ልዩ ከሆነች ድንግል ማርያም ይህ የአምላክ መወለድ ምን ይደንቅ
ዲ.ን ብሩክ አሸናፊ
ቀን ታህሣስ 27 ቀን 2007 ዓ.ም.
«ኦ ዝ መንክር ልደተ አምላክ እማርያም እምቅድስት ድንግል፤ ልዩ ከሆነች ድንግል ማርያም ይህ የአምላክ መወለድ ምን ይደንቅ» ውዳሴ ማርያም ዘሐሙስ
ይህ ቃል በ፫፻፮ ዓ.ም ገደማ በሜሶጶጣሚያ ውስጥ በምትገኘው በንጽቢን ተወልዶ፣ የጸጋህን ማዕበል ግታልኝ እስኪል ድረስ ጸጋ እግዚአብሔር በዝቶለት እጅግ ብዙ ድርሳናትን የደረሰው፣ በጉባኤ ኒቅያ መምህሩ ከነበረው የንጽቢን ጳጳስ ያዕቆብ ጋር የተገኘው፣ ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ እመቤታችንን ባመሰገነበት ውዳሴ ማርያም በተሰኘው መጽሐፉ ላይ ልዩ እና ድንቅ የሆነውን የጌታችንን ልደት አድንቆ በሐሙስ ክፍል ላይ የጻፈው ነው።
በተለምዶ ማንም ሊያደርገው የማይችለው ነገር ሲደረግ፣ ተደርጎ የማያውቅ፣ ይደረጋልም ተብሎ የማይታሰብ ነገር ሆኖ ተከስቶ ስንመለከት ድንቅ ነው እንላለን። ይህንን ዓለም ከነግሳንግሱ በስድስት ቀን ብቻ በማሰብ፣ በመናገር እና ሰውን ደግሞ በቅዱስ እጁ በመሥራት የፈጠረውን አምላካችን እግዚአብሔርን ስናስብ ደግሞ እግዚአብሔር ሥራው ድንቅ ነው ከማለት ውጪ ምንም ቃላት የለንም፤ ቅዱስ ዳዊት «ግሩም እና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ”(መዝ.፻፴፱፥፲፬) እንዲል። እግዚአብሔር ይህንን ዓለም ከፈጠረበት ጥበቡ ይልቅ ይህንን ዓለም ያዳነበት ጥበቡ ደግሞ እጅግ ድንቅ ነው። በዙፋኑ ሆኖ ማዳን እየቻለ ለሰው ልጆች ያለውን ፍቅር ለመግለጽ ተነግሮ በማያልቅ እና ልዩ በሆነ ልደት ተወልዶ፣ ራሱን አዋርዶ፣ በፈጠረው ፍጥረት ተዋርዶ፣ በሞቱ ዓለምን ያዳነበት ጥበቡ ድንቅ ነው። ቅዱስ ኤፍሬምም ይህንን መግለጫ የሌለውን የጌታችንን ልደት በተናገረበት አንቀጹ «ልዩ ከሆነች ድንግል ማርያም ይህ የአምላክ መወለድ ምን ይደንቅ» ብሎ አድንቆ ጽፏል። የቆጵሮሱ ሊቀ ጳጳስ ኤጲፋንዮስም «ስለ እግዚአብሔር ወልድ ቅድመ ዓለም ከአብ ያለ እናት ድኅረ ዓለም ያለ አባት ከእመቤታችን ለተወለደው ልደት ድንቅ ነው ከማለት በቀር ሌላ ፍጡራዊ መግለጫ ቋንቋ የለንም» ብሏል። ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም «ከሰው ዘር በዚህ ዓይነት ልደት የተወለደ የለም» ብሎ አድንቋል። ይህንን ድንቅ የሆነውን እና ከእርሱ በፊትም ከእርሱ በኋላም ሊከሰት የማይችለውን አንድ ጊዜ ብቻ ለዓለም የተገለጠውን የጌታችንን ልደት ድንቅ ያስኙትን የተወሰኑትን ምክንያቶች ውቅያኖስን በማንኪያ የመጨለፍ ያህል እንደሚከተለው እናያለን።
1. የአምላክ ሰው መሆን
መለኮት ረቂቅ ነው።
