“ተወልደ ኢየሱስ በቤተ ልሔም ዘይሁዳ”(ቅ. ያሬድ)
ታኅሣሥ 28 ቀን 2004 ዓ.ም.
በቀሲስ ደመቀ አሸናፊ
በጌታችንና በአምላካችን በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የተደረገልን ፍፁም ሥርየትና እርቅ ግልጥ ሆኖ የተጀመረው በነገረ ልደት ነው። የጌታችን ልደት በነገረ ድኅነት ትልቅ ስፍራ የያዘና እግዚአብሔር ሰው ሆኖ ዓለምን ያዳነበት ጥበቡ ፍፁም ልዩ መሆኑን ያሳየ ነው። መስተፃርራን የነበሩ ሰማይና ምድር፣ ሰውና መላእክት በአንድነት ለምስጋና ታድመዋል። የእረኞች አንደበት ከመላእክት ጋር ለሰማያዊ ምስጋና ብቁ የሆነበት፤ ግዕዛን የሌላቸው እንስሳት ሰራኢ መጋቢያችን፣ በዘባነ ኪሩቤል በሰማያት የምትገለጥ አንተ ነህ ሲሉ እስትንፋሳቸውን የገበሩለት፤ የምድር ነገስታት በሥልጣንህ ሽረት በመንግሥህ ህልፈት የሌለብህ የነገስታት ንጉሥ አንተ ነህ ሲሉ ወርቅን ለመንግሥቱ፣ ዕጣንን ለክህነቱ፣ ከርቤን ለህማሙ ዕጅ መንሻን ያበረከቱለት፤ ወላዲተ አምላክ ቅድስት ድንግል ከጻድቁ ዮሴፍ ጋር ያን ልዩ ክብር የዩበት፤ ይህ ልደት በእውነት ልዩ ነው።
ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ በረቡዕ ውዳሴ ማርያም በጌታ ልደት የተደረገልንን ድንቅ የማዳን ሥራ በተናገረበት ድርሳኑ እንዲህ ነበር ያለው፦ “በጨለማና በሞት ጥላ ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች ታላቅ ብርሃን ወጣላቸው፤ በቅዱሳን የሚያድር እግዚአብሔር እኛን ለማዳን ልዩ ከሆነች ድንግል ሰዉ ሆኗልና ኑ ይህን ድንቅ እዩ፣ ስለተገለጠልን ምስጢር ምስጋና አቅርቡ ሰው የማይሆን ሰው ሆኗልና ቃል ተዋህዷልና ቅድምና የሌለው ሥጋ ጥንታዊ ቀዳማዊ ሆነ፣ ዘመን የማይቆጠርለት መለኮት ዘመን ተቆጠረለት።”
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ “ይህች ቤተልሔም መንግሥተ ሰማያትን መሰለች” አለ፤ የጌታን ልደት በተናገረበት አንቀጽ። በአባታችን በቀዳማዊ አዳም ምክንያት ያጣናትን ልጅነት ሊሰጠን ዳግማዊ አዳም ክርስቶስ የመንግሥተ ሰማያትን የምስጋና ኑሮ በቤተልሔም ገልጧልና። ስለዚህ ነገር ነቢየ እግዚአብሔር ሚክያስ “አንቺ ቤተልሔም ኤፍራታ አንቺ ከይሁዳ አእላፍ መካከል ትሆኝ ዘንድ ታናሽ ነሽ ከአንቺ ግን አወጣጡ ከቀድሞ ጀምሮ ከዘላለም የሆነ በእስራኤል ላይ ገዢ የሚሆን ይወጣልና፤” በማለት የተነበየውም ስለዚህ ነበር ፤ ሚክ5፥2። “ወአንቲኒ በቤተልሔም ምድረ ኤፍራታ ኢትቴሃቲ እምነገሥተ ይሁዳ እስመ እምኔኪ ይውጽእ ንጉሥ ዘይርዕዮሙ ለህዝብየ እስራኤል” እንዲል ቅዱስ ኤፍሬም።
ቤተልሔም ማለት ቤተ ህብስት፣ የህብስት ቤት፣ የእንጀራ ቤት ማለት ነው። ይህም ካሌብ እስራኤል ዘሥጋ ምድረ ርስት፣ ኢያሪኮን “ሃይል ዘእግዚአብሔር ኲናት ዘኢያሱ” ብለው በኢያሱ መስፍንነት ሲወርሱ ከኢያሱ የተሰጠችው ምድር፣ ኬብሮን ነበረች። ይህችም የይሁዳ ምድር በኋላም የቅዱስ ዳዊት ከተማ የሆነች ናት። አስቀድሞ ካሌብ ከብታ የምትባል ሚስት አግብቶ በሚስቱ ከብታ አላት ትርጓሜውም የምስጋና ቤት ማለት ነው፤ ይህም ካሌብ በመንፈሰ እግዚአብሔር በዚህች ምድር የሚገለጠውን የክርስቶስ የልደቱን ነገር፣ እና የመላእክትን ምስጋና ስለተረዳ ነበር። በኋላም ካሌብ ኤፍራታ የምትባል ሚስት አገባ ቦታዋን በዚህች ሚስቱ እንደገና ኤፍራታ ብሎ ጠራት። ኤፍራታ ማለት ፀዋሪተ ፍሬ፣ ፍሬ በውስጧ ያለባት ማለት ነው። ይህችውም የእመቤታችን ምሳሌ ናት የህይወት ፍሬ ክርስቶስን ወልዳልናለችና፤ አንቲ ውእቱ ዕፅ ቡሩክ ፍሬኪኒ ፍሬ ሕይወት እንዳለ ቅዱስ ያሬድ በአንቀጸ ብርሃን። ቤተልሔም ይህን ስያሜዋን ያገኘችው ካሌብ ከኤፍራታ ባገኘው ልጁ በልሔም ነው፤ ልሔም ማለት ህብስት፣ እንጀራ ማለት ነው ይህም ምሳሌነቱ የጌታ ነው፤ ይኸውም አማናዊ፣ እውነተኛ የሕይወት እንጀራ፣ህብስት ክርስቶስ ሥጋውን ቆርሶ ደሙን አፍስሶ ሊያድነን የመወለዱ ምሳሌ ነው። “ከሰማይ የወረደ ህያው እንጀራ እኔ ነኝ ሰው ከዚህ እንጀራ ቢበላ ለዘላለም ይኖራል እኔም ስለዓለም ህይወት የምሰጠው እንጀራ ሥጋዬ ነው።” እንዲል ዮሐ 6፥51።
በክርስቶስ ልደት መላእክት ባልተለመደ ሁኔታ ከሰዎች ጋር ተባብረው “ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ሥምረቱ ለሰብእ” በሰማያት ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን ሰላምም ለሰው ልጅ በምድር እርሱ በሚፈቅደው እያሉ ንጉሥ ክርስቶስን አመሰገኑ። ሉቃ 2፥14። በሰማያት በዘባነ ኪሩቤል የሚገለጥ፤ ፍፁማን ግሩማን በሚሆኑ መላእክት፣ ሊቃነ መላእክት፣ ሥልጣናት፣ አጋእዝት የሚመሰገን ሰማያዊው ንጉሥ ዛሬ ስለእኛ ፍቅር ሲል ሊነገር በማይችል ፍፁም ትህትና ከመ ሕጻናት ታቅፎ፣ ከኀጢአት ብቻዋ በቀር የኛን ባህሪ ባህርዩ አድርጎ ፍፁም አምላክ ሲሆን ፍፁም ሰው ሆኗልና።”ሕፃን ተወልዶልናልና፥ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይኾናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፥ኀያል አምላክ፥የዘለዓለም አባት፥የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል።” ትኢሳ 9፥6።
ለዚህ ለክርስቶስ ፍቅር አንክሮ ይገባል፤ በሙሉ አፍአዊና ውሳጣዊ ህሊናችን እርሱን ዘውትር እናመስግን። ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ዻውሎስ ይህን ፍፁም ፍቅር ለሰው ልጅ በኀጢዓት ተዳድፈን ለነበርን መደረጉን እያሰበ በአንክሮ “ታስበው ዘንድ ሰው ምንድር ነው፧ወይስ ትጐበኘው ዘንድ የሰው ልጅ ምንድር ነው፤ ከመላእክት ይልቅ በጥቂት አሳነስኸው፤ የክብርና የምስጋና ዘውድ ጫንኽለት፥በእጆችኽም ሥራ ላይ ሾምኸው፤ዅሉን ከእግሮቹ በታች አስገዛኽለት” በማለት ይናገራል። ዕብ 2፥6።እኛም በክርስቶስ የተጠራን ሁላችን ይህን ያምላክ ፍቅር ዘወትር በልቡናችን እንድንስልና ከባልንጀሮቻችን ጋር በትህትናና በፍቅር እንድንኖር ሲመክረን፦ “እያንዳንዱ ለራሱ የሚጠቅመውን አይመልከት፥ለባልንጀራው ደግሞ እንጂ፤ በክርስቶስ ኢየሱስ ያለች ይህች ሃሳብ በእናንተ ዘንድ ደግሞ ትኑር፤ እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከሰው ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ አልቆጠረም ነገር ግን፥የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ኾኖ ራሱን ባዶ አደረገ፤” ይለናል፤ ፊል 2፥5።
ይህ የጌታ ልደት የቤተ ክርስቲያን አንድነት ነው። ሁሉ በአንድነት የተሰባሰቡበት በጋራ የዘመሩበት፤ በዚይች በበረት፣ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ምሳሌ በሆነችው ጌታችን ከመሀል ከእናቱ ጋራ እንዲሁም አረጋዊ ዮሴፍ ከማሕበረ ጻድቃን፣ ሰማያውያን መላእክት፣ እረኞች፣ ሰባሰገል ነገሥታት፣ እንስሣትም ሳይቀሩ ባንድነት የተገኙባት የፍቅርና ያንድነት ቤት ናት። ስለዚህ እኛም የክርስቶስ አባግዓ መርዔቱ፣ የመንጋው በጎች፣ የቤተ ክርስቲያን ልጆች በፍፁም አንድነት መኖር እንዳለብን “ወንድሞች ሆይ፥ዅላችኹ አንድ ንግግር እንድትናገሩ፤ ባንድ ልብና ባንድ ሃሳብም የተባበራችኹ እንድትኾኑ እንጂ መለያየት በመካከላችኹ እንዳይኾን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እለምናችዃለኹ።” የተባለውም ስለዚህ ነውና። 1ኛቆሮ 1፥10። በማለት ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ዻውሎስ ያስተምረናል። የጌታችንና የአምላካችን የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደቱ በዓል በረከት ከሁላችን ጋር ይሁን። አሜን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር። አሜን።