የአውሮፓ ማዕከል ሥራ አስፈጻሚ የገጽ ለገጽ ስብሰባውን አካሄደ።

መጋቢት 10 ቀን 2007 ዓ.ም.

በኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ. ማኅበረ ቅዱሳን የአውሮፓ ማዕከል ሥራ አስፈጻሚ ጉባኤ የ፳፻፯ ዓ.ም. የመጀመሪያውን የገጽ ለገጽ ስብሰባ በዴንማርክ ሀገር በኮፐንሀገን ከተማ በቅዱስ ማርቆስ የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ከመጋቢት ፬-፮ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. አካሄደ።

የሥራ አስፈጻሚ አባላቱ አርብ መጋቢት ፬ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. ኮፐንሀገን ከተማ የተገኙ ሲሆን፣ ምሽቱን ከዴንማርክ ግንኙነት ጣቢያ አባላት ጋር የጋራ የጸሎት መርሐ ግብር በማድረግ ስብሰባውን ጀምረዋል። ከጸሎቱ በመቀጠል በዴንማርክ የደብረ ምሕረት ቅዱስ አማኑኤል ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ የሆኑት መልአከ ምሕረት ቆሞስ አባ ዘሚካኤል ደሬሳ እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት አጭር ቃለ ወንጌልና ምክር ሰጥተዋል። በመቀጠልም የማዕከሉ ሰብሳቢ ዲ/ን ሰሎሞን አስረስ የስብሰባውን አላማ ሲገልጹ ሥራ አስፈጻሚ አባላቱ በተለያዩ ሀገራት ሆነው በስካይፕና በስልክ ከሚያደርጉት ስብሰባ በተጨማሪ አባላቱ በአካል ተገናኝተው የበለጠ ተግባብተውና ተቀራርበው አገልግሎቱን ለማፋጠን እና የማእከሉን ያለፉት ስድስት ወራት አፈጻጸም ለመገምገም እና ቀጣይ አቅጣጫዎችን ለማመላከት ይረዳል በሚል ታሳቢነት መሆኑን ገልጸዋል።

ቅዳሜ መጋቢት ፭ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. ጠዋት ስብሰባው በጸሎተ ኪዳን የተጀመረ ሲሆን የማዕከሉ የ፳፻፯ ዓ.ም. የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት የአፈጻጸም ዘገባ በአገልግሎት ክፍል ኃላፊዎች ቀርቦ ከተገመገመ በኋላ በቀረው ግማሽ ዓመት ማዕከሉ ትኩረት አድርጎ ሊሠራባቸው በሚገባ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጓል። የቀጣና ማዕከላት እና የግንኙነት ጣቢያዎች አፈጻጸም ዘገባም በአባላት፣ በቀጣና ማዕከላት እና በግንኙነት ጣቢያዎች ማስተባበሪያ ክፍል ለጉባኤው የቀረበ ሲሆን ከማዕከሉ በሚያስፈልጋቸው ድጋፍና ክትትል ላይም ጉባኤው ተወያይቷል። በስብሰባው ላይ የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጸሐፊ አቶ ተስፋዬ ቢሆነኝ በስካይፕ ተገኝተው ማኅበሩ አሁን ስላለበት የአገልግሎት ሁኔታ ገለጻ በማድረግ የማኅበሩን መልዕክት አስተላልፈዋል። የውጭ ማዕከላት ማደራጃና ማስተባበበሪያ ዋና ክፍልም የማዕከሉን የአንደኛ ሲሦ ዓመት አፈጻጸም በተመለከተ እንዲሁ በስካይፕ ከጉባኤው ጋር ውይይት አድርጓል። ሥራ አስፈጻሚ ጉባኤው በስብሰባው ሌሎች አጀንዳዎች ላይም ሰፊ ውይይት አድርጓል።

የሥራ አስፈጻሚ አባላቱ እሑድ መጋቢት ፮ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. ጠዋት በደብረ ምሕረት ቅዱስ አማኑኤል ቤተ ክርስቲያን ጸሎተ ቅዳሴ ከተካፈሉ በኋላ ከሰዓት ከዴንማርክ ግንኙነት ጣቢያ አባላት ጋር ግንኙነት ጣቢያው አሁን ስላለበት ነባራዊ ሁኔታ፣ በቀጣይ ሊሰራ ስላቀዳቸው ተግባራት እና ከማእከሉ ሊደረግለት ስለሚገባው ድጋፍ ሰፊ ውይይት አድርገዋል።

በማእከሉ ታሪክ የመጀመሪያ የሆነው ይህ ስብሰባ በአጠቃላይ የተሳካ እና በሥራ አስፈጻሚ አባላቱ ዘንድ የበለጠ መግባባትን፣ መቀራረብን እና ለአገልግሎት መነሳሳትን የፈጠረባቸው መሆኑን አባላቱ ገልጸዋል። እንደዚህ አይነት ስብሰባዎች በዓመት ከአንድ ጊዜ በላይ የቀጣና ማዕከላትን እና ግንኙነት ጣቢያ ተወካዮችን ባካተተ መልኩ መካሄድ እንዳለባቸው የሥራ አስፈጻሚ አባላቱ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

በመጨረሻም የሥራ አስፈጻሚ አባላቱ በነቃ ተሳትፎ፣ በጥሩ አቀባበል እና መስተንግዶ ጉባኤው የተሳካ እንዲሆን ያደረጉትን የዴንማርክ ግንኙነት ጣቢያ አባላት በማመስገን የስብሰባው ፍጻሜ ሆኗል።