«አምላክ እንደ ፀሐይና ጨረቃ ክበብ፣ እንደ ሰውም መጠን ያለው አይደለም ድንቅ ነው እንጂ፤ የሰው ኅሊና የመላእክትም አእምሮ በማይደርስበት በአርያሙ የሚኖር ነው።» አባ ሕርያቆስ። አበው «ከነፋስ የሰው ነፍስ ትረቃለች፤ ከነፍስ ደግሞ መላእክት ይረቃሉ፤ ከመላእክት ደግሞ የመላእክት ኅሊናቸው ይረቃል፤ ከመላእክት ኅሊና ደግሞ የሥላሴ አካል ይረቃል።» ይላሉ። መለኮት ረቂቅ ሆኖ፣ አባ ሕርያቆስ እንደተናገረው የሰው ኅሊና የመላእክት አእምሮ የማይደርስበት ሆኖ ሳለ ከሥጋ ተዋሕዶ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ እንደሰው ታየ፤ ዘመን ተቆጠረለት። ቅዱስ ኤፍሬምም «ኑ ይህንን ድንቅ እዩ ስለተገለጠልንም ምሥጢር ምስጋና አቅርቡ ሰው የማይሆን ሰው ሆኗልና፣ ቃል ተዋሕዷልና፤ ጥንት የሌለው ሥጋ ጥንታዊ ቀዳማዊ ሆነ፤ ዘመን የማይቆጠርለት መለኮት ዘመን ተቆጠረለት፤ የማይታወቅ ተገለጠ፤ የማይታይ ታየ፤ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ በርግጥ ሰው ሆነ፤ ትላንት የነበረው፣ ዛሬም ያለው፣ መቼም የሚኖረው» ብሎ አድንቋል።
መለኮት በሁሉ የመላ ነው።
ጊዜ፣ ቦታ እና ሁኔታ ሰውን ይወስኑታል እንጂ የፈጠራቸውን፣ ያስገኛቸውን አምላክን መወሰን አይቻላቸውም። አምላክ በዚህ ጊዜ ነበረ በዚህ ጊዜ ደግሞ አልነበረም የሚባል አይደለም።የሌለበት ጊዜ ፈጽሞ የሌለ ለዘመኑ ጥንት ለአኗኗሩ ፍጻሜ የሌለው ነው፤ በዚህ ቦታ አለ በዚህ ደግሞ የለም ሊሉት አይቻልም። የሌለበት ቦታ የሌለ በሁሉ የመላ ነው እንጂ፤ ሁኔታዎች ይወስኑታል የማይባል ይልቁን እነርሱን የሚወስናቸው ነው። ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ስለ አምላክ ምሉዕነት በተናገረበት አንቀጹ «ሦስቱ አካላት በአንድ መለኮት እነርሱ በሚያውቁት ማናቸውም ፍጥረት በማያውቀው በዚህ ዓለምም ከዓለምም ውጪ ምሉዓን ናቸው፤ የፈጠሩትን ፍጥረት እነርሱ ይወስኑታል እንጂ እርሱ አይወስናቸውም፤ ከመወሰን ውጪ ናቸው።» ብሏል።
ቃል በሥጋ ተወለደ።
ወልደ አብ ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ ማርያም ተገለጠ። ይህ ደግሞ የበለጠ የሚያስደንቅ ምሥጢር ነው። ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ይህንን ሲተረጉም «ማንኛውም ፍጥረት የሚወልደውን የሚፈጥረው አይደለም፤ የሚሠራውንም የሚወልደው አይደለም፤ ያልተፈጠረ የተወለደ የእግዚአብሔር ቃል መወለዱ እንደ ፍጡራን ከፍጡር አባት አይደለም፤ ስለዚህ የተወለደ እንጂ የተፈጠረ አይደለም» ብሏል። ወንጌላዊው ዮሐንስም «በመጀመሪያው ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፥ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ። ይህ በመጀመሪያው በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ። ሁሉ በእርሱ ሆነ፥ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም።…ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ» ብሎ የተወለደው ፈጣሬ ዓለማት እግዚአብሔር መሆኑን መስክሯል። ሁሉን የፈጠረ፣ ሁሉ በእርሱ የሆነ አምላክ ከእናታችን ከድንግል ማርያም ተወልዶ ሰው ሲሆን እንደ ፫፻፲፰ቱ ሊቃውንት አባቶቻችን በሃይማኖት ጸሎታችን «የተወለደ እንጂ ያልተፈጠረ» እያልን እናመሰግነዋለን። (ዮሐ ፩፥፩–፲፬)
ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል እግዚአብሔር ወልድ ሰው ሲሆን ከሥላሴ አንድነት ሳይለይ ነው። ይህንንም ነባቤ መለኮት የተባለው ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሳርያ ሲተረጉም «ወልድ ከአብ ተወለደ ቢባልም በከዊነ ቃልነት በአብና በመንፈስ ቅዱስ አካል ውስጥ ምን ጊዜም ያለና የሚኖር የሦስቱ አካላት አንድ ቃል ነው» ብሎ እግዚአብሔር ወልድ ሰው ሆኖ ለዓይን ጥቅሻ ያህል እንኳን ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ እንዳልተለየ አስረድቷል።
2. ተዋሕዶ
መለኮት እና ትስብእት ከሁለት አካል አንድ አካል፣ ከሁለት ባሕርይ አንድ ባሕርይ የሆኑበት፣ ለሥሙ ክብርና ምሥጋና ይግባውና ሐራ ጥቃ ቃል ሥጋ ወደ መሆን ተለውጧል እንደሚለው ሳይሆን ያለ መለወጥና ያለ መቀላቀል፣ ንስጥሮስ ማርያም በወለደችው አብ የወለደው አደረበት እንደሚለው ሳይሆን ያለ ኅድረት፣ አንድ የሆኑበት የተዋሕዶ ምሥጢር እጅግ ድንቅ ነው። የቤተክርስቲያን መዶሻ እየተባለ የሚጠራው ቅዱስ ቄርሎስ ሐራ ጥቃ የተባለው መናፍቅ «ቃል ሥጋ ሆነ» የሚለውን ብቻ ይዞ «ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ» የሚለውን ባለማስተዋል ሲስት «አቤቱ አንተ ለትውልድ ሁሉ መጠጊያ ሆነሃልና» የሚለውን ጠቅሶ እግዚአብሔር አጥር ቅጥር መጠጊያና ግንብ ሆነ ማለት ነውን? በማለት፣ ንስጥሮስ የተባለው መናፍቅም «ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ» የሚለውን ይዞ ሰይፍ በአፎቱ፣ ዳዊትም በማኅደሩ እንደሚያድር ዓይነት «ቃል ሥጋ ሆነ» የሚለውን ባለማስተዋል ሲስት እግዚአብሔር በሙሴ እና በኢያሱ አድሮ ነበር ሲባል ሙሴ እና ኢያሱ አማኑኤል አልተባሉም፤ ይልቁን አማኑኤል የተባለው ከእመቤታችን ከሥጋዋ ሥጋን፣ ከነፍሷ ነፍስን ነስቶ ከሁለት አካል አንድ አካል፣ ከሁለት ባሕርይ አንድ ባሕርይ በመሆን ሰው የሆነ አምላክ ወልደ አብ ወልደ ማርያም ጌታችንና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን በመናገር ተዋሕዶ «ቃል ሥጋ ሆነ» የሚለውንና «ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ» የሚለውን በአንድነት የሚገልጽ መሆኑን መስክሯል።(ዮሐ ፩፥፩–፲፬፣መዝ ፹፱፥፩፣ነገረ ቅዱሳን ቁጥር ፫፣ገጽ ፻፶፪ ፥ ፻፶፬)
የመለኮት ባሕርይ ሕያው፣ ሁሉን ቻይ፣ ሁሉን አዋቂ፣ በሁሉ ያለ፣ በሁሉ ላይ የሠለጠነ፣ የማይራብ፣ የማይጠማ፣ የማይደክም፣ የማይተኛ፣ የማይታመም እና የማይሞት ነው። የሥጋ ባሕርይ ደግሞ በአንጻሩ ውሱን፣ የሚራብ፣ የሚጠማ፣ የሚደክም፣ የሚታመም እና የሚሞት ነው። ረቂቅ የሆነው የማይታየው እና የማይዳሰሰው የመለኮት አካል ግዙፍ ከሆነው፣ ከሚታየው እና ከሚዳሰሰው የሥጋ አካል ጋር መዋሐዱ፣ እንዲሁም ባሕርየ መለኮት ከባሕርየ ሥጋ፣ ርቀት ከግዝፈት፣ ምልዓት ከውሱንነት ጋር መዋሐዱ እጅግ ይደንቃል። የዚህን ድንቅ ምሥጢር ምሳሌም እግዚአብሔር በሙሴ በኩል በደብረ ኮሬብ ላይ በሐመልማሉ እና በነበልባሉ አስቀድሞ ገልጦልናል። ረቂቁ እሳት ግዙፉን ቁጥቋጦ ሳያቃጥለው፣ ግዙፉ ቁጥቋጦም ረቂቁን እሳት ሳያጠፋው በመጠባበቅ የመለኮትን እና የሥጋን ተዋሕዶ ቁልጭ አድርጎ አሳይቶናል። (ዘጸ ፫፥፪)
በዚህ ድንቅ የተዋሕዶ ምሥጢር የቃል ገንዘብ ለሥጋ፣ የሥጋ ገንዘብ ለቃል ሆነ። ቅዱስ ቄርሎስ ይህንን በመለኮት እና በትስብእት መካከል ያለውን ምሥጢራዊ ግብር ሲናገር «ሐዲስ ኪዳን ክርስቶስን በየጥቂቱ አደገ ይላል፤ ማደግ የትስብእት ገንዘብ ነው መለኮትማ በዓለምም ከዓለምም ውጪ በማንኛውም ቦታ የመላ ነውና ከተዋሐደው ሥጋ ጋር አንድ አካል አንድ ባሕርይ ስለሆነ በሥጋ ባሕርይ በየጥቂቱ ማደግን ገንዘብ አደረገ» ብሏል። በማከልም «ከእኛ ባሕርይ በተለየ አካሉ በተዋሐደው ሥጋ እንደታመመ እንደሞተ እናምናለን፤ እርሱ ራሱ እግዚአብሔር ወልድ የባሕርይ አምላክ እንደመሆኑ የተዋሐደውን ሥጋ ከሙታን ለይቶ እንዳስነሳው፣ ያስነሳውም ሌላ እንዳይደለ እናምናለን፤ ክርስቶስ የማይታመም ፍጹም አምላክ፣ እንደዚህም ሁሉ የሚታመም ፍጹም ሰው ነው» ብሏል። በምሳሌም ሲያስረዳ «ከብረት ጋር የተዋሐደ እሳት በመዶሻ ሲመታ የእሳቱ ባሕርይ እንዳይጎዳ፣ በሰውም ውስጥ ያለች ነፍስ ሰውየው በሠይፍ በተቆረጠ ወይም በእሳት በተቃጠለ ጊዜ ነፍሱ ከመቆረጥና ከመቃጠል የተለየች ወይም መከራ እንዳያገኛት እንደዚሁም ሁሉ መለኮት በሥጋ ውስጥ እንደዚሁ ነው» ብሏል። ሥግው ቃል አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለበርጠሜዎስ ቅዱስ ምራቁን ከአፈር ለውሶ በደረቅ ግንባር ላይ ዓይንን በመፍጠር እና ለሐዋርያት ትንሣኤውን ሊሰብክ ግዙፍ ሥጋ ሊያደርገው የማይችለውን ረቂቁን መለኮት ስለተዋሐደ በዝግ ቤት በመግባት ይህንን ድንቅ ምሥጢር ገልጦልናል። (ሉቃ ፪፥፴፱፣ዮሐ ፪፥፲፱ ዮሐ ፱፥፩-፯ ዮሐ ፳፥፲፱)
3. ቃልን ፀነሰችው።
ዓለምን በእጁ የያዘ በማኅፀነ ድንግል ማርያም ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን ሲወሰን፣ ዘመን የምንቆጥርበትን ፀሐይን የፈጠረ አምላክ ይሁንልኝ ይደረግልኝ ከሚለው የእመቤታችን መልስ ጀምሮ የዕለት ፅንስ ሆኖ ዘመን ሲቆጠርለት ከመመልከት በላይ ምን የሚደንቅ ነገር ይኖር ይሆን! አባ ሕርያቆስም ይህንን ሲያደንቅ «ከአባቱ አጠገብ ሳይለይ ቃል ወደ አንቺ መጣ ሳይወሰን ፀነስሽው፤ በላይ ሳይጎድል በታችም ሳይጨመር በማኅፀንሽ ተወሰነ፤ መጠንና መመርመር የሌለበት እሳተ መለኮት በሆድሽ አደረ፤ በምድራዊ እሳት እንመስለው ዘንድ አይገባም፤ ለእሳትስ መጠን አለው ልክም አለው፤ መለኮት ግን ይህንን ያህላል ይህንንም ይመስላል ሊባል አይቻልም» ብሏል። ይህ የዓለምን ታሪክ የቀየረ ለሁሉ ድንቅ የሚሆን ምሥጢር እንዲፈፀም ምክንያት የሆነችውን የቅድስት ድንግልንም የፅንሷን ነገር ሲመረምር «ድንግል ሆይ እሳተ መለኮት በሆድሽ ባደረ ጊዜ ፊቱ እሳት፣ ልብሱ እሳት፣ ቀሚሱ እሳት እንደምን አላቃጠለሽ? ሰባት የእሳት ነበልባል መጋረጃ በሆድሽ ውስጥ ወዴት ተዘጋጀ? ወዴትስ ተጋረደ? ከጎንሽ በቀኝ ነውን? ወይስ ከጎንሽ በግራ ነውን? ትንሽ አካል ስትሆኚ የሚያንጸባርቅ ነደ እሳት የሚከበው ኪሩቤል የተሸከሙት ዙፋን በሆድሽ ውስጥ በወዴት ተዘጋጀ? ወዴትስ ተተከለ?» ብሎ ሥጋዊ ደማዊ የሆነ አእምሮ ባፈለቀው ፍጡራዊ ቋንቋ ሊመለሱ የማይችሉ መልሳቸው እንዲሁ ማድነቅ ብቻ የሆኑ ጥያቄዎችን እየጠየቀ አድንቋል።
ፈጣሪዋን በማኅፀኗ የተሸከመች ብቸኛ ፍጥረት በሕግ በሆነ ሩካቤ ከሐና ከኢያቄም የተወለደች፣ በንጽሕና በቅድስና በቤተ መቅደስ የኖረች፣ ከሰማየ ሰማያት የበሰለ ሰማያዊ ኅብስትን የበላች፣ ከሰማየ ሰማያት የተቀዳ ሰማያዊ መጠጥን የጠጣች፣ ከእርሷ አስቀድሞ ከእርሷም በኋላ እንዳሉ ሴቶች እድፍ የማታውቅ በንጽሕና በቅድስና ያጌጠች፣ የሰማይ መላእክት የጎበኟት እና ካህናት ያመሰገኗት ከፍጡራን ሁሉ በላይ ከፈጣሪ በታች የሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ብቻ ነች። ቅዱስ ኤፍሬምም «ከቅዱሳን ክብር የማርያም ክብር ይበልጣል፤ የአብን ቃል ለመቀበል በተገባ ተገኝታለችና፤ መላእክት የሚፈሩትን ትጉሆች በሰማያት የሚያመሰግኑትን ድንግል ማርያም በማኅፀንዋ ተሸከመችው፤ ይህች ከኪሩቤል ትበልጣለች ከሱራፌልም ትበልጣለች፤ ከሦስቱ አካላት ለአንዱ ማደሪያ ሆናለችና» ብሎ አመስግኗታል። ሌሎች ሴቶችን ብናከብራቸው ነቢያትን፣ ጻድቃንን ወለዳችሁልን ብለን ነው፤ እርሷን ግን እመ አምላክ፣ ወላዲተ አምላክ ብለን አብልጠን እናከብራታለን።
4. ያለ ዘር፣ያለ ሩካቤ በድንግልና ተፀንሶ በድንግልና መወለዱ
ምድር ያለ ዘር፣ ሴት ያለ ወንድ ትፀንስ ዘንድ ሕገ-ተፈጥሮ አይፈቅድም፡፡ የጌታ ፅንስ ግን እንዲህ አይደለም፤ ወንጌላዊው ማቴዎስ ስለዚህ ሲገልጽ «ለዮሴፍ ታጭታ ሳለች ሳይገናኙ በመንፈስ ቅደስ ፀንሳ ተገኘች» (ማቴ ፩፥፲፰) እንዳለ የጌታ ፅንስ ከሦስት ግብራት ንፁህ ነው፡፡ ይኸውም ከዘር፣ ከሩካቤ እና ከሰስሎተ ድንግልና ነው። ጌታችን ሲፀነስ ሩካቤ አልተፈፀመም፤ ዘርዐ ብእሲ አላስፈለገም፤ የእመቤታችን ድንግልናም አልተለወጠም፡፡ በዚህ እውነትም የተወለደልን ሕፃን ኃያል አምላክ ወይም ሁሉን ቻይ መሆኑን ገለጠልን፡፡ የጌታችን ልደቱም እንደ ፅንሰቱ ሁሉ ልዩ ነው፤በልደቱ የእናቱን ድንግልና አልለወጠውም። «ወደ ምሥራቅ ወደሚመለከተው በስተውጭ ወዳለው ወደ መቅደሱ በር አመጣኝ ተዘግቶም ነበር፤ እግዚአብሔርም ይህ በር ተዘግቶ ይኖራል እንጂ አይከፈትም ሰውም አይገባበትም የእስራኤል አምላክ ገብቶበታልና ተዘግቶ ይኖራል፡፡» እንዲል። ምሥራቅ የእመቤታችን ምሳሌ የእውነተኛዉ ፀሐይ መውጫ ናትና፣ መቅደሰ የማኅፀንዋ ፱ ወር ከ ፭ ቀን ተመስግኖበታልና፣ በር የማኅተመ ድንግልናዋ፣ ተዘግቶ ይኖራል ማለቱ ለዘላለም እናትነትን ከድንግልና አስተባብራ ፀንታ መኖሯን ሲገልጥ ነው፡፡ (ማቴ ፩፥፲፰፣ሉቃ ፩፥፳፮-፶፮፣ሕዝ ፵፬፥፩-፫፣ውዳሴ ማርያም ትርጓሜ)
ከመፅነሷ በፊት፣ በፀነሰችም ግዜ፣ ከፀነሰችም በኋላ ድንግል ናት። ከመውለዷ በፊት፣ በወለደችም ግዜ፣ ከወለደችም በኋላ ድንግል ናት። ይህ በግብረ አምላካዊ የተፈፀመው የእመቤታችን እናትነትን ከድንግልና እመቤትነትን ከገረድነት ጋር አስተባብሮ መያዝ እመቤታችንን ከፍጥረታት ሁሉ ልዩ ያደርጋታል። ቅዱስ ኤፍሬም «ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዳዊት አገር ከእርሷ ስለተወለደ አምላክን የወለደች ማርያምን ዛሬ እናመስግናት እናትና ድንግልን ሁለቱንም ሆናለችና።» እንዳለ።
በአጠቃላይ እንዳሰበ የሚሠራ እንደፈቀደም የሚያከናውን፣ ለሥራው ረዳት አጋዥ አማካሪ የማይሻ፣ ሁሉን ከባሕርይ የሚያከናውን አምላክ ከላይ ሳይጎድል በከብቶች ግርግም መወለዱ፣ አድግ እና ላህም እስትንፋሳቸውን መገበራቸው፣ ሰማያውያን መላእክት ከምድራውያን እረኞች ጋር ማመስገናቸው የሚያስደንቅ ነው። በሰማይም ሆነ በምድር ከምድርም በታች በሁሉ የሚሠራ፣ በሁሉ የሚያዝ፣በሁሉ ላይ የሠለጠነ፣ ማንም ማን ለምን ይህን ታደርጋለህ ብሎ ሊከለክለው ሊያግደው ሊያስቆመው የማይቻል፣ ይበልጥ ገላጭ በሆነ ቃል የሚሳነው ነገር የሌለ አምላካችን ከአእምሯችን በላይ የሆነውን ልደቱን፣ ቅዱሳት መላእክት «ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ሥምረቱ ለሰብእ» ብለው እንዳመሰገኑት እኛም ዝም ብለን ከማድነቅና ከማመስገን በቀር ምንም አንደበት የለንም።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር