ሠለስቱ ደቂቅ

እንደምን ሰነበታችሁ ልጆች?ደህና ናችሁ ልጆች? ዛሬ ስለ ሦስቱ ልጆች ታሪክ እንነግራችኋለን በደንብ ተከታተሉን እሺ፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚነግረን፣ በድሮ ጊዜ እግዚአብሔርን የማይፈራ ናቡከደነፆር የሚባል የባቢሎን ንጉሥ ነበር፡፡ይህም ንጉሥ ከወርቅ የተሰራ ትልቅ ጣኦት አቁሞ ሕዝቡንም ሁሉ ሰበሰበና ለጣኦቱ እንዲሰግዱ አዘዘ፡፡ ለጣኦት ያልሰገደ ግን በእሳት ውስጥ ይጣላል ብሎ አዋጅ አስነገረ፡፡

ሠለስቱ ደቂቅከሕዝቡም መካከል ሚሳቅ፤ሲድራቅ እና አብደናጎም የተባሉት ልጆች ግን ለጣኦቱ አንሰግድም አሉ፡፡ምክንያቱም እግዚአብሔርን ስለሚወዱ ለእርሱ ስለሚገዙ ነው፡፡ንጉሡ እነዚህ ልጆች ለጣኦቱ አንሰግድም በማለታቸው በጣም ተቆጥቶ ካልሰገዱም ወደ እሳት እንደሚጣሉ ነገራቸው፡፡ልጆቹም የሚያመልኩት አምላክ በሰማይ እንዳለና እርሱም ከእሳቱ እንደሚያድናቸው ነገሩት፡፡ ንጉሡም በመለሱለት መልስ ይበልጥ ተቆጣ፡፡ እሳቱንም ይነድ ከነበርው ሰባት እጥፍ እንዲያነዱትና ወደ እሳቱ ውስጥ እንዲጥሏቸው አዘዘ፡፡

አያችሁ ልጆች፣ ሲድራቅ ሚሳቅና አብደናጎም ወደ እሳቱ ተጣሉ ነገር ግን እሳቱ አላቃጠላቸውም፡፡ በእሳት ውስጥ ሆነው እግዚአብሔርን በመዝሙር እያመሰግኑ ሳለ ከእነርሱም ጋር ከእሳቱ ሊያድናቸው ከእግዚአብሔር ዘንድ የተላከው መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ታየ፡፡ ንጉሱም በእሳቱ ውስጥ አራት ሆነው በደስታ ሲመላለሱ አይቶ በጣም ስለተገረመ ከእሳቱ እንዲያወጧቸው አዘዘ። እነሚሳቅም ከፀጉራቸው አንዲቷ እንኳን ሳትቃጠል በሰላም ከእሳቱ ወጡ፡፡ንጉሡም ባየው ተዓምር ተደንቆ በፊታቸውም ለእግዚአብሔር ሰገደ።

አያችሁ ልጆች! አናንያ አዛርያ ሚሳኤል በጣም ጎበዝ ልጆች ናቸው፤ አምላካቸው እንደሚያድናቸው በሁሉም ቦታ ቢሄዱ ከእነርሱ ጋር እንደሆነ ስለሚያምኑ እሳቱን አልፈሩም፡፡እግዚአብሔርም ስለእምነታቸው ጽናት እሳቱን አቀዘቀዘው፡፡በሰላም ከእሳቱም አወጣቸው፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር