የጀርመን ንዑስ ማዕከል ሦስተኛውን ዐውደ ርዕይ በሙኒክ ከተማ አካሄደ።

ሚያዚያ 02 ቀን 2011 ዓ.ም

በጀርመን ንዑስ ማዕከል

“ቤተ ክርስቲያናችንን እንወቅ አስተምህሮዋን እንጠንቅቅ” በሚል መሪ ቃል፥ የተዘጋጀው ዐውደ ርእይ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ለሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በማኅበሩ ንዑሳን ማዕከላት አስተባባሪነት እየቀረበ የሚገኝ ሲኾን፥ ዋና ዓላማውም ቤተክርስቲያንን ለምዕመናን በማስተዋወቅ አስተምህሮዋንና ኹሉን ዓቀፍ ህልውናዋን ለማስቀጠል የበኩሉን አስተዋጽዖ ለማድረግ ነው።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮና ማንነት፤ ሐዋርያዊ አገልግሎቷንና በዘመናት የገጠማትን ተጋድሎ፥ እንዲኹም በአሁኑ ወቅት አንዳንድ ያሉባትን ውስንነቶች ጭምር የሚያስረዳው ዐውደ ርዕይ በጀርመን ቫርያ ግዛት ዋና ማዕከል በኾነችው በሙኒክ ከተማ በደብረ ብስራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ለኢትዮጵያውያንንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን መጋቢት ፳፩ እና ፳፪፥፪፻፲፩ ዓ/ም በጥሩ ሁኔታ ቀርቧል።

ዐውደ ርዕዩ በብፁዕ አቡነ ናትናኤል የምሥራቅ ወለጋ ቄለም ወለጋና ሆሮ ጉድሩ አህጉረ ስብከት ጳጳስ ቃለ ምዕዳን ተባርኮ የተከፈተ ሲኾን፥ በአካባቢው የሚገኙ የአብያተ ክርስቲያናት አስተዳዳሪዎችና አገልጋዮችም በመክፈቻው ላይ ተገኝተዋል። ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ከመክፈቻ ፕሮግራሙ ባስተላለፉት አባታዊ መልእክት እንዲህ ዓይነቱ ዝግጅት በሰማያት ያለውን እግዚአብሔርን የሚገልጥ፥ በሰዎች ፊት የሚበራ መልካም ሥራ ስለኾነ ሊቀጥልና ሊበረታታ እንደሚገባው አስገንዝበዋል። ብፁዕነታቸው አክለውም እነዚህ መንፈሳዊ ጉባዔያት ሰውን ወይም ማኅበራትን ለማክበርና ስምን ለማስጠራት ታስበው የሚደረጉ ሳይኾኑ፥ እግዚአብሔር እንዲመሰገንና ህዝበ ክርስቲያኑ በአምልኮ ጸንቶ መንግስቱን እንዲወርስ የሚያስችሉ ስለኾኑ፥ አሁን ባሉበት ኹነት የእግዚአብሔርንና የቤተ ክርስቲያንን ክብር አጉልተው በመግለጥ እንዲቀጥሉ አደራ ብለዋል።

 

ዐውደ ርዕይውን የተከታተሉት ብዙዎች ምዕመናን በበኩላቸው በዚህ መልኩ የተዘጋጁ መንፈሳዊ ዐውደ ርዕይዎችን ዐይተው እንደማያውቁና በዝግጅቱም ደስተኞች እንደኾኑ ገልጸዋል። ቤተ ክርስቲያናችን ዘመኑን ዋጅታ፥ ትውልዱን ለመጠበቅ እየተጋች መኾኑን የሚያሳይ መልካም ጅምር ነው፥ በማለትም ስለ ዐውደ ርዕይው የነበራቸውን ስሜት አካፍለዋል። ወደፊትም እንዲህ በተደራጀ መልኩ ዝግጅቶች በተደጋጋሚ ቢደረጉ መልካም ነው፥ በማለት አዘጋጁን የጀርመንን ንዑስ ማእከልን አሳስበዋል።

ዐውደ ርዕዩ በኹለት ቀን ዝግጅት በዘጠኝ ዙር ተጎብኝትዋል። ከከተማው ውጭ ያሉ ማኅበራትም ብዙ ኪሎ ሜትሮችን ተጉዘው በመምጣት ተሳታፊዎች ሆነዋል። ዐውደ ርዕዩ በሌሎች አካባቢ እንዲቀርብ በቀረበው ጥያቄ መሠረት ባጭር ጊዜና በተቀናጀ መልኩ በሌሎች የበቫርያ ግዛት በሚገኙ ከተሞች ለማሳየት እቅድ ላይ እንዳለም በንዑስ ማእከሉ ተጠቁማል።

በቦታው ከተዘጋጀው ዐውደ ርዕይ በተጨማሪ በእለተ እሑድ ከቅዳሴ በኋላ ከ350 በላይ ለሚኾኑ የደብሩ ምዕመናን ማኅበረ ቅዱሳን በ2011 ዓ/ም ሊሠራቸው ካቀዳቸው የፕሮጀክት እቅዶች አምስት ያክሉን በመምረጥ ከአጭር ዘጋቢ ፊልም ጋር ገለጻ ተደረጓል። የፕሮጀክት ገለጻው ዓላማ የማኅበሩን እቅንቅስቃሴ በሐሳብ፥ በጉልበትና በገንዘብ ለመደገፍ ፈቃደኛ የኾኑ አቅም ያላቸው አካላት ተሳትፎ እንዲያደርጉ ለማሳወቅ ታስቦ የቀረበ ሲኾን፥ ብዙዎችም በደስታ ተከታትለው፥ ቀና ምላሻቸውንም አሳይተውበታል። በመጨረሻም ዐውደ ርዕዩ እሑድ ከቀኑ 11 ሰዓት ላይ ተጠናቋል።