ሀገረ ስብከቱ አብይ ጉባዔ አደረገ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በደቡብ፤ ደቡብ ምሥራቅና ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት በሮም ኢጣሊያ የሀገረ ስብከቱ አብይ ጉባዔ ተደረገ።

ብፁዕ አቡነ ሙሴበብፁዕ አቡነ ሙሴ የደቡብ፤ ደቡብ ምሥራቅና ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ሰብሳቢነት በሀገረ ስብከቱ ሥር ያሉት አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት አስተዳዳሪዎች እና የሰባካ መንፈሳዊ ጉባዔ ተወካዮች በተገኙበት መስከረም 18 እና 19 ቀን 2004 ዓ.ም. በሮም ኢጣሊያ ሀገረ ስብከቱን በአዲስ ለማጠናከር ታስቦ የተዘጋጀ አብይ ጉባዔ ተደርጓል።

ጉባዔው 16 ተሳታፊዎች ነበሩት። ጉባዔውን በጸሎታቸው የከፈቱት ብፁዕነታቸው የሀገረ ስብከቱ መጠናከር የሚያስገኘውን ፋይዳ ከልምዳቸው እና ከቃለ ዓዋዲው በመነሳት በሰፊው አብራርተዋል። ሀገረ ስብከቱ ቢጠናከር ያልተቋረጠ እና ማዕከላዊነቱን የጠበቀ አገልግሎት ለመስጠት፤ አስተዳደራዊ እና ሌሎች ችግሮችም ሲከሰቱ ወቅታዊ መፍትሔ ለመስጠት፤ ቤተክርስቲያን በሌለበት ህዝቡን አስተባብሮ ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን በተከተለ መንገድ ቤተክርስቲያን ለመትከል እና አጠቃላይ የአስተዳደር ሥራው መዋቅሩን ጠብቆ እንዲሄድ ለማስቻል እንደሚረዳም አስገንዝበዋል። የጉባዔው ተሳታፊ አባቶች እና የሰበካ መንፈሳዊ ጉባዔ ተወካዮችም ሀገረ ስብከቱ ቢጠናከር ሊያስገኘው የሚችለውን ጥቅም እና ሀገረ ስብከቱ ባለመጠናከሩ ምክንያት የተፈጠሩትን ከፍተኛ የአሠራር ጉድለቶች እና ያስከተሏቸውን ችግሮች ለጉባዔው ይፋ አድርገዋል።

ጉባዔው በሁለት ቀን ስብሰባው በቀረቡለት አጀንዳዎች ላይ በጥልቀት ተወያይቶ የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳልፏል። የሀገረ ስብከቱን ሥራ አስኪያጅ እና ዋና ጸኃፊ መርጧል፤ የሀገረ ስብከቱን የ2004 ዓ.ም.ዓመታዊ በጀት አጽድቋል፤ አምስት አባላት ያሉት የሀገረ ስብከት የስብከተ ወንጌልና ልማት ኮሚቴ አቋቁሟል።በ2004 ዓ.ም. እንዲከናወኑ ከተያዙ ዕቅዶች ውስጥም፡- ሀገረ ስብከቱ ህጋዊ እውቅና እንዲያገኝ መስራት፤ የስብከተ ወንጌል መርሐ ግብራትን ማዘጋጀት፤የገቢና ወጪ መሰብሰቢያ ደረሰኞችን ለየአጥቢያ ቤተክርስቲያናት ማዳረስ እና የሀገረ ስብከቱን መካነ ድር(ድረ ገጽ) መገንባት የሚሉት ይገኙበታል።

ብፁዕነታቸው ባስተላለፉት አባታዊ ምክርና መመሪያ አገልጋዮች የተሰጣቸውን ከፍተኛ የቤተክርስቲያን አደራ በአግባቡ እንዲወጡ ፤ ለምዕመናንም አርአያ እንዲሆኑ እና በሥራ የሚተረጎም መንፈሳዊ አገልግሎት እንዲሰጡ መክረዋል። የሰበካ መንፈሳዊ ጉባዔ አገልግሎትም ማዕከላዊነትን የጠበቀ እና በዕቅድ የሚመራ እንዲሆን አሳስበዋል።

የጉባዔው ተሳታፊዎች
የጉባዔው ተሳታፊዎችም ማኅበረ ምዕመኑን በማስተባበር ለሀገረ ስብከቱ መጠናከር አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብታዋል። የቀጣዩ ዓመት አብይ ጉባዔ ከመሰከረም 13 እስከ መስከረም 16 2005 ዓ.ም. እንዲሆን የወሰነው ጉባዔ በብፁዕነታቸው አባታዊ ምክር፤ ጸሎት እና ቡራኬ ተፈጽሟል።