ ዐረገ ዳንኤልም ከአንብሶች አፍ ዳነ።” /ዝማሬ ዘቅዱስ ያሬድ ዘገብር ኄር/

ከላይ ከተዘረዘሩት የጾም ጥቅም በተጨማሪ በአግባቡ ወዶ ፈቅዶ በሚጾሙና በማይጾሙ መካከል ያለው ልዩነት እንደሚከተለው እንመልከት፣

. በጾም፣

  • በጾም ከታዘዘ መከራ መዳን ይችላል። የነነዌ ሰዎች እሳት ከሰማይ ወርዶ ሊያጠፋቸው በነበረ ጊዜ ከታዘዘ መከራ የዳኑት በጾም ነው :: “ የነነዌ ሰዎች እግዚአብሔርን አመኑ፣ ለጾም አዋጅ ነገሩ ከታላቁ ጀምሮ እስከ ታናሹ ድረስ ማቅ ለበሱ እግዚአብሔር ተመልሶ ይጸጸት እንደሆነ፣ ከጽኑ ቁጣውም ይመለስ እንደሆነ ማን ያውቃል? እግዚአብሔርም ከክፉ መንገዳቸው እንደተመለሱ ሥራቸውን አየ። እግዚአብሔርም ያደርግባቸው ዘንድ በተናገረው ክፉ ነገር ተጸጽቶ አላደረገውም።” /ትን .ዮና. .፲። ትን ዩኢ.. ፲፪።/ የሰው ልጆች እግዚአብሔርን ሲበድሉ ኃጢአት ሲያበዙ የቅጣት መከራ ከእግዚአብሔር ዘንድ ይታዘዛል :: ከዚህ መከራ ለመዳን ደግሞ ጾም እጅግ አስፈላጊ ነው ::

  • በጾም ከአጋንንት ቁራኛ ነፃ መውጣት ይችላል። በተለይ በዚህ ዘመን አጋንንት በሰው ልጆች ላይ እጅግ የሰለጠኑበት፣ ሰዎችም ለአጋንንት የተንበረከኩበት/ የተገዙበት ዘመን ነው:: ይህ የሆነው ግን ሁሉም ሰው ወዶ ፈቅዶ ነው ማለት አይቻልም። ከአጋንንት ቁራኛ ነፃ የሚወጣበትን መንገድ ስለማያውቅ ሊሆን ይችላል :: ለአጋንንት ጸሩ ደግሞ ጾም ነው። ጌታችንና መድኃኒታች ኢየሱስ ክርስቶስ በዘመነ ሥጋዌው ሲያስተምር፣ ደቀመዛሙርቱ ሊያወጡት ያልቻሉትን ጋኔን ካወጣ በኋላ ወደእርሱ ቀርበው ‘’እኛ ማውጣት ያልቻልነው ስለ ምን ነው?‘’ ብለው በጠየቁት ጊዜ ስለ እምነታቸው ማነስ መሆኑን ከነገራቸው በሁዋላ ‘’ይህ ወገን በጸሎትና በጾም ካልሆነ በምንም ሊወጣ አይችልም“ አላቸው። /ማር ..፳፱/። ስለዚህ አጋንንትን ለማውጣት ጾም ወሳኝ መፍትሔ መሆንን መረዳት ይቻላል:: ያለጾም አጋንንትን ማውጣት አይቻልም።

  • ጾም ልመናችን እንዲሰማ ይረዳናል፣ የሰው ልጅ ብዙ የሚፈልገው ነገር አለ። ያንንም ማግኘት ይፈልጋል። ነገር ግን የሚፈልገውን ብቻ ሳይሆን፣ የሚጠቅመውን መርጦ የሚሰጥ እግዚአብሔር ነው። በጎ የሆነውን የምንፈልገውን ነገር ለማግኘት ጾም ያስፈልጋል። ‘’ስለዚህም ነገር ጾምን፣ ወደ እግዚአብሔር ለመንን፣ እርሱም ተለመነን።“ በማለት ጾም እግዚአብሔርን መለመኛና ጸሎታችን እንዲሰማ የሚያደርግ መሆኑን መረዳት ይቻላል :: /ዕዝ . . ፳፪ / ዩኢ ./

. ባለመጾም፣

  • ከላይ በ “ሀ”ሥር የተዘረዘሩትን በሙሉ የምናጣው ባለመጾማችን ነው። ጾም ልጓም ፍሬሃ ጥዑም ጾም ልጓም ናት ፍሬዋም ጣፋጭ ነው :: ይላልና ባለመጾማችን ከክፉ መንገዶች የመጠበቅ ልጓም ይፈታል። ሰዎች በሚሠሩት ሥራ በኑሮአቸው በትዳራቸውና በመሳሰሉት ሁሉ የማይደሰቱ ይሆናሉ። /.ያሬድ ጾመ ድጓ ዘቅድስት ዘረቡዕ/

. ላለጾም የምንሰጠውን ምክንያት ማስወገድ

አዳምና ሔዋን የታዘዙትን ትዕዛዝ ባፈረሱ ጊዜ ማለት ዕፀ በለስን በልተው ሲፈረድባቸው ለመብላታቸው አንዱ በአንዱ ያመካኙ ነበር። ነገር ግን ምክንያቱ ሊያድናቸው አልቻለም። ‘’ወይቤ አዳም በእሲትየ አንተ ወሀብከኒ ምስሌየ ትንበር ይእቲ ወሀበተኒ ወበላዕኩ፣ ከኔጋር እንድትሆን የሰጠኸኝ ሴት እርስዋ ከዛፉ ሰጠችኝና በላሁ።’’ /ዘፍ .. ፲፪/። ምን ጊዜም ምክንያት ለሐጥያት መፍትሔ መሆን አይችልም:: በተለይ በስደት የሚኖሩ ኦርቶዶክሳውያን ቤተክርስቲያን በቅርባችን የለም፣ በስደት ሀገር ነው ያለነው፣ ወዘተ፣ በማለት አለመጾም በቂ ምክንያት መሆን አይችልም።‘’ ከልብ ካለቀሱ እንባ አይገድም’’ እንዲሉ፣ ከልብ ከታሰበበት በየትኛውም ቦታ ሆኖ በጾም ከእግዚአብሔር ጋር መገናኘት ይቻላል :: ሠለስቱ ደቂቅ ባቢሎን በስደት በነበሩጊዜ ንጉሡ ናቡከደነፆር በግድ ምግብ እንዲመገቡ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር። ሠለስቱ ደቂቅ ግን ይህንን ምክንያት አድርግው ከመጾም አልተቆጠቡም። /ትን . ዳን .. /። ይልቁንም በዚያ በስደት ሀገር ለሚደርስባቸው መከራ ሁሉ መፍትሔው ጾም መሆኑ ስለገባቸው በትህርምት ላይ እያሉ፣ በሥራም ከተሰማሩ በኋላ አጠንክረው በመቀጠላቸው እግዚአብሔር ከሁሉም መከራ እንደጠበቃቸው ማስታወስ ተገቢ ነው።

ባጠቃላይም ’’እስመ ጾም ይትባየፃ ለኩሉ ምግባር ትሩፍ፣ ጾም የትሩፋት ሥራ ሁሉ ይስማማዋል’’:: /ማር ይስሐቅ አንቀጽ ፬ ም.ፍ ፮/። በጾማችን ወቅት ከስግደት፣ ከጸሎት፣ ከምጽዋት ጋር ጾምን ማስተባበር ያስፈልጋል። ለምሳሌ በጾም ወቅት መቼም ቁርሳችንን መልሰን በምሳ ላይ ስለማንመገበው፣ የቁርሳችንን ድርሻ ለበጎ ተግባር ማዋል ይገባል :: ምን ጊዜም መንፈሳዊ ተግባራት አንዱ ከአንዱ ተለይቶ ብቻውን የሚተገበር አይደለም። ጾም ከጸሎት ከስግደት ጋር፣ ሥጋውና ደሙን መቀበል ከንስሐ ጋር ካልሆነ ለጽድቅ አያበቃም። ማንም ሰው ትሩፋትን ለምሥራት የተለየ ብዙ እውቀት ሊኖረው ይገባል ተብሎ አይጠበቅም። ትሩፋት መሥራት/ በጎ ሥራ መሥራት ለመንፈሳዊ ሕይወታችን በጣም ጠቃሚ መሆኑ ማወቅ ይገባል። ይህን ደግሞ እንደ አቅማች መፈጸም እንችላለን :: እግዚአብሔር ከአቅማችን በላይ አይጠብቅብንም። እንዲያውም ’’ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ ወደ እኔ ኑ እኔምአሳርፋችኋለሁ ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ እኔ የዋህ በልቤም ትሁት ነኝና; ለነፍሳችሁ ዕረፍት ታገኛላችሁ ቀንበሬም ልዝብ ሸክሜም ቀሊል ነው።’’ ይለናል። /ማቴ.፲፩ . ፳፯/። አሁን የምንጀምረውን ጾመ ፍልሰታ ሐዋርያት አባቶቻችን ጾመው እርገትዋን ያዩበት በረከት የተቀበሉበት በመሆኑ እኛም ልጆቻቸው በሚመችም በማይመችም ቦታ ያለን ጾመን የእመቤታችን በረከት እንዲደርሰን በያለንበት መትጋት አለብን።

የእግዚአብሔር ቸርነት የእመቤታችን አማላጅነት የቅዱሳን ምልጃ አይለየን! አሜን።