በጀርመን ሀገር 2ኛው የሐዊረ ሕይወት ጉዞ ተካሄደ

በአውሮፓ ማዕከል መገናኛ ብዙኀን እና ቴክኖሎጂ አገልግሎት ክፍል

መጋቢት 16 ቀን 2007 ዓ.ም.

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ማኀበረ ቅዱሳን በአውሮፓ ማዕከል የጀርመን ቀጣና ማዕከል አዘጋጅነት የሐዊረ ሕይወት (የሕይዎት ጉዞ) መርሐ ግብር ከመጋቢት 11 እስከ 13 /2007ዓ.ም በክሩፈልባክህ (Kroeffelbach) ከተማ በሚገኘው በቅዱስ እንጦንስ የግብፅ ገዳም (Sankt-Antonius Kloster) ለሁለተኛ ጊዜ ተካሄደ። በመርሐ ግብሩ ላይ ከተለያዩ የጀርመን ከተሞች የመጡ ከ200 በላይ ምዕመናን ተሳትፈውበታል::

fft st Antonie monastry

የጉባኤው ተሳታፊዎች አርብ ምሽት 1 ሰዓት ተኩል ላይ ከፍርንክፈረት 64.5 ኪ.ሜ ላይ እርቀት በሚገኘው የቅዱስ እንጦንስ የግብፅ ገዳም የተገኙ ሲሆን፤ የገዳሙ አባቶችም የመጣውን እንግዳ በትህትና በመቀበልና ለሁሉም የማረፊያ ቦታ ሰጥተዋል።

በመርሃ ግብሩ መሰረት የእራት ማዕድ በአባቶች ተባርኮ እንግዶች ከተመገቡ በኋላ የጀርመን ቀጣና ማዕከል ሰብሳቢ ዲያቆን ዶክተር ያብባል ሙሉዓለም እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት የጉዞውን ዓላማ ገልጸዋል። ከዚህ በማስቀጠል ዲያቆን ያረጋል አበጋዝ ‹‹ቀን ቀጥሮአልና ይመጣል›› በሚል ርዕሥ ተነሥተው ነገረ ምጽአቱን የተመለከተ የወንጌል ትምህርት ተሰጥቶ የመጀመሪያው ዕለት መርሐ ግብር ተጠናቋል።

የቅዳሜ እለቱ መርሐ ግብር / ተሳታፊዎች የግል ጸሎት ቤተክርስትያኑ ውስጥ አድርሰው ቁርስ በጋራ ከተመገቡ በኋላ ከ3፡00 ሰዓት ጀምሮ «የመንፈሳዊ እድገት መሰረቶች እና ማነቆዎቹ» በሚል ርዕስ የደቡብ፣ ደቡብ ምሥራቅና ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት ዋና ጸሐፊ እና በጀርመን ሃገር የካስል ደብረ ቀራንዮ መድኃኔ ዓለም እና የዳርምሽታት ሐመረ ኖህ ኪዳነምህረት አብያተክርስቲያናት አስተዳዳሪ በሆኑት መጋቤ ምሥጢር ኀሩይ ኤርምያስ ሰፋ ያለ ትምህርት ተሰጥቷል። በመቀጠልም በአብይ ጾም ፮ኛው እሁድ ገብር ኄርን አስመልክቶ በቤተክርስቲያን የሚዘመሩ መዝሙራትን በጀርመን ሀገር የካርልስሩኸ ምዕራፈ ቅዱሳን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ የሆኑት መልአከ ስብሐት ተክሌ ሲራክ በዜማ አሰምተው ትርጉማቸውን እና መልእክታቸውንም ለጉባኤው አብራርተዋል።

hh5

በእለቱ ከምዕመናን ለተሰበሰቡ ጥያቄዎች በመጋቤ ምሥጢር ኀሩይ ኤርምያስ እና በዲያቆን ያረጋል አበጋዝ ሰፋ ያለ ጊዜ ተወስዶ መልስ ተሰጥቶባቸዋል። በዚህ መርሃ ግብር ላይ ስርዓተ ቤተክርስቲያን፣ የፈውስ ስርዓት በቤተ ክርስቲያን፣ ነገረ ድኅነት፣ ነገረ ማርያም እና ሌሎችንም ርዕሰ ጉዳዮችም ተነስተዋል። በመቀጠልም ዲያቆን ያረጋል አበጋዝ «መጽሐፍ ቅዱስ ምንነቱ እና እንዴት እንጠቀምበት» በሚል ርዕስ በሁለት ክፍል ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ምንነት እና ሲነበብ ሊደረጉ የሚገባቸውን ጥንቃቄዎችን በተመለከተ ሰፊ ትምህርት ተሰጥቷል::

በማስቀጠልም በአሁኑ ወቅት በስደት ወደ አውሮፓ ሀገሮች በብዛት እየመጡ ያሉት ስደተኞች የሚደርስባቸውን ችግር በተለይም ክርስቲያኖች በዚህ የስደት ወቅት ከቤተክርስቲያናቸው ወጥተው እንዲቀሩ እየደረሰባቸው ያለውን ፈተና የሚያስገነዝብ ገለፃ በዲያቆን ዶክተር ያብባል ሙሉዓለም ተሰጥቶአል። ማኅበረ ቅዱሳን በጀርመን ሀገር የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ ስደተኞች የሚሰጠውን የትምህርተ ወንጌል እና የምክር አገልግሎት ለመደገፍ የተዘጋጀ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር የተካሄደ ሲሆን፤ የተገኘው ገቢም ስደተኞች የሚኖሩበት መጠለያ ድረስ ሄደው ለሚያስተምሩ መምህራን ትራንስፓርት፣ የምስል ወድምጽ እንዲሁም የህትመት ትምህርቶችን መግዣ እንደሚውል ተግልጧል።

የቅዳሜ ምሽት መርሐ ግብር በበዲያቆን ያረጋል አበጋዝ አጠር ያለ ትምህርት ከተሰጠ በኋላ በመጨረሻም የማኀበረ ቅዱሳንን ማንነት አላማውን እና የአገልግሎቱን አድማስ የሚያሳዩ አጫጭር መርሃ ግብሮች ተስተናግደው የዕለቱ መርሃ ግብር በጸሎት ተዘግቷል።

በዚህ ዓመት የተዘጋጀው መርሐ ግብር በ2006 ዓ.ም ከተካሄደው ለየት ባለ መልኩ ለሕፃናት ለብቻቸው መርሐ ግብር ተዘጋጅቶ፤ ከ4 እስከ 13 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ሕፃናት እንደ ጎልማሶች ሁሉ ነፍሳቸውን በእግዚአብሔር ቃል ሲመግቡ ነበር።

hh3

እሁድ ጠዋት የመርሃ ግብሩ ተሳታፊዎች በገዳሙ የቅዳሴ ጸሎት ተሳትፈዋል። ጸሎተ ቅዳሴው ከተጠናቀቀ በኋላ የሐዊረ ሕይወት ተሳታፊዎች በቅዳሴ ጸሎቱ ላይ ከተሳተፉት ግብጻዊያን እህት እና ወንድሞቻቸው ጋር ቁርስ በጋር ተመግበው የሐዊረ-ሕይወት መርሀ ግብሩ ፍፃሜ ሆኗል።

በአጠቃላይ ቀጣና ማዕከሉ በአይነቱ በአውሮፓ ልዩ የሆነውን ይህን መርሐ ግብር ለሁለተኛ ጊዜ ሲያዘጋጅ በ2006 ዓ.ም ግንቦት ላይ ካካሄደው የመጀመሪያው የሐዊረ ሕይወት ጉዞ ልምድ በመውሰድ መርሐ ግብሩን በተሳካ ሁኔታ አካሂዷል። ተሳታፊዎችም በመርሐ ግብሩ እጅግ እንደተደሰቱ እና ለመንፈሳዊ ሕይወታቸው መጠንከር በጣም ጠቃሚ ጉዳዮችን የተማሩበት እንደነበር የገለጹ ሲሆን በዓመት ከአንድ ጊዜ በላይ ቢደረግ የሚሉ አስተያየቶችም ተጠቁመዋል።

በመጨረሻም ቀጣና ማዕከሉ ስለ ሁሉም ነገር ልዑል እግዚአብሔርን በማመስገን እንዲሁም ለመርሐ ግብሩ መሳካት ከፍተኛ ትብብር ላደረጉት፣ ያለ ምንም ወጪ ከ200 በላይ ሰዎችን ላስተናገዱት ለቅዱስ እንጦንስ ገዳም አባቶች በእግዚአብሔር ስም ከፍ ያለ ምስጋናውን አቅርቧል።

እኛም ቀጣና ማዕከሉ ለሌሎች ቀጣና ማዕከላት እና ግንኙነት ጣቢያዎች አርአያ በሚሆን መልኩ ካካሄዳቸውው የሐዊረ ህይዎች ጉዞዎች ልምድ በመውሰድ እንዲሁም የነበሩ ድክመቶችን በመቅረፍ በቀጣይ ለሚያዘጋጀው 3ኛው ሐዊረ ሕይወት የበለጠ በርትቶ እንዲሠራ የእግዚአብሔር ረዳትነት አይለያችሁ እንላለን።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!