እስክመጣ ድረስ ያላችሁን ጠብቁ (ራእ ፪፡፳፭)
በዲ/ን ሰሎሞን መኩሪያ
ጥቅምት 29 ቀን 2006 ዓ.ም.
ይህንን ኃይለ ቃል የተናገረው ቅዱስ እግዚአብሔር በሐዋርያዉና ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ አማካኝነት ነው። ቅዱስ ዮሐንስ ከዓሣ አጥማጅነት ከተጠራበት ጊዜ አንስቶ ጌታችንን እስከ እግረ መስቀል ድረስ ተከተሎታል፤ በዚያም የጌታችንን መከራ እየተመለከተ ቢያዝንና ቢያለቅስ ይጽናና ዘንድ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን እንሆ እናትህ በማለት የእናትነት ቃል ኪዳን ተቀብሏል። እርሷንም ወደ ቤቱ ወስዶ ፲፭ ዓመት ታጥቆ አገልግሏታል።
በስብከተ ወንጌልም ኤፌሶን ሂዶ በዚያም ወንጌልን ለማስተማር ከጣዖት አምላኪው ንጉስ ድምጥያኖስ ብዙ መከራን ተቀብሏል። በዚያም ለነበሩ ምእመናን የሃይማኖት ጽናትንና መከራ በመቀበልን እያስተማረ ሰባት አብያተ ክርስትያናትን ከመሠረተ በሁዋላ ከንጉስ ድምጥያኖስ ግዞት ተፈርዶበት ፍጥሞ ወደ ምትባል ደሴት ተግዞ በዚያም በምድርና በሰማይ ያለውን ወደፊትም የሚደረገውን ነገር በራእይ ተገልጾለት ጽፏል። በኋላም በ፺፱ ዓመቱ ሞትን ሳያይ የተሰወረ የቤተ ክርስቲያናችን ታላቅ ቅዱስ ነው። (ማቴ ፬፥፲፱፥ ዮሐ ፲፱፥፳፮፤ ዮሐ ፳፩፳–፳፬)
ቅዱስ ዮሐንስ በአረመኔውና ጨካኙ ንጉሥ ድምጥያኖስ ግዞት ተፈርዶበት በፍጥሞ ደሴት ሳለ ለቅዱሳን የሚገለጥ ቅዱስ እግዚአብሔር በራእይ ተገለጠለት። እግዚአብሔርም ለቅዱስ ዮሐንስ ለሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት አስተዳዳሪዎች መልእክትን ይልክ ዘንድ እንዲህ ብለህ ጻፍ በማለት ትእዛዝ ሰጠው። በወቅቱ ቤተ ክርስቲያንን ያስተዳድሩ የነበሩ አስተዳዳሪዎች መልካም አገልግሎት ቢኖራቸውም በተቃራኒው ደግሞ አገልግሎታቸውን የሚያስነቅፍ ተግባር ይሰሩ እንደነበር ቅዱስ ዮሐንስ በክታቡ በዝርዝር አስቀምጧል። እግዚአብሔር መልካም አገልግሎትን በምሥጋና፣ ለእርሱ የማይመች ሥራን ደግሞ በወቀሳና በማስጠንቀቂያ በዮሐንስ አማካኝነት መልእክት እንዲደርሳቸው አድርጓል።
ከእነዚህም መካከል በትያጥሮን ለሚገኘው የቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ “ሥራህንና ፍቅርህን እምነትህንም አገልግሎትህንም ትዕግሥትህንም ከፊተኛውም ሥራህ ይልቅ የኋለኛው እንዲበዛ አውቃለሁ። ዳሩ ግን። ነቢይ ነኝ የምትለውን ባሪያዎቼንም እንዲሴስኑና ለጣዖት የታረደውን እንዲበሉ የምታስተምረውንና የምታስተውን ያችን ሴት ኤልዛቤልን ስለምትተዋት የምነቅፍብህ ነገር አለኝ፤ ንስሐም እንድትገባ ጊዜ ሰጠኋት ከዝሙትዋም ንስሐ እንድትገባ አልወደደችም።” (ራእ ፪፥፲፱_፳፩) የሚል መልእክት ከቅዱስ ዮሐንስ ደረሰው። ይህ መልክት በቀጥታ ለትያጥሮን ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ይጻፍ እንጂ መልክቱ ግን ዛሬም ቤተ ክርስቲያንን በማስተዳደር ላይ ለሚገኙ አባቶች ሁሉ ነው። የትያጥሮን አስተዳዳሪ ፍራትንና ዝምታን አሶግዶ ኤልዛቤልን ከመጥፎ ተግባሯ እንድትመለስ ማስተማር፣ መምከርና መገሠጽ ይችል ነበር፤ ዳሩ ግን አላደረገውም። ቅዱስ ዮሐንስ ለትያጥሮን አስተዳዳሪ ብቻ ጽፎ መልክቱን አልቋጨም፤ ይልቁንም ለምእመናን ምን ማድረግ እንደሚገባቸው በግልጽ አስቀምጧል። ያቺን ክፉና አምንዝራ ሴት ኤልዛቤልን ተከትለው በኃጢአት ሰጥመው ለሚገኙ ምእመናን ንስሐ እንዲገቡና ከክፉ ሥራቸው እንዲመለሱ፤ ንስሐ ባይገቡ ግን የሥጋ መከራና የነፍስ ሞት እንደሚጠብቃቸው መልክቱን በሚገባ አስተላልፏል።
በተቃራኒው ደግሞ ከዚህች ሴት ርቀው፣ ክፉ ሥራዋንም ተጠይፈው አምላካቸውን እግዚአብሔርን አክብረውና ሕጉንም ጠብቀው ለኖሩትም እንዲሁ መልክቱን በሚያበረታና በሚያጸና መልኩ አስተላልፏል። ለርዕሳችን መነሻ በአደረግነም ኃይለ ቃል “እስክመጣ ድረስ ያላችሁን ጠብቁ” ብሎ በሀይማኖታቸው እንዲጸኑ፣ በአገልግሎታቸው እንዲበረቱ፣ ከኃጢአት እዲርቁና ያላቸውን መንፈሳዊ ጸጋ እንዲጠብቁ በአጽንኦት መክሯቸዋል። ይህ ኃይለ ቃል ለትያጥሮ ክርስቲያኖች ብቻ ሳይሆን ዛሬ ላይ ላለን ለእኛና ለትውልድ ሁሉ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም በእለተ ምጽዓት እስኪመጣ ድረስ ልንጠብቀውና ልንተገብረው የሚገባንን ነገር ያስገነዝበናል። ጌታችን በአካለ ሥጋ በምድር በነበረበት ጊዜ “ብትውዱኝ ትእዛዜን ጠብቁ” (ዮሐ ፲፬፥፲፭) ብሎ ትእዛዙንና ሕጉን ከጠበቅን ልጅነታችንና ወዳጅነታችን ዘላለማዊ እንደሚሆን አስተምሮናል። እንደ ትያጥሮን ሰዎች እስክመጣ ድረስ ያላችሁን ጠብቁ እንደተባሉ ሁሉ እኛም እስከ ሕይወታችን ፍጻሜ ድረስ ልንተገብራቸው የሚገቡ ሦስት አበይት መንፈሳዊ ተግባራትን እንመልከት።
ሀ፡ ሀይማኖት
ሀይማኖት ሰው ከእግዚአብሔር ጋር የሚገናኝበት ቀጥተኛ መንገድ ነው። ነቢዩ ኤርምያስ በትንቢቱ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ በመንገድ ላይ ቁሙ ተመልከቱ መልካሚቱ መንገድ ወዴት እንደሆነች እወቁ። በእርሷም ላይ ሂዱ፤ ለነፍሳቸሁም እረፍት ታገኛላችሁ።” (፮፥፲፮) ነቢዩ ሰዎች ስለሚመላለሱበት የእግር መንገድ ገዶት አይደለም። መንገድ የተባለች ሃይማኖት ናት። የቀደመችው የተባለችውም መላእከት፣ ነቢያት፣ ሐዋርያት፣ ሰማእታት፣ ጻድቃን ቅዱሳን የሄዱባት ከእግዚአብሔር ዋጋ ያገኙባት እኛ ዛሬ እየሄድንባት (እያመንባት) ያለችው ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖታችን ናት።
እግዚአብሔር የመሰረታትን ይቺን የቀደመችው መንገድ ሃይማኖታችንን አጽንተን እንድንጠብቅ ያስፈልጋል። ነገር ግን አንዳንድ ሰዎች ሃይማኖትን የተከተሉ የሚመስሉት የሚፈልጉትን ሥጋዊ ነገር ከእግዚአብሔር እስከሚያገኙ ድረስ ብቻ ይሆናል። ሌሎች ደግሞ ሀይማኖት የሚጠበቀው በሀገር ቤት እንጂ በባእድ ሀገር ሃይማኖትን መጠበቅ አስቸጋሪ ነው ብለው ስጋዊ ምክንያት ሲያቀርቡ ይሰማሉ። በተቃራኒው ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚያስረዳን በባእድ ሀገር ሀይማኖታቸውን ጠብቀው በመገኘታቸው እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር መሆኑ በተደረገላቸው ተአምራት የተመሰከረላቸው ብዙ ቅዱሳን አሉ። ለምሳሌ በትንቢተ ዳንኤል (፫፥፩) ጀምሮ የምናገኛቸው ሶስቱ ወጣቶች በሃይማኖት ምክንያት ወደ ሚነደው እሳት እስኪጣሉ ደርሰው ሃይማኖታቸውን አልካዱም፤ ወደ እሳቱ ቢጣሉም አምላካችን እግዚአብሔር መልአኩ ቅዱስ ገብርልን ልኮ አሳቱን አጠፋላቸው። በዚህ የሃማኖታቸው እውነተኝነት የእነርኡም ጽናት በመገለጹ ሌሎች ወደ አግዚኣብሔር ፊታችውን እንዲመልሱ ምክንያት ሆኗል። እኛንም እንደ ሠለስቱ ደቂቅ በሀይማኖታችን እንድንጸና ሐዋርያው ቅዱስ ዻውሎስ “ጸንተን ሃማኖታችንን አንጠብቅ “ (ዕብ ፬፥፲፬) ፤ ሐዋርያው ይሁዳም “ለቅዱሳን ኣንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለተሰጠው ሐይማኖት ተጋደሉ” (ይሁዳ ፩፥፫) እንዲል ። ስለዚህ ኣምላካችን ወደ እኛ አስኪመጣ ድረስ ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ሃማኖታችንን አጽንተን መጠበቅ ያስፍልጋል።
ለ፡ ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያንን
ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ለትያጥሮን ሰዎች እግዚአብሔር አስኪመጣ ድረስ እንዲጠብቁ ከአዘዛቸው ነገሮች አንዱ ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያንን ነው። በጊዜው የትያጥሮን ሰዎች በኤልዛቤል ምክንያት ለጣኦት የተሰዋውን እስከመብላት ደርሰው ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያንን አፍርሰው ነበር። ቅዱስ ዮሐንስ ከእግዚአብሔር በተገለጠለት ራእይ ይህን ክፉ ተግባራቸውን ነቅፎባቸዋል። እኛም በሃይማኖት የምንፈጽመውን ሥርዐት ሰርተው የሰጡንና ያሳዩን ቅዱሳን ሐዋርያት አባቶቻችን ናቸው። በመሆኑም ሥርዐተ ቤተክርስቲያንን እንድንጠብቅ ሀይማኖታዊ ግዴታ አለብን። ሐዋርያው ቅዱስ ዻውሎስም “ሁሉ በስርአት አና በአግባብ ይሁን” እንዲል (፩ ቆሮ ፲፬፥፵) ኢትዮጵያዊው ሊቅ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫም “ወባቲ ለዛቲ ቤተ ክርስቲያን ሥርዐተ መላእክት አርአያ ዘበሰማያት ቤተክርስቲያንሰ ትትመሰል በጽርሃ አርያም ዘላእሉ፤ ለ ቤተ ክርስቲያን በሰማይ እንዳሉ መላእክት ያለ ሥርዐት ስላላት ጽርሃ ኣርያምን(ሥላሴ የሚመሰገኑብትን) ትመስላለች” ብሏል ።ስለዚህ ሰማያዊ ሥርዐት ያላትን ቤተ ክርስቲያን ኣባቶቻችን ከነሙሉ ሥርዐትዋ ጠብቀው እንዳስረከቡን እኛም ይህንን ጠብቀን ለልጆቻችን ልናስረክብ ያስፈልጋል።
ሐ፡ መልካም ሥነ ምግባር
ሌላው ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ እስክመጣ ድረስ ያላችሁን ጠብቁ ብሎ ያዘዘው በመልካም ሥነ ምግባር መጽናትን ነው። ሰው ድካም የሚስማማው ሥጋ የለበሰ፣ በሥጋ የሚሞት ቢሆንም በነፍስ የማይሞት ዘላለማዊ እንደ እግዚአብሔር መላእክት ህያው ሆኖ ሊኖር ተስፋ ያለው ነው።ስለዚህ ለስጋዊ ህይውቱ የሚያስፈልገውን ለማግኘት መድከም (መስራት) እንደሚጠበቅበት ሁሉ መንፋሳዊ ህይወቱን ለማጽናት ከአምላኩ ጋር ያለዉ ግኑኝንነት ፍጹም የጠበቀ ሊሆን ይገባል። ይኼውም መንፈሳዊ ትሩፋቶችን በመስራት ነው። ቅዱስ ጳውሎስ በገላቲያ መልእክቱ የጠቀሳቸውን የመንፈስ ፍሬዎች፣ ጾም፣ጸሎት፣ስግደት፣ምጽዋት ወዘተ ገንዘብ ማድረግ ናቸው። እነዚህ ተግባራት የሰውን (የክርስቲያንን ሰውነት) ለመንፈሳዊነት የሚያበረቱ ናቸው። ነገር ግን አንዳንድ ሰዎች የባዕድ ሀገር ኑሮ ለጾም ለጸሎት አይመችም በሚል የተሰነካከለ ምክንያት በማቅረብ ከመልካም ምግባር በመራቅ ቀስ በቀስ መንፋሳዊነታቸውን እየቀነሱ ሲሄዱ ብሎም ሲተዉት ይታያሉ። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “አርነታችሁ ለሥጋ ምክንያትን አይስጥ” (ገላ ፭፥፲፫ ) እንዳለ ሁሉ ሰው በምክንያት ከእግዚአብሔር ማምለጥ አይችልምና ሥጋዊ ምክንያትን አርቀን፣ ፈተናን ታግሰን በመልካም ምግባር መጽናት ይገባናል። ቅዱስ ጴጥሮስም “መንፋሳዊ ቤት ለመሆን ተሰሩ” (፩ጰጥ ፪፥፭) እንዲል።
በአጠቃላይ ቅዱስ ዮሐንስ እስክመጣ ድረስ ያላችሁን ጠብቁ ብሎ እንደነገረን በ40 እና በ80 ቀን ያገኘነውን የመንፈስ ቅዱስ ልጅነት አጽንተን በሀይማኖትና በመልካም ምግባር ጎልምሰን መንፈሳዊ ፍሬ አፍርተን መጠበቅ ይኖርብናል። ሁላችንም እስካሁኗ ስዓት መኖራችንን እንጂ ከዚህች ጊዜ ጀምሮ ሕይወታችን በእኛ መዳፍ ውስጥ አለመሆኗን ተረድተን በንስሐ ታጥበን በቅዱስ ሥጋው እና ክቡር ደሙ ታትመን ያለንን መንፈሳዊ ጸጋ ጠብቀን መኖር ያስፈልጋል። ይህን እንድናደርግ የስላሴ ቸርነት፣ የእመቤታችን ምልጃና የቅዱሳን ተራዳይነት አይለየን፡አሜን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!