ሆሣዕና

በኤርምያስ ልዑለቃል

መጋቢት 30 ቀን 2009 ዓ.ም.

ሆሣዕና ቃሉ የዕብራይስጥ ሲሆን ትርጉሙም አሁን አድን ማለት ነው። በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት መሠረት የታላቁ ዓቢይ ጾም ስምንተኛ እሑድ የሆሣዕና በዓል በድምቀት የሚከበርበት ዕለት ነው። በዚህ ዕለት ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በታላቅ ትህትና በአህያ ጀርባ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ያደረገውን ጉዞ የሚዘክር ቃለ እግዚአብሔር በስፋት ይደርሳል። በአራቱም ወንጌላውያን በቅዱስ ማቴዎስ፣ ማርቆስ፣ ሉቃስ ና ዮሐንስ ይህንኑ የፍጹም ትህትና እና የፍቅር ጉዞ አስመልክቶ የተጻፉ የወንጌል ክፍሎች  (ማቴ 21፥1-17 ፣ ማር 11፥1-10 ፣  ሉቃ 19፥28-44 ፣ ዮሐ 12፥9-19) በቅድስተ ቤተ ክርስቲያን ዑደት እየተደረገ በአራቱም አቅጣጫዎች ይነበባሉ።

Hosaena_icon_1

 

“አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ እጅግ ደስ ይበልሽ፤አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ እልል በዪ፤እነሆ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው፤ ትሑትም ሆኖ በአህያም በአህያይቱ ግልገል በውርጫይቱላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል” ዘካ 9፥9

ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅዱሳን ሐዋርያት ጋር ወደ ኢየሩሳሌም ባደረገው ጉዞ ቢታንያና ቤተ ፋጌ አካባቢ ሲደርሱ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን እንዲህ አላቸው “በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ፥ በዚያን ጊዜም የታሰረች አህያ ከውርንጫዋ ጋር ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁ አምጡልኝ ማንም አንዳች ቢላችሁ ጌታቸው ይሻቸዋል በሉ፤ ወዲያውም ይሰዱአችኋል” (ማቴ 21፥2-3)። እነርሱም ለምን እና እንዴት ሳይሉ ያለ አንዳች ጥያቄ በፊታቸው ወዳለው መንደር ተጉዘዋል። እርሱ ቀድሞ የነበረውን፣ አሁንም ያለውን፣ ወደፊትም የሚኖረውን የሚያውቅ አምላክ መሆኑን ተረድተዋልና። የታዘዙት ደቀመዛሙርት ጌታ እንደነገራቸው በመንደሩ የታሰረች አህያ ከነውርንጫዋ አግኝተው እንደታዘዙት ማሰሪያዋን ሲፈቱ ባለንበረቶቹ ወጥተው ለምንድን ነው? ብለዋቸዋል። “እነርሱም እንደታዘዙት ለጌታ ያስፈልጉታል አሉ”። እውነት ነው እርሱ እግዚአብሔር ነውና የፈለገውን ለመከልከል የሚቻለው ማንም የለም። እናም ባለቤቶቹ ያለማጉረምረም ለጌታ የሚያስፈልገውን ሰጡ። ደቀ መዛሙርቱ ከእስር የፈቷቸውን አህያና ውርንጫ ወደጌታ አመጡ እርሱም በአህያ ጀርባ ተቀመጠ።

የጌቶች ጌታ የንጉሦች ንጉሥ የሆነ አምላካችን፥ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለምን ለማዳን ወደዚህ ዓለም ሲመጣ ራሱን ዝቅ አድርጎ በቤተልሔም በከብቶች በረት እንደተገኘ ሁሉ በአህያ ጀርባ ተቀመጠ። ይህ ለአንዳንዶች እንደመሰላቸው በአጋጣሚ የተደረገ ሳይሆን ቀደም ብሎ በብሉይ ኪዳን በመንፈስ ቅዱስ መሪነት በነቢዩ ዘካርያሰ ትንቢት የተነገረለት አምላካዊ ምስጢር ነው። “አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ፥ እጅግ ደስ ይበልሽ፤ አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ፥ እልል በዪ፤ እነሆ፥ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው፤ ትሑትም ሆኖ በአህያም፥ በአህያይቱ ግልገል በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል” (ዘካ 9፥9)። እንኳን ፈሪሳውያኑና ሕዝቡ፥ አብረውት የነበሩ ቅዱሳን ሐዋርያት እንኳን ይህ ስለ እርሱ እንደተነገረ የተረዱት እርሱ በመስቀል ላይ ከከበረ በኋላ ነው። ”ደቀ መዛሙርቱም ይህን ነገር በመጀመሪያ አላስተዋሉም፤ ነገር ግን ኢየሱስ ከከበረ በኋላ በዚያን ጊዜ ይህ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈ ይህንም እንዳደረጉለት ትዝ አላቸው” እንዲል (ዮሐ 12፥16)። በትርጓሜ ወንጌል አህያዋና ውርንጫይቱ ምሳሌነትም አላቸው:- ቀድሞ አባቶች ነቢያት ዘመነ ጸብ የሆነ እንደሆነ በፈረስ ተቀምጠው፣ ዘገር ነጥቀው ይታያሉ። ዘመነ ሰላም የሆነ እንደሆነ በአህያ ተቀምጠው መነሳንስ ይዘው ይታያሉ። አምላካችንም እንደ ከበሩ ነገሥታት ሥርዓት በተንቆጠቆጠ ሰረገላና በፈረስ ሳይሆን በአህያ ውርንጫ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም መግባቱ መንግሥቱ የሰላምና የፍጹም ትህትና መሆኗንና ሁሉም ሰው ተገዶ እና ፈርቶ ሳይሆን በፈቃዱ የሚገባባት መሆኗንም ለማሳየት ነው። አንድም:- ውርንጫይቱ ቀድሞ ምንም ጭነት የማያውቃቸው ሕግን ያልተቀበሉ በሕግ ያልኖሩ አሕዛብ ምሳሌ ስትሆን፣ ጭነት የለመደች አህያይቱ ደግሞ ሕግና ሥርዓት ተሰርቶላቸው የነበሩ የእስራአል ምሳሌ ናት። ኪሩቤል ዙፋኑን የሚሸከሙለት እርሱ ራሱን ዝቅ አድርጎ በተናቀች እንሰሳ ላይ መቀመጡ ዕጹብ ድንቅ ነው!

በዚያን ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ልብሳቸውን እያወለቁ በአህያዪቱ ላይ ጎዘጎዙለት። ”ከሕዝቡም እጅግ ብዙዎች ልብሳቸውን በመንገድ ላይ አነጠፉ” (ማቴ 21፥8)። መንፈስ ቅዱስ ክብሩን የገለጠላቸው ሕፃናትና ሌሎችም ብዙዎች የድል ማብሠሪያ ወይም የድል አድራጊነት ምልክት የሆነውን የዘንባባ ዝንጣፊ እየጎዘጎዙና እልል እያሉ ሆሣዕና በአርያም በጌታ ስም የሚመጣ የእስራኤል ንጉሥ የተባረከ ነው እያሉ ተቀበሉት። ዮሐ 12፥12-13። የጨለማውን ኃይል በሞቱ ድል የሚነሣ እውነተኛ ድል አድራጊ ንጉሥ ነውና መንፈስ ቅዱስ መርቷቸው የዘንባባ ዝንጣፊን ይዘው ተቀበለውታል። በሰው እይታ ምንም አያውቁም የተባሉ ለጋ ሕፃናት የእግዚአብሔር መንፈስ እየመራቸው ”ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ እያሉ እየጮሁ ዘመሩለት”። ጌታችን በፍጹም ትህትና በከብቶች በረት በቤተልሔም በተገኘ ጊዜ ቅዱሳን መላእክት እመቤታችንን እና ልጇን ከበው ያመሰገኑትን ምስጋና ደቀ መዛሙርቱም በትህትና በአህያ ጀርባ ላይ በተቀመጠ ጊዜ ደግመው ”በሰማይ ሰላም በአርያምም ክብር ይሁን” እያሉ አቀረቡለት ሉቃ 19፥37-38። እርሱ የተወለደው ለሰላም ነውና መንፈስ ቅዱስ ባወቀ በታላቅ ድምጽ እንደ ልደቱ ቀን ሁሉ ቅዱሳን ሐዋርያቱ “በሰማይ ሰላም በአርያምም ክብር” አሉ ግሩም ድንቅ  ነው!

በሰማይ ያለ ዕረፍት የሚመሰገን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ተገኝቶ የሕፃናቱን፣ የደቀ መዛሙርቱንና የሕዝቡን ምስጋና ተቀበለ። በዚህ ታለቅ ምስጋና ወደኢየሩሳሌም ሲቃረብ ከምስጋናው ድምጽና ከእርሱም ግርማ የተነሳ ”መላው ከተማ ይህ ማን ነው? ብሎ ተናወጠ” (ማቴ 21፥10)። እርሱማ ቅድመ ዓለም የነበረ፣ አሁንም ያለ፣ ዓለምንም አሳልፎ ለዘለዓለም በመንግሥቱ የሚኖር አምላክ ወልደ አምለክ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ሕፃናቱ ደቀ መዛሙርቱና ሕዝቡ የዘንባባ ዝንጣፊ ይዘው፣ ልብሳቸውን አውልቀው በመንገዱ እያነጠፉለት ”አቤቱ እባክህ አሁን አድን፥ ሆሣዕና በአርያም” እያሉ ሲዘምሩ የካህናት አለቆች፣ ጻፎችና ፈሪሳውያን ብስጭታቸውን መቆጣጠር አልተቻላቸውም። ይህም በንግግራቸው ይታወቃል፥- ”ነገር ግን የካህናት አለቆችና ጻፎች ያደረገውን ድንቃ ድንቅ በመቅደስም ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ እያሉ የሚጮኹትን ልጆች ባዩ ጊዜ፥ ተቈጥተው እነዚህ የሚሉትን አትሰማምን? አሉት። ኢየሱስም፥- እሰማለሁ፤ ከሕፃናትና ከሚጠቡት አፍ ምስጋናን ለራስህ አዘጋጀህ የሚለውን ቃል ከቶ አላነበባችሁምን? አላቸው”። ማቴ 21፥15-16። መዝ 8፥2። በሌላም ሥፍራ ”ከሕዝብም መካከል ከፈሪሳውያን አንዳንዱ:- መምህር ሆይ፥ ደቀ መዛሙርትህን ገሥጻቸው አሉት። መልሶም:- እላችኋለሁ፥ እነዚህ ዝም ቢሉ ድንጋዮች ይጮኻሉ አላቸው” (ሉቃ 19፥ 39-40)። ይህም መልስ ትንቢቱ ይፈጸም ዘንደ ግድ ነውና አይሆንላችሁም የሚል ነው። የካህናት አለቆች፣ ጻፎችና ፈሪሳውያን ጥረት ምስጋናው እንዲቋረጥ ነበር አልሆነላቸውም እንጂ።

ጌታችን ኢየሩሳሌም መግቢያ ላይ ሲደርስ ከተማይቱን አይቶ እንዲህ እያለ አለቀሰላት:- ”ለሰላምሽ የሚሆነውን በዚህ ቀን አንቺስ ስንኳ ብታውቂ፤ አሁን ግን ከዓይንሽ ተሰውሮአል ወራት ይመጣብሻልና፥ ጠላቶችሽም ቅጥር ይቀጥሩብሻል ይከቡሻልም በየበኵሉም ያስጨንቁሻል፤ አንቺንም በአንቺም ውስጥ የሚኖሩትን ልጆችሽን ወደ ታች ይጥላሉ፥ በአንቺ ውስጥም ድንጋይ በድንጋይ ላይ አይተዉም፥ የመጐብኘትሽን ዘመን አላወቅሽምና” (ሉቃ 19፥41-44)። እርሱ ሁሉን የሚያውቅ ነውና ከተማይቱ የሰላም ንጉሥን አሳልፎ በመስጠት የምታጣውን ሰላምና የሚከተላትን ቅጣት ያውቃልና እንባውን አፈሰሰላት። ዕለተ ሆሣዕና ይህ ሁሉ እውነት የሚዘከርባት ታላቅ ዕለት ናት።

በሆሣዕና ዕለት ከተፈጸሙት ተግባራት ምን እንማራለን?

  • ፍጹም ትህትናን

ነብዩ ኢሳይያስ ”እግዚአብሔርን በረጅምና ከፍ ባለ ዙፋን ላይ ተቀምጦ አየሁት፥ የልብሱም ዘርፍ መቅደሱን ሞልቶት ነበር”(ኢሳ 6፥1)። ብሎ የተናገረለት የጌቶች ጌታ የንጉሦች ንጉሥ የሆነ አምላክ ራሱን ዝቅ አድርጎ በአህያ ጀርባ መቀመጡ ፍጹም ትህትናን ያስተምረናል። በከበረ  ቃሉ ”ከእኔ ተማሩ፥ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፥ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ” (ማቴ 11᎓29) እንዳለን የከበረች ትህትናን ከባለቤቱ መማር ይገባናል። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ስለጌታ ትህትና የተናገረውንም ማስተዋል ይገባል ”እርሱ አምላካችን የሁሉ ፈጣሪና የማይመረመረ ክብር ያለው ንጉሥ ሆኖ ሳለ ለክብሩ በሚገባ ባማረና በተንቆጠቆጠ ቤት አልተወለደም ራሱን ዝቅ አድርጎ በበረት ተገኘ እንጂ። በዚህ ዓለም ባለጠግነትና ብዕል ከተትረፈረፈች እናት አልተወለደም ከደሀይቱ ንጽህት ቅድስት ድንግል ተወለደ እንጂ። የትህትና አባት ነውና ደቀ መዛሙርቱን ሲመርጥ እንኳ እንደ ዓለም ምርጫ ተናጋሪዎችና ጥበበኞች አዋቂዎች የተባሉትን ልምረጥ አላለም ከድሀ ቤተሰብ የተገኙ ድሆችን መረጠ እንጂ። ሊያሰተምር በተጓዘበት ሁሉ ከፍ ያለ ዙፋን ዘርጉልኝ መደገፊያ ትራስ አምጡልኝ አላለም ዝቅ ብሎ በምድር ተቀመጠ እንጂ። በሰው ሁሉ ፊት ሲቆም በዕንቁ የተሰራ ልብስ ልልበስ አላለም ከሰዎች እንደ አንዱ ለብሶ ተገኘ እንጂ። ወደ ኢየሩሳሌም ሲጓዝም ፈረስ ጫኑልኝ፣ ልጓም ሳቡልኝ፣ ሰረገላ አዘጋጁልኝ፣ ሠራዊት አቁሙልኝ አላለም ዝቅ ብሎ በአህያ ጀርባ ተቀመጦ ተጓዘ እንጂ” ይህ ግሩም ነገር ነው! ቅዱስ አባ መቃርስም እንዲህ ብሏል ”ጌታ እኛን ስለማዳን እንዲህ ራሱን ዝቅ ካደረገ እኛ ስለራሳችን መዳን ምን ያህል ትህትና ያስፈልገን ይሆን?” የትሁታን አምላክ በቃልም በግብርም ያሰተማረንን የትህትና ግብር ዕለት ዕለት ልናስበው ልንኖረውም ይገባል። ትህትና የተለየው ሕይወት ከእግዚአብሔር መንግሥት ለራቀ ሰው ምልክቱ ነወና።

  • ክብር እና ምስጋናን

የጌታችን የኢየሩሳሌም ጉዞ  በምስጋና እና በክብር የተሞላ ነበር። ደቀ መዘሙርቱ፣ ሕፃናቱ እና እጅግ ብዙ ሕዝብ ደግሞ የለበሱትን አውልቀው መንገድ ላይ እያነጠፉ፣ የዘንባባ ዝንጣፊ እየጎዘጎዙና እያወዛወዙ፣ ሆሣዕና በአርያም እያሉ ዘምረውለታል። ይህ ክብር የካህናት አለቆችን፣ ጻፎችንና ፈሪሳውያንን ደሰ አላሰኘም።

እኛስ ዛሬ እንደ ሕፃናቱ በፊቱ የሚቀርብ እርሱም የሚቀበለው የጸሎትና የምስጋና ሕይወት ይዘናልን? ደቀ መዛሙርቱ ልብሳቸውን እንዳነጠፉለት በንስሐ የነጻ ሕይወታችንን ልናቀርብ ተዘጋጅተናልን? ለምለም የዘንባባ ዝንጣፊን የመሰለ ደምቆ የሚታይ ምግባር  በእጃችን አለን?

  • የእግዚአብሔርን ፍቅርና ርኅራኄ

ጌታችን በኢየሩሳሌም ደጅ ሲቀርብ ከተማይቱን አይቶ ማልቀሱ ለሰው ያለውን ፍጹም ፍቅርና ርህራሄ ያሳየናል። ለሰላም የመጣ አምላክ ነውና ሰላሙን ባለመቀበል ልባቸውን የሚያጸኑ ብዙዎች በኢየሩሳሌም እንዳሉ አይቶአልና ከኀዘኑ የተነሳ የከበረ ዕንባውን አፍስሷል። የካህናት አለቆችና ጻፎች የሚያመሰግኑ ሕፃናትን ድምጽ ላለመስማት ጆሮአቸውን በመድፈን፥ ኋላም ዝም አሰኝልን በማለት በገሃድ ጥላቻቸውን ገልጠዋል። እርሱ የፍቅርና የርህራሄ አምላክ ነውና ልባቸውን አይቶ ስለእነርሱ እንባውን አፈሰሰ። የርህራሄው ጥልቅነት የሚደንቀው ከዕንባው በላይ የከበረ ደሙን በፍጹም ፍቅር ስለ ሁሉ ሊያፈሰ በታላቅ ትህትና በመካከላቸው መገኘቱ ነው።

እግዚአብሔር አምላካችን ፍጹም ትህትና፣ ፍቅርና ርኅራኄ የተሞላ የምስጋና ሕይወት ያድለን ዘንድ፤ መጪውንም ሳምንት በሰላም አሳልፎ ለብርሃነ ትንሣኤው እንዲያደርሰን ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን።

አነሳስቶ ላስጀመረን አስጀምሮ ላስፈጸመን ለልዑል እግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይሁን፤ ለዘለዓለሙ አሜን!