ቀርቦሙ እግዚእ ኢየሱስ ወሖረ ምስሌሆሙ (ጉዞ ከእግዚአብሔር ጋር) ሉቃስ 24÷13-45
በቀሲስ ኃይለኢየሱስ ተመስገን
ሚያዚያ 21 ቀን 2009 ዓ.ም.
ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን ……………. በዓቢይ ኃይል ወሥልጣን
አሰሮ ለሰይጣን …………………………..አግአዞ ለአዳም
ሰላም ……………………………………… እም ይእዜሰ
ኮነ…………………………………………..ፍሥሐ ወሰላም
“ክርስቶስ በታላቅ ኃይልና ሥልጣን ከሙታን ተለይቶ ተነሣ ፤ ዲያብሎስን አሰረው አዳምን ነጻ አወጣው ፤ ሰላም ከዛሬ ጀምሮ ሰላም ሆነ”
13.ወይእተ ዕለተ እንዘ የሐውሩ ክልኤቱ እምውስቴቶሙ ሀገረ እንተ ርኅቅት እምኢየሩሳሌም መጠነ ስሳ ምዕራፍ እንተ ስማ ኤማኁስ።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የትንሳኤ በኵር ሆኖ ከሙታን መካከል በተነሣበት ዕለት በሰንበተ ክርስቲያን ከመቶ ሃያዎቹ የክርስቶስ ቤተሰቦች ውስጥ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት ከኢየሩሳሌም 60 ምዕራፍ ያህል ወደምትርቀው ኤማኁስ ወደምትባለው መንደር ሲሄዱ ስላጋጠማቸው ወንጌል የሚነግረንን አባቶቻችን ያስተማሩንን እንመለከታለን።
ቅዱስ ሉቃስ በጻፈው ወንጌል የተጠቀሰው የቀልዮጳ ስም ብቻ በመሆኑ(ሉቃስ 24÷18) ሁለቱ የኤማኁስ መንገደኞች ራሱ ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ እና ቀልዮጳ እንደሆኑ ይነገራል። አባቶቻችንም ሉቃስን ዘውእቱ ቀልዮጳ/ሉቃስ ማለት የቀልዮጳ ሌላ ስም ነው/ በማለት ሁለቱ የኤማኁስ መንገደኞች ሉቃስና ኒቆዲሞስ ናቸው ብለው በወንጌል ትርጓሜ ላይ አስቀምጠዋል።
ምዕራፍ(Stadia) የሮማውያን እና የግሪካውያን የጥንት የርቀት መለኪያ ነው። Stadia በብዙ ሲሆን በነጠላ ደግሞ Stadium ይባላል። Stadium 185 ሜትር ጋር ተመጣጣኝ የሆነ ርቀት ነው። በዚህ ስሌት ኤማኁስ ከኢየሩሳሌም (60 *185 ሜ) 11.1 ኪ.ሜ ወይም 7 ማይል ገደማ ርቀት ያላት መንደር እንደንደነበረች ይነገራል።
14.ወይትናገሩ በበይናቲሆሙ በእንተ ኩሉ ዘኮነ
ስለተደረገው ነገር ሁሉ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መገረፍ፣ መሰቀል፣ ስለሞቱ፣ አይሁድ በግፍ እንደወነጀሉት፣ ስለደግነቱ፣ ስለአዋቂነቱ ሲወያዩ ሲነጋገሩ ሳለ
15.ወእንዘ እሙንቱ ይትናገሩ ወይትኀሠሥዎ ለዝንቱ ቀርቦሙ እግዚእ ኢየሱስ ወሖረ ምስሌሆሙ።
ነገረ ክርስቶስን ሲጨዋወቱ ሲመረምሩ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቀርቦ ከእነርሱ ጋር ሄደ። ጌታቸውን እንደሻቱት አውቆ አምላካችን የሩቅ አምላክ አይደለምና ወደ እነሱ ቀረበ። አጥርቶ የማያይ ሰው በመንገድ መሪ እንዲያስፈልገው ትንሣኤውን እንዳልተረዱት አውቆ ሊያስተምራቸው ሊመራቸው አብሯቸው ተጓዘ ቅዱስ ያዕቆብ በመልእክቱ ያዕ 4 ÷ 8 “ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ ወደ እናንተም ይቀርባል” እንዳለው በልባቸውና በአንደበታቸው አምላካቸውን ስላሰቡ ወደ አምላካቸው ስለቀረቡ አምላክ በጉዟቸው መሪ አስተማሪ ሆናቸው አብሯቸውም ተጓዘ። በዚህ ዘመን ጓደኛ ከወዳጁ ባል ከሚስቱ ልጆች ከወላጆቻቸው እኛ ሁላችን በቤታችን በመሥሪያ ቦታችን በተቀደሰው በእግዚአብሔር ስፍራ እንኩዋን ሳይቀር ስንገናኝ የምንጨዋወተው ሀሜትን፣ ርኵሰትን ዘረኝነትን ነው። ለዚህም ነው ዛሬ በቃየል መንገድ ስንጓዝ አምላካችን በመንገዳችን ከእኛ ጋር አብሮን የማይጓዘው።
16.ወተእኅዘ አዕይንቲሆሙ ከመ ኢያእምርዎ
እንዳያውቁት ዓይናቸው ከዕውቀት ተገታ። የአምላካቸው ትንሳኤ በእነርሱ ዘንድ ተዘንግቶ ሥለነበር፤ በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ስለነበሩ አምላካቸውን አላወቁትም።
ተስፋ መቁረጥ ትልቅ ስንፍና ነው። ሰነፍ ደግሞ የእግዚአብሔርን ሀለዎት ይጠራጠራል። “ይብል አብድ በልቡ አልቦ እግዚአብሔር” እንዳለ መዝ 13 ÷ 1
17.ወይቤሎሙ እግዚእነ ምንትኑ ዝንቱ ነገር ዘትትናገሩ በበይናቲክሙ እንዘ ተሐውሩ ትኩዛኒክሙ
ለስም አጠራሩ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አላዋቂ ሥጋን መዋሐዱን አስቀድሞ፤ እንደማያውቅ ሆኖ፤ ካላዋቂነት ወደ ዕውቀት ለማምጣት እንዲህ በድካም ሆናችሁ የምትነጋገሩት ምንድን ነው አላቸው።
ሁልጊዜም የበረቱት ቅዱሳን በድካማቸው በችግራቸው በኃዘናቸው ጊዜ እንኳን ሳይቀር የሚያሳስባቸው ነገረ እግዚአብሔር ነው። ብርሃነ ዓለም የተባለው ቅዱስ ጳውሎስ በ2ኛ ቆሮ 11 ÷ 28 የቀረውንም ነገር ሳልቆጥር ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ሐሳብ ነው እንዳለ፡፡
18.ወአውሥአ አሐዱ እምኔሙ ዘስሙ ቀለዮጳ ወይቤሎ አንተኑ ባሕቲትከ ነግድ ዘኢሀለውከ በኢየሩሳሌም። ወኢያእመርከኑ ዘኮነ በውስቴታ በዝንቱ መዋዕል።
አምላካቸው መምህራቸው ክርስቶስ በተአምራቱና በትምህርቱ በሕዝቡ ሁሉ ዘንድ ታዋቂ ስለነበር ከነርሱ አንዱ ቀልዮጳ አንተ ብቻህን በኢየሩሳሌም አልነበርክምን በዚህ ወራት በርሷ የተደረገውን አታወቅምን አለው።
19. ወይቤሎሙ ኢየሱስ ምንትኑ ውእቱ ወይቤልዎ በእንተ ኢየሱስ ናዝራዊ፡፡
ጌታም ምንድነው አላቸው።እነርሱም የናዝሬቱ ኢየሱስን ነገር ይነግሩት ጀምር።
ብእሲ ጻድቅ ደግ እና የእውነት ሰው
ምግብን አበርክቶ የሚያበላ፣ ለድሆች ለተቸገሩት የሚራራ፣ ሐጢአተኞችን የማይንቅ ከቀራጮች ጋር በማእድ የሚቀመጥ
ወነቢይ አዋቂ የሆነ
በልብ የታሰበውን በአንደበት ሳይነገር የሚያውቅ፤ ስላለፈው ስላለው ስለሚመጣውም ሁሉ የሚናገር፤ የፈሪሳዊያንን ተንኮላቸውን የሚያውቅባቸው
ዘኮነ ከሃሌ በቃሉ ወበምግባሩ በቅድመ እግዚአብሔር ወበቅድመ ሰብእ
በተናገረው ነገር በሚሠራው ሥራ በእግዚአብሔርም ዘንድ በሰውም ዘንድ ማድረግ የሚቻለው። ሙት ማስነሣት፣ ዓይን ማብራት፣ድውይ መፈውስ የሚቻለው፤ የሚሳነው ነገር የሌለ መሆኑን በቁጭት በቅንአት ሆነው የኤማኁስ መንገደኞች ለማያውቁት ሰው ለአምላካቸው ስለ አምላካቸው መሰከሩ። የኤማኁስ መንገደኞች ስለአምላካቸው ሲመሰክሩ አብሯቸው ያለው ሰው ከአይሁድ ወገን መሆኑን እና አለመሆኑን ከሊቃነ ካህናቱ ጋር ነገር ሰርቶ እኛንም ያስቀጣን ይሆን ሳይሉ ብልበ ሙሉነት መስክረዋል።
ዛሬ እኛ ስለ ቤተክርስቲያን ስለ ሃይማኖታችን ስለ ማኅበራችን ስለ አንድነታችን ስንጠየቅ መጀመሪያ ዙሪያ ገባውን መቃኘት የተለመደ ነው፡፡ ጭራሽ አንዳንዶቻችንማ በፈሊጥ መኖር ይገባል በማለት ሲያሙ ማማት ሲያወድሱ ማሞቅን የዕለት ተዕለት ተግባራችን ድርገነዋል። አምላካችን እንደ አባቶቻችን ሃይማኖታችንን በጽብአት የምንመሰክር ያድርገን።
20.ወዘከመ አግብእዎ ሊቃነ ካህናት ወመኳንንቲሆሙ ወኮነንዎ በሞት ወሰቀልዎ
በሐዘን በቁጭት ሆነው የካህናት አለቆችና አለቆቻቸው ለሞት ፍርድ አሳልፈው እንደሰጡት እንደሰቀሉት አብሯቸው ለሚጓዘው ላላወቁት አምላካቸው ነገሩት
21. ወንህነሰ ነአምን ቦቱ ከመ ውእቱ ሀለዎ ያድኅኖሙ ለእስራኤል። ወምስለ ዝንቱ ኩሉ ሠሉስ ዮምእምዘኮነ ዝንቱ
እምነታቸውንም ሲገልጡ እኛ ግን እርሱ እስራኤልን ያድናቸው ዘንድ እንዳለው ሁሉን ማድረግ እንደሚቻለው እናምናለን አሉ። ከዚህም ሁሉ ጋር ይህ ከተደረገ ዛሬ ሦሥተኛ ቀን ነው። አምላክ ቀስ እያደረገ ነገረ ትንሣኤን እንዲያስቡ ስለረዳቸው ቀኑን አስበው ሦሥት ቀን ሆነው አሉት።
22.ወቦ አንስትኒ እለ አንከራ ወነገራነ እለ ጌሣ ኀበ መቃብር ወኢረከባ ሥጋሁ
ወደመቃብር ገስግሰው ሂደው ሥጋውን ባያገኙ አድንቀው የነገሩን ሴቶች አሉ። ሦሥት ቀን ሆኖታል ካሉ በኋላማ ስለትንሳኤው ሐሳባቸውን ወስደው ሥጋው በመቃብር እንዳልተገኘ ነገሩት።
23.ወተሠውጣ ወነገራነ ከመ ርእያ ርእየተ መላእክት እለ ይቤልዎን በእንቲአሁ ከመ ሐይወ
መቃብሩን ያዩ ዘንድ የሄዱ ቅዱሳት አንስት ኢትፍርሃ አንትንሰ እስመ አእምር ከመ ኢየሱስሃ ዘተሰቅለ ተኃሥሣ። እናንተስ አትፍሩ የተሰቀለውን ኢየሱስ እንድትሹ አውቃለሁ።ተንሥአ ኢሀሎ ዝየሰ ተነስቶአል እንጅ በዚህ የለም ብለው የነገሩአቸውን የመላእክትን መልክ እንዳዩ ከመቃብር ተመልሰው ነገሩን።
24.ወቦ እምኔነሂ እለ ሖሩ ኀበ መቃብር ወኢረከቡ ከማሁ በከመ ይቤላ አንስት ወሎቱሰ ኢረከብዎ
ከኛም ወገን ወደ ማቃብር የሄዱ እነ ቅዱስ ጴጥሮስ እና ቅዱስ ዮሐንስ ሴቶች እንዳሉት መቃብሩ ባዶ ሆኖ አገኙት አሉ። እርሱን ግን አላገኙትም።
25.ወይቤሎሙ እግዚእ ኢየሱስ ኦ አብዳን ወጉንዱያነ ልብ ለኢአሚን በኩሉ ዘይቤሉ ነቢያት
ካደመጣቸው በኋላ ነቢያት በተናገሩት ነገር ሁሉ ልቦናችሁ ከማመን የዘገየ እናንተ ያላስተዋላችሁ እያለ እየገሠጸ የጎደላቸውን ሁሉ ሊሞላላቸው ዓይናቸውን ይገልጥላቸው ጀመር።
26.አኮኑ ከመዝ ጽሑፍ ክመ ሀለዋ ለክርስቶስ ከመ ይትቀተል ወይባእ ውስተ ስብሐቲሁ
ክርስቶስ መከራ ይቀበል ዘንድ ወደ ክብሩም ይገባ ዘንድ እንዲገባው ተጽፎ የለምን ብሎ ባለማስተዋላቸው ስንፍናቸውን ገሰፀ
27.ወአኀዘ ይፈክር ሎሙ እምነ ሙሴ ወዘነቢያት ወእምኩሉ መጻሕፍት ዘበእንቲአሁ
ከኦሪት ከመጻሕፍተ ነቢያት ስለእርሱ የተጻፉ እና ስለእርሱ የሚናገሩ መጻሕፍትን እየጠቀሰ እየተረጎመ ይነግራቸው ጀመር።
❖ ኢሳ 53 ÷ 7 “ተጨነቀ ተሰቃየ አፉንም አልከፈተም፣ ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት በሸላቾቹም ፊትም እንደሚል በግ እንዲሁ አፉን አልከፈተም ተብሎ በፈቃዱ እንደሚሞት መነገሩን።”
❖ መዝ.67፥1 “ይትነሣእ እግዚአብሔር ወይዘረው ፀሩ /እግዚአብሔር ይነሣል ጠላቶቹም ይበተናሉ”
❖ መዝ.77፥65 “ወተንሥአ እግዚአብሔር ከመ ዘንቃሕ እምንዋም ወከመ ኃያል ወኅዳገ ወይን ወቀተለ ፀሮ በድኅሬሁ/ እግዚአብሔር ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ተነሣ የወይን ስካር እንደተወው እንደ ኃያልም ሰው ጠላቶቹንም በኋላው መታ”
❖ መዝ.3፥5“አንሰ ሰከብኩ ወኖምኩ ወተንሣእኩ እስመ እግዚአብሔር አንሥአኒ/እኔ ተኛሁ አንቀላፋሁም እግዚአብሔር አሥነስቶኛልና ተ’ነሣሁ”
❖ ዮሐ 2 ÷ 19 “ይህን ቤተመቅደስ አፍርሱት በሦሥተኛው ቀን አሥነሳዋለሁ” ብሎ በፈቃዱ እንደሚነሣ የተናገረውን ለነቢያቱ ለሐዋርያቱ የተገለጠውን ምስጢር በብሉይ የተመሰለውን ምሳሌ እያስረዳ እየተረከ ነገረ ትንሣኤውን በልቡናቸው ሳለባቸው አብራርቶም አስረዳቸው።
28.ወቀርቡ ሀገረ ኀበ የሐውሩ ባቲ ወአኃዘ ይትረኃቆሙ፡፡
ወደ ሚሄዱበት ሀገር፤ ወደ ኤማሁስ በቀረቡ ጊዜ ይርቃቸው ጀመር።
29.ወአገበርዎ ወይቤልዎ ንበር ምስሌነ እስመ መስየ ወተቆልቆለ ፀሐይ።
መሽቶ ፀሐይ ገብቷልና ከእኛ ጋር እደር ብለው ግድ አሉት እርሱም ከእርሳቸው ጋር ሊያድር ገባ።
የአብርሃም ልጆች ናቸውና እንደዚያ መጻሕፍትን እየተረጎመ አለማወቃቸውን እየገሠፀ ያስተማራቸውን አምላካቸውን በቤታቸው እንዲያድር በልቦናቸው እንዲቀመጥ አብሯቸው እንዲሆን ግድ አሉት። ቀኑን በመንገዳቸው የመራቸውን በምሸትም አብሩዋቸው እንዲያድር ተማጸኑት።
30.ወእምዝ እንዘ ይረፍቅ ምስሌሆሙ ነሥአ ኅብስተ ባረከ ወፈተተ ወወሀቦሙ
ከነርሱ ጋርም ተቀምጦ ሳለም ዳቦውን አንሥቶ ጸሎተ ማዕድ ጸልዮ ቆርሶ ሰጣቸው። ምትሐት ያይደለ በእውነት ሰው በእውነት ፍፁም አምላክ የሆነ አምላክ በፍቅር ተወዳጅቶ አብሩዋቸው በማዕድ ተቀመጠ ኅብስቱን ባርኮ ሲሰጣቸው
31.ወተከሥታ አዕይንቲሆሙ ወአእመርዎ ወእምዝ ተሠወረ እምኔሆሙ ወኃጥእዎ
አእምሮዋቸው ተመለሰላቸው አወቁት ከዚህ በኋላ ተሰወረባቸው።
32.ወይቤሉ በበይናቲሆሙ አኮኑ ይነድደነ ልብነ ወይርኅቀነ እንዘ ይነግረነ በፍኖት ወይፌክር ለነ መጻሕፍተ
እርስ በርሳቸው እንዲህ አሉ ልቡናችን ያዝን ይጸጸት የለምን በመንገድ እየነገረን ሲርቀን መጻሕፍትን ሲተረጉምልን እናውቅ ብለን ብለው ወደ ልቡናቸው ተመለሱ
33.ወተንሥኡ ሶቤሃ ይእተ ሰዓተ ወተሰውጡ ኢየሩሳሌም
በዚያን ሰዓት ፈጥነው ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ። አሥራ አንዱን ሐዋርያት ተሰብስበው አገኟቸው እያለ ታሪኩ የጌታን መገለጥ ይቀጥላል። ከዚህ ከኤማኁስ መንገደኞች ብዙ የምንማረው ቁም ነገር አለ። ከብዙ በጥቂቱ በዚህ ዘመን ላለን ክርስቲያኖች አብነት ይሆኑ ዘንድ የተወሰኑትን እናንሣ
- በድካም ሳሉ ይነጋገሩ የነበሩት ነገረ እግዚአብሔርን ነው።
መጻሕፍት ተዘከሮ እግዚአብሔር አምላክከ በኩሉ ጊዜ ወበኩሉ ሰዓት አምላክህን እግዚአብሔርን በጊዜው ሁሉ አስበው/ ብለው እንዲመክሩን በሐዘንም ሆነ በደስታ፣ በመዋረድም ይሁን በከፍታ ሳለን ሁልጊዜ ነገረ እግዚአብሔርን ማሰብ ተገቢ ነው። ቅዱሳን በልቡናቸው ነገረ እግዚአብሄርን እያሰቡ ይመሰጣሉ እኛም ልቡናን ከሚያደክም ዋዛ ፈዛዛ ከሚበዛበት ከዚህ ዓለም ሐሳብና ወሬ ከሀሜት ከማይጸዳው ተንኮል ንትርክ ሽንገላ ከሞላበት ንግግር ይልቅ ነገረ እግዚአብሔርን ማሰብ ይገባናል።
- ስለ አምላካቸው የሰጡት ምስክርነት ደግ ሰው፤ አዋቂ የሆነ፤ በተናገረው ነገር በሚሠራው ሥራ በእግዚአብሔር ዘንድ በሰውም ዘንድ ማድረግ የሚቻለው ብለው ነበር ስለአምላካቸው የገለጡት። ዛሬ እኛ የማእድ ጸሎት ለማድረግ እንኳን ሃይማኖታችን መግለጥ እንፈራለን። ርትዕት በሆነችው ሃይማኖት ውስጥ እየተመላለስን ለሌሎች ሃይማኖታችን ለማሳወቅ እንቸገራለን። በሰው ፊት የሚመሰክርልኝን በአባቴ ፊት እመሰክርለታለሁ የሚለውን አስበን በልባችንም በአንደበታችንም ስለ አምላካችን መግለጥ ይገባናል።
- ወደ ኢየሩሳሌም ፈጥነው ተመለሱ።
ከሰላም ከተማ የቤተክርስቲያን ምሳሌ ከምትሆን ከኢየሩሳሌም ወደ ኤማኁስ ተስፋ በመቁረጥ ጉዞዋቸውን ያደረጉ ሉቃስ እና ኒቆዲሞስ ነገረ ትንሣኤውን በተረዱ ጊዜ ፈጥነው ወደ ኢየሩሳልም ተመለሱ። እኛም በስህተት መንገድ ውስጥ በሆንን ጊዜ የአበው ካህናትን ምክርና ተግሣጽ የሊቃውንት መምህራንን ትምህርት ሰምተን ልቡናችንም በፍቅረ እግዚአብሔር ተቃጥሎ ወደ ኢየሩሳሌም ቤተክርስቲያን መመለስ ያስፈልገናል።
ስብሐት ለእግዚአብሔር ልዑል ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር አሜን